ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ የሚፈጠር ጭንቀት ምንድን ነው?
ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ የሚፈጠር ጭንቀት ምንድን ነው?
ፒቲ ኤስ ዲ በቀድሞዎቹ ዓመታት የሚታወቀው ሼል ሾክ (የጦር ሜዳ ጭንቀት) በሚል ስያሜ ሲሆን ስለ በሽታው ይደረጉ የነበሩት ጥናቶች በዋነኛነት ያተኩሩ የነበረው ከዘመቻ በተመለሱ ወታደሮች ላይ ነበር። ዛሬ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። ወታደር ባትሆንም እንኳ ፒ ቲ ኤስ ዲ ሊያጋጥምህ ይችላል። የሆነ ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ ከደረሰብህ ለእንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት ልትጋለጥ ትችላለህ።
ሁኔታው የጦር ሜዳ ውሎ ወይም የግዳጅ ወሲብ ለመፈጸም የሚደረግ ሙከራ አለበለዚያም የመኪና አደጋ ሊሆን ይችላል። የዩናይትድ ስቴትስ የፒ ቲ ኤስ ዲ ብሔራዊ ማዕከል ያዘጋጀው የመረጃ ሰነድ “አንድ ግለሰብ ፒ ቲ ኤስ ዲ ይዞታል ሊባል የሚችለው አሰቃቂ ሁኔታ ሲያጋጥመው ነው” ይላል። በተጨማሪም ይህ ሁኔታ “በግለሰቡ አካል ላይ በሆነ መልኩ ጉዳት ያደረሰ ወይም ሊያደርስ የነበረ መሆን ይኖርበታል።”
ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ጄን እንደሚከተለው ትላለች:- “ድንገተኛ የሆነ አስደንጋጭ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ሰውነት አንዳንድ ሆርሞኖችን በከፍተኛ መጠን እንደሚያመነጭና እነዚህም ሆርሞኖች የስሜት ሕዋሳት ለአደጋ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ እንደሚያደርጉ ተገንዝቤያለሁ። እንደ ወትሮው ቢሆን የሆርሞኖቹ መጠን አደጋው ካለፈ በኋላ ወደ ቀድሞ መጠናቸው ይመለሳሉ። በፒ ቲ ኤስ ዲ ሕሙማን ላይ ግን ከፍ እንዳሉ ይቆያሉ።” ሁኔታው ከተከሰተ ቆየት ያለ ቢሆንም የፈጠረባት ድንጋጤ ቤቱን ለቅቆ እንዲወጣ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለመቀበል እምቢተኛ እንደሆነ ተከራይ ከጄን አእምሮ ውስጥ አልወጣ ብሏል።
አሰቃቂ ሁኔታ አጋጥሞህ ከነበረና ሁኔታው ተመሳሳይ ችግር ጥሎብህ የሄደ ከሆነ ይህ የደረሰው ባንተ ላይ ብቻ አለመሆኑን መገንዘብህ በጣም አስፈላጊ ነው። ሊንዳ ኢ ሌድሬይ የተባሉት ደራሲ ስለ ግዳጅ ወሲብ በጻፉት መጽሐፍ ላይ ፒ ቲ ኤስ ዲ “ሊቆጣጠሩ ያልቻሉት አስደንጋጭ ሁኔታ አጋጥሟቸው በነበሩ ጤነኛ ሰዎች ላይ የሚደርስና ማንም ሰው ሊያጋጥመው የሚችል ቀውስ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ፒ ቲ ኤስ ዲ ማንም ሰው ሊያጋጥመው የሚችል ቀውስ ነው ይባል እንጂ አሰቃቂ ሁኔታ አጋጥሞት የነበረ ሁሉ ፒ ቲ ኤስ ዲ ይይዘዋል ማለት አይደለም። ሌድሬይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “በ1992 ተደርጎ በነበረ አንድ ጥናት የግዳጅ ወሲብ ተፈጽሞባቸው ከነበሩት ሴቶች መካከል 94 በመቶ የሚሆኑት ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ከአንድ ሳምንት በኋላ ዋነኞቹ የፒ ቲ ሴስ ዲ ምልክቶች የታዩባቸው ሲሆን ከአሥራ ሁለት ሳምንታት በኋላ ግን የሕመሙ ምልክቶች የታዩባቸው ሴቶች 47 በመቶ የሚሆኑት ነበሩ። በ1993 በሚኒያፖሊስ የወሲብ ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች እርዳታ ወደሚሰጠው ማዕከል ከመጡት ሴቶች መካከል ሃምሳ በመቶ የሚሆኑት የግዳጅ ወሲብ ከተፈጸመባቸው ከአንድ ዓመት በኋላ የፒ ቲ ኤስ ዲ ምልክቶች ታይተውባቸዋል።”
እነዚህ አሐዛዊ መረጃዎች ፒ ቲ ኤስ ዲ በጣም የተስፋፋ ችግር፣ እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች ከሚገምቱት በላይ በጣም የተስፋፋ መሆኑን ያሳያሉ። በበሽታው የሚሠቃዩ ሰዎች ዓይነትና ለችግሩ ምክንያት የሆነው ሁኔታም በጣም የተለያየ ነው። አሊግዛንደር ሲ ሚክፋሌንና ላርስ ዋይሳት የተባሉት ደራሲዎች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች አሰቃቂ ሁኔታዎች ሰላም በሰፈነባቸው ጊዜያትና ወታደሮች ባልሆኑ ሰዎች ላይ፣ እንዲሁም ጦር ሜዳ ላይ በዋሉ ወታደሮችና የጦርነት ሰለባ በሆኑ ሰዎች ላይ ብዙ ጊዜ መድረሳቸውንና ሁኔታዎቹ የደረሱባቸው
ብዙዎቹ ሰዎችም በፒ ቲ ኤስ ዲ መያዛቸውን አረጋግጠዋል።” እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች በአንዳንድ ዓይነት የሕክምና ሂደቶችና በድንገተኛ ልብ ሕመም ምክንያት ፒ ቲ ኤስ ዲ ይዟቸዋል።ከላይ የተጠቀሱት ደራሲዎች “ፒ ቲ ኤስ ዲ በጣም የተስፋፋ ችግር ሆኗል” ብለዋል። በመቀጠል ሲያብራሩ “1, 245 በሚያክሉ አሜሪካውያን ወጣቶች ላይ በጅምላ በተካሄደ ጥናት 23 በመቶ የሚያክሉት አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወይም በሌሎች ላይ የተፈጸመ የኃይል ድርጊት አይተው እንደነበረ ተረጋግጧል። ይህ ሁኔታ ከገጠማቸው አምስት ወጣቶች መካከል አንዱ የፒ ቲ ኤስ ዲ ምልክቶች ታይተውበታል። ይህም ባሁኑ ጊዜ 1.07 ሚልዮን የሚያክሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አሜሪካውያን ወጣቶች በፒ ቲ ኤስ ዲ እንደሚሠቃዩ ይጠቁማል” ብለዋል።
ይህ አሐዛዊ መረጃ ትክክል ከሆነ በአንድ አገር ብቻ በዚሁ ሕመም የሚሠቃዩ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች አሉ ማለት ነው! እነዚህንና በቀረው የዓለም ክፍል የሚኖሩትን በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሕሙማን ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል?
ምን ማድረግ ይቻላል?
ፒ ቲ ኤስ ዲ እንደያዘህ ከተሰማህ ወይም የምታውቀው ሌላ ሰው በዚህ ሕመም እንደተጠቃ ካመንክ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች እነሆ:-
የነበረህ መንፈሳዊ ፕሮግራም እንዳይስተጓጎል ጥረት አድርግ። “ሁልጊዜ በአካባቢያችን በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ እገኛለሁ” ትላለች ጄን። “የሚነገረውን ነገር በትኩረት መከታተል በምቸገርበት ጊዜ እንኳን ይሖዋ አምላክ እንዲህ ባለው ቦታ እንድገኝ እንደሚፈልግብኝ አውቃለሁ። በጉባኤው ውስጥ የሚገኙት ሁሉ ከፍተኛ ፍቅር ያሳዩኝና
ያጽናኑኝ ነበር። እነርሱ ያሳዩኝ ፍቅርና አሳቢነት ባሳለፍኩት የሥቃይ ጊዜ ሁሉ በእጅጉ ጠቅሞኛል።” ጄን በመቀጠል “የመዝሙርን መጽሐፍ ማንበቤም በጣም ይረዳኝ ነበር። የተጠቁ ሰዎች ያቀረቧቸው ጸሎቶች የኔን የውስጥ ስሜት የገለጹልኝ ይመስለኝ ነበር። መናገር የፈለግኹትን በጸሎት መግለጽ ሲያቅተኝ ‘አሜን’ ብቻ እላለሁ” ብላለች።ሕመምተኛውን ከማበረታታት ወደኋላ አትበል። የደረሰበትን አሰቃቂ ሁኔታ እያስታወሰ የሚሠቃይ የቅርብ ሰው ካለህ የሚያሳየው ስሜት በጣም የተጋነነ ወይም አንተን ሆን ብሎ ለማስቸገር የሚያደርገው እንዳልሆነ ተረዳለት። ስሜቱ ስለደነዘዘ ወይም ስለተጨነቀ፣ አለበለዚያም በጣም ስለተቆጣ እርሱን ለመርዳትና ለመደገፍ የምታደርገውን ጥረት በምትፈልገው መጠን ለመቀበል አይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ተስፋ ቆርጠህ አትተወው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “እውነተኛ ባልንጀራ ሁልጊዜ ይወድዳል፣ ለመከራም ጊዜ የሚወለድ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17 NW
በዚህ ሕመም የሚሠቃየው ሰው ሕመሙን ለመቋቋም ያስችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ተጨማሪ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ተገቢ ያልሆኑ ዘዴዎችን ለይቶ ማወቅና ማስወገድ ይኖርበታል። ሕጋዊ ያልሆኑ አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች እንዲሁም የአልኮል መጠጦች ከነዚህ የሚመደቡ ናቸው። አልኮል፣ አደገኛ
መድኃኒቶችና ዕፆች ጊዜያዊ እፎይታ ሊያስገኙ ቢችሉም የባሰ ችግር ውስጥ ይከታሉ። አብዛኛውን ጊዜ ከማኅበራዊ ኑሮ መገለልን፣ እርዳታ ሊሰጡ ከሚፈልጉ ሰዎች መራቅን፣ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ሱስን፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣን፣ የምግብ ፍላጎት ማጣትን ወይም ከመጠን በላይ መብላትንና ሌሎች ጎጂ ባሕርያትን ያስከትላሉ።ጥሩ ብቃት ያለው የጤና ባለሙያ አማክር። ግለሰቡ ፒ ቲ ኤስ ዲ እንደሌለበት ሊረጋገጥ ይችል ይሆናል። በዚህ ሕመም መያዙ ከተረጋገጠ ግን ጥሩ ውጤት የሚያስገኙ ሕክምናዎች አሉ። * የባለሙያ እርዳታ እየተሰጠህ ከሆነ ለባለሙያው ሐቀኛ ሆነህ ከላይ የተዘረዘሩትን ባሕርያት እንድታሸንፍ እንዲረዳህ ጠይቀው።
አካላዊ ቁስል ብዙውን ጊዜ ፈጥኖ ይሽራል። በፒ ቲ ኤስ ዲ የሚሠቃዩ ሰዎች ግን ብዙ ዓይነት ቁስል፣ ማለትም የአእምሮ፣ የመንፈስና የአካል ቁስል የደረሰባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ሕመም የሚሠቃየው ግለሰብና አብረውት ያሉ ሰዎች ፈውስ ለማስገኘት ሊያደርጓቸው የሚችሏቸውን ተጨማሪ ነገሮች ያብራራል። በተጨማሪም በአሰቃቂ ሁኔታ ሳቢያ በደረሰባቸው ከፍተኛ የስሜት መረበሽ የሚሠቃዩ ሰዎች ምን ዓይነት ተስፋ ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸው ይገልጻል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.15 የይሖዋ ምሥክሮች ማንኛውንም ዓይነት አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ሕክምና የተሻለ እንደሆነ አድርገው በመጥቀስ አይመክሩም ወይም አያበረታቱም።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በአሰቃቂ ሁኔታዎች ሳቢያ የሚፈጠር ጭንቀት የሚያስከትላቸው ምልክቶች
አሰቃቂ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው የነበሩ በርካታ ሰዎች ብዙ ጊዜ ያሳለፉት ሁኔታ ወደ አእምሮአቸው ተመልሶ እየመጣ ያስቸግራቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሕመምተኞቹ ይህን መቆጣጠር ወይም ማስወገድ አይችሉም። በዚህ ምክንያት እንደሚከተሉት ያሉ ሁኔታዎች ሊደርሱባቸው ይችላሉ:-
• ያጋጠማቸው አሰቃቂ ሁኔታ አሁን እየደረሰባቸው እንዳለ ሆኖ ይሰማቸዋል
• መጥፎ ሕልምና ቅዠት
• ጮክ ያለ ድምፅ ሲሰሙ ወይም ሳያስቡት ከኋላቸው ሰው ሲመጣ ከልክ በላይ መደንገጥ
• መንቀጥቀጥና ማላብ
• የልብ መምታት ወይም የመተንፈስ ችግር
• ያዩት፣ የሰሙት፣ ያሸተቱት፣ የቀመሱት ወይም የተሰማቸው ነገር አጋጥሟቸው የነበረውን አሰቃቂ ሁኔታ ሲያስታውሳቸው መረበሽ
• ሥጋት ወይም ፍርሃት፤ ዳግመኛ ለአደጋ እንደተጋለጡ አድርጎ ማሰብ
• ደርሶባቸው የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውሳቸው ነገር ሲያጋጥማቸው ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው በድንገት መረበሽ፣ መቆጣት ወይም መበሳጨት
• ሐሳብን ለማሰባሰብ አለመቻል ወይም በትክክል የማሰብ ችግር
• እንቅልፍ የማጣት ችግር
• የመንፈስ ዕረፍት ማጣትና ሁልጊዜ አደጋ ይደርስብኛል ብሎ መጠራጠር
• የስሜት መደንዘዝ
• ሌሎችን መውደድ አለመቻል ወይም ለማንኛውም ነገር ስሜት አልባ መሆን
• በአካባቢው ያሉ ሁኔታዎች እንግዳ ወይም ያልተለመዱ እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ
• ከዚህ በፊት ያስደስቷቸው ለነበሩ ነገሮች ፍላጎት ማጣት
• አደጋው በደረሰበት ጊዜ የተፈጸሙ ዋነኛ ሁኔታዎችን ለማስታወስ መቸገር
• በአካባቢያቸው ካለ ዓለምና በዙሪያቸው ከሚከናወኑ ነገሮች የመገለል ስሜት
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተለያዩ አሰቃቂ ሁኔታዎች ፒ ቲ ኤስ ዲ ሊያስከትሉ ይችላሉ