አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክለኛ ነውን?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክለኛ ነውን?
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎች ኃይላቸውን አላግባብ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። በ20ኛው መቶ ዘመን ብቻ 170,000,000 የሚሆኑ ሰዎች በራሳቸው ፖለቲካዊ አገዛዝ እንደተገደሉ አንድ ግምታዊ አኃዝ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል እንደተናገረው ምንጊዜም ሰው ሰውን የሚገዛው ለጉዳቱ ነው።—መክብብ 8:9
አንዳንዶች የሰው ልጅ ኃይሉን አላግባብ እንደሚጠቀምበት ሲመለከቱ አምላክ ጠላቶቹን ለማጥፋት ኃይሉን የሚጠቀምበትን መንገድ በተመለከተ ጥርጣሬ ሊያድርባቸው ይችላል። አይሁዳውያን አምላክ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት የተስፋይቱ ምድር ነዋሪዎች የነበሩትን ከነዓናውያን አላጠፏቸውምን? (ዘዳግም 20:16, 17) ደግሞስ አምላክ ራሱ እርሱን የሚቃወሙትን መንግሥታት በሙሉ እንደሚፈጫቸውና እንደሚያጠፋቸው ተናግሮ የለምን? (ዳንኤል 2:44) አንዳንድ ቅን ሰዎች አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ሁልጊዜ ፍትሐዊ ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳባቸዋል።
ኃይልን አላግባብ መጠቀም
ኃይልን መጠቀም መቻል ለአንድ መንግሥት ሕልውና ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ያወጣቸው ድንጋጌዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ የማይችል መስተዳድር ጥርስ እንደሌለው አንበሳ ነው። ለምሳሌ ያህል ፖሊስ አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን አላግባብ እንደሚያንገላታ ቢታወቅም እንኳ የፖሊስ ኃይል ጭራሽ አያስፈልግም ሊል የሚችል ይኖራልን? ደግሞስ ሕግን የማስፈጸም ኃይል ያለው የፍትሕ ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን የሚክድ ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ሊኖር ይችላልን?
የኃይል እርምጃን በማውገዝ በሰፊው የሚታወቁት ሞሃንዳስ ጋንዲ አንድ ጊዜ እንዲህ ብለው ነበር:- “አንድ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ደም የሸተተው ሰው ሰይፍ በእጁ ይዞ ፊቱ ያገኘውን ሁሉ መግደል ቢጀምርና ማንም ከነሕይወቱ ሊይዘው ባይደፍር ይህንን አእምሮው የተቃወሰ ግለሰብ እስከ ወዲያኛው የሚያሰናብት ማንም ሰው ለሕዝቡ እንደ ባለውለታ እንደሚቆጠር የታወቀ ነው።” አዎን፣
ጋንዲ እንኳን ኃይል መጠቀም የሚያስፈልግባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ተገንዝበው ነበር።በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የተረጋጋ ኅብረተሰብ እንዲኖር ኃይል የመጠቀም አስፈላጊነት አሌ የማይባል ነው። ስለዚህ በአጠቃላይ ሲታይ ሰዎች ኃይል መጠቀምን ሲያወግዙ ኃይልን አላግባብ መጠቀምን መቃወማቸው ነው።—መክብብ 4:1-3
“መንገዶቹ ሁሉ ፍትህ ናቸውና”
አምላክ ኃይሉን አላግባብ እንደተጠቀመበት የሚያሳይ አንድም የታሪክ ማስረጃ የለም። ኃይሉን አምባገነናዊ በሆነ መንገድ ለመግዛት አይጠቀምበትም። በፍቅር ተገፋፍተን እንድናመልከው ይፈልጋል። (1 ዮሐንስ 4:18, 19) እንዲያውም አምላክ የተሻለ አማራጭ ካለ ኃይል መጠቀምን አይመርጥም። (ኤርምያስ 18:7, 8፤ 26:3, 13፤ ሕዝቅኤል 18:32፤ 33:11) የኃይል እርምጃ መውሰድ ከመረጠም ማንኛውም ሰው አካሄዱን ማስተካከል እንዲችል በቅድሚያ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (አሞጽ 3:7፤ ማቴዎስ 24:14) ጨካኝና ፈላጭ ቆራጭ አምላክ ቢሆን እንደዚህ ያደርግ ነበር?
አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ስልጣንን ከሚጠቀሙት ሰዎች ድርጊት ጋር በምንም ዓይነት አይነጻጸርም። ሙሴ ስለ ይሖዋ ሲናገር “መንገዶቹ ሁሉ ፍትህ ናቸውና። የፍርድ ማጓደል የሌለበት የታማኝነት አምላክ . . . ነው” ብሏል። (ዘዳግም 32:4 NW ) የአምላክ መንግሥት እንደ ሰብዓዊ አምባገነን መንግሥታት ቀጥቅጠህ ግዛ የሚል መርህ የለውም። እስካሁን ድረስ ኃይሉን የተጠቀመው ፍጹም ከሆነው የፍቅር፣ የጥበብና የፍትሕ ባሕርይው ጋር በሚስማማ መንገድ ነው።—መዝሙር 111:2, 3, 7፤ ማቴዎስ 23:37
ለምሳሌ ክፉዎችን በጥፋት ውኃ ያጠፋው ለብዙ ዓመታት ማስጠንቀቂያ ካስነገረ በኋላ ነው። ማንኛውም ሰው መርከቡ ውስጥ መግባትና ሕይወቱን ማትረፍ ይችል ነበር። እንዲህ ያደረጉት ግን ስምንት ሰዎች ብቻ ናቸው። (1 ጴጥሮስ 3:19, 20፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) በኢያሱ ዘመንም እስራኤላውያን ምግባረ ብልሹ የሆኑትን ከነዓናውያን ያጠፉት ከ400 ዓመት በፊት የተነገረውን የአምላክን ፍርድ ለማስፈጸም ነበር። (ዘፍጥረት 15:13-21) በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ከነዓናውያኑ ይሖዋ ለእርሱ የተመረጡ ሕዝብ አድርጎ እስራኤላውያንን እንደወሰደ የሚያሳዩትን ጠንካራ ማስረጃዎች ሳይገነዘቡ እንደማይቀሩ የታወቀ ነው። (ኢያሱ 2:9-21፤ 9:24-27) ቢሆንም ከገባዖናውያን በስተቀር ምሕረትን የጠየቀም ሆነ ሰላምን በመሻት የመጣ አንድም የከነዓን መንግሥት አልነበረም። ከዚያ ይልቅ ከነዓናውያኑ በይሖዋ ላይ ልባቸውን ማደንደን መርጠዋል።—ኢያሱ 11:19, 20
አምላክ ስልጣኑ አለው
አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበትን መንገድ ለመረዳት ስንሞክር መሠረታዊ ሐቅ ከሆነው በአምላክ ፊት ካለን ቦታ መጀመር አለብን። ነቢዩ ኢሳይያስ “እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ” በማለት በትህትና አምኗል። (ኢሳይያስ 64:8) አምላክ የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ኃይሉን በፈለገው መንገድ ሊጠቀምበት እንደሚችል ግልጽ ነው። እንደ ሰሎሞን እኛም የአምላክን ስልጣን አምነን በመቀበል እንዲህ ማለት እንችላለን:- “የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና፤ ይህንስ ለምን ታደርጋለህ? ማን ይለዋል?”—መክብብ 8:4፤ ሮሜ 9:20, 21
አምላክ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ምድራዊ ሕይወት መስጠትም ሆነ መልሶ መውሰድ ይችላል። በእርግጥም ሰዎች አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበትን መንገድ በተመለከተ ጥያቄ የማንሳት መብቱም ሆነ የአእምሮ ብቃቱ የላቸውም። ሰው አስተሳሰቡን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ማስማማትን መማር አለበት። “ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን?” በማለት ይሖዋ ጥያቄ አቅርቧል።—ሕዝቅኤል 18:29፤ ኢሳይያስ 45:9
ይሖዋ ኃይላቸውን አላግባብ የሚጠቀሙበትንና የሌሎችን መብት የሚረግጡትን ሰዎች ከምድር ላይ ለማስወገድ የሚያነሳሳው የፍትህ ባሕርይውና ለሰዎች ያለው ፍቅር ነው። ይህ የኃይል እርምጃ ሰላም ወዳድ የሆኑ የሰው ዘሮች የሚናፍቁትን ተስማሚ ሁኔታ ያሰፍናል። (መዝሙር 37:10, 11፤ ናሆም 1:9) በዚህም የአምላክ አገዛዝ ፍትሐዊነትና ትክክለኛነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይረጋገጣል።—ራእይ 22:12-15