ክርስትያኖች በዘመን መለወጫ በዓል መካፈል ይኖርባቸዋልን?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ክርስትያኖች በዘመን መለወጫ በዓል መካፈል ይኖርባቸዋልን?
“በዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ የከሰዓት በኋላው ጊዜ ከወትሮው በተለየ መልኩ ረጭ ያለ ነው” ይላሉ በብራዚል የሕክምና ዶክተር የሆኑት ፈርናንዱ። “ከዚያም ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ በስለት ተወግተው ወይም በጥይት ተመትተው የቆሰሉ ሰዎች፣ የመኪና አደጋ የደረሰባቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች እንዲሁም በባሎቻቸው የተደበደቡ ሚስቶች መጉረፍ ይጀምራሉ። በሁሉም አጋጣሚዎች ማለት ይቻላል የችግሩ መንስኤ የአልኮል መጠጥ ነው።”
ከላይ ካለው አንጻር አንድ የብራዚል ጋዜጣ የዓመቱን የመጀመሪያ ቀን ዓለም አቀፍ የአንጎበር ቀን ብሎ መጥራቱ ምንም አያስደንቀንም። አንድ የአውሮፓ የዜና ወኪል ደግሞ “የዘመን መለወጫ በሕይወታቸው ውስጥ ለፈንጠዝያ ትልቅ ግምት የሚሰጡ ተራ ሰዎች የሚያከብሩት በዓል ነው” ከማለቱም ሌላ ይህ በዓል “በሰው ልጅና በአልኮል መካከል በሚደረገው የማያቋርጥ ትግል ውስጥ አንድ ተጨማሪ ዙር” እንደሆነ ገልጿል።
እርግጥ ሁሉም ሰው የዘመን መለወጫን በመስከርና የዓመፅ ድርጊቶችን በመፈጸም ያሳልፈዋል ማለት አይደለም። እንዲያውም ብዙዎች የዚህ በዓል አስደሳች ትዝታዎች አሏቸው። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ፈርናንዱ እንዲህ ይላሉ:- “ልጆች እያለን የዘመን መለወጫ ዋዜማ በጉጉት የምንጠብቀው ነገር ነበር። ብዙ ዓይነት ጨዋታዎች፣ ምግቦችና የአልኮል መጠጦች ነበሩ። እኩለ ሌሊት ሲሆን ተቃቅፈን እየተሳሳምን ‘መልካም አዲስ ዓመት!’ እንባባል ነበር።”
ዛሬም በተመሳሳይ ብዙዎች ሚዛናቸውን ሳይስቱ የዘመን መለወጫን እንደሚያከብሩ ይሰማቸዋል። ያም ሆኖ ክርስትያኖች የዚህን ተወዳጅ በዓል አመጣጥና ትርጉም መመርመራቸው ጠቃሚ ይሆናል። የዘመን መለወጫ በዓል ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ይጋጫልን?
ታሪክ ምን ይላል?
የዘመን መለወጫ ዛሬ የተጀመረ በዓል አይደለም። ተቀርጸው የተገኙ ጥንታዊ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት በሦስተኛው ሺህ ዓመት ከዘአበ ሳይቀር በባቢሎን ይከበር ነበር። በመጋቢት አጋማሽ ላይ የሚከበረው ይህ በዓል ከፍተኛ ቦታ
ይሰጠው ነበር። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ “በሥነ ሥርዓቱ ላይ ማርዱክ የተባለው አምላክ አገሪቱ በቀጣዩ ዓመት የሚኖራትን ዕጣ ይወስን ነበር” ይላል። የባቢሎናውያን የዘመን መለወጫ በዓል ለ11 ቀናት የሚቆይ ሲሆን መሥዋዕቶችን፣ ሰልፎችን እንዲሁም የመራባት ሥርዓተ አምልኮን ያካትት ነበር።ለተወሰነ ጊዜ ሮማውያንም ዓመቱን የሚጀምሩት በመጋቢት ወር ነበር። በ46 ከዘአበ ግን ንጉሠ ነገሥት ጁሊየስ ቄሣር የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ጥር እንዲሆን ደነገገ። ያ ቀን የመጀመሪያዎች አምላክ ለሆነው ለጃኑስ የተወሰነ ነበር፤ አሁን ደግሞ የዓመቱ የመጀመሪያ ቀንም ሊሆን ነው። ቀኑ ቢለወጥም ፈንጠዝያ የተሞላው አከባበሩ ግን አልተቀየረም። የማክሊንቶክ እና ስትሮንግ ሳይክሎፔድያ ስለ በዓሉ አከባበር ሲገልጽ በጥር መጀመሪያ ላይ ሰዎች “መረን በለቀቁ ድርጊቶችና አረመኔያዊ በሆኑ አጉል እምነቶች ይጠመዱ ነበር” ይላል።
ዛሬም ቢሆን በዘመን መለወጫ በዓል አከባበር ላይ ከአጉል እምነት የመነጩ ልማዶች ይታያሉ። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ የደቡብ አሜሪካ አገሮች ብዙዎች አዲሱን ዓመት በቀኝ እግራቸው ቆመው ይቀበሉታል። ሌሎች ደግሞ ጥሩንባ ይነፋሉ እንዲሁም ርችቶችን ይተኩሳሉ። በቼክ ባሕል የአዲስ ዓመት ዋዜማ የምስር ሾርባ የሚበላበት ጊዜ ሲሆን ስሎቫካውያን ደግሞ ገንዘብ ወይም በዓሣ ገላ ላይ የሚገኘውን ቅርፊት ከጠረጴዛ ልብሱ በታች የማስቀመጥ ባሕል አላቸው። ከክፉ ገድ ለመጠበቅና ብልጽግናን ለማስገኘት ተብለው የሚደረጉት እነዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የዘመን መሸጋገሪያ የአዲሱ ዓመት ዕድል የሚወሰንበት ጊዜ ነው የሚለው ጥንት የነበረ እምነት ነጸብራቅ ናቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
መጽሐፍ ቅዱስ “በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን” በማለት ክርስቲያኖችን አጥብቆ ይመክራቸዋል። * (ሮሜ 13:12-14፤ ገላትያ 5:19-21፤ 1 ጴጥሮስ 4:3) መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዛቸው መረን የለቀቁ ተግባራት በዘመን መለወጫ በዓል ላይ ባብዛኛው ስለሚንጸባረቁ ክርስቲያኖች በዚህ በዓል አይካፈሉም። ይህ ማለት ግን ክርስቲያኖች ደስታ የራቃቸው ሰዎች ናቸው ማለት አይደለም። እንዲያውም የአምላክ አገልጋዮች ደስተኞች እንዲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ደጋግሞ እንደሚናገር ያውቃሉ። ደግሞም ደስተኛ የሚሆኑበት ብዙ ምክንያት አላቸው። (ዘዳግም 26:10, 11፤ መዝሙር 32:11፤ ምሳሌ 5:15-19፤ መክብብ 3:22፤ 11:9) መጽሐፍ ቅዱስ በመብልና በመጠጥ ደስታ እንደሚገኝም ይናገራል።—መዝሙር 104:15፤ መክብብ 9:7ለ
ይሁን እንጂ እስካሁን እንደተመለከትነው የዘመን መለወጫ በዓል አከባበር ከአረማዊ ልማዶች ጋር የተሳሰረ ነው። የሐሰት አምልኮ በይሖዋ አምላክ ዓይን ርኩስና አስጸያፊ በመሆኑ ክርስቲያኖች የዚህ ዓይነት መሠረት ካላቸው ልማዶች ይርቃሉ። (ዘዳግም 18:9-12፤ ሕዝቅኤል 22:3, 4) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው?” ጳውሎስ “ርኵስንም አትንኩ” በማለት ጨምሮ የተናገረበት በቂ ምክንያት ነበረው።—2 ቆሮንቶስ 6:14-17ሀ
ክርስትያኖች በአጉል እምነቶች መካፈል ደስታንም ሆነ ብልጽግናን ለማግኘት ዋስትና እንደማይሆንና ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን ሞገስም እንደሚያሳጣ ይገነዘባሉ። (መክብብ 9:11፤ ኢሳይያስ 65:11, 12) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች በአኗኗራቸው ልከኞችና ራሳቸውን የሚገዙ እንዲሆኑ አጥብቆ ይመክራል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 11) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የክርስቶስን ትምህርቶች እንደሚከተል ለሚናገር ሰው በእንደዚህ ዓይነት መረን የለቀቀ የፈንጠዝያ በዓል መካፈል ተገቢ አይሆንም።
የዘመን መለወጫ በዓል አከባበር የቱንም ያህል ቀልብ የሚስብና ማራኪ መስሎ ቢታይ መጽሐፍ ቅዱስ “ርኵስንም አትንኩ” እንዲሁም “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ሲል ይመክረናል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ለሚታዘዙት ይሖዋ እንዲህ ሲል አስደሳች ዋስትና ሰጥቷል:- “እኔም እቀበላችኋለሁ፣ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።” (2 ቆሮንቶስ 6:17ለ–7:1) በርግጥም ለሱ ታማኝ ለሚሆኑት ዘላለማዊ በረከትና ብልጽግናን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።—መዝሙር 37:18, 28፤ ራእይ 21:3, 4, 7
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.12 በአንደኛው መቶ ዘመን እነዚህ ተግባራት በሮም የተለመዱ ስለነበሩ ጳውሎስ ስለ ‘ፈንጠዝያና ስካር’ ያቀረበው ሐሳብ በዘመን መለወጫ በዓል ወቅት የሚደረጉትንም ሳይጨምር አይቀርም።