በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ፀረ ቫይረስ ሻይ

ሮይተርስ ኸልዝ ኢንፎርሜሽን እንደዘገበው የቤተ ሙከራ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናቶች እንዳመለከቱት “የተለያዩ የሻይ ዓይነቶች ቫይረሶችን የሚገድሉ ወይም የሚያደነዝዙ ይመስላል። የተለያዩ የጥቁርና የአረንጓዴ ሻይ ዓይነቶች እንዲሁም በትኩሱ የሚጠጣና የቀዘቀዘ ሻይ እንደ ኸርፐስ ሲምፕሌክስ 1 እና 2 እንዲሁም T1 ባሉት ቫይረሶች በተበከለ የእንስሳት ሕዋስ ላይ ተሞክረዋል። ምርምሩን ያካሄዱት የኒው ዮርክ ፔስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሚልተር ሺፈንባወር እንዳሉት “የቀዘቀዘ ወይም መደበኛ ሻይ [የኸርፐስ] ቫይረሶችን በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ጨርሶ ይገድላል ወይም ያደነዝዛል።” በT1 ቫይረሶችም ላይ ተመሳሳይ ውጤት ታይቷል። ሻይ የእነዚህን ቫይረሶች ሕልውና እንዴት እንደሚጻረር እስካሁን በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም ሻዩ በጣም ተበርዞ ከቀጠነ በኋላ እንኳን በቫይረሶቹ ላይ ያለው ኃይል እንዳልጠፋ ተመራማሪዎቹ አረጋግጠዋል። ጥቁሩ ሻይ ከአረንጓዴ ሻይ የበለጠ የፀረ ቫይረስነት አቅም እንዳለው ታውቋል።

የስልክ ዕዳ

ዘ ሳንዴይ ቴሌግራፍ ጋዜጣ እንዳለው የአውስትራሊያ ወጣቶች “ከ18 ዓመት ያላለፉ ወጣቶች ጭምር የተከመረባቸውን የሞባይል ስልክ ዕዳ መክፈል አቅቷቸዋል። አንዳንድ ወጣቶች በማስታወቂያዎችና በዱቤ መደወል እንደልብ በመቻሉ ተታልለው በሺህ በሚቆጠር ዶላር የስልክ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል። የአውስትራሊያ ንግድ ሚኒስትር የሆኑት ጆን ዋትኪንስ እየተስፋፋ ስለመጣው ስለዚህ አዝማሚያ ሲናገሩ “ባሁኑ ጊዜ አንዳንድ ወጣቶች ባለ ዕዳ ሆነውና ዕዳቸውን የማይከፍሉ የሚል መጥፎ ስም አትርፈው ከትምህርት ቤት ይመረቃሉ። እንዲህ ባለ ሁኔታ ኑሮን መጀመር በጣም የሚያሳዝን ነው” ብለዋል። ጋዜጣው ወጣቶችን እንዲህ ባለው የዕዳ ወጥመድ እንዳይያዙ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል። የምታደርገው የስልክ ጥሪ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍልህ በቅድሚያ አረጋግጥ። ዕዳ እንዳይጠራቀምብህ በቅድሚያ በተከፈለ የስልክ ሂሣብ ተጠቀም። ወጪህን ለመቀነስ አነስተኛ ዋጋ በሚከፈልባቸው ሰዓቶች ለመደወል ሞክር።

የመኖሪያ ቤት እጦት እየተስፋፋ ነው

“ተመድ በ1948 ባወጣው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ላይ ጥሩ የሆነ ቤት ማግኘት እጅግ አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ነገር እንደሆነ ገልጿል። ሆኖም ይህ ድንጋጌ ከወጣ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያለፈ ቢሆንም ቤት የማግኘት መብት አሁንም ሊረጋገጥ አልቻለም” ይላል ቢ ቢ ሲ ያወጣው የዜና ዘገባ። ተመድ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በዓለም ዙሪያ 30 ሚልዮን ሕፃናትን ጨምሮ 100 ሚልዮን ሰዎች ቤት እንደሌላቸው የሚገመት ሲሆን ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን በመግለጽ አስጠንቅቋል። በታዳጊ አገሮች ለችግሩ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፉ መምጣታቸው እንደሆነ ተመድ ይገልጻል። ከዚህም በተጨማሪ በደቡብ ምሥራቅ እስያና በአፍሪካ ወደ 600 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ንጽሕናቸው ባልተጠበቀና በቂ ውኃ በሌለባቸው እጅግ የተጨናነቁ ደሳሳ ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ። የበለጸጉት አገሮችም ከዚህ ችግር ነፃ አይደሉም። በዩናይትድ ስቴትስ እስከ 700, 000 የሚደርሱ ሰዎች የሚኖሩት ጎዳና ላይ ነው። በአንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከ1, 000 ሰዎች መካከል 12ቱ መኖሪያ ቤት የላቸውም።

ወንጀል የሚያስከትለው ከፍተኛ ኪሳራ

“በእንግሊዝና በዌልስ የሚፈጸመው ወንጀል በኅብረተሰቡ ላይ በየዓመቱ የ60 ቢልዮን ፓውንድ [85 ቢልዮን ዶላር] ኪሳራ እያደረሰ ይገኛል” ሲል የለንደኑ ዚ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል። ትክክለኛ መረጃን መሠረት በማድረግ በአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተገለጸው ይህ አኃዝ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት ጋር ሲነጻጸር 6.7 በመቶ ይሆናል። ሆን ተብሎም ሆነ ሳይታሰብ የሚፈጸሙ ነፍስ ግድያዎች ከፍተኛ ኪሳራ በማስከተል ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው ሲሆን ሁለቱም ዓይነት የነፍስ ግድያ ወንጀሎች እያንዳንዳቸው በአገሪቱ ላይ የሚያደርሱት ኪሳራ በአማካይ ከ1 ሚልዮን ፓውንድ [1.4 ሚልዮን ዶላር] በላይ ይሆናል። በአንጻሩ ኃይል በመጠቀም የሚፈጸሙ ሌሎች ከባድ ወንጀሎች እያንዳንዳቸው በአማካይ 19, 000 ፓውንድ [27, 000 ዶላር] ኪሳራ ያደርሳሉ። በአገሪቱ ላይ ከሚደርሰው አጠቃላይ ኪሳራ አንድ አራተኛ የሚሆነው በማጭበርበርና ሰነዶችን አስመስሎ በመሥራት በሚፈጸሙ ወንጀሎች ሳቢያ የሚከሰት ነው። እነዚህ አኃዞች “ወንጀልን በመፍራት የሚወጡ ወጪዎችን፣ የድርጊቱ ሰለባ በሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ፣ መንግሥት ወንጀልን ለመከላከል የሚያወጣውን ገንዘብ . . . ወይም ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚቀርበውን የካሣ ጥያቄ” አይጨምሩም ሲል ጋዜጣው አክሎ ገልጿል።

በልጆች ላይ የሚደርሱ ድንገተኛ አደጋዎች

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በ26 አገሮች ያካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው በዓለማችን ሀብታም አገሮች ውስጥ ለልጆች ሕይወት መቀጠፍ ዋነኛው መንስኤ ድንገተኛ አደጋ ነው። “ጥናቱ በተካሄደባቸው አገሮች ከ1 እስከ 14 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ በሞት ከሚቀጠፉት ልጆች መካከል 40 በመቶዎቹ የሚሞቱት በሚደርስባቸው ጉዳት ሳቢያ” ሲሆን በዚህ ሁኔታ በየዓመቱ የሚሞቱት ልጆች ቁጥር ወደ 20, 000 ይጠጋል ሲል የጃፓኑ ማይኒቺ ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል። ድህነት፣ በነጠላ ወላጅ ማደግ፣ ብዙ ልጆች ማሳደግና ወላጆች በአልኮልና በዕፅ ሱስ መጠመዳቸው ልጆች ለጉዳት እንዲጋለጡ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ዩኒሴፍ “የራስ ቁር ማድረግ፣ ሰዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ ፍጥነት አለማሽከርከር፣ በመኪናዎች ውስጥ የሕፃናት መቀመጫ ማስገጠም፣ በጉዞ ወቅት የአደጋ መከላከያ ቀበቶ ማሰር፣ መድኃኒቶች ሕፃናት በቀላሉ ሊከፍቷቸው የማይችሏቸው መክደኛዎች እንዲኖሯቸው ማድረግ፣ ጭስ በሚፈጠርበት ጊዜ ድምፅ የሚያሰሙ መሣሪያዎች ቤት ውስጥ ማስገጠምና ልጆች በሚጫወቱባቸው አካባቢዎች ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እንዳይኖሩ ጥንቃቄ ማድረግን የመሳሰሉ አስተማማኝ የአደጋ መከላከያዎች” ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አጥ​ብቆ አሳስቧል።

“በመላእክት ታምናለህ?”

ይህ ጥያቄ ከ500 ለሚበልጡ የኪውቤክ ነዋሪዎች ቀርቦ የነበረ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 66 በመቶ የሚሆኑት አዎንታዊ መልስ ሰጥተዋል። የካናዳው ለ ዡርናል ደ ሞንትሬያል እንደዘገበው ከሆነ አንድ ተመራማሪ ብዙዎች በመንፈሳዊ ኃይል እምነት ሊያድርባቸው የቻለው የቡዲዝም ሃይማኖት በግዛቲቱ ባሳደረው ተጽዕኖ ጭምር እንጂ በሮማ ካቶሊክ ብቻ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ሆኖም የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት ማርታን ዦፍርዋ ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል በዲያብሎስ መኖር ያመኑት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸው በጣም አስገርሟቸዋል። “የሚያሳስበው ብዙዎች አዎንታዊ የሆነውን ነገር ብቻ የመቀበል አዝማሚያ ያላቸው መሆኑ ነው። በመላእክት መኖር እናምናለን፤ በዲያብሎስ መኖር ግን አናምንም። አሉታዊ የሆነውን ነገር ወደ ጎን ገሸሽ እናደርጋለን” ሲሉ ገልጸዋል።

በፈረንሳይ የሚገኝ የተሰወረ አደጋ

ከአንደኛውና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተረፉ 1.3 ሚልዮን ቶን የሚገመቱ ለሕይወት አደገኛ የሆኑ መሣሪያዎች በፈረንሳይ ከርሰ ምድር ውስጥ ተቀብረው ይገኛሉ በማለት ለ ፊጋሮ ሪፖርት አድርጓል። የቀድሞዎቹ የጦር ግንባሮች ብዙ ዘመን ባስቆጠሩ ቦምቦችና የኬሚካል ጥይቶች የተሸፈኑ በመሆናቸው አሁንም ድረስ በሰዎችም ሆነ በአካባቢው ላይ አደጋ እየፈጠሩ ነው። በፊት ሰው አልባ የነበሩ አካባቢዎች አሁን ሰው የሚኖርባቸው ወይም ኢንዱስትሪ የተተከለባቸው በመሆናቸው ቦምብ አስወጋጅ ጓዶች በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ የስልክ ጥሪዎችን ያስተናግዳሉ። እንዲህም ሆኖ በመቶ የሚቆጠሩ አደጋዎች የሚደርሱ ሲሆን ከ1945 እስከ 1985 ድረስ ባሉት ጊዜያት ከ600 የሚበልጡ ባለሙያዎች በሥራ ላይ እያሉ ሞተዋል። በዚህ ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህን የጦር መሣሪያዎች ለማስወገድ 700 ዓመታት ሊወስድ ይችላል።

ለአገር ጎብኚዎች ውኃ?

“በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ የመዝናኛ ሥፍራዎች ተጨማሪ መዋኛዎችና የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ በሚፈልጉ አገር ጎብኚዎች እየተጥለቀለቁ በመሆኑ የውኃ አቅርቦታቸው በመሟጠጥ ላይ ይገኛል” በማለት የለንደኑ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል። “ችግሩ መጠነ ሰፊና ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ነው” በማለት የቱሪዝም ጉዳይ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ትሪሻ ባርኔት ተናግረዋል። “አንዳንድ ጊዜ [በአፍሪካ] አንድ ቧንቧ ብቻ ያለው መንደር ታገኛላችሁ። በአንጻሩ ግን እያንዳንዱ ሆቴል በየክፍሉ የቧንቧ ውኃና ገላ መታጠቢያ አለው።” አንድ ዓለም ዓቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ድርጅት እንዳሰላው ስፔይንን የሚጎበኝ አንድ አገር ጎብኚ በቀን 880 ሊትር ውኃ ሲጠቀም የአገሪቱ ነዋሪ ግን የሚጠቀመው 250 ሊትር ውኃ ብቻ ነው። ደረቅ የአየር ንብረት ባለበት አገር የሚገኝ 18 የጎልፍ መጫወቻ ጉድጓዶች ያሉት አንድ ሜዳ 10, 000 ነዋሪ ያላት ከተማ የሚያስፈልጋትን ያህል ውኃ ይፈልጋል። የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት በሰጠው ግምት መሠረት 100 አገር ጎብኚዎች በ55 ቀናት ውስጥ የሚጨርሱት የውኃ መጠን 100 መንደርተኞችን ለ15 ዓመታት ሊመግብ የሚችል ሩዝ ማብቀል ይችላል።

ማጨስ የሚያስከትለው አደጋ

“በሳንባ ካንሰር ከሚሞቱት ሲጋራ የማያጨሱ ስምንት ሰዎች መካከል አንደኛው የሚሞተው ሌላ ሰው የሚያጨሰውን የሲጋራ ጭስ በመሳብ በሚፈጠር ካንሰር ነው” በማለት በጃፓን ብሔራዊ የካንሰር ማዕከል የምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ናኦሂቶ ያማጉቺ ተናግረዋል። ሳይንቲስቶች እዚህ ግኝት ላይ የደረሱት በሳንባ ካንሰር በሞቱ 52, 000 በሚያክሉ ሰዎች ላይ በተካሄደ ጥናት ነው። በተጨማሪም “ለረዥም ጊዜያት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው መርዛማ የሆኑት ካርቦን ሞኖኦክሳይድና ካንሰር የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች በከፍተኛ መጠን የሚገኙት ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ወደ ውስጥ በሚያስገቡት ጭስ ውስጥ ሳይሆን ወደማያጨሱት ሰዎች በሚቦነው የሲጋራ ጭስ ውስጥ ነው” በማለት አሳሂ ሺምቡን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። በ1999 የጃፓን መንግሥት 14, 000 በሚያክሉ ሰዎች ላይ ባደረገው ጥናት መሠረት ሥራ ወይም ትምህርት ቤት ከሚውሉት 35 በመቶ የሚያክሉ ሰዎችና ቤት ውስጥ ከሚውሉት 28 በመቶ የሚያክሉ ሰዎች ሌላ ሰው ለሚያጨሰው የሲጋራ ጭስ የተጋለጡ ናቸው። “አጫሾች ሁለቱን ቡድኖች ለመለየት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እስኪጠይቅ ድረስ በማያጨሱ ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ እንዳሉ ሊያውቁት ይገባል” በማለት ያማጉቺ ተናግረዋል።