በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለልጆቻችሁ ማንበብ ለምን አስፈለገ?

ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለልጆቻችሁ ማንበብ ለምን አስፈለገ?

ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለልጆቻችሁ ማንበብ ለምን አስፈለገ?

“የተጎሰቋቆለና . . . የኦቾሎኒ ቅቤ የተቀባባ መጽሐፍ እየጎተተች መጣችና ጭኔ ላይ ወጥታ ለመቀመጥ እየተንጠላጠለች . . . ‘አስነብበኝ፣ አባባ፣ አስነብበኝ’ አለችኝ።”—⁠ዶክተር ክሊፈርድ ሺመልስ የትምህርት ፕሮፌሰር

ልጆች አንድን ነገር የመቅሰም ችሎታቸው ፈጣን ነው። አንጎል በፍጥነት የሚዳብረው ከሦስት ዓመት ዕድሜ በታች ባለው ጊዜ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ። እንደ ማንበብ፣ ማንጎራጎር እና ፍቅር ማሳየት ያሉት የወላጆች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ለልጁ ጤናማ እድገት ወሳኝ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ዕድሜያቸው ከሁለት እስከ ስምንት ዓመት የሆኑ ልጆች ካሏቸው ወላጆች መካከል ለልጆቻቸው በየቀኑ የሚያነቡት ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው። ‘ለልጄ አነበብኩ አላነበብኩ ያን ያህል ለውጥ ያመጣልን?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል።

የንባብ ፍቅር ማሳደር

ባለሞያዎች ለልጆች ማንበብ በእርግጥ ለውጥ እንደሚያመጣ ይናገራሉ። ማንበብን ባህሉ ያደረገ ሕዝብ መፍጠር (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በኋለኛው የሕይወት ዘመን የተዋጣላቸው አንባቢዎች ለመሆን የሚያስችላቸውን እውቀት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ከሁሉ የተሻለው አማራጭ ድምፅን ከፍ አድርጎ ለልጆች ማንበብ ነው። በተለይ ይህን ማድረጉ ውጤታማ የሚሆነው ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት ባሉት ዓመታት ነው።”

ልጆች የሚነበቡላቸውን ታሪኮች ሲያዳምጡ በመጽሐፉ ገጾች ላይ ያሉት ፊደላት በንግግር ከምንጠቀምባቸው ቃላት ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ገና ከትንሽነታቸው መገንዘብ ይጀምራሉ። በመጻሕፍት ላይ ከሚቀርበው የቋንቋ አጠቃቀምም ጋር ይለማመዳሉ። ድምፅን ከፍ አድርጎ ስለ ማንበብ የሚናገር አንድ የመመሪያ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ለልጁ አንድ ነገር ባነበብንለት ቁጥር ‘የደስታ ስሜት’ የሚፈጥር መልእክት ወደ አእምሮው ማስተላለፋችን ነው። እንዲያውም ልጁ ለመጻሕፍትና ለጽሑፎች በአጠቃላይ ፍቅር እንዲያድርበት የሚያደርግ ማስታወቂያ ተብሎ ሊጠራ ይችላል።” በልጆቻቸው ውስጥ እንደዚህ ዓይነት የመጽሐፍ ፍቅር የሚኮተኩቱ ወላጆች በሕይወታቸው በሙሉ አንባቢ የመሆን ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋሉ።

በዙሪያቸው ያለውን ዓለም እንዲያውቁ መርዳት

ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለልጆቻቸው የሚያነብቡ ወላጆች ስለ ሰዎች፣ ስለ ቦታዎች እና ስለተለያዩ ነገሮች ጠቃሚ እውቀት እያስጨበጧቸው ነው። በመጻሕፍት አማካኝነት በአንጻራዊ ሁኔታ በትንሽ ወጪ ልጆች ዓለምን “እንዲዞሩ” ማድረግ ይቻላል። ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ እናቱ ታነብለት የነበረውን የሁለት ዓመቱን አንቶኒን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እናቱ እንዲህ ትላለች:- “አራዊት ወደሚጠበቁበት ቦታ ያደረገው የመጀመሪያ ጉብኝት ለሱ ድጋሚ የመጎብኘት ያህል ነበር።” ድጋሚ መጎብኘት? ትሉ ይሆናል። አዎን፣ ምንም እንኳን አንቶኒ የሜዳ አህዮቹን፣ አንበሶቹን፣ ቀጭኔዎቹንና ሌሎቹን እንስሳት በአካል ሲመለከት የመጀመሪያው ቢሆንም እነዚህን እንስሳት አስቀድሞ ያውቃቸው ነበር።

እናቱ እንዲህ በማለት አክላ ተናግራለች:- “አንቶኒ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከብዙ ሰዎች፣ እንስሳት፣ ከተለያዩ ነገሮችና አንዳንድ ሐሳቦች ጋር በመጻሕፍት አማካኝነት ተዋውቋል።” ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ ድምፅን ከፍ አድርጎ ለልጆች ማንበብ የሚኖሩበትን ዓለም በደንብ እንዲያውቁ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት

ልጆች ወደፊት በሚወስዷቸው እርምጃዎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዝንባሌዎች የሚያዳብሩት በእድገታቸው የመጀመሪያ ዓመታት ነው። ስለዚህ ወላጆች በመተማመን፣ እርስ በርስ በመከባበርና በመግባባት ላይ የተመሠረተ የቅርብ ግንኙነት ለማዳበር የሚያስችል መሠረት መጣል ይገባቸዋል። ንባብ በዚህ ረገድ እንደ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል።

ወላጆች ጊዜ ወስደው ልጆቻቸውን እቅፍ አድርገው ሲያነቡላቸው “እወድሃለሁ/ሻለሁ” ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። ፊቢ የተባለች በካናዳ የምትኖር እናት አሁን ስምንት ዓመት ለሆነው ልጅዋ ማንበብ ያስገኘውን ውጤት ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “እኔና ባለቤቴ እንደዚህ ማድረጋችን ናታን ከኛ ጋር ላለው የጠበቀ ግንኙነት ትልቅ አስተዋጽዎ እንዳደረገ ይሰማናል። ግልጽ ሆኖ ማንኛውንም ነገር ይነግረናል፤ ብዙውን ጊዜም የሚሰማውን ያጫውተናል። በመካከላችን ልዩ ትስስር ፈጥሯል።”

ሲንዲ ልጅዋ አንድ ዓመት ገደማ ከነበረችበትና ለአንድ ወይም ለሁለት ደቂቃ ያህል ቁጭ ብላ ማዳመጥ ከምትችልበት ጊዜ አንስቶ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ታነብላት ነበር። በዚህ ረገድ የባከነው ጊዜና የተደረገው ጥረት ውጤት አስገኝቷልን? ሲንዲ ስለሁኔታው ስትገልጽ “ወዳጃዊና የተረጋጋ መንፈስ የተንጸባረቀበት የንባብ ወቅት መኖሩ በራሱ ብዙውን ጊዜ አበጌል በትምህርት ቤት ስላጋጠማት ነገር ወይም ከጓደኛዋ ጋር ስለተፈጠረ ችግር እንድትነግረን ይገፋፋታል” ብላለች። እንደዚህ ዓይነት ምላሽ ቢያገኝ የማይደሰት የትኛው ወላጅ ነው? ድምፅን ከፍ አድርጎ ማንበብ በእርግጥም በወላጅና በልጅ መካከል የጠበቀ ትስስር እንዲኖር ያደርጋል።

ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ችሎታዎችን እንዲያዳብሩ መርዳት

ጠንካራ ቤተሰብ ለመመስረት የሚረዱ 3 ነገሮች (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ዛሬ ልጆቻችን ከቴሌቪዥንና ከሌሎች ምንጮች አእምሮን የሚያቆሽሹ ብዙ ነገሮች ስለሚቀስሙ ከራሳቸው የሥነ ምግባር መስፈርት ጋር ተስማምተው እንዲኖሩና ስለ ሕይወታቸው ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ለመርዳት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አእምሮአቸውን የሚያድስ፣ ማስተዋልና ጥበብ የሚሰጣቸው እንዲሁም በጎ ተጽዕኖ የሚሆናቸው ነገር ያስፈልጋቸዋል።” ገንቢና ጤናማ ተጽዕኖ ለማሳደር ከማንም የተሻለ አጋጣሚ ያላቸው ወላጆች ናቸው።

አንድ ልጅ በንግግርም ሆነ በጽሑፍ ራሱን መግለጽን እንዲማር በመጽሐፎች ውስጥ ከሚገኙት ውስብስብና በሥርዓት የተዋቀሩ ዓረፍተ ነገሮች ጋር መተዋወቁ ጠቃሚ ነው። ሕፃናት መጻሕፍት ያስፈልጓቸዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ አዘጋጅ ዶረቲ በትለር እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ግለሰብ የሚያፈልቀው ሐሳብ ጥራት በቋንቋ ችሎታው ላይ የተመካ ነው። ትምህርት በመቅሰምና የማሰብ ችሎታን በመጠቀም ረገድ ቋንቋ ዓቢይ ሚና ይጫወታል።” ውጤታማ በሆነ መንገድ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ ለጥሩ ግንኙነት የደም ሥር ነው።

ለልጆች ጥሩ መጻሕፍት ማንበብ መልካም ሥነ ምግባር እንዲያዳብሩ ሊረዳቸው ይችላል። ከልጆቻቸው ጋር የሚያነቡና ውይይት የሚያደርጉ ወላጆች ልጆቻቸው ችግሮችን የመፍታት ችሎታ እንዲያዳብሩ ይረዷቸዋል። ሲንዲ ለልጅዋ ለአበጌል ስታነብላት አበጌል በታሪኩ ውስጥ ላሉት ሁኔታዎች የምትሰጠውን ምላሽ በደንብ ትከታተላለች። “ወላጆች እንደመሆናችን መጠን ስውር ባሕርይዋን ይበልጥ ልናውቅና የተሳሳቱ አመለካከቶችን ገና ከመጀመሪያው እንድታስወግድ ልንረዳት እንችላለን።” በእርግጥም ለልጆች ጮክ ብሎ ማንበብ አእምሮንና ልብን ያሰለጥናል።

ንባቡን አስደሳች አድርጉት

ለልጆቻችሁ በምታነቡበት ጊዜ ዘና ያለ፣ ሥርዓት ያልበዛበትና የሚያስደስት ሁኔታ እንዲኖር በማድረግ “ሳይጨነቁ” የሚከታተሉበትን መንገድ ፍጠሩ። አስተዋይ ወላጆች ንባባቸውን መቼ ማቆም እንዳለባቸው ያውቃሉ። ሊና እንዲህ ትላለች:- “አንዳንድ ጊዜ ሁለት ዓመት የሆነው አንድሩ በጣም ይደክመውና ረዘም ላለ ጊዜ አርፎ አይቀመጥም። ስሜቱን እየተመለከትን የንባብ ፕሮግራማችንን እናሳጥረዋለን። አንድሩ ስለ ንባብ አሉታዊ ስሜት እንዲያድርበት ስለማንፈልግ ከሚችለው በላይ አንጫነውም።”

ድምፅን ከፍ አድርጎ ማንበብ በጽሑፍ የሰፈረውን ማነብነብ ማለት ብቻ አይደለም። ልባቸው ስቅል ብሎ እንዲከታተሏችሁ ለማድረግ የስዕል መጽሐፉን ገጽ መቼ እንደምትገልጡ ማወቅ አለባችሁ። ወጥ በሆነ መንገድ አንብቡላቸው። ድምፅን መለዋወጥና ማጥበቅ ታሪኩን ሕያው ያደርገዋል። በድምፃችሁ ውስጥ የሚንጸባረቀው የጋለ ስሜት ለልጃችሁ መረጋጋት ሊፈጥርለት ይችላል።

ልጃችሁ ንቁ ተሳታፊ ሲሆን የሚገኘውም ጥቅም የዚያኑ ያህል የላቀ ይሆናል። አልፎ አልፎ ቆም እያላችሁ ስሜቱን ለመግለጽ የሚያስችሉ ጥያቄዎችን አቅርቡ። አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉ መልሶችን በመስጠት የልጃችሁን መልስ አስፉ።

በመጽሐፍ ምርጫችሁ ረገድ ጠንቃቆች ሁኑ

ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ነገር ጥሩ መጽሐፍ መምረጥ መቻላችሁ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ደግሞ ቀደም ብሎ ዝግጅት ማድረግ ይጠይቃል። መጻሕፍቱን በጥንቃቄ ምረጡ፤ ገንቢ ወይም አስተማሪ መልእክት ባላቸውና ጥሩ ሥነ ምግባር የተንጸባረቀባቸው ታሪኮችን በያዙ መጻሕፍት ብቻ ተጠቀሙ። ሽፋኑን፣ ሥዕሎቹንና አጠቃላይ የአጻጻፍ ስልቱን በደንብ በመመልከት ለእናንተም ሆነ ለልጃችሁ የሚስቡ ሆነው ያገኛችኋቸውን መጻሕፍት ምረጡ። ልጆች ብዙውን ጊዜ አንድ ተመሳሳይ ታሪክ በተደጋጋሚ እንዲነበብላቸው ይጠይቃሉ።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ወላጆች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌን ወደውታል። * መጽሐፉ ወላጆች ከትናንሽ ልጆቻቸው ጋር ሆነው እንዲያነቡት ተብሎ የተዘጋጀ ሲሆን ልጆች ጥሩ አንባቢዎች እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን ጉጉትም ያሳድገዋል።

ለልጆቻቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያነብቡ ወላጆች ልጆቹ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የሚጠቅማቸውን ጥሩ የንባብ ልማድ እንዲያዳብሩ ይረዷቸዋል። ጆአን ስለ ልጅዋ ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “ጄኒፈር ትምህርት ቤት ከመግባትዋ በፊት ማንበብና መጻፍ መቻሏና ለንባብ ፍቅር ማሳደርዋ ትልቅ ነገር ቢሆንም ከዚህ ይበልጥ ግን ለታላቁ ፈጣሪያችን ለይሖዋ ፍቅር ማዳበር ችላለች። ጄኒፈር በምታደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ እንዲመራት በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መመካትን ተምራለች።” በእርግጥም ልጃችሁ አንድን ነገር እንዲማር ከምትረዱት ይልቅ ለዚያ ነገር ፍቅር እንዲያድርበት ብትረዱት የበለጠ ዋጋ ሊኖረው ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.24 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለልጃችሁ ስታነቡ

• ገና ሕፃናት እያሉ ጀምሩ።

• ልጃችሁ ተረጋግቶ ሊያዳምጥ የሚችልበትን ጊዜ ምረጡ።

• እናንተም ልጃችሁም የምትወዷቸውን ታሪኮች አንብቡ።

• በተቻላችሁ መጠን አዘውትራችሁና በስሜት አንብቡ።

• ጥያቄዎች በመጠየቅ ልጃችሁን አሳትፉት።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጭ]

Photograph taken at the Wildlife Conservation Society’s Bronx Zoo