ከበርካታ አካባቢዎች የተገኘ ድጋፍና አዘኔታ
ከበርካታ አካባቢዎች የተገኘ ድጋፍና አዘኔታ
ፈቃደኛ ሠራተኞች ከሌሎች የዩናይትድ ስቴትስ አካባቢዎችና ከሌሎች አገሮች መጥተዋል። እንደነዚህ ካሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች አንዱ የ29 ዓመቱ ቶም (ከላይ የሚታየው) ሲሆን በኦታዋ፣ ካናዳ የእሳት አደጋ ሠራተኛ ነው። ለንቁ! እንደሚከተለው ብሏል:- “የደረሰውን ሁኔታ በቴሌቪዥን ከተመለከትኩ በኋላ ወንድሞቼ ለሆኑት የኒው ዮርክ የእሳት አደጋ ሠራተኞች የሞራል ድጋፍ ለመስጠት ፈለግኩ። ዓርብ ዕለት ወደ ኒው ዮርክ በመኪና ተጓዝኩና ቅዳሜ ዕለት እርዳታ ለመስጠት አደጋው በደረሰበት ቦታ ተገኘሁ። የፍርስራሹን ክምር በአካፋ እያፈሰ ከሚያነሳው የአካፋ ብርጌድ ጋር እንድሠራ ተመደብኩ።
“የወደቁ የእሳት አደጋ ሠራተኞችን ማንነት የሚያሳውቅ ፍንጭ እየፈለግን ስለነበረ ፍርስራሹን የምናነሳው ቀስ እያልን ነበር። የተዘጋ በር ለመክፈትና ቧንቧ ለመዝጋት የሚያገለግል ጉጠት መሳይ መሣሪያ አገኘሁ። በጣም አድካሚ ሥራ ነበር። ለ50 ፈቃደኛ ሠራተኞች አንድ ገልባጭ መኪና ለመሙላት ሁለት ሰዓት ያህል ይወስድ ነበር።
“ሰኞ ዕለት መስከረም 17 ቀን ባለፈው ማክሰኞ ወደ ሕንጻው ዘልለው የገቡ የእሳት አደጋ ተከላካዮች አስከሬን አግኝተን አወጣን። በዚያ ወቅት ያየሁትን ፈጽሞ አልረሳም። ሁሉም ነፍስ አድን ሠራተኞች ሥራቸውን አቁመውና የጭንቅላት መከላከያ ቆባቸውን አውልቀው ቀጥ ብለው ቆሙ። ለወደቁት ባልደረቦቻችን ክብር ያደረጉት ነበር።
“በአደጋው ሥፍራ የደረሰውን ሁኔታ ቆም ብዬ ስመለከት በዛሬው ጊዜ ሕይወት ምን ያህል አላፊ ጠፊ እንደሆነ ተገነዘብኩ። ስለ ሕይወቴ፣ ስለ ሥራዬና ስለ ቤተሰቤ እንዳስብ አደረገኝ። ሥራዬ ለአደጋ የሚያጋልጥ ቢሆንም ሰዎችን ለመርዳት፣ አልፎ ተርፎም ሕይወት ለማዳን የሚያስችል በመሆኑ እርካታ ያስገኛል።”
ምሥክሮች ተግባራዊ እርዳታ አበርክተዋል
አደጋው ከደረሰ በኋላ በነበሩት ሁለት ቀናት 70 የሚያክሉ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተጠልለው ነበር። አርፈውበት የነበረውን የሆቴል ክፍልና ሻንጣቸውን ያጡ ሰዎች ማረፊያ ቦታና ቅያሪ ልብስ አግኝተዋል። ምግብም ቀርቦላቸዋል። ምናልባትም ከዚህ ሁሉ ይበልጥ ያስፈልጋቸው የነበረውን ማጽናኛና ድጋፍ በቂ ልምድ ካላቸው ክርስቲያን ሽማግሌዎች አግኝተዋል።
በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ግራውንድ ዜሮ ተብሎ በተጠራው የአደጋ ሥፍራ በነፍስ አድን ሥራ ተሰማርተው ለነበሩ ሠራተኞች አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ልከዋል። ለእሳት አደጋ መከላከያ መሥሪያ ቤት የእሳት አደጋ ተከላካዮችን ወደ አደጋው ሥፍራ የሚያደርስ መጓጓዣ ቀርቧል። የይሖዋ ምሥክርና የጽዳት ሠራተኛ የሆነው የ39 ዓመቱ ሪካርዶ (ከላይ በስተቀኝ) በመቶ ከሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን በብዙ ኩንታል የሚገመት የፍርስራሽ ክምር በማስወገዱ ሥራ ተካፍሏል። ለንቁ! እንደሚከተለው ብሏል:- “የሚታየው ነገር በተለይ የጠፉ ጓዶቻቸውን ይፈልጉ ለነበሩት የእሳት አደጋ ሠራተኞች በጣም የሚያስጨንቅ ነበር። አንዱን የእሳት አደጋ ሠራተኛ ከነሕይወቱ ጎትተው ሲያወጡ አይቻለሁ። አንደኛው የእሳት አደጋ ሠራተኛ ከላይ በወደቀበት የሌላ ሰው አስከሬን ተመትቶ
ሞቷል። በርካታ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ያለቅሱ ነበር። እኔም መቋቋም አቅቶኝ አለቀስኩ። በዚያ ዕለት የእነርሱን ያህል ድፍረት ያሳየ ሌላ ማንም ሰው አልነበረም።”“ጊዜና አጋጣሚ”
አደጋው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ከእነዚህ መካከል አደጋው በደረሰበት ቦታ ወይም በዚያ አካባቢ የተገኙ ቢያንስ 14 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። የ65 ዓመቷ ጆይስ ከሚንግስ የትሪኒዳድ ተወላጅ ስትሆን በዓለም ንግድ ማዕከል አካባቢ ጥርሷን ለመታከም ቀጠሮ ነበራት። የሚያሳዝነው ግን ቀጠሮዋ አደጋው በደረሰበት ሰዓት ነበር። በጭሱ ታፍና ከወደቀች በኋላ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወሰደች። ሊያድኗት ግን አልቻሉም። በእርሷ ላይ የደረሰው በሌሎች በርካታ ሰዎች ላይ የሚደርሰው “ጊዜና አጋጣሚ፣ NW ” የሚያስከትለው ሁኔታ ነው። (መክብብ 9:11) በቀናተኛ ወንጌላዊነቷ የምትታወቅ ሴት ነበረች።
ካልቪን ዶውሰን (ሣጥኑን ተመልከት) በደቡቡ ሕንጻ 84ኛ ፎቅ ላይ ለአንድ የንግድ አገናኝ ኩባንያ ይሠራ ነበር። ቢሮው ውስጥ ስለነበረ የሰሜኑ ሕንጻ በአውሮፕላን ከተመታ በኋላ ወዲያውኑ ሕንፃውን በግልጽ መመልከት ችሎ ነበር። ከቢሮው ውጭ የነበረው አሠሪው ስልክ ደውሎ የደረሰውን ሁኔታ እንዲነግረው ይጠይቀዋል። እንዲህ ይላል:- “ካልቪን ያየውን ሊነግረኝ ሞከረ። ‘ሰዎች እየዘለሉ ነው!’ አለኝ። ወዲያው እንዲወጣ፣ ሌሎቹም ቢሮውን ጥለው እንዲወጡ እንዲያደርግ ነገርኩት።” ካልቪን መውጣት አልቻለም። አሠሪው በመቀጠል “ካልቪን በጣም ግሩም ሰው ነበር። ሁላችንም፣ መንፈሳዊ ዝንባሌ የሌለን ጭምር በጣም እንወደዋለን። አምላክን የሚፈራና ሰብዓዊነት ያለው ሰው በመሆኑ እናደንቀዋለን” አለ።
ሌላው የአደጋው ሰለባ የሆነ የይሖዋ ምሥክር የአራት ልጆች አባትና በኒው ዮርክ የእሳት አደጋ መሥሪያ ቤት ካፒቴን የነበረው ጀምስ አማቶ (ከጀርባ ባለው ገጽ ላይ በስተቀኝ በኩል ከታች) ነው። ያውቁት የነበሩ ሰዎች በጣም ደፋር ከመሆኑ የተነሣ “ሰዎች ሸሽተው ሲሮጡ እያየ እንኳን በእሳት በተያያዘ ሕንጻ ውስጥ ዘልሎ ይገባል” ብለውለታል። ጀምስ በሌለበት የባታልዮን አዛዥነት ማዕረግ ተሰጥቶታል።
ሌላው የይሖዋ ምሥክር የእሳት አደጋ ሠራተኛ የሰባት ዓመት የሥራ ልምድ ያለው ጆርጅ ዲፓስኳሊ ነው። ሜሊሳን አግብቶ ጆርጅያ ሮዝ የተባለች የሁለት ዓመት ሴት
ልጅ አፍርቷል። በአንድ የስታተን ደሴት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ሽማግሌ የነበረ ሲሆን ሕንጻው በተደረመሰበት ጊዜ በደቡቡ ሕንጻ 10ኛ ፎቅ ላይ ይገኝ ነበር። እርሱም ሌሎችን ለማዳን ሲል ሕይወቱን ከፍሏል።እነዚህ ሰዎችን ለማዳን በጀግንነት ሲጋደሉ ከሞቱ በመቶ የሚቆጠሩ የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ ፖሊሶችና የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው። የእነዚህ የነፍስ አድን ሠራተኞች ጀግንነት ከልክ በላይ ተጋንኖአል ማለት አይቻልም። የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ሩዶልፍ ጁልያኒ የማዕረግ እድገት ለተሰጣቸው የእሳት አደጋ ሠራተኞች ንግግር ሲያደርጉ እንዲህ ብለዋል:- “በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ግንባራችሁን ሳታጥፉ ወደፊት ለመግፋት ፈቃደኛ መሆናችሁ የሁላችንንም መንፈስ አነሳስቷል። . . . ከኒው ዮርክ ከተማ የእሳት አደጋ መከላከያ መሥሪያ ቤት የበለጠ የድፍረትና የጀግንነት ምሳሌ . . . ልናገኝ አንችልም።”
የማጽናኛ አገልግሎት
ከአደጋው በኋላ በነበሩት ቀናት 900, 000 የሚያክሉት በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሐዘን ላይ ለወደቁት ሁሉ የማጽናኛ መልእክት ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ለጎረቤቶቻቸው ያላቸው ፍቅር ያዘኑትን ለማጽናናት ገፋፍቷቸዋል። (ማቴዎስ 22:39) በተጨማሪም በአገልግሎታቸው ወቅት በጭንቀት ለተዋጠው የሰው ዘር ብቸኛው እውነተኛ ተስፋ ምን እንደሆነ ለመጠቆም ጥረት አድርገዋል።—2 ጴጥሮስ 3:13
ምሥክሮቹ በአቀራረባቸው ለሰዎች አዘኔታ ያሳያሉ። ዓላማቸው ከቅዱሳን ጽሑፎች የሚገኘውን ማጽናኛ ማድረስና “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” ያለውን የክርስቶስን ምሳሌ መከተል ነው።—ማቴዎስ 11:28-30
በማንሃተን አካባቢ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የተውጣጡ ሽማግሌዎች አደጋው ወደደረሰበት አካባቢ እንዲገቡና በዚያ የነበሩትን የነፍስ አድን ሠራተኞች እንዲያጽናኑ ተፈቅዶላቸዋል። ሠራተኞቹ እጅግ አዎንታዊ የሆነ ምላሽ ሰጥተዋል። “በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የሠፈረውን ሐሳብ ስናካፍላቸው ዐይኖቻቸው እንባ ያቀርሩ ነበር” ሲሉ አገልጋዮቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የነፍስ አድን ሠራተኞች በአንድ ወደብ ላይ በቆመ ጀልባ ውስጥ ከድካማቸው በማገገም ላይ ነበሩ። “ሰዎቹ ባዩት ነገር ቅስማቸው ተሰብሮ ስለነበረ ፈዝዘውና አቀርቅረው ተቀምጠው ነበር። ከጎናቸው ተቀመጥንና አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አካፈልናቸው። እንዲህ ያለው ማጽናኛ በጣም እንደሚያስፈልጋቸው ከገለጹልን በኋላ ሄደን ስላነጋገርናቸው በጣም አመሰገኑን።”
አደጋው ከደረሰ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ቀርበው ያነጋገሯቸው ሰዎች በአብዛኛው የሚያነቡት ነገር ይፈልጉ ስለነበረ በሺህ የሚቆጠሩ ብሮሹሮች በነጻ ተሰጥቷቸዋል። ከተሰጧቸው ብሮሹሮች መካከል የምትወደው ሰው ሲሞት፣ ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣ ይሆን?፣ አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የሚሉት ይገኙበት ነበር። በተጨማሪም በሁለት የንቁ! እትሞች ማለትም “አዲሱ የአሸባሪነት ገጽታ” (ግንቦት 22, 2001) እና “ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ የሚፈጠረውን ጭንቀት መቋቋም” (ነሐሴ 22, 2001) በሚሉት (የእንግሊዝኛ) እትሞች የመጀመሪያ ገጾች ላይ የወጡት ተከታታይ ርዕሶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። ምሥክሮቹ በአብዛኞቹ አጋጣሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንሣኤ የሚሰጠውን ተስፋ አብራርተዋል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) ይህን አጽናኝ መልእክት በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ለማድረስ ሳይቻል አልቀረም።
ቆም ብለን እንድናስብ ሊያደርገን ይገባል
በኒው ዮርክ ከተማ ላይ የደረሰው ዓይነት አሳዛኝ አደጋ ሁላችንም ቆም ብለን ሕይወቴን ምን ለማድረግ እየተጠቀምኩበት ነው? ብለን እንድናስብ ሊያደርገን ይገባል። ለራሳችንና ለግል ፍላጎታችን ብቻ ነው የምንኖረው ወይስ ሌሎችን የሚያስደስት ነገር ለማድረግ እንሞክራለን? ነቢዩ ሚክያስ “እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” ሲል ጠይቋል። (ሚክያስ 6:8) ትህትና ወደ አምላክ ቃል ዘወር እንድንልና ሙታን ያላቸውን እውነተኛ ተስፋ፣ እንዲሁም አምላክ በምድር ላይ ገነታዊ ሁኔታ እንዲሰፍን በቅርቡ ምን እንሚያደርግ መርምረን እንድናውቅ ሊገፋፋን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጣቸው ተስፋዎች ይበልጥ ለማወቅ የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንድትገናኝ አበክረን እናሳስብሃለን።—ኢሳይያስ 65:17, 21-25፤ ራእይ 21:1-4
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
የታትያና ጸሎት
የካልቪን ዶውሰን ባለቤት ሊና የሰባት ዓመት ልጅዋ አባትዋ ቤት እንደማይመለስ ካወቀች ከጥቂት ቀናት በኋላ ስለጸለየችው ጸሎት ለንቁ! ተናግራለች። ሊና ጸልያ ከጨረሰች በኋላ ታትያና “እማዬ፣ እኔስ መጸለይ እችላለሁ?” ስትል ጠየቀቻት። እናትዬዋም ተስማማች። ታትያና እንደሚከተለው በማለት ጸለየች:- “የሰማዩ አባታችን ይሖዋ፣ ለዚህ ምግብና ለዚህ ለዛሬው ቀን ሕይወታችን እናመሰግንሃለን። መንፈስህ ከእኔና ከእማዬ ጋር ሆኖ እንዲያጠነክረን እንለምንሃለን። አባዬም በሚመለስበት ጊዜ ጠንካራ እንዲሆን መንፈስህ እንዲረዳው እንጠይቅሃለን። በሚመለስበት ጊዜ ቆንጆ፣ ጠንካራ፣ ደስተኛና ጤነኛ ሆኖ እንድናገኘው እንለምንሃለን። በኢየሱስ ስም . . . ኡ ረስቼው፣ አደራ፣ እማዬን አበርታልኝ። አሜን።”
ሊና፣ ታትያና የደረሰውን ሁኔታ በትክክል የተረዳች ስላልመሰላት “ቲያና በጣም ጥሩ ነው። ግን የኔ ቆንጆ፣ አባዬ እንደማይመለስ አውቀሻል?” ስትል ጠየቀቻት። ወዲያው ታትያና በድንጋጤ ክው አለች። “አይመለስም እንዴ?” አለቻት። እናቲቱም “አዎ፣ አይመለስም” አለቻት። “የነገርኩሽ መስሎኛል እኮ። አባዬ እንደማይመጣ የተረዳሽ መስሎኝ ነበር።” ታትያናም “ግን በአዲሱ ዓለም ይመጣል እያልሽ ስትነግሪኝ ነበር” ስትል መለሰች። በመጨረሻም ሊና ልጅዋ ምን ማለትዋ እንደነበረ ስለገባት “አዝናለሁ ታትያና፣ በትክክል አልተረዳሁሽም ነበር። አባዬ ነገ ይመጣል ማለትሽ መስሎኝ ነበር” አለቻት። ሊና “አዲሱ ዓለም ይህን ያህል እውን ሆኖ ስለታያት በጣም ደስ አለኝ” ብላለች።