በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ምናልባት አሁን ይለወጥ ይሆናል”

“ምናልባት አሁን ይለወጥ ይሆናል”

“ምናልባት አሁን ይለወጥ ይሆናል”

ሮክሳና * በደቡብ አሜሪካ አንድ የተከበረ ቀዶ ሐኪም አግብታ የምትኖር ደስ የምትልና ፍልቅልቅ የሆነች የአራት ልጆች እናት ነች። “ባለቤቴ የሴቶችን ቀልብ የሚማርክና በብዙ ወንዶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ሰው ነው” ትላለች። ይሁን እንጂ የሮክሳና ባለቤት የቅርብ ጓደኞቻቸው እንኳ የማያውቁት መጥፎ ጎን አለው። “ቤት ውስጥ አውሬ ነው። በጣም ይቀናል።”

ሮክሳና ታሪኳን መናገር ስትቀጥል የመረበሽ ስሜት ፊቷ ላይ በግልጽ ይነበብ ነበር። “ችግሩ የተፈጠረው በተጋባን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ነው። ወንድሞቼና እናቴ ሊጠይቁን መጥተው ነበር። ከእነሱ ጋር በሳቅ በጨዋታ ደስ የሚል ጊዜ አሳለፍኩ። ይሁን እንጂ እነሱ ተመልሰው ሲሄዱ ባለቤቴ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ሶፋ ላይ በኃይል ወረወረኝ። የሆነውን ነገር ማመን አቃተኝ።”

ሮክሳና የገጠማት ፈተና በዚህ ቢያበቃ ደግ ነበር። ላለፉት በርካታ ዓመታት በተደጋጋሚ ተደብድባለች። የሚፈጸምባት በደል አንድ ወጥ የሆነ ዑደት ያለው ይመስላል። ባለቤቷ ይደበድባታል፣ ከዚያም ይቅርታ እንድታደርግለት በመወትወት ሁለተኛ እንደማይነካት ቃል ይገባል። ጠባዩ ቢያንስ ለጥቂት ጊዜ ይሻሻላል። ከዚያ በኋላ ግን ሁሉ ነገር እንደ አዲስ ያገረሻል። “ምናልባት አሁን ይለወጥ ይሆናል እያልኩ ሁልጊዜ አስባለሁ” ትላለች ሮክሳና። “ቤቱን ጥዬ ከወጣሁ በኋላ እንኳን ተመልሼ እገባለሁ።”

ሮክሳና ባሏ የሚፈጽምባት የኃይል ድርጊት አንድ ቀን የከፋ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል ስጋት አለባት። “እኔን፣ ልጆቹንና ራሱን እንደሚገድል ዝቶብኛል” ትላለች። “አንድ ቀን ጉሮሮዬ ላይ መቀስ ሊሰካብኝ ነበር። ሌላ ጊዜ ደግሞ ሽጉጥ ጆሮ ግንዴ ላይ ደግኖ ምላጩን ሳበው! ደግነቱ ጥይት አልነበረውም። ሆኖም በድንጋጤ ልሞት ምንም አልቀረኝም ነበር።”

የዝምታ ቅርስ

እንደ ሮክሳና ሁሉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ጠበኛ በሆኑ ወንዶች በደል ይፈጸምባቸዋል። * ብዙዎቹ የሚደርስባቸውን መከራና ሥቃይ ከመናገር ዝምታን ይመርጣሉ። ጉዳዩን ማሳወቁ ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ይሰማቸዋል። በሚስቶቻቸው ላይ በደል የሚፈጽሙ ብዙዎቹ ባሎችም ቢሆኑ “ሚስቴ በትንሽ በትልቁ ትሸበራለች” ወይም “ማጋነን ትወዳለች” በማለት የሚቀርብባቸውን ውንጀላ ያስተባብላሉ።

ብዙ ሴቶች በገዛ ቤታቸው የበለጠ ደህንነት ሊሰማቸው ሲገባ ከአሁን አሁን ጥቃት ይደርስብኛል በሚል ፍርሃት ዘወትር ተሸማቅቀው መኖራቸው በጣም ያሳዝናል። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ሲታዘንለት የሚታየው ድርጊቱን የሚፈጽመው ሰው እንጂ ጥቃቱ የሚደርስባት ሴት አይደለችም። እንዲያውም አንዳንዶች ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ይደበድባል ብለው ለማመን በጣም ይቸገራሉ። ለምሳሌ አኒታ የተባለች አንዲት ሴት በሌሎች ዘንድ አክብሮት ያተረፈው ባሏ እያደረሰባት ስላለው በደል በተናገረች ጊዜ የገጠማትን ሁኔታ ተመልከት። “ከሚያውቁን ሰዎች አንዱ ‘እንዴት እንዲህ ያለውን የተከበረ ሰው ትወነጅያለሽ?’ አለኝ። ሌላው ደግሞ ራስሽ እያስቆጣሽው መሆን አለበት አለኝ! ባለቤቴ የሚፈጽመው ድርጊት ከተጋለጠም በኋላ እንኳ አንዳንዶቹ ጓደኞቼ ይሸሹኝ ጀመር። ‘ይህ የተለመደ የወንዶች ባሕርይ’ ስለሆነ ችዬ መኖር እንደነበረብኝ ተሰምቷቸዋል።”

አኒታ የደረሰባት ሁኔታ እንደሚያሳየው ባለ ትዳሮች በትዳር ጓደኞቻቸው ላይ የሚፈጽሙትን በደል ብዙዎቹ ሰዎች አምነው ለመቀበል ይቸገራሉ። አንድ ሰው እወዳታለሁ በሚላት ሴት ላይ እንዲህ ጨካኝ እንዲሆን የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? የኃይል ድርጊት ሰለባዎችስ እርዳታ ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 በዚህ ተከታታይ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.7 ብዙ ወንዶችም የኃይል ድርጊት እንደሚፈጸምባቸው እናምናለን። ሆኖም ከወንዶቹ ይበልጥ ለጉዳት የተጋለጡት ሴቶቹ እንደሆኑና የሚደርስባቸውም ጉዳት በጣም የከፋ እንደሆነ የተካሄዱት ጥናቶች አመልክተዋል። በመሆኑም እነዚህ ርዕሶች በሴቶች ላይ በሚደርሰው በደል ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በቤት ውስጥ የሚፈጸም በደል ብዙ ዓይነት መልክ አለው

የተባበሩት መንግሥታት በሴቶች ላይ የሚፈጸምን በደል ለማስቀረት ያወጣው ድንጋጌ እንደሚለው ከሆነ “በሴቶች ላይ የሚፈጸም በደል” የሚለው ሀረግ “በይፋም ይሁን በድብቅ በሴቶች ላይ የሚፈጸምን አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም አእምሯዊ ጉዳት ወይም ሥቃይ የሚያስከትል ወይም ሊያስከትል የሚችል በጾታ ላይ የተመሠረተ በደል” የሚያመለክት ከመሆኑም በላይ “እንዲህ ያሉትን ድርጊቶች ለመፈጸም መዛትን፣ ያልፈለጉትን ነገር እንዲያደርጉ ማስገደድን ወይም በማን አለብኝነት ነፃነታቸውን መግፈፍን ይጨምራል።” በተጨማሪም ይህ በደል “ድብደባን፣ በሕፃናት ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ወሲባዊ በደል፣ ከጥሎሽ ጋር በተያያዘ የሚፈጸም በደልን፣ በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸምን የግዳጅ ወሲብ፣ የሴቶችን ግርዛትና ሌሎች በሴቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ባሕላዊ ልማዶችን ጨምሮ በቤተሰብና በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ አካላዊ፣ ወሲባዊና ሥነ ልቦናዊ በደል መፈጸምን” ያካትታል።