በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማይናወጥ አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር

የማይናወጥ አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር

የማይናወጥ አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር

ኤል ሳልቫዶር የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ጥር 13, 2001 ከረፋዱ 5:⁠34 ላይ በሬክተር መለኪያ 7.6 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ድፍን ኤል ሳልቫዶርን ያናወጠ ከመሆኑም በላይ ንዝረቱ ከፓናማ አንስቶ እስከ ሜክሲኮ ድረስ ተሰምቷል። አብዛኞቹ ሰዎች ነውጡ በተከሰተበት ወቅት እያከናወኑት የነበረው ሥራ ፈጽሞ አይረሳቸውም።

“በጣም ኃይለኛ የሆነው ነውጥ ጋብ እንዳለ ቀና ብለን ስናይ የተራራው አናት ለሁለት ተገምሶ ለጥቂት ሰከንዶች ባለበት ቆሞ አየን” ስትል ሚርያም ኬሳታ ታስታውሳለች። “ልጄ ‘እማዬ! አምልጪ! አምልጪ!’ ብላ ጮኸች።” ከዚያም ተራራው ከጎን በኩል ተንዶ እነሱ ወዳሉበት ተንከባልሎ መጣ። በንዌቫ ሳን ሳልቫቶር ወይም በሌላ መጠሪያው በሳንታ ቴክላ በምትገኘው የላስ ኮሊናስ መንደር ወደ 500 ገደማ ሰዎች ያለቁ ሲሆን ወደ 300 የሚሆኑ ቤቶች ደግሞ ደብዛቸው ጠፍቷል።

“የመሬት መንቀጥቀጡ ሲጀምር ገና ከቤት ወጥቼ ፌርማታው ላይ መቆሜ ነበር” ስትል ሮክሳና ሳንቼስ ሁኔታውን ገልጻለች። “ነውጡ እንዳቆመ አንዲት ሴት የወደቁባትን ቦርሳዎች እንድታነሳ ካገዝኋት በኋላ ‘ቤተሰቦቼ ስለኔ ማሰባቸው ስለማይቀር ወደ ቤት ብመለስ ይሻላል’ ብዬ አሰብኩ።” ሮክሳና መታጠፊያውን ስትዞር መንገዱ ከተራራው በተናደው አፈር ተዘግቷል። ቤቷ በቦታው የለም!

አፋጣኝ ዕርዳታ መስጠት

በኤል ሳልቫዶር የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች አጠቃላይ ቁጥር ከ28, 000 በላይ ሲሆን የአደጋ ቀጣና በሆነው በሳልቫዶር የባሕር ዳርቻ አካባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይኖራሉ። በኤል ሳልቫዶር የሚኖሩ ምንም እንኳ ብዙዎች ከደረሰባቸው የስሜት ቀውስ ገና ያላገገሙ ቢሆንም ወዲያው ትኩረት ያደረጉት የሌሎችን ፍላጎት ለማሟላት ነው። በሳንታ ቴክላ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ማርዮ ስዋሬስ እንዲህ ይላል:- “የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተ ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወንድሞች ስልክ ደወሉልኝ። የተወሰኑ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ከቤታቸው መውጫ መንገድ እንዳጡ ተነገረኝ። ወዲያው የፈቃደኛ ሠራተኛ ቡድን ተቀናጀ።

“ምናልባት የተወሰነ ግድግዳ ተደርምሶ መውጫ አጥተው ሊሆን ስለሚችል ፍርስራሹን አንስቶ መተላለፊያ የመክፈት ጉዳይ ቢሆን ነው ብለን አሰብን። ይሁን እንጂ አንዳችንም ብንሆን አደጋው ያን ያህል ስፋት ይኖረዋል ብለን አልገመትንም። እንዲያውም አካባቢው እንደደረስን ቤቶቹ የነበሩበትን ቦታ ጠየቅን። የቆምነው ቤቶቹ ላይ እንደሆነ ሲነገረን በጣም ደነገጥን! ቤቶቹ እስከ ሁለተኛው ፎቅ ድረስ ሦስት ሜትር ከፍታ ባለው አፈር ተውጠዋል። ሁኔታው በጣም አስጨናቂ ነበር!”

የከሰዓት በኋላው ጊዜ እየተገባደደ ሲሄድ በግምት ወደ 250 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች በአቅራቢያው ከሚገኙ ጉባኤዎች ዕርዳታ ለመስጠት ወደ አካባቢው ጎረፉ። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ በዶማ፣ በአካፋ፣ በፕላስቲክ ባልዲና በባዶ እጃቸው ብቻ እየታገዙ ከሞት የተረፉትን ሰዎች ለማዳን ከፍተኛ ርብርብ አደረጉ። ይሁን እንጂ በሳንታ ቴክላ በሕይወት የተረፉት በጣም ጥቂቶች ናቸው። ታፍነው አሊያም ብዙ ቶን ክብደት ያለው አፈር ሥር ተጨፍልቀው ከሞቱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል።

የተቀናጀ የዕርዳታ አቅርቦት

በመላ አገሪቱ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ዕርዳታ በመስጠቱ ሥራ መሳተፍ ጀመሩ። በኮማሳግዋ፣ በኦሳትላን፣ በሳንታ ኤሌና፣ በሳንትያጎ ዴ ማሪያ እና በኡሱሉታን ከተሞች የሚኖሩ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች መኖሪያ ቤታቸውን አጥተዋል። የመንግሥት አዳራሾችና የግል መኖሪያ ቤቶች የመሰባሰቢያ ማዕከላት ሆኑ። ተጓዥ የበላይ ተመልካች የሆነው ኤድወን ኤርናንዴስ “ከፍተኛ መጠን ያለው ዕርዳታ ነው የተሰባሰበው። ወንድሞች ምግብ፣ ልብስ፣ ፍራሽ፣ መድኃኒትና ለቀብር የሚያስፈልግ ገንዘብ ሳይቀር ይዘው መጥተዋል” ብሏል።

በአገሩ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ያቋቋመው የዕርዳታ ኮሚቴ በመሬት መንቀጥቀጡ እምብዛም ያልተጎዱ ጉባኤዎች በቡድን በቡድን ተደራጅተው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ጉባኤዎች ባስቸኳይ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች እንዲያቀርቡ ዝግጅት አደረገ። ከ10 እስከ 20 የሚሆኑ ምሥክሮችን ያቀፉ ቡድኖች ተቋቁመው አስፈላጊውን የጥገና ሥራ እንዲያከናውኑ ተደረገ።

ከዚህ በተጨማሪ መደበኛ ተግባራቸው የመንግሥት አዳራሾች ግንባታ ሥራ ማካሄድ የሆነው የይሖዋ ምሥክሮች የአካባቢ የሕንፃ ግንባታ ኮሚቴዎች ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ለወደመባቸው ወንድሞች ጊዜያዊ መኖሪያ የሚገነቡ ቡድኖችን አደራጁ። ኤል ሳልቫዶር ውስጥ የቆርቆሮ ዋጋ በጣም በመናሩ በጓቴማላ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ቆርቆሮ በዕርዳታ ላከ። የዩናይትድ ስቴትስና የሆንድራስ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ደግሞ ለመጠለያዎቹ አውታር ለመሥራት የሚያገለግል ጠርብ ላኩ።

ሥራው በጥድፊያ እየተካሄደ ሳለ በመካከሉ መጠነኛ ነውጦች ይከሰቱ ነበር። የአንዳንድ አካባቢ ነዋሪዎች ባጠቃላይ በፕላስቲክ ድንኳኖችና ባረጁ አንሶላዎች ተጠልለው መንገድ ላይ ለመተኛት ተገድደዋል። ፍርሃትና ጭንቀት ነግሦ ነበር። እስከ የካቲት 12 ባለው ጊዜ ውስጥ ከዋናው ነውጥ በኋላ በድምሩ 3, 486 መጠነኛ ነውጦች ተመዝግበዋል።

ሌላ ከባድ ነውጥ

የመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ በደረሰ በወሩ የካቲት 13, 2001 ከጠዋቱ 2:​22 ላይ በሬክተር መለኪያ 6.6 የተመዘገበ ሁለተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ መካከለኛውን የኤል ሳልቫዶር ክፍል መታ። አሁንም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች ነፍስ የማዳንና ዕርዳታ የማሰባሰቡን ሥራ በከፍተኛ ትጋት ተያያዙት። ኖዬ ኢራኤታ የሚባል አንድ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እያንዳንዱ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት መሪ በቡድኑ ውስጥ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች እንዴት እንደሆኑ ለማወቅ ፍለጋ ጀመረ።”

የሳን ቪሴንቴ እና የኮሁቴፔኬ ከተሞች እንዲሁም በአቅራቢያቸው ያሉት አካባቢዎች ክፉኛ ነበር የተመቱት። ሳን ፔድሮ ኖኑአልኮ፣ ሳን ሚጌል ቴፕአሶንቴስ እና ሳን ህዋን ቴፕአሶንቴስ የሚባሉት ከተሞች የፍርስራሽ ክምር ሆኑ። የተረፈ ነገር የለም በሚያሰኝበት በካንዴላርያ ኩስከትላን በአንድ ደብር የሚገኝ ትምህርት ቤት ፈርሶ ከ20 በላይ ልጆች ጨርሷል። በዚያ የሚኖር ሳልቫዶር ትሬኾ የሚባል የይሖዋ ምሥክር ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ አንድ ሰው መንገድ ላይ ሆኖ ‘ወንድም ትሬኾ!’ ብሎ ሲጣራ ሰማሁ። መጀመሪያ ከአቧራው የተነሳ ምንም ነገር ማየት አልቻልኩም ነበር። ከዚያም ከኮሁቴፔኬ የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች ድንገት ብቅ አሉ። እኛን ለመጠየቅ ነበር የመጡት!”

አጎራባች ጉባኤዎች ለሁለተኛ ጊዜ በደረሰው በዚህ አደጋ ለተጠቁት ወንድሞች የሚያስፈልጉ የዕርዳታ ዕቃዎችን ለማቅረብ እንደገና ተቀናጁ። እነሱ ራሳቸው ችግር ላይ ቢሆኑም እንኳ ዕርዳታ የመስጠት መብት ለማግኘት ልመና ያቀረቡት በመቄዶንያ ይኖሩ የነበሩ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተዉትን አርአያ ተከትለዋል። ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ የንብረት ውድመት የደረሰባቸው በሳንትያጎ ቴክሳክዋንጎስ ከተማ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞች በአቅራቢያቸው ባለው በሳን ሚጌል ቴፕአሶንቴስ ለሚገኙ ወንድሞቻቸው የሚሆን ትኩስ ምግብ አዘጋጅተዋል።

በጥቅሉ ኤል ሳልቫዶር ውስጥ በተከሰቱት የመሬት ነውጦች ሳቢያ ከ1, 200 ሰዎች በላይ እንዳለቁ የተገመተ ሲሆን አጎራባች በሆነችው በጓቴማላ ደግሞ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።

አድናቆት የተቸረው ጥረት

የይሖዋ ምሥክሮች ጉዳት የደረሰባቸውን ለመርዳት ያደረጉት የተቀናጀ ጥረት በሌሎች የዕርዳታ ሰጪ ቡድኖች ዘንድ አድናቆት አትርፏል። የብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ኮሚቴ መኪና አንዳንድ ቁሳቁሶች ለማድረስ ጊዜያዊ መጠለያ ሆኖ ወደሚያገለግል አንድ የመንግሥት አዳራሽ መጣ። የኮሚቴው ተወካይ የሆነች አንዲት ሴት “ካየናቸው መጠለያ ጣቢያዎች ሁሉ ሥርዓታማ ሆኖ ያገኘነው የመጀመሪያው ይኼ ነው። ለዚህ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ!” ብላለች። በሌሎች መጠለያ ጣቢያዎች እንደታየው መኪናውን ከበው የሚጋፉም ሆነ የሚገፈታተሩ ሰዎች አልነበሩም። እንዲያውም በቅድሚያ የዕርዳታ ቁሳቁስ የታደለው ለአረጋውያን ነበር።

ምሥክሮቹ የሚሰጡት ዕርዳታ ለእምነት ጓደኞቻቸው ብቻ የተገደበ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል በሳን ቪሴንቴ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ በደርዘን የሚቆጠሩ የጎረቤት ሰዎች በመንግሥት አዳራሹ ግቢ ውስጥ ተጠልለው ነበር። ሬኺና ዱራን ዴ ካንያስ እንዲህ ብላለች:- “እዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ያሉት ሰዎች በጣም ደጎች ናቸው። እዚህ ልንቀመጥ የቻልነው በራቸውን ከፍተው ‘ግቡ!’ ስላሉን ነው። ሌላው ቀርቶ ማታ እኛ ስንተኛ እነሱ በየተራ ይጠብቁን ነበር።”

መኖሪያ ቤቶች መሥራት

በንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት ከተገመተ በኋላ ለቅርንጫፍ ቢሮው ምን ያህል መኖሪያ ቤቶች እንደሚያስፈልጉ ሐሳብ ቀረበ። ቤታቸው ለፈረሰባቸው ወንድሞች የጊዜያዊ መኖሪያ ግንባታ ተጀመረ። በተጨማሪም መጠነኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤቶች ጥገና ተደረገላቸው። በትጋትና በቅልጥፍና የሚሠሩት የግንባታ ቡድኖች ከፍተኛ ትኩረት የሳቡ ሲሆን በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች ወጥተው ይመለከቷቸው ነበር።

አንዲት ሴት ከከተማው መስተዳድር እንደሚላኩ ተነግሯቸው ለረጅም ጊዜ ሲጠብቋቸው የቆዩት የዕርዳታ ሠራተኞች ስለመሰሏት ፍርስራሹን ለማጽዳት ሊረዳት የመጣ ሰው እንደሌለ በመግለጽ ቅሬታዋን ለማሰማት መጥታ ነበር። የሰፈሩ ልጆች “እትዬ፣ እነዚህ እኮ ከከተማው መስተዳደር የተላኩ ሰዎች አይደሉም። እነዚህ የአምላክ መንግሥት ሠራተኞች ናቸው!” አሏት። ሞይሴስ አንቶንዮ ዲአስ የሚባል የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች ዕርዳታ የሚሰጡበትን መንገድ ማየቱ ያስደስታል። ድርጅታቸው የላቀ አንድነት ያለው ከመሆኑም በላይ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና ምስኪን የሆንነውን ሰዎች ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። አብሬአቸው ስሠራ ቆይቻለሁ፤ በዚሁ የመቀጠል ሐሳብም አለኝ።”

ጊዜያዊ መኖሪያ የተሠራላት አንዲት ክርስቲያን እህት እያነባች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥታለች:- “እኔና ባለቤቴ በመጀመሪያ ለይሖዋ ከዚያም ፈጽሞ ባያውቁንም እንኳ እኛን ለመርዳት ከተፍ ላሉት ለእነዚህ ወንድሞች ያለንን አመስጋኝነት የምንገልጽበት ቃላት የለንም።”

እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ ችግር ላይ ለወደቁ ወንድሞች 567 ጊዜያዊ ቤቶች የገነቡ ሲሆን ወደ 100 ገደማ የሚሆኑ ተጨማሪ ቤተሰቦች ደግሞ ጉዳት የደረሰበት ቤታቸውን የሚጠግኑበት ቁሳቁስ ተሰጥቷቸዋል። ችግር ላይ የወደቁት ቤተሰቦች ራሳቸውን የሚያስጠልሉበት ቤት ካገኙ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ትኩረታቸውን ጥገና ወደሚያስፈልጋቸው ወይም በአዲስ መልክ መገንባት ወዳለባቸው 92 የመንግሥት አዳራሾች አዞሩ።

የሰዎችን ሕይወት መልሶ መገንባት

ሕንፃዎችንና መኖሪያ ቤቶችን ከመገንባት በተጨማሪ ብዙዎች በተለይ መንፈሳዊነታቸውና ስሜታዊ ደህንነታቸው እንዲጠናከር ለተደረገላቸው ዕርዳታ አመስጋኝነታቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሚርያም እንዲህ ብላለች:- “መጠነኛ የሆኑ የምድር ነውጦች መከሰታቸውን ቀጥለው ስለነበር አንዳንድ ጊዜ ልቤ ይከዳኝ ነበር። ሆኖም ወንድሞች ምንጊዜም ማበረታቻና ማጽናኛ ይሰጡን ነበር። ወንድሞች ባይኖሩ ኖሮ ምን ይውጠን ነበር?”

በጉባኤ ዝግጅት አማካኝነት የተገለጸው የይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ የመሬት መንቀጥቀጡ ጉዳት ያደረሰባቸውን ወንድሞች አስደናቂ በሆነ መንገድ ለሥራ አነሳስቷቸዋል። በመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት በኮማሳግዋ ከጉዳት ወይም ከውድመት የተረፈ የይሖዋ ምሥክሮች ቤት የለም ማለት ይቻላል። ሆኖም በዚያ ከሚኖሩት 17 ምሥክሮች መካከል 12ቱ በሚያዝያና በግንቦት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የተመዘገቡ ሲሆን 2 ምሥክሮች ደግሞ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የዘወትር የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነዋል።

በሁለተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ ክፉኛ በተጎዳው የኩስከትላን ክልል የሚገኙ ጉባኤዎች በመጋቢት ልዩ ስብሰባ አድርገው 1, 535 የደረሰ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር የተመዘገበ ሲሆን 22 ተጠማቂዎች ነበራቸው። ብዙዎች ቤታቸውን በቅርቡ ያጡ ቢሆንም ለመሰብሰቢያ አዳራሹ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ማዋጣታቸው የስብሰባውን አስተባባሪዎች ያስገረመ ጉዳይ ነበር።

በሳን ቪሴንቴ የሚኖር አንድ ምሥክር የብዙዎችን የአመስጋኝነት ስሜት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የተፈጥሮ አደጋ በሚደርስበት ወቅት ድርጅቱ የሚወስደውን እርምጃ ጽሑፎች ላይ አንብቤ ነበር። አሁን ግን በዓይኔ የማየት አጋጣሚ ያገኘሁ ከመሆኑም በላይ የወንድማማች ኅብረቱ የሚሰጠውን ድጋፍ አግኝቻለሁ። ክርስቲያናዊ ፍቅር በተግባር ሲገለጽ ተመልክተናል። የዚህ አንድነት ያለው ሕዝብ አባል መሆን ታላቅ መብት ነው!”

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በላስ ኮሊናስ የመሬት መንቀጥቀጡ ያስከተለው ናዳ ከ300 በላይ ቤቶችን ቀብሯል

[ምንጭ]

ከገጽ 13-5 ላይ ከታች ያለው:- Courtesy El Diario de Hoy

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንደረተኞቹ በነፍስ ማዳን ሥራቸው ዶማ፣ አካፋና ባልዲ ተጠቅመዋል

[ምንጭ]

Courtesy of La Prensa Gráfica (photograph by Milton Flores/Alberto Morales/Félix Amaya)

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቴፔኮዮ የሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ፍርስራሽ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቴፔኮዮ የሚኖሩ ወንድሞች ስብሰባዎቻቸውን ማካሄድ እንዲችሉ ወዲያው መጠለያ ሠርተዋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የይሖዋ ምሥክሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ የመንግሥት አዳራሾችን እንደገና የገነቡ ከመሆኑም በላይ ከ500 የሚበልጡ ጊዜያዊ ቤቶችንም ሠርተዋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አመስጋኝ የሆኑ አንዲት ነጠላ እናትና ሴት ልጅዋ የፈረሰውን ቤታቸውን መልሶ ለማቆም የተካሄደውን የግንባታ ሥራ ሲመለከቱ