አስደንጋጭ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ
አስደንጋጭ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ
“ጩቤ ይዣለሁ! አንድ ድምፅ ብታሰሚ እገድልሻለሁ!”
ወቅቱ በጋ ነው። በአንድ ደስ የሚል ቀን ከቀትር በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው የ17 ዓመቷ ጄን * በቨርጂንያ ዩ ኤስ ኤ በሚገኝ አንድ የሕዝብ መናፈሻ የመንሸራተቻ ጫማዋን አድርጋ ትጫወታለች። ድንገት መናፈሻው ጭር ሲልባት ለመሄድ ተነሣች። በቤተሰቦቿ መኪና አጠገብ ተቀምጣ የመንሸራተቻ ጫማዋን ማውለቅ እንደጀመረች አንድ የማታውቀው ሰው ተጠጋት። ከላይ የተጠቀሱትን አስደንጋጭ ቃላት ከተናገረ በኋላ ለሩካቤ ሥጋ ጠየቃትና እንቅ አድርጎ ወደ መኪናው ገፍትሮ ሊያስገባት ሞከረ። የቻለችውን ያህል ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ብትጮህም ሰውየው አልለቀቃትም።
“ምንም ማድረግ እንደማልችል ተሰማኝ” ትላለች ጄን በኋላ ስትናገር። “የዝሆንና የትንኝ ጥል ይመስል ነበር። ቢሆንም መጮሄንና መታገሌን ቀጠልኩ። በመጨረሻም ወደ አምላክ ተጣራሁና ‘ይሖዋ እባክህ እንዲህ ያለው ነገር እንዲደርስብኝ አትፍቀድ!’ አልኩ።” በዚህ ጊዜ ጥቃት የሰነዘረባት ሰው ሳይደነግጥ አልቀረም። በድንገት ለቀቃትና ከአካባቢው ሸሸ።
ሊደፍራት የሞከረው ሰው መኪናው ውስጥ ሲገባ ጄን መኪናዋ ውስጥ ገብታ ከቆለፈች በኋላ መንቀጥቀጥ ጀመረች። ተንቀሳቃሽ ስልኳን አነሳችና ራሷን እንደ ምንም አረጋጋች። ወደ ፖሊስ ጣቢያ ደውላ የተጠርጣሪውን መኪና ትክክለኛ መግለጫና የታርጋ ቁጥር በመስጠቷ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተያዘ።
አስደሳች ፍጻሜ ሆነ ማለት ነው?
አዎን፣ ግን ወዲያው አይደለም። የጄን ሥቃይ ገና መጀመሩ ነበር። ፖሊሶችና ጋዜጦች በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆና ወዲያውኑ እንደዚያ ያለ እርምጃ ለመውሰድ ማሰብ መቻሏን ቢያደንቁም ጄን ግን የመጀመሪያ ድንጋጤዋ ካለፈ በኋላም ቢሆን ልትረጋጋ አልቻለችም። “ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ከፍተኛ የሆነ የስሜት መረበሽ ደረሰብኝ። መላ አካላቴ በፍርሃት ስለተዋጠ እንቅልፍ አልወስድ አለኝ። ይህ ከደረሰብኝ ከበርካታ ሳምንታት በኋላ እንኳን ማጥናት ወይም አእምሮዬ በአንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር ማድረግ አልቻልኩም። አልፎ አልፎ ድንገተኛ የሆነ የመርበትበት ስሜት ያጋጥመኛል። በትምህርት ቤት ጥቃት ያደረሰብኝን ሰው የሚመስል አብሮኝ የሚማር ልጅ ሰዓት ስንት እንደሆነ ሊጠይቀኝ ትከሻዬን መታ ሲያደርግ ራሴን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ደነገጥኩ” ትላለች።
“በከፍተኛ ሐዘን ተዋጥኩ። ከወዳጆቼ መሸሽ ጀመርኩ። በዚህ ምክንያት የደረሰብኝ ብቸኝነት የመንፈስ ጭንቀቴን አባባሰው። ይህ ጥቃት እንዲደርስብኝ በመፍቀዴ ራሴን መውቀስ ጀመርኩ። ከዚያ በፊት የነበረኝን ደስተኛና ሰው አማኝ ባሕርይ በማጣቴ በጣም አዘንኩ። ቀድሞ የነበረኝ ስብዕና ፈጽሞ የሞተ መሰለኝ” ብላለች።
በጄን ላይ የታዩት ሁኔታዎች ፒ ቲ ኤስ ዲ (ፖስት ትራውማቲክ ስትሬስ ዲስኦርደር) የተባለው ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ የሚፈጠር ጭንቀት ከሚያስከትላቸው ምልክቶች አንዳንዶቹ ናቸው። ፒ ቲ ኤስ ዲ ምንድን ነው? በዚህ የሚያሽመደምድ የስሜት ቀውስ የሚሰቃዩትን ግለሰቦች ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል? የሚቀጥለው ጽሑፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 ስሟ ተለውጧል።