በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ግንባር ቀደሞቹ ቀሳፊ በሽታዎች

“በቫይረሶች፣ በባክቴሪያዎችና በጥገኛ ተውሳኮች የሚመጡ በሽታዎች አሁንም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዙዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ግንባር ቀደሞች ናቸው” ሲል ፍራንክፈርተር አልጌማይነ ዞንታግስሳይቱንግ ገልጿል። በሦስት በሽታዎች ብቻ ማለትም በኤድስ፣ በወባና በሳንባ ነቀርሳ “በየዓመቱ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያዙ ከመሆኑም በላይ ወደ 10 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ።” ጋዜጣው እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በ20ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ብዙ ጠበብት እንኳ ሳይቀሩ ተዛማች በሽታዎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እየተዳከመ ይሄዳል የሚል እምነት አድሮባቸው ነበር። ሆኖም የኤድስ፣ የእብድ ላም በሽታና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአፍ ተግር በሽታ ወረርሽኞች ከተከሰቱ ወዲህ በግልጽ እንደታየው ተዛማች የሆኑ ጀርሞች [አሁንም ድረስ] በሰውና በእንስሳት ላይ አስፈሪ ጥላ እንዲያጠላ አድርገዋል። . . . በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ቦታዎች በጣም አደገኛ የሆኑ ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች ፈጽሞ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተከስተዋል።” ብዙውን ጊዜ ለዚህ መንስኤ የሚሆነው የራሳቸው በዓይን የማይታዩት ዘአካላት ተፈጥሯዊ ባሕርይ ቢሆንም የሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤና ሁኔታም እነዚህ በሽታ አማጭ ዘአካላት እንዲከሰቱና እንዲዛመቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

በሃይማኖታዊ ቅርሶች ላይ የሚካሄድ ዘረፋ

“ሕጉ ቢጠብቅም እንኳ በአውሮፓ በሃይማኖታዊ ቅርሶች ላይ የሚካሄደው ስርቆትና ንግድ ምንም የመቀነስ አዝማሚያ አልታየበትም” ሲል ላ ክርዋ የተባለው የፈረንሳይ የካቶሊክ ጋዜጣ አስተያየቱን ሰጥቷል። ከሚሰረቁት ቅርሶች መካከል መስቀል፣ የተለያዩ ቁሳቁሶች፣ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ዕቃዎች፣ ቅርጻ ቅርጾች፣ የቀለም ቅቦች አልፎ ተርፎም መሠዊያዎች ይገኙበታል። ዓለም አቀፉ የሙዚየሞች ምክር ቤት እንዳለው ከሆነ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቼክ ሪፑብሊክ ከ30, 000 እስከ 40, 000 የሚሆኑ ቅርሶች የተሰረቁ ሲሆን በኢጣሊያ ደግሞ ከ88, 000 በላይ ቅርሶች ተሰርቀዋል። በተጨማሪም 87 ካቴድራሎች ያሏት ፈረንሳይም ዋነኛ የሌቦች ዒላማ ሆናለች። ከ1907 እስከ 1996 ድረስ ባሉት ዓመታት “ታሪካዊ መታሰቢያዎች” ተደርገው የሚታዩ ወደ 2, 000 የሚጠጉ ዕቃዎች በፈረንሳይ ከሚገኙ ሃይማኖታዊ ተቋሞች ውስጥ የተዘረፉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የተመለሱት ከ10 በመቶ አይበልጡም። ወደ ቤተ ክርስቲያናት በቀላሉ መግባት የሚቻል በመሆኑና ብዙውን ጊዜ ጥበቃው የላላ በመሆኑ እንዲህ ያለውን ዘረፋ መቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ ነው።

አደገኛ እየሆነ የመጣው የለንደን የውኃ መጠን

በለንደን “[ከተማይቱን] ከታች እንዳያጥለቀልቃት የተሰጋውን ውኃ በፓምፕ ለማውጣት ጉድጓዶች እየተቆፈሩ ነው” ይላል ዚ ኢኮኖሚስት ያወጣው ዘገባ። በለንደን ትራፋልጋር አደባባይ ከመሬት በታች ያለው ውኃ በአሁኑ ጊዜ ወደ ላይ በመጨመር በ40 ሜትር ጥልቀት ላይ ይገኛል። ኢንዱስትሪዎች በሚልዮኖች ጋሎን የሚቆጠር ውኃ ከመሬት ውስጥ ያወጡ በነበረበት ባለፈው ምዕተ ዓመት መጀመሪያ ላይ 93 ሜትር ጥልቀት ላይ ይገኝ እንደነበር ይገመታል። በዓመት ወደ 3 ሜትር ገደማ ወደ ላይ ከፍ የሚል ሲሆን የለንደንን የምድር ውስጥ የባቡር መስመር፣ የምድር ውስጥ የኤሌክትሪክ መስመሮችና በከተማይቱ ውስጥ ያሉትን በርካታ ሕንፃዎች መሠረት አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። ወደ 50 የሚጠጉ ጉድጓዶች መቆፈር እንዳለባቸው ተገምቷል። “የአካባቢ ጥበቃ ድርጅቱ እንደገመተው ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በለንደን ከመሬት በታች በየቀኑ ወደ [50 ሚልዮን ሊትር (10 ሚልዮን ጋሎን)] ውኃ በፓምፕ ይወጣል” ሲል መጽሔቱ ዘግቧል። ይሁንና ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ማድረግ እንዲቻል ይህ አኃዝ በአሥር ዓመት ውስጥ በእጥፍ ማደግ አለበት።

‘የምናስበውን ያህል የተለየን ፍጡራን አይደለንም’

“ራሳችንን ከፍ አድርገን የምንመለከትበት ምንም ምክንያት እንደሌለ የአሁኑን ያህል የተገነዘብንበት ጊዜ የለም” ይላል ኒው ሳይንቲስት። “ምንም እንኳ በሰው ልጅ ጄኖም ውስጥ ያለውን ኬሚካላዊ ቅንብር ማወቅ በመቻላችን የምንኩራራ ቢሆንም ጄኖሙ ራሱ ግን የምናስበውን ያህል የተለየን ፍጡራን እንዳልሆንን ያስገነዝበናል። እኛ ያሉን ጂኖች ብዛት ከአንድ ባክቴሪያ ጂኖች አምስት ጊዜ እጥፍ፣ ከአንድ ትል ጂኖች አንድ ሦስተኛ ጊዜና ከአንድ ዝንብ ጂኖች ሁለት ጊዜ እጥፍ ገደማ ብቻ እንደሚበልጥ ተረጋግጧል።” በተጨማሪም “40 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ጂኖቻችን ወስፋትና መሰል ትላትሎች ካሏቸው ጂኖች ጋር፣ 60 በመቶዎቹ ከትንኝ ጂኖች ጋር እና 90 በመቶዎቹ ከአይጥ ጂኖች ጋር ተመሳሳይ ናቸው።” ስለ ሰው ልጅ ጄኖም ማወቃችን ዘርን በተመለከተ ያለንን አመለካከትም እንድንለውጥ ያደርገናል ይላል መጽሔቱ። ሁለት ግለሰቦች ሊመሳሰሉና የአንድ ዘር አባላት ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ጂኖቻቸው በጎሳ ፈጽሞ ከማይገናኙ ሁለት ሰዎች በበለጠ ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል። የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ሉዊጂ ካቫልሊ-ስፎርትሳ “የአንድ ዘር አባላት በሆኑ ሰዎች መካከልም እንኳ ከፍተኛ ልዩነት ያለ በመሆኑ በተለያዩ ዘሮች መካከል ልዩነት እንዳለ አድርጎ ማሰቡ ሞኝነት ነው” ብለዋል።

የታሸገ ውኃና የቧንቧ ውኃ

“የታሸገ ውኃ በጣም እየተለመደ በመምጣቱ በዓለም ዙሪያ ከ700 በላይ ዓይነት የታሸገ ውኃ ምርቶች ይገኛሉ” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። ሆኖም “ብዙውን ጊዜ በውድ ዋጋ በሚሸጠው የታሸገ ውኃና በቧንቧ ውኃ መካከል ያለው ልዩነት የውኃ መያዣው ብቻ ነው።” ዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት (ደብሊው ደብሊው ኤፍ) እንዳመለከተው ከሆነ “በብዙ አገሮች፣ የታሸገ ውኃ ምንም እንኳ 1, 000 ጊዜ እጥፍ የበለጠ ዋጋ ቢያወጣም ከቧንቧ ውኃ ይበልጥ ንጹሕ ወይም አስተማማኝ ላይሆን ይችላል።” የቧንቧ ውኃ መጠቀም የገንዘብ ወጪን ለመቀነስ ብቻ ሳይሆን የአካባቢ ብክለትንም ለመቀነስ ይረዳል። ውኃን በፕላስቲክ ኮዳዎች አሽጎ ለመሸጥ በየዓመቱ 1.5 ሚልዮን ቶን ፕላስቲክ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን “የፕላስቲክ ኮዳዎቹ በሚመረቱበት ጊዜም ሆነ በሚወገዱበት ጊዜ የሚፈጠሩት መርዛማ ኬሚካሎች በአየር ጠባይ ላይ ለውጥ የሚያስከትሉ ጋዞች ከአየሩ ጋር እንዲደባለቁ ሊያደርጉ ይችላሉ።” የደብሊው ደብሊው ኤፍ ኢንተርናሽናል የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ቢክሻም ጉጃ እንዳሉት ከሆነ “የታሸገ ውኃ አምራች በሆነው ኢንዱስትሪ ላይ ከሚካሄደው ቁጥጥር የበለጠ በአውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ በቧንቧ ውኃ ላይ ክትትል ለማድረግ የሚያስችሉ መስፈርቶች አሉ።”