በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሞስኮ ምስጋና የተቸረው ሥራ

በሞስኮ ምስጋና የተቸረው ሥራ

በሞስኮ ምስጋና የተቸረው ሥራ

በ1998፣ በሞስኮ ግዛት በሚገኘው በገለቪንስኪ ማዘጋጃ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ እንዲታገድ የሚጠይቅ ክስ ቀረበ። ስለዚህ በገለቪንስኪ ግዛት መስተዳደር የሚገኙ ባለሥልጣናት በቅርቡ የይሖዋ ምሥክሮችን ማመስገናቸው እርስ በርሱ የሚጋጭ ጉዳይ ይመስል ይሆናል።

አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ከሞስኮ ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ሳለ ምሥክሮቹ ከከተማው ባለሥልጣናት ምስጋና ሊያገኙ የቻሉት በምን ምክንያት ነው? በዚያ የሚኖሩ ምሥክሮች ያደረጉትን እንቅስቃሴ በመጠኑ መዳሰሳችን መልሱን እንድናገኝ ያስችለናል።

በሞስኮ የሚኖሩ ምሥክሮች

በ1950ዎቹ አጋማሽ ሞስኮ አንድም የይሖዋ ምሥክር ከማይገኝባቸው ጥቂት የዓለማችን መዲናዎች መካከል አንዷ ነበረች። ለምን? ወደ ሌላ ቦታ ተግዘው እንደተወሰዱት በሶቪየት ኅብረት እንደሚኖሩት በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ በሞስኮ የሚኖሩ ወንድሞችም ተመሳሳይ ዕጣ ስለደረሳቸው ነው። ተግዘው የተወሰዱት ወዴት ነው? አብዛኞቹ የተጋዙት በሳይቤሪያ ወደሚገኙ የጉልበት ሥራ ወደሚሠራባቸው ካምፖች ነበር።

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ጥቂት ሞስኮባውያን በወቅቱ በሩሲያ ታግደው በነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጅዋቸው ጽሑፎች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። በ1970ዎቹ አጋማሽ በዚያን ጊዜ የነበሩት ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ሞስኮ ውስጥ በሚገኘው የሙራት ሻኪሮቭ አፓርታማ ውስጥ ተሰብስበው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። በ1980ዎቹ የዚህ አነስተኛ ቡድን አባላት ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንዲጀምሩ ማድረግ ችለው ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች በሶቪየት ኅብረት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መጋቢት 1991 ሕጋዊ እውቅና ሲያገኝ በሞስኮ የሚገኝ አንድ ትልቅ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ በይፋ ተግባሩን ማከናወን ጀመረ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥክሮቹ ስደት ይደርስባቸው የነበረው ለምን እንደሆነ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር የማወቅ ጉጉት አደረባቸው። በመሆኑም ነሐሴ 1991 በዩክሬይን፣ ኪየቭ የአውራጃ ስብሰባ ሲደረግ ከ2, 000 የሚበልጡ ወንድሞች ስብሰባው ላይ ለመገኘት ከሞስኮ 890 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በዚያ ከተጠመቁት 1, 843 ሰዎች መካከል የሚገኙ ናቸው።

በ1993 በሞስኮ ሎኮሞቲቭ ስታዲዮም ተደርጎ በነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ከ30 ከሚበልጡ አገሮች የመጡ 23, 743 ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር። በዚሁ ዓመት መጨረሻ በሞስኮ ከተማ ዙሪያ ያሉት ጉባኤዎች ቁጥር ወደ 21 ከፍ ብሎ ነበር። ዛሬ ከስምንት ዓመታት ገደማ በኋላ በዚያው አካባቢ 104 ጉባኤዎች ይገኛሉ።

በዚህ ዓመት በሰኔና በሐምሌ ወራት በሞስኮ በተካሄዱት አራት የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ 18, 292 ሰዎች የተገኙ ሲሆን 546 ሰዎችም ተጠምቀዋል። ከምሥክሮቹ ጋር መጽ​ሐፍ ቅዱስ የሚያጠኑት ሰዎች ቁጥር በሚያስገርም ፍጥነት እድገት እያደረገ መምጣቱ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ ለማሳገድ የሞስኮ ባለሥልጣናትን ለመገፋፋት አነሳስቷቸዋል።

በ1998 መግቢያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማሳገድ የታቀደው ክስ በገለቪንስኪ ፍርድ ቤት ቀረበ። በመጨረሻ የካቲት 23, 2001 ምሥክሮቹ ከቀረበባቸው ክስ ነፃ መሆናቸውን የፍርድ ቤቱ ዳኛ ወሰኑ። ይሁን እንጂ ሞስኮ ለሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው የይግባኝ ጥያቄ በድጋሚ እንዲመረመር ለመጀመሪያው ፍርድ ቤት ተመልሶ ተላከለት።

ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ምሥክሮቹን ለማሳገድ ጥረት እያደረጉ ሳለ በሞስኮ የገለቪንስኪ ግዛት መስተዳደር ባለሥልጣናት ምሥክሮቹን ያመሰገኑት ለምንድን ነው?

አዲስ የመሰብሰቢያ ቦታ

ታኅሣሥ 1998 ምሥክሮቹ ከሚኻይልኮቭስኪ መናፈሻ ጋር የሚዋሰን አንድ ትልቅ ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ ገዙ። ከዚህ ቀደም ሕንፃው የባሕል ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ከተወሰነ ጊዜ በፊት ምሥክሮቹ ይህን ትልቅ ሕንፃ ማደስ የጀመሩ ሲሆን ሕንፃው 22 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የሚሰበሰቡባቸው አምስት የመንግሥት አዳራሾች ወይም የመሰብሰቢያ ቦታዎች ይኖሩታል።

ባለፈው ሚያዝያ 15 የገለቪንስኪ ግዛት አንዲት አስተዳዳሪ ሚያዝያ 21 ላይ ምሥክሮቹ የሚኻይልኮቭስኪን መናፈሻ እንዲያጸዱ ጥያቄ አቀረቡ። በሩሲያ የአካባቢው ነዋሪዎችና ኅብረተሰብ የመናፈሻ ቦታዎችንና አውራ ጎዳናዎችን በተሟላ ሁኔታ ለማጽዳት በጋራ መሥራታቸው የተለመደ ነገር ነው። ሚያዝያ 17 ምሥክሮቹ ሥራውን በምን መልኩ እንደሚያካሂዱ ተሰብስበው ተነጋገሩ። ስብሰባው ላይ ወደ 700 ገደማ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ተወሰነ።

ሥራውን ዳር ማድረስ

ሚያዝያ 18 ምሥክሮቹ ለገለቪንስኪ ግዛት ባለሥልጣናት ምን ያህል ቅጠል መሰብሰቢያ መንሽና ሌሎች መሣሪያዎች እንደሚያስፈልጓቸው ባሳወቁበት ወቅት ባለሥልጣናቱ ወደ 700 የሚጠጉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ይገኛሉ ብለው ለማመን ከብዷቸው ነበር። ሚያዝያ 21 ከጠዋቱ 3:​30 ላይ የመስተዳድሩ ሠራተኞች መናፈሻው ሲደርሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች አስቀድመው በቦታው ተገኝተው ነበር። ሆኖም በእጃቸው የነበራቸው መሣሪያ 200 ብቻ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ 200 ገደማ ተጨማሪ የቅጠል መሰብሰቢያ መንሽ ተገኘ። መሣሪያ ያላገኙ ወንድሞች በእጃቸው ቆሻሻ እየሰበሰቡ በፕላስቲክ ከረጢት ውስጥ ይጨምሩ ነበር። ከዚህም በላይ ምሥክሮቹ ትልቁን ኩሬ ለማጽዳት ቦቲ ጫማና ጀልባ ይዘው መጥተው ነበር።

ከመስተዳድሩ ቢሮ የመጡት ተወካዮች በተመለከቱት ነገር በጣም ተደነቁ። ተወካዮቹ እንዳስተዋሉት ሰዎቹ ሥራቸውን የሚያከናውኑት የራሳቸውን ቤት የሚያጸዱ ያህል በደስታና በሙሉ ኃይላቸው ነበር። ባጠቃላይ በሚኻይልኮቭስኪ መናፈሻ በተካሄደው የማጽዳት ሥራ አንድ ሺህ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የተካፈሉ ሲሆን ከ250 ቶን በላይ ቆሻሻም ተወግዷል። በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ መናፈሻው እንደዚህ ንጹህ ሆኖ ተመልክተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ባለሥልጣናቱ በተከናወነው ሥራ የተደነቁ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል። በገለቪንስኪ ግዛት የሚኖሩ አንድ ባለሥልጣን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የሞስኮ ሰሜናዊ ክልል አስተዳደር የሆነው የገለቪንስኪ ግዛት መስተዳደር የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ የሚኻይልኮቭስኪን መናፈሻ ለማጽዳት ላከናወነው ሥራ ምስጋናውን ያቀርባል።” ተባባሪ ባለሥልጣን የሆኑ አንድ ሌላ ሰው ተመሳሳይ የምስጋና ቃላት ከገለጹ በኋላ “ይህ ክቡርና አስፈላጊ ሥራ ወደ መናፈሻው ለሚመጡት ሁሉ ጥቅምና ደስታ ያመጣላቸዋል” ሲሉ ደምድመዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች እንደዚህ ባለው ፕሮጀክቶች መካፈልም ሆነ በመኖሪያ አካባቢያቸው ያሉ ቦታዎችን ማስዋብ የሚያስደስታቸው ቢሆንም እንኳ በዛሬው ጊዜ የሚያከናውኑት ዋነኛ ሥራ በመላው ምድር ላይ ገነትን ስለሚያመጣው መስተዳደር ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ማሳወቅ ነው። (ማቴዎስ 24:​14) የሚኻይልኮቭስኪን መናፈሻ እያጸዱ በነበረበት ወቅት አንዳንዶች እያከናወኑ ያሉት ተግባር ከአርማጌዶን በኋላ መላውን ምድር ለማስዋብ ለሚካሄደው ሥራ ጥሩ ሥልጠና እንደሆነ ተናግረዋል።​—⁠ራእይ 16:​14, 16

በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ አፍቃሪዎች በሙሉ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት በፈጠረበት ወቅት ለምድር ባወጣው ዓላማ መሠረት መላዋ ምድር መናፈሻ መሰል ውብ ቦታ የምትሆንበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ።​—⁠ዘፍጥረት 1:​28፤ 2:​8, 9, 15፤ ራእይ 21:​3, 4

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1970ዎቹ አጋማሽ በሙራት ሻኪሮቭ አፓርታማ ላይ ይሰበሰቡ የነበሩት አንድ ላይ ተገናኝተው

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዚህ ዓመት በሞስኮ በተካሄዱት አራት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በድምሩ 18, 292 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቀድሞው የባሕል ማዕከል ሕንፃ ከታደሰ በኋላ አምስት የመንግሥት አዳራሾች ሊወጣው ችሏል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከ250 ቶን በላይ ቆሻሻ ተወግዷል