በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ የሚፈጠር ጭንቀት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል!

በአሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ የሚፈጠር ጭንቀት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል!

በአሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ የሚፈጠር ጭንቀት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል!

ምናልባት ጦር ሜዳ ዘምተህ የነበርክ ሰው ትሆንና ያሳለፍከው አሰቃቂ ሁኔታ በአእምሮህ እየተመላለሰ ጦርነቱ አሁንም ገና ያላለቀ ሆኖ እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። ወይም እንደ ግዳጅ ወሲብ ያለ አረመኔያዊ ተግባር የተፈጸመብሽ ትሆኚና በተፈጸመብሽ አሰቃቂ ወንጀል ሳቢያ በከፊል በድን እንደሆንሽ ይሰማሽ ይሆናል። አለበለዚያም የምትወደው ሰው በተፈጥሮ ወይም በሌላ አደጋ ሞቶብህ ከዚያ ሰው ተነጥለህ መኖር ትልቅ ሥቃይ ሆኖብህ ይሆናል።

ታዲያ እንደነዚህ ያሉት ስሜቶች ሊለወጡ የሚችሉ ይመስልሃል? አዎን፣ ይችላሉ ብለን በእርግጠኝነት መመለስ እንችላለን። ይህ እስከሚሆንበት ጊዜ ግን የስሜት ቁስለት የደረሰባቸው ሁሉ ከአምላክ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ማጽናኛ ለማግኘት ይችላሉ።

የደረሰብንን የስሜት ቁስል ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ

ሁለት ሺህ ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወቱን ለአደጋ ያጋለጡ አስደንጋጭ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር። ስለ አንዳንዶቹ ሁኔታዎች የሰጠው መግለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከአቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፣ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፣ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 1:​8, 9

በዚህ ጊዜ የደረሰበት ሁኔታ ምን እንደነበረ በትክክል ማወቅ ባንችልም የስሜት ቁስል ያስከተለበት ነገር እንደነበረ ግን የተረጋገጠ ነው። (2 ቆሮንቶስ 11:​23-27) ታዲያ ጳውሎስ እንዴት ሊቋቋመው ቻለ?

በእስያ ያሳለፈውን መከራ መለስ ብሎ በማስታወስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፣ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 1:​3, 4፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

አዎን፣ አሰቃቂ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸው ሁሉ ‘ከምሕረት አባትና ከመጽናናት ሁሉ አምላክ’ እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ። ታዲያ ይህን እርዳታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

እርዳታ ማግኘት እንዴት ይቻላል?

በመጀመሪያ እርዳታ እንዲሰጥህ ጠይቅ። የስሜት መሽመድመድ እንደደረሰብህ ከተሰማህ ልክ እንደ አንተ ተሰምቷቸው የነበሩ ሌሎች ሰዎች እንዳሉ አስታውስ። ይህን የመሰለውን ስሜት ተቋቁመው ያሳለፉ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ደስተኞች ናቸው። ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ እነርሱም በተፈተኑበት ጊዜ ከአምላክ አግኝተውት የነበረውን መጽናናት ‘በማንኛውም ዓይነት መከራ ሥር ለሚገኙ ሰዎች’ ማካፈል እንደሚገባቸው ይሰማቸዋል። የምትቀርበውን የይሖዋ ምሥክር ጠጋ ብለህ “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ እርዳታ የምታገኝበትን መንገድ እንዲያመለክትህ ጠይቅ።

በጸሎት ጽና። በውስጥህ የታፈነው የቁጣ ስሜት እየተናነቀህ መጸለይ ካቃተህ መንፈሳዊ ብቃት ያለው ሌላ ሰው አብሮህ እንዲጸልይ ጠይቅ። (ያዕቆብ 5:​14-16) ከይሖዋ አምላክ ጋር በምትነጋገርበት ጊዜ ‘እርሱ ስለ አንተ ያስባልና የሚያስጨንቅህን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣል።’ (1 ጴጥሮስ 5:​7) ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ ለእያንዳንዱ አገልጋይ እንደሚያስብ ደግመው ደጋግመው ይገልጻሉ።

የመዝሙር 94 ጸሐፊ እንደሚከተለው ሲል ስለጻፈ የስሜት ቁስለት ያስከተለበት አሰቃቂ ሁኔታ ሳይደርስበት አልቀረም:- “እግዚአብሔር ረዳቴ ባይሆን ኖሮ፣ ነፍሴ ወደ ዝምታው ዓለም ፈጥና በወረደች ነበር። እኔ ‘እግሬ አዳለጠኝ’ ባልሁ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ደግፎ ያዘኝ። የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።”​—⁠መዝሙር 94:​17-19 አ.መ.ት

የገጠማቸው አሰቃቂ ሁኔታ ባስከተለባቸው የስሜት ቁስል የሚሠቃዩ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በፍርሃት ወይም በቁጣ ማዕበል እንዲዋጡ ሊያደርጋቸው በሚችል ‘የውስጥ ጭንቀት’ ይረበሻሉ። ይሁን እንጂ ከልብ የመነጨ ጸሎት ‘ደግፎ በመያዝ’ እንደነዚህ ያሉትን ስሜቶች ተቋቁመህ እንድታሳልፍ ሊረዳህ ይችላል። ይሖዋ እንደ አፍቃሪ ወላጅ እንደሆነና አንተ ደግሞ በእቅፉ ውስጥ አድርጎ እንደሚንከባከብህ ሕፃን ልጅ እንደሆንክ አድርገህ አስብ። “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አስታውስ።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​7

ከአካል፣ ከአእምሮም ሆነ ከመንፈሳዊ በሽታ የሚዳነው ቀስ በቀስ ነው። ስለዚህ ባጋጠማቸው አሰቃቂ ሁኔታ በእጅጉ የተጎዱ ሰዎች እንደጸለዩ ወዲያው የአእምሮ ሰላም ያገኛሉ ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ አይሆንም። ቢሆንም ሳያቋርጡ መጸለይ በጣም አስፈላጊ ነው። ሕመምተኛው በደረሰበት የስሜት ቁስለት ከመሸነፍና ተስፋ ከመቁረጥ እንዲድን ያስችለዋል።

የአምላክን ቃል እያነበብክ አሰላስል። ሐሳብህን መሰብሰብና በምታነበው ነገር ላይ ማተኮር የሚያስቸግርህ ከሆነ ሌላ ሰው የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን አብሮህ እንዲያነብ ጠይቅ። አገልጋዮቹ ምን ያህል የተጨነቁ ወይም ተስፋ የቆረጡ ቢሆኑ ይሖዋ ለእነርሱ ያለው ርኅራኄና አሳቢነት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳዩ ምንባቦችን ትመርጥ ይሆናል።

ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ የተጠቀሰችው ጄን በመዝሙር ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ምንባቦች ማጽናኛ አግኝታለች። ከእነዚህ መካከል መዝሙር 3:​1-8፤ 6:​6-8፤ 9:​9, 10፤ 11:​1-7፤ 18:​5, 6፤ 23:​1-6፤ 27:​7-9፤ 30:​11, 12፤ 31:​12, 19-​22፤ 32:​7, 8፤ 34:​18, 19፤ 36:​7-​10፤ 55:​5-9, 22፤ 56:​8-​11፤ 63:​6-8፤ 84:​8-​10፤ 130:​1-6 ይገኙበታል። በአንድ ጊዜ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ለማንበብ አትሞክር። ከዚህ ይልቅ ካነበብክ በኋላ ለማሰላሰልና ለመጸለይ በቂ ጊዜ ውሰድ።

ታይቶ የማያውቅ የጭንቀት ዘመን

በጊዜያችን የግዳጅ ወሲብ፣ ግድያ፣ ጦርነትና አላስፈላጊ የሆነ የኃይል ድርጊት እጅግ መስፋፋቱ የሚያሳዝን ቢሆንም ሊያስደንቀን አይገባም። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ‘የዓመፅ መብዛት’ የጊዜያችን መለያ ባሕርይ እንደሚሆን አመልክቷል። በማከልም ‘የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል’ ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 24:​7, 12

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ የሚፈጠር ጭንቀት በጣም የተስፋፋ ሲሆን ይህም የሆነው በአብዛኛው ኢየሱስ በተነበያቸው ሁኔታዎች ምክንያት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማቴዎስ ምዕራፍ 24፣ በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ እንደተመዘገበው ኢየሱስ በዚህ ዓለም የመጨረሻ ቀን ብሔራት አቀፍ ጦርነቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች እንደሚበዙ፣ ሕገ ወጥነት እንደሚስፋፋና ፍቅር እንደሚጠፋ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አክሎ እንደተናገረው ከዚህ የምንገላገልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

ኢየሱስ በመላው ዓለም የሚደርሰውን ጭንቀትና ‘የታላቁን መከራ’ መጀመር ከገለጸ በኋላ ሰዎች ማድረግ ስለሚኖርባቸው ነገር የተናገረውን ልብ በል:- “ቤዛችሁ ቀርቧልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ።” (ማቴዎስ 24:​21-31፤ ሉቃስ 21:​28) አዎን፣ የዓለም ሁኔታ እየከፋና እየተባባሰ መሄዱን ስንመለከት በዚህ ጭንቀት ፈጣሪ የነገሮች ሥርዓት ላይ የሚወርደው ታላቅ መከራ ክፋትን በሙሉ ጠራርጎ በማጥፋትና ለአዲስ የጽድቅ ሥርዓት በር በመክፈት እንደሚደመደም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠1 ዮሐንስ 2:​17፤ ራእይ 21:​3, 4

መዳናችን የሚመጣው የክፋትና የዓመፅ መጠን ጣሪያ ላይ ከደረሰ በኋላ መሆኑ እንግዳ ነገር ሊሆንብን አይገባም። አምላክ በኖህ ዘመን በነበረው ጥንታዊ ዓለምና በሰዶምና ጎሞራ ይኖሩ በነበሩ ምግባረ ብልሹ ሰዎች ላይ ፍርዱን ያወረደው ይህን ከመሰለ ሁኔታ በኋላ ነው። እነዚህ ጥንት የተፈጸሙ መለኮታዊ ፍርዶች ወደፊት የሚሆነውን ነገር ይጠቁማሉ።​—⁠2 ጴጥሮስ 2:​5, 6

በአሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ የሚፈጠር ጭንቀት የሚያከትምበት ጊዜ

በአሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ በሚፈጠር ጭንቀት (ፒ ቲ ኤስ ዲ) በመሠቃየት ላይ ከሆንክ ይህ እያሰቃየኝ የሚገኘው መጥፎ ትውስታ ፈጽሞ የሚጠፋበት ጊዜ ይመጣ ይሆን ብለህ ታስብ ይሆናል። አዎን፣ በእርግጥ ይመጣል። ይሖዋ አምላክ ኢሳይያስ 65:​17 ላይ “እነሆ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፣ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም” ብሏል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በአሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ የሚፈጠረው ሥነ ልቦናዊ ጠባሳ ፈጽሞ ሊሽር የማይችል መስሎ ቢታየንም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የተነሳ የሚከሰተው የስሜት መረበሽ አንድ ቀን ፈጽሞ እንደሚወገድ ይህ ጥቅስ ያረጋግጥልናል።

ጄን ዛሬ የግዳጅ ወሲብ ከተቃጣባት ከአንድ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች አቅኚ አገልጋይ (የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ) ሆና በማገልገል ላይ ነች። በቅርቡ ስትናገር “የቀድሞ እኔነቴ የተመለሰልኝ ጥቃቱ ከደረሰብኝ ከስምንት ወር በኋላ የክሱ ሂደት አልቆ ወንጀለኛው ሲፈረድበት ነበር” ብላለች። “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ አሁን ያለኝ ደስታና ሰላም ይኖረኛል ብዬ ልገምት አልችልም ነበር። ይሖዋ አስደሳች የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋና ይህንንም ተስፋ ለሌሎች የማካፈል መብት ስለሰጠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።”​—⁠መዝሙር 27:​14

ፒ ቲ ኤስ ዲ ከሚያስከትለው ተስፋ ቢስነትና የስሜት መደቆስ ጋር በመታገል ላይ ከሆንክ ይህ ተስፋ አንተንም ሊያበረታ ይችላል።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ችግሩን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል

[በገጽ 23 እና 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ቃል ማንበብህና መጸለይህ ደግፎ ሊያቆምህ ይችላል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቅርቡ በአሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ የሚፈጠር የስሜት ቀውስ የሚያከትምበት ጊዜ ይመጣል