መንትዮቹ ሕንጻዎች የተደረመሱበት ዕለት
መንትዮቹ ሕንጻዎች የተደረመሱበት ዕለት
መስከረም 11 ቀን 2001 በኒው ዮርክ ከተማ፣ በዋሽንግተን ዲ ሲ እና በፔንስልቬንያ የደረሱት ክስተቶች በሚልዮን ምናልባትም በቢልዮን በሚቆጠሩ የዓለም ነዋሪዎች አእምሮ ላይ በቀላሉ ሊሽር የማይችል ጠባሳ ጥለው አልፈዋል። ኒው ዮርክ በሚገኘው የዓለም የንግድ ማዕከልና ዋሽንግተን ውስጥ በሚገኘው የፔንታጎን ሕንፃ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን የሚገልጸውን ዜና በሰማህበት ወይም ባየህበት ወቅት የት ነበርክ?
ይህን የሚያክል ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት፣ ይባስ ብሎ ደግሞ ይህን የሚያክል ብዙ ሕይወት በቅጽበት መጥፋቱ መላውን የሰው ልጅ ቆም ብሎ እንዲያስብ አድርጎታል።
በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ልንሰጣቸውና ልንመርጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች ምን ያገኘነው ትምህርት አለ? እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች ራስን መሥዋዕት ማድረግ፣ ርኅራኄ፣ ጽናትና ራስ ወዳድ አለመሆን የመሳሰሉት መልካም የሰው ልጅ ባሕርያት በግልጽ እንዲታዩ ያስቻሉት እንዴት ነው? በዚህ ርዕስም ሆነ ቀጥሎ ባለው ርዕስ ለሁለተኛው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይሞከራል።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ታሪካቸውን ይናገራሉ
በኒው ዮርክ አደጋው እንደደረሰ ወዲያውኑ የመሬት ውስጥ ለውስጥ መጓጓዣው በመዘጋቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከታችኛው ማንሃተን የወጡት የብሩክሊንንና የማንሃተንን ድልድዮች በእግር ተሻግረው ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ዋና መሥሪያ ቤት ጽሕፈት ቤትና የፋብሪካ ሕንጻ በግልጽ ለማየት ይችሉ ነበር። ከአደጋው ያመለጡ አንዳንድ መጠለያ ፈላጊዎች ወደነዚህ ሕንጻዎች መጥተዋል።
የአንዲት የይሖዋ ምሥክር ልጅ የሆነችው አሊሻ (በስተቀኝ) በመጀመሪያ ከደረሱት መካከል ነበረች። መላ ሰውነትዋ በአመድና በአቧራ ተሸፍኗል። * እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “ወደ ሥራ በምሄድበት ባቡር ላይ እንዳለሁ ከዓለም የንግድ ማዕከል የሚወጣውን ጭስ ተመለከትኩ። አደጋው በደረሰበት አካባቢ ስደርስ መሬቱ በመስተዋት ስብርባሪ ተሸፍኗል። የቃጠሎው ትኩሳት ይሰማኝ ነበር። ሰዎች በሁሉም አቅጣጫዎች ይሯሯጣሉ። ፖሊሶች ሰዎችን ከአደጋው አካባቢ ለማስወጣት እየሞከሩ ነበር። የጦር ሜዳ ይመስል ነበር።
“መጠለያ ለማግኘት ወደ አንድ በቅርብ የሚገኝ ሕንጻ ሮጥኩ። በዚህ ጊዜ ሁለተኛው አውሮፕላን በስተደቡብ የሚገኘውን ሕንጻ ሲመታው የተፈጠረውን ፍንዳታ ሰማሁ። የነበረውን ትዕይንት በቃላት መግለጽ በጣም ያስቸግራል። አካባቢው በሙሉ በጥቁር ጭስ ተሸፈነ። ከአደጋው ቀጣና እንድንርቅ ተነገረን። ኢስት ሪቨርን አቋርጦ ወደ ብሩክሊን በሚሻገር ጀልባ ላይ ተጫንኩ። እንደተሻገርኩ ቀና ብዬ ስመለከት ‘WATCHTOWER’ የሚል ግዙፍ አርማ አየሁ። የእናቴ ሃይማኖት ዋና መሥሪያ ቤት ነው። ወዲያው ወደ ጽሕፈት ቤቱ ሕንጻ አመራሁ። የተሻለ እንክብካቤ ላገኝ የምችልበት ሌላ ቦታ እንደሌለ ተገንዝቤ ነበር። ለመተጣጠብና ወላጆቼን ደውዬ ለማነጋገር ቻልኩ።”
ዌንደል (በስተቀኝ) በሁለቱ ሕንጻዎች መካከል በሚገኘው ማርዮት ሆቴል በበረኝነት ይሠራ ነበር። እንዲህ በማለት የደረሰበትን ይተርካል:- “የመጀመሪያው ፍንዳታ በደረሰበት ጊዜ በሆቴሉ መግቢያ አዳራሽ ሥራ ላይ ነበርኩ። የሕንጻው ፍርስራሽ በያለበት ሲወድቅ ተመለከትኩ። ከመንገዱ ማዶ አሻግሬ ስመለከት በእሳት እየተቃጠለ ያለ ሰው መሬት ላይ ወድቆ አየሁ። ኮቴንና ሸሚዜን ቀድጄ አወለቅኩና እሳቱን ለማጥፋት ሮጥኩ። ሌላም መንገደኛ ሊረዳኝ መጣ። ሰውዬው ለብሶት የነበረው ልብስ በሙሉ ከጫማውና ከካልሲው በስተቀር ተቃጥሏል። ወዲያው የእሳት አደጋ ሠራተኞች መጥተው ሕክምና ወደሚያገኝበት ቦታ ወሰዱት።
“ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሲ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን የዜና ክፍል ባልደረባ የሆነው ብራያንት ገምበል ስለደረሰው ሁኔታ የዓይን ምሥክር ከሆነ ሰው
መረጃ ለማግኘት ስልክ ደወለ። በቨርጂንያ ደሴት የሚኖሩት ቤተሰቦቼ ዘገባውን በቴሌቪዥን ሲሰሙ በሕይወት ያለሁ መሆኔን አወቁ።”ቁመቱ 1 ሜትር ከ95 የሆነውና ፈርጠም ያለ ቁመና ያለው ዶናልድ የሚሠራው በዓለም የገንዘብ ማዕከል ሲሆን በነበረበት ሕንጻ 31ኛ ፎቅ ላይ ሆኖ ከፊት ለፊቱ የሚገኙትን መንትያ ሕንጻዎችና ማርዮት ሆቴልን አሻግሮ ይመለከት ነበር። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ያየሁት ነገር በጣም ስላስደነገጠኝ ክው ብዬ ቀረሁ። ብዙ ሰዎች ከሰሜኑ ሕንጻ መስኮቶች እየዘለሉና እየተወረወሩ ይወድቁ ነበር። በድንጋጤ እየተርበተበትኩ ከነበርኩበት ሕንጻ የቻልኩትን ያህል በፍጥነት ሮጥኩ።”
ሌላው ገጠመኝ ደግሞ በ60ዎቹ ዓመታት ዕድሜ በምትገኝ አንዲት እናትና በ40ዎቹ ዓመታት በሚገኙ ሁለት ሴት ልጆቿ ላይ የደረሰው ሁኔታ ነው። ሩትና እህቷ ጆኒ ከእናታቸው ከጃኒስ ጋር በመንትዮቹ ሕንጻዎች አጠገብ በሚገኝ ሆቴል አርፈው ነበር። ነርስ የሆነችው ሩት እንዲህ በማለት ትተርካለች:- “መታጠቢያ ቤት ውስጥ እንዳለሁ እናቴና እህቴ ቶሎ ውጪ እያሉ ሲጮሁ ሰማሁ። የነበርነው 16ኛው ፎቅ ላይ ሲሆን የሕንጻው ፍርስራሽ በያለበት ሲወድቅ ከበስተማዶ ለማየት ይችሉ ነበር። እንዲያውም እናቴ የአንድ ሰው ገላ አሽቀንጥረው እንደወረወሩት ነገር በአቅራቢያው የነበረን አንድ ጣሪያ ተሻግሮ ሲወድቅ አይታለች።
“ተጣድፌ ልብሴን አጠለቅኩና ፎቁን መውረድ ጀመርን። በጣም ብዙ ጩኸት ይሰማ ነበር። መንገድ ላይ ወጣን። ፍንዳታዎችን ከመስማታችንም በላይ የእሳት ነበልባሎች አየን። የስታተን ደሴት የጀልባ መጓጓዣ ወደሚገኝበት በስተደቡብ ወደሚገኘው ወደ ባትሪ መናፈሻ እንድንሸሽ ተነገረን። መንገድ ላይ እንዳለን የአስም በሽታ ከሚያሰቃያት እናታችን ተነጠልን። ከዚህ ሁሉ ጭስ፣ አመድና አቧራ እንዴት መትረፍ ትችላለች? ለግማሽ ሰዓት ያህል ፈለግናት፣ ግን ልናገኛት አልቻልንም። ይሁን እንጂ በጣም ብርቱና በቀላሉ የማትርበተበት ሴት እንደሆነች እናውቅ ስለነበረ በመጀመሪያ ላይ እምብዛም አልተጨነቅንም።
“በመጨረሻ ወደ ብሩክሊን ድልድይ እንድናመራና ወደ ማዶ እንድንሻገር አመለከቱን። በብሩክሊን በኩል ወደሚገኘው የድልድዩ ጫፍ ስንደርስና ‘WATCHTOWER’ የሚለውን ትልቅ አርማ ስንመለከት ምን ያህል እፎይታ እንደተሰማን ገምቱ! አሁን ከአደጋው እንዳመለጥን ተረዳን።
“ጥሩ አቀባበልና የማረፊያ ቦታ ተሰጠን። በተጨማሪም በቂ ልብስ ስላልነበረን ተጨማሪ ልብስ አገኘን። እናታችን ግን የት ደረሰች? ሌሊቱን በሙሉ በየሆስፒታሉ ብናጠያይቅም ልናገኛት አልቻልንም። በማግስቱ ጠዋት አምስት ተኩል አካባቢ መልእክት ደረሰን። እናታችን ምድር ቤት በእንግዳ መቀበያ ክፍል እየጠበቀችን ነበር! ምን አጋጥሟት ይሆን?”
እናቲቱ ጃኒስ ታሪኩን ትቀጥላለች። “ከሆቴሉ እየተጣደፍን ስንወጣ ከእኛ ጋር ልትወጣ ያልቻለችው አረጋዊት ወዳጄ ሁኔታ አሳሰበኝ። ተመልሼ ተሸክሜያት ልወጣ ፈለግኩ። ይህን ማድረግ ግን በጣም አደገኛ ነበር። በትርምሱ መካከል ከልጆቼ ተነጠልኩ። ቢሆንም ብዙ አላሳሰበኝም። ምክንያቱም በጣም አስተዋዮች ሲሆኑ ሩት ደግሞ የሠለጠነች ነርስ ነች።
“ፊቴን ባዞርኩበት ሁሉ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ብዙ
ሰዎች፣ በተለይ ልጆችና ጨቅላ ሕፃናት ነበሩ። የቻልኩትን ያህል ሰው ረዳሁ። አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች እንደጉዳታቸው ክብደት እየተለዩ ሕክምና እንዲያገኙ ወደሚደረግበት አካባቢ ሄድኩ። አቧራና ጥላሸት የተጋገረባቸውን ፓሊሶችና የእሳት አደጋ ሠራተኞች እጅና ፊት በማጠብ አገዝኳቸው። እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ቆየሁ። ከዚያ በኋላ ወደ ስታተን ደሴት በሚሄደው የመጨረሻ ጀልባ ተሳፈርኩ። ምናልባት ልጆቼ በዚያ መጠለያ አግኝተው ይሆናል ብዬ አሰብኩ። ግን አላገኘኋቸውም።“ጠዋት ላይ ወደ ማንሃተን በሚመለሰው የመጀመሪያ ጀልባ ላይ ልሳፈር ሞከርኩ። ግን የአደጋ ሠራተኛ ስላልሆንኩ ልሳፈር አልቻልኩም። በዚህ ጊዜ ረድቼው የነበረ አንድ ፖሊስ አየሁ። ጠራሁትና ‘ጆን! ወደ ማንሃተን መመለስ ያስፈልገኛል’ አልኩት። ‘ነይ ተከተይኝ’ አለኝ።
“ማንሃተን እንደደረስኩ ወደ ማርዮት ሆቴል አቀናሁ። አረጋዊቷን ወዳጄን የምረዳበት ዕድል አገኝ ይሆናል ብዬ አሰብኩ። ልረዳ የምችልበት ምንም መንገድ አልነበረም። ሆቴሉ ሙሉ በሙሉ ፈራርሷል። መሐል ከተማው ረጭ ብሏል። ፊታቸው በሐዘን ከተዋጠ የዛሉ ፖሊሶችና የእሳት አደጋ ሠራተኞች በቀር የሚታይ ነገር የለም።
“ወደ ብሩክሊን ድልድይ አቀናሁ። ወደ ድልድዩ ሌላኛ ጫፍ እየቀረብኩ ስሄድ በተደጋጋሚ አይቼው የነበረውን ‘WATCHTOWER’ የሚል አርማ ተመለከትኩ። ምናልባት ልጆቼን እዚያ አገኛቸው ይሆናል ብዬ አሰብኩ። እውነትም እንግዳ መቀበያው ክፍል መጥተው አገኙኝ። ምን ያህል ተቃቅፈን እንደተላቀስን ልትገምቱ ትችላላችሁ!
“በዚያ ሁሉ ጭስ፣ አቧራና አመድ መሃል አስሙ አንድም ጊዜ አልተነሳብኝም። በጣም የሚያስደንቅ ነው። እፈልግ የነበረው ሌሎችን መርዳት እንጂ ለሌሎች ሸክም መሆን ስላልነበረ ሳላቋርጥ እጸልይ ነበር።”
“በዚህ አካባቢ አውሮፕላን ማረፊያ የለም!”
በ20ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ሬቸል ለንቁ! ዘጋቢ እንደሚከተለው ብላለች:- “በታችኛው ማንሃተን የምኖርበት ሕንጻ በሚገኝበት ማዕዘን እየሄድኩ እንዳለሁ የአውሮፕላን ጩኸት ሰማሁ። ድምፁ በጣም ከፍተኛ ስለነበረ ቀና ብዬ ተመለከትኩ። ማመን አቃተኝ። በጣም ግዙፍ የሆነ አውሮፕላን ወደ መሬት እየወረደ ነው። ይህን በሚያክል ፍጥነት ወደ ቁልቁል የሚወርደው ለምንድን ነው ብዬ አሰብኩ። በዚህ አካባቢ አውሮፕላን ማረፊያ የለም! አብራሪው መቆጣጠር አቅቶት ይሆን? ወዲያው አንዲት ሴት ‘አውሮፕላኑ ሕንጻውን መታው!’ ብላ ስትጮህ ሰማሁ። ከበስተሰሜኑ ሕንጻ በጣም ግዙፍ የሆነ የእሳት ነበልባል ወጣ። በሕንጻው ውስጥ በጣም ትልቅ የጨለመ ክፍተት ተመለከትኩ።
“በሕይወቴ ይህን የመሰለ አሰቃቂ ነገር አይቼ አላውቅም። እውነት አልመሰለኝም። አፌን ከፍቼ በቆምኩበት ደርቄ ቀረሁ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁለተኛውም ሕንጻ በሌላ አውሮፕላን ተመታና ሁለቱም ሕንጻዎች ተደረመሱ። ብርክ ያዘኝ። ፈጽሞ ልቋቋም የማልችለው ሁኔታ ነበር!”
“መዋኘት ካለብኝም እዋኛለሁ”
የ16 ዓመቷ ደኒዝ ከዓለም ንግድ ማዕከል በስተደቡብ በኩል ትንሽ ራቅ ብሎ ከሚገኘው የአሜሪካን ስቶክ ኤክስቼንጅ ሕንጻ አጠገብ ወዳለው ትምህርት ቤቷ ገና መድረሷ ነበር። “3:00 ሰዓት ሞልቷል። ምንነቱን አልወቅ እንጂ አንድ ነገር እንደደረሰ አውቄያለሁ። የነበርኩት ትምህርት ቤቱ በሚገኝበት ሕንጻ 11ኛ ፎቅ ላይ ሲሆን የታሪክ ክፍለ ጊዜ ነበር። ሁሉም ተማሪዎች በፍርሃት ተውጠዋል። ያም ሆኖ አስተማሪዋ ፈተና እንድንወስድ ፈልጋ ነበር። እኛ ግን ወጥተን ወደቤታችን መሄድ ፈለግን።
“ወዲያው ሁለተኛው አውሮፕላን በስተደቡብ ያለውን ሕንጻ ሲመታው የነበርንበት ሕንጻ ተናወጠ። ይሁን እንጂ አሁንም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ አላወቅንም። አንድ ሰው ‘ሁለት አውሮፕላኖች መንትዮቹን ሕንጻዎች መምታታቸውን’ በመልእክት መቀበያ ራዲዮ አማካኝነት ለአስተማሪያችን ሲነግራት ሰማሁ። ‘ባለንበት መቆየት ምክንያታዊ አይደለም። ይህ የአሸባሪዎች ጥቃት ስለሆነ ቀጥሎ የስቶክ ኤክስቼንጅ ሕንጻ ይመታል’ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ ወጣን።
“ወደ ባትሪ ፓርክ በሩጫ ወረድን። ወደኋላ ዞር አልኩና ምን እየሆነ እንዳለ ተመለከትኩ። የደቡቡ ሕንጻ ሊደረመስ እንደተቃረበ ተመለከትኩ። በአካባቢው ያሉትም ሕንጻዎች መደርመሳቸው እንደማይቀር አሰብኩ። አፍንጫዬና ጉሮሮዬ በአመዱና በአቧራው ተዘግቶ ስለነበረ የምተነፍሰው በከፍተኛ ችግር ነበር። ‘መዋኘት ካለብኝ እዋኛለሁ’ ብዬ በማሰብ ወደ ኢስት ሪቨር እግሬ አውጭኝ አልኩ። እየሮጥኩ እንዳለሁ ይሖዋ እንዲያድነኝ እጸልይ ነበር።
“በመጨረሻ ወደ ኒው ጀርሲ በሚሄድ ጀልባ ላይ ተሳፈርኩ። እናቴ ልታገኘኝ የቻለችው ከአምስት ሰዓት በኋላ ቢሆንም ሕይወቴ ተርፏል!”
“ዛሬ የሕይወቴ መጨረሻ ይሆን?”
በፕሪንስተን፣ ኒው ጀርሲ የሚኖረው የ28 ዓመቱ ጃሽዋ በስተ ሰሜኑ ሕንጻ 40ኛ ፎቅ ላይ ያስተምር ነበር። እንዲህ በማለት የተከሰተውን ያስታውሳል:- “ድንገት ቦምብ የፈነዳ መሰለ። ሕንጻው ስለተንቀጠቀጠ ‘የምድር መናወጥ ይሆናል’ ብዬ አሰብኩ። ወደ ውጭ ስመለከት ለማመን የሚያዳግት ነገር አየሁ። ጭስና ፍርስራሽ በያለበት ይወረወር ነበር። ለተማሪዎቹ ‘የጀመራችሁትን ሁሉ ትታችሁ ቶሎ እንውጣ!’ አልኳቸው።
“በጭስ መታፈን ወደጀመሩት ደረጃዎች ወረድን። ከየቧንቧው ውኃ ይፈስ ነበር። በፍርሃት የተሸበረ ሰው ግን አልነበረም። ከሚነደው እሳት ጋር ፊት ለፊት እንዳንፋጠጥ በደህና ለመውጣት የሚያስችለንን መውረጃ ለመምረጥ እንዲያስችለን አለማቋረጥ እጸልይ ነበር።
“በሩጫ እየወረድኩ እንዳለሁ ‘ዛሬ የሕይወቴ መጨረሻ ይሆን?’ እያልኩ አስብ ነበር። ወደ ይሖዋ አለማቋረጥ እጸልይ ነበር። ወዲያው ያልተለመደ ዓይነት ሰላም ተሰማኝ። እንዲህ ያለ ውስጣዊ ሰላም ተሰምቶኝ አያውቅም። ያን ወቅት ፈጽሞ አልረሳውም።
“በመጨረሻ ከሕንጻው ስንወጣ ፖሊሶች ያገኙትን ሰው በሙሉ ከአካባቢው ያስወጡ ነበር። ወደ ሕንጻዎቹ ዞር ስል ሁለቱም ሕንጻዎች ተሰንጥቀው እንደተከፈሉ ተመለከትኩ። በቅዠት ዓለም ውስጥ ያለሁ መሰለኝ።
“ወዲያው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ትንፋሻቸውን ቀጥ ያደረጉ ይመስል አካባቢው አስፈሪ በሆነ ፀጥታ ተዋጠ። መላው ኒው ዮርክ ፀጥ ረጭ ያለ ይመስል ነበር። ከዚህ ተከትሎ የሰዎች የሲቃ ጩኸት ተሰማ። የደቡቡ ሕንጻ እንደቆመ መደርመስ ጀምሮ ነበር። የጭስ፣ የአመድና የአቧራ ማዕበል እየተምዘገዘገ መጣብን። ፊልም ላይ የሚታይ አስፈሪ ትዕይንት ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ በፊልም ላይ ሳይሆን በገሐዱ ዓለም እየተፈጸመ ያለ ሁኔታ ነበር። የጭሱ ደመና ሲደርስብን መተንፈስ አቃተን።
“ወደ ማንሃተን ድልድይ እንደደረስኩ መለስ ብዬ ስመለከት የሰሜኑ ሕንጻ በጣም ግዙፍ ከሆነው የቴሌቪዥን ማማው ጋር ሲደረማመስ አየሁ። ድልድዩን ማቋረጥ እንደጀመርኩ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ወደ ቤቴል በደህና እንድደርስ መጸለይ ጀመርኩ። በሕይወቴ በሙሉ እንደዚያ ቀን፣ ያን ቦታ በማየቴ የተደሰትኩበት ቀን የለም። በፋብሪካው ሕንጻ ግድግዳ ላይ በየቀኑ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚመለከቱት ‘በየዕለቱ የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን አንብብ!’ የሚለው ትልቅ ጽሑፍ ይታያል። ‘አሁን ደርሻለሁ፣ ጉዞዬን ማቆም የለብኝም’ ብዬ አሰብኩ።
“ያየኋቸውና ያሳለፍኳቸው ሁኔታዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት እንደሚኖርብኝ በማይረሳ ሁኔታ አስገንዝበውኛል።”
“ሰዎች ከሕንጻው ላይ ሲዘልሉ አየሁ”
የ22 ዓመቷ ጄሲካ የደረሰውን ሁኔታ የተመለከተችው ከመሬት ውስጥ ለውስጥ መጓጓዣ ጣቢያ እንደወጣች ነበር። “ቀና ብዬ ስመለከት አመድ፣ ፍርስራሽና ብዙ ዓይነት የብረት ቁርጥራጭ ሲወርድ አየሁ። በሕዝብ ስልክ ለመጠቀም በርካታ ሰዎች ቆመው ይጠብቃሉ። ብዙዎቹ ወረፋው ስለዘገየባቸው በጭንቀት ተውጠዋል። መረጋጋት እንድችል ጸለይኩ። ወዲያው ሌላ ፍንዳታ ተሰማ። የብረትና የመስተዋት ስብርባሪዎች እየተምዘገዘጉ ወረዱ። ‘ሌላ አውሮፕላን ነው!’ የሚል ጩኸት ሰማሁ።
“ቀና ብዬ አየሁ። በጣም የሚያሰቅቅ ትዕይንት ነው። ጭስና የእሳት ነበልባል እየተምዘገዘገ ከሚወጣባቸው ላይኛ ፎቆች ሰዎች ይዘልሉ ነበር። አንድ ወንድና ሴት አሁንም ድረስ ይታዩኛል። ለጥቂት ጊዜ መስኮቱን አንቀው ያዙ። ከዚያም ለቀቁትና ወደታች ተወረወሩ። በጣም ይዘገንናል!
“በመጨረሻ ወደ ብሩክሊን ድልድይ ደረስኩና እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ የማያስችለውን ጫማዬን አውልቄ በብሩክሊን በኩል ወዳለው የወንዙ ዳርቻ ሮጥኩ። ወደ መጠበቂያ ግንብ ጽሕፈት ቤት ሕንጻ ገባሁና ወዲያው መረጋጋት እንድችል ረዱኝ።
“ያን ዕለት ማታ እቤት እንደገባሁ ‘ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ የሚፈጠረውን ጭንቀት መቋቋም’ በሚል ርዕስ በነሐሴ 22, 2001 ንቁ! * (እንግሊዝኛ) ላይ የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች አነበብኩ። በጣም የሚያስፈልገኝ ትምህርት ነበር!”
የአደጋው መጠንና ስፋት ሰዎች በሚችሉት ሁሉ እንዲረዳዱ ገፋፍቷል። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ታሪክ ይዳስሳል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.7 ንቁ! በዚህ አጭር ዘገባ ሊካተቱ የማይችሉ በርካታ ከአደጋው ያመለጡ ሰዎችን አነጋግሯል። የእነዚህ ሰዎች ትብብር የትረካችንን ትክክለኛነት ለማረጋገጥና የተሟላ ለማድረግ በእጅጉ ረድቶናል።
^ አን.42 ይህ ርዕስ በዚህ መጽሔት ገጽ 17-24 ላይ ይገኛል።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሙሉ በሙሉ የወደሙ
1 የሰሜኑ ሕንፃ 1 የዓለም የንግድ ማዕከል
2 የደቡቡ ሕንፃ 2 የዓለም የንግድ ማዕከል
3 ማርዮት ሆቴል 3 የዓለም የንግድ ማዕከል
7 7 የዓለም የንግድ ማዕከል
ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው
4 4 የዓለም የንግድ ማዕከል
5 5 የዓለም የንግድ ማዕከል
L ዋን ሊበርቲ ፕላዛ
D ዶይቸ ባንክ 130 ሊበርቲ ጎዳና
6 የዩ. ኤስ. የጉምሩክ መሥሪያ ቤት
N S የሰሜን እና የደቡብ የእግረኛ ድልድዮች
በከፊል ጉዳት የደረሰባቸው
2F 2 የዓለም የገንዘብ ማዕከል
3F 3 የዓለም የገንዘብ ማዕከል
W ዊንተር ጋርደን
[ምንጭ]
As of October 4, 2001 3D Map of Lower Manhattan by Urban Data Solutions, Inc.
[ሥዕሎች]
ከጫፍ:- የደቡቡ ሕንጻ በመጀመሪያ ተደረመሰ
ከላይ:- አንዳንዶች መጠለያ ፍለጋ ወደ መጠበቂያ ግንብ ሕንፃዎች ሮጠው ነበር
በስተቀኝ:- በመቶ የሚቆጠሩ የእሳት አደጋና የነፍስ አድን ሠራተኞች አደጋው በደረሰበት ሥፍራ ደከመኝ ሳይሉ ይሠሩ ነበር
[ምንጮች]
AP Photo/Jerry Torrens
Andrea Booher/FEMA News Photo
[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ የሥዕሎቹ ምንጮች]
AP Photo/Marty Lederhandler
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጭ]
AP Photo/Suzanne Plunkett