በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሰውነትህ ውስጥ ያለ ረቂቅ “የጭነት መኪና”

በሰውነትህ ውስጥ ያለ ረቂቅ “የጭነት መኪና”

በሰውነትህ ውስጥ ያለ ረቂቅ “የጭነት መኪና”

ከአምስት ቀናት በፊት አንዲት ፍሬ ሕዋስ (nucleus) የያዘ ሕዋስ ነበር። ሕዋሱ ከፍተኛ ዕድገት የሚያደርግበትና የሚራባበት ወቅት ካለፈ በኋላ ግን በኃይል በመኮማተር ፍሬ ሕዋሱን ገፍቶ ያስወጣዋል። በዚህ ጊዜ ሬቲኩሎሳይት ተብሎ ይጠራል። ይህ ምንድን ነው? በሰውነትህ ውስጥ ካለው ደም ጋር ለመቀላቀል የተቃረበ ዕድገቱን ያላጠናቀቀ ቀይ የደም ሕዋስ ነው። ከሁለት እስከ አራት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ዕድገቱን ያጠናቀቀ ቀይ የደም ሕዋስ ይሆናል።

ይህ ትንሽ ሕዋስ በብዙ መልኩ ከጭነት መኪና ጋር ይመሳሰላል። “ጭነት” የሚሸከመው ሄሞግሎቢን በተባለው ኦክሲጅን የሚያመላልስ ፕሮቲን አማካኝነት ሲሆን በአራት ወር የሕይወት ዘመኑ በመላ ሰውነትህ ውስጥ ወደ 250 ኪሎ ሜትር ገደማ እንደሚጓዝ ይገመታል። ሰውነትህ ውስጥ ወደ አሥር ቢልዮን ገደማ ፀጉሮዎች (ጥቃቅን የደም ሥሮች) ያሉ ሲሆን አጠቃላይ ርዝመቱ የምድርን ዙሪያ ሁለት እጥፍ ያክላል። በመላው የሰውነት ክፍሎች ኦክሲጅን ለማዳረስ በትሪሊዮኖች የሚቆጠሩ ኤሪትሮሳይትስ (ቀይ የደም ሕዋሳት) ያስፈልጋሉ።

ይህ በጣም አነስተኛ የሆነ “የጭነት መኪና” በሰውነትህ የደም ዝውውር ሥርዓት ውስጥ ያለማቋረጥ ይጓዛል። የሚጓዝበት ፍጥነት እንደ ሁኔታው ይለያያል። ሕዋሱ በሴኮንድ ወደ 120 ሴንቲ ሜትር ገደማ በሚሆነው የመጨረሻ ፍጥነቱ የሚጓዘው ከልብ ተነስቶ የደም “ዐቢይ አውራ ጎዳና” በሆነው ዐቢይ ደም ወሳጅ በኩል ሲያልፍ ነው። ሕዋሱ ወደ ሰውነት “መገንጠያ መንገዶች” ሲገባ ቀስ በቀስ ፍጥነቱ እየቀነሰ ሄዶ ጫፍ ላይ ወዳሉት ፀጉሮዎች ሲደርስ በሴኮንድ 0.3 ሚሊ ሜትር ይጓዛል።

የደም ሕዋስ የሚመነጨው ከየት ነው?

ጤነኛ በሆኑ ሰዎች አብዛኛው የደም ሕዋስ የሚዘጋጀው መቅኒ ውስጥ ነው። በየቀኑ ለእያንዳንዱ ኪሎ የሰውነትህ ክብደት አጥንትህ ውስጥ ያለው መቅኒ 2.5 ቢልዮን ቀይ ሕዋሳት፣ 1 ቢልዮን ግራኑሎሳይትስ (ነጭ ሕዋሳት) እና 2.5 ቢልዮን ደም አርጊ ሕዋሳት ያዘጋጃል። ይህ ከዚያ በማይተናነስ መጠን በየቀኑ የምታጠፋውን ሕዋስ ይተካል። ጤናማ የሆነ ዐዋቂ ሰው በየሴኮንዱ የሚያጠፋቸውን በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ቀይ የደም ሕዋሳት መልሶ ይተካል።

ዕድገቱን ያልጨረሰ ቀይ የደም ሕዋስ ከመቅኒ ወደ ደም ዝውውር ለመግባት መቅኒ ውስጥ ወዳሉት ትንንሽ የደም ሥሮች (ሳይነሶይድስ) የውጭ ግድግዳ በመቅረብ የመፍለሻ ቀዳዳ በሚባለው ጠባብ ቀዳዳ በኩል ሾልኮ ከደም ጋር ይቀላቀላል። ለሌሎች ሦስት ቀናት ያህል ሕዋሱ ሄሞግሎቢን ማዘጋጀቱን ይቀጥላል። ከዚያ በኋላ ግን ዕድገቱን ያጠናቀቀ ቀይ የደም ሕዋስ ወይም ኤሪትሮሳይት እንደመሆኑ መጠን ሄሞግሎቢን ማዘጋጀቱን ያቆማል።

ዐቢይ እና ሳምባዊ የደም ዝውውር

በ17ኛው መቶ ዘመን ዶክተሮች ሁለት ዓይነት የደም ዝውውሮች መኖራቸውን ተገነዘቡ። በዐቢይ የደም ዝውውር የሰውነትህ ረቂቅ “የጭነት መኪናዎች” ማለትም ቀይ ሕዋሳት ከልብህ ተነስተው ወደ ሰውነትህ ህብረሕዋሳት ያመራሉ። እዚያ ሲደርሱ የጫኑትን ኦክሲጅን አራግፈው በካርቦን ዳይኦክሳይድ መልክ የተቀመጠውን ቆሻሻ ይጭናሉ። ይህ ሂደት ውስጣዊ ትንፈሳ ተብሎ ይጠራል። ከዚያም ቀይ ሕዋሳቱ ወደ ልብ ይመለሳሉ። በሳምባዊ የደም ዝውውር “የጭነት መኪናዎቹ” የሚላኩት ወደ ሳምባ ነው። እዚያ ካርቦን ዳይኦክሳይድ አራግፈው ኦክሲጅን ጭነው ይመለሳሉ። ስለዚህ ሳምባዊ የደም ዝውውር አየር ወደ ሰውነትህ እንዲገባና እንዲወጣ ያደርጋል።

የቀይ ደም ሕዋሳት እጥረት ሲፈጠር

አንዳንድ ጊዜ የቀይ ደም ሕዋሳቱ መጠን ከተለመደው በታች ይሆናል። ይህን ሁኔታ ዶክተሮች ደም ማነስ ብለው ይጠሩታል። የተለያዩ መንስዔዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል (1) በቀይ የደም ሕዋሳት መፈጠር ወይም ዕድገት ላይ የሚከሰት እክል (2) የሚሞቱት ሕዋሳት ቁጥር መበራከት እና (3) ከፍተኛ የደም መፍሰስ ይገኙበታል። ደም ማነስ ሥር የሰደደ ብግነት ወይም እብጠት በሚኖርበትም ጊዜ ይከሰታል።

ደም ውስጥ ያለው የብረት መጠን በጣም ሲበዛ ወይም ሲያንስ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። የብረቱ መጠን በጣም አነስተኛ ሲሆን ቀይ ሕዋሶቹ የዕድገት ሂደታቸውን በትክክል አይጨርሱም። ከዚህም የተነሳ ሕዋሶቹ ከተለመደው ውጪ አነስተኛ መጠንና የገረጣ ቀለም ይኖራቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ የብረትን መጠን የሚጨምር መድኃኒት መውሰድ ለችግሩ መፍትሄ ያስገኛል። አንዳንድ ጊዜ በደም ውስጥ ያለው የብረት መጠን በጣም ከፍተኛ ይሆናል። ይህ የሚከሰተው ጉዳት የደረሰባቸው ቀይ ሕዋሳት ተቀድደው በደም ሥርዓት ውስጥ ብረት ሲረጭ ነው። በዚህ ጊዜ የሰውነት ክፍሎች ባጠቃላይ ቀስ በቀስ ይመረዛሉ። በተለይ የልብ መመረዝ ከሁሉ የከፋ ነው። በዚህ ችግር የሚሰቃዩ በሽተኞች ባመዛኙ ሥር በሰደደ የልብ ሕመም ሳቢያ ለሞት ይዳረጋሉ።

የደም ሕዋሳት በሰውነትህ ውስጥ የሚያከናውኑትን ተግባር በሙሉ ዘርዝሮ ለመጨረስ ብዙ መጽሐፍ ማስፈለጉ አይቀርም። ይሁንና እዚህ ላይ በጥቂቱ የተገለጸው አስደናቂ የሆነው ውስብስብ አፈጣጠራቸው ሕይወትን የነደፈውና የፈጠረው አካል ያለውን ጥበብ በጉልህ እንደሚያሳይ ግልጽ ነው። በጥንት ጊዜ ከነበሩት አምላኪዎቹ አንዱ የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለውን ታላቅ ፈጣሪ አስመልክቶ “በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን” ብሏል።​—⁠ሥራ 17:​28