በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያለዕድሜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ጉዳቱ ምንድን ነው?

ያለዕድሜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ጉዳቱ ምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ  . . .

ያለዕድሜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ጉዳቱ ምንድን ነው?

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምህርት ቤት ያሉ አንዳንድ ወንዶች ልጆች አብሬያቸው እንድወጣ ወይም የሴት ጓደኛቸው እንድሆን እየጠየቁኝ ነው።”​—የ11 ዓመቷ ቤኪ *

“በትምህርት ቤታችን ያሉት አብዛኞቹ ልጆች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥረው ይጫወታሉ። እንዲያውም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ኮሪደሩ ላይ ሲሳሳሙ ማየት አዲስ ነገር አይደለም።”​—የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሊየና

ብዙ ወጣቶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥረው መጫወት የሚጀምሩት በልጅነታቸው ነው። መገናኛ ብዙሃንም ምንም ጉዳት የሌለው መዝናኛ ይመስል የተለመደ ነገር አድርገው ያቀርቡታል። የአሥራ ሁለት ዓመቷ ኦኔደ እንዲህ ትላለች:- “በትምህርት ቤት ሁሉም ልጆች ማለት ይቻላል የወንድ ጓደኛ ወይም የሴት ጓደኛ አላቸው።” ጄኒፈር የተባለች ወጣት ሴት ደግሞ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ጓደኞቻቸው ጋር አዘውትረው እየተቀጣጠሩ የሚጫወቱ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ልጆች ነበሩ።” አክላም እንዲህ ብላለች:- “እኔም 11 ዓመት ሲሆነኝ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሬ እንድጫወት እኩዮቼ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ይሰማኝ ጀመር።”

እንግዲያው በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ የማትጫወቱ ከሆነ እንደተገለላችሁ ሊሰማችሁ ይችላል። እንዲያውም እንደዚያ ባለማድረጋችሁ ምክንያት ሊተርቧችሁና ሊያፌዙባችሁ ይችላሉ። ጄኒፈር ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራ ለመጫወት እንዳልደረሰች ስለተሰማት አብራቸው እንድትወጣ ግብዣ ያቀረቡላትን ወንዶች አትቀበልም ነበር። ውጤቱ ምን ሆነ? ጄኒፈር እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “አሾፉብኝ፤ እንዲሁም መቀለጃ አደረጉኝ።” ማንም ሰው እንዲቀለድበት አይፈልግም። ይሁን እንጂ ሌሎች ስላደረጉት ብቻ እናንተም ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ መጫወት ይኖርባችኋልን? ተቀጣጥሮ መጫወት ማለት ራሱ ምን ማለት ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው?

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ማለት ምን ማለት ነው?

ብዙ ወጣቶች ከአንድ ተቃራኒ ጾታ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ የሚያሳልፉ ቢሆንም ‘እንዲሁ ጓደኛሞች ነን እንጂ የተለየ ግንኙነት የለንም’ ሲሉ ይደመጣሉ። ይሁን እንጂ ተቀጣጥሮ መጫወትም አላችሁት አብሮ መሆን ወይም እንዲያው መጠያየቅ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አንዳቸው ለሌላኛቸው የተለየ ትኩረት በመስጠት አብረው ጊዜ ማሳለፍ ሲጀምሩ ባብዛኛው ከተራ ጓደኝነት ያለፈ ነገር እንዳለ ግልጽ ነው። ደግሞም ከተቃራኒ ጾታ ጋር መጫወት የግድ በአካል መገናኘትን አይጠይቅም። በኢንተርኔት ቻት ሩም፣ በስልክ፣ በደብዳቤ ወይም በኤሌክትሮኒክስ መልእክት የሚደረጉ ውይይቶችም በዚሁ ሥር ሊጠቃለሉ ይችላሉ።

አሁን የሚነሳው ጥያቄ አብዛኛውን ጊዜያችንን ተቃራኒ ጾታ ካለው ተመሳሳይ ሰው ጋር ብቻ ማሳለፍ ምን ያህል ክብደት የሚሰጠው ጉዳይ ነው? የሚለው ነው።

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ሊያስከትል የሚችላቸው አደጋዎች

በምሳሌ 30:​19 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰውም መንገድ ከቈንጆ ጋር” ስለመሆኑ ይናገራል። ይህ አባባል እንደሚጠቁመው በወንድና ሴት መካከል ያለው ግንኙነት የራሱ አቅጣጫ አለው። ሁለቱም ወገኖች የጎለመሱና የአምላክን የሥነ ምግባር መስፈርቶች የሚያከብሩ ሲሆኑ ተቀጣጥሮ መጫወት ወደ ፍቅርና በኋላም ክቡር ወደሆነ ጋብቻ ሊመራ ይችላል። በመሠረቱ አምላክም ወንድና ሴትን የፈጠራቸው እርስ በርስ እንዲሳሳቡ አድርጎ ነው። ይሁን እንጂ የትዳርን ኃላፊነቶች ለመሸከም ካልደረሳችሁስ? አለጊዜው መቀጣጠር በመጀመራችሁ ራሳችሁን ለአደጋ እያጋለጣችሁ ነው።

ለምን? ምክንያቱም ከተቃራኒ ጾታ ጋር ረዘም ያለ ሰዓት ባሳለፋችሁ መጠን ስሜታችሁ መነሳሳቱ የማይቀር ነው። ሳታውቁት ያንን ሰው ለማግኘት መናፈቅ ትጀምራላችሁ። አብራችሁ በማትሆኑበት ጊዜ ስለ እሱ ወይም ስለ እሷ ታስባላችሁ። አብዛኛውን ጊዜ ግን እነዚህ ስሜቶች የአንድ ወገን ብቻ ይሆኑና አንደኛው ወገን ልቡ ይሰበራል። ሁለቱም ወገኖች ተመሳሳይ ስሜት ቢኖራቸው እንኳን ከሁለት አንዳቸው ለጋብቻ ያልደረሱ ወይም ያልበሰሉ ከሆኑ ብስጭትና ሐዘን ይከተላል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ወዴት ሊመራ ይችላል? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፣ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?” ይላል።​—⁠ምሳሌ 6:27

ኒና የተባለች ወጣት ያጋጠማትን ተመልከት። እንዲህ ትላለች:- “በኢንተርኔት ከአንድ ወጣት ጋር ተዋወቅሁ። በየቀኑ በቻት ሩም አማካኝነት ለረዥም ሰዓታት እናወራ ነበር። ስሜቴ በእርሱ ስለተማረከ ሕይወቴ ከሱ ጋር የተሳሰረ ሆነ። ግንኙነታችን አልዘለቀም። ግንኙነቱ ሲቋረጥ ግን ጭንቀት ውስጥ ወደቅሁ። ከዚያም ግንኙነታችን በመቋረጡ ምክንያት ራሱን ሊገድል እንደሆነ ነገረኝ። ያ ደግሞ የባሰ አስጨነቀኝ።” ኒና ያለፈውን መለስ ብላ ስታስበው እንዲህ ትላለች:- “ይህን ያህል መሥዋዕትነት ሊከፈልለት አይገባም! ግንኙነታችን ከተቋረጠ ሁለት ዓመት ያለፈ ቢሆንም እኔ ግን አሁንም በመንፈስ ጭንቀት እሰቃያለሁ።” ኒና ከሌላ ሰው ጋር ስሜታዊ ቅርርብ ለመፍጠር ዕድሜዋ ገና አልደረሰም ነበር።

‘የሰውም መንገድ ከቈንጆ ጋር ነው’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር የጾታ ግንኙነትንም ሊያመለክት የሚችል መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። በዛሬው ጊዜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት ባብዛኛው ለፆታ ግንኙነት እንደ መንደርደሪያ ነው። እንደዋዛ እጅ ለእጅ በመያያዝ ብቻ ይጀምር ይሆናል። ከዚያም እንዲያው አቀፍ ማድረግና ጉንጭ ላይ መሳሳም ይቀጥላል። ዕድሜያቸው ለጋብቻ የደረሰና ቃል የተገባቡ ሁለት ወጣቶች የዚህ ዓይነት የፍቅር መግለጫዎች መለዋወጣቸው አንድ ነገር ነው። ለጋብቻ ያልደረሱ ሁለት ሰዎች የዚህ ዓይነት ባሕርይ ማሳየታቸው ግን ሳያስፈልግ የጾታ ፍላጎትን ከማነሳሳት በቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። “የፍቅር” መግለጫዎች እያደር መስመር እየሳቱ ሊሄዱ ወይም ርኩስ ድርጊት ወደ መፈጸም ሊመሩ ይችላሉ። ከዚያም አልፈው ወደ ዝሙት ድርጊቶች ሊያደርሱ ይችላሉ። *

ዝሙት የሚያስከትላቸው መዘዞች መራራ ናቸው። ዝሙት የሚፈጽሙ አንዳንዶች በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች ይያዛሉ። ሌሎች ደግሞ ለራሳቸው የነበራቸውን ጥሩ ግምት ያጣሉ እንዲሁም ሕሊናቸው ይቆስላል። አንዳንድ ወጣት ሴቶች ያረግዛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” ብሎ ማዘዙ አያስገርምም! (1 ቆሮንቶስ 6:13, 18፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3) ያለጊዜው ተቀጣጥሮ ከመጫወት መቆጠብ ይህንን ትእዛዝ ለማክበር ይረዳችኋል።

ተቀጣጥሮ መጫወት መቼ ቢጀመር ይሻላል?

ይህ ማለት ግን እስከ መቼም ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ መጫወት አትችሉም ማለት አይደለም። ሆኖም በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኙ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ “አፍላ የጉርምስና ዕድሜ” ብሎ በሚጠራው የዕድሜ ክልል ውስጥ ሳትሆኑ አትቀሩም። (1 ቆሮንቶስ 7:​36 NW ) ይህ የወደፊት ማንነታችሁ ገና መቀረጽ የሚጀምርበት ወቅት ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ በአካል፣ በስሜትና በጾታ ፍላጎቶቻችሁ ረገድ መጎልመስ ትጀምራላችሁ። የጾታ ፍላጎቶቻችሁን ጨምሮ ስሜቶቻችሁ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚሁ ስሜቶች በቶሎ ይለወጣሉ። በዚህ ምክንያት በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚመሠረት ፍቅር ባብዛኛው አይዘልቅም። አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ የመጫወት ልማዴ ያዝ ለቀቅ ዓይነት ነበር።”

በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ‘በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ’ ተቀጣጥሮ መጫወት መጀመር ምክንያታዊነት አይሆንም። እውነተኛ ማንነታችሁን፣ የምትወዷቸውንና የምትጠሏቸውን ነገሮች እንዲሁም ልትደርሱባቸው የምትፈልጓቸውን ግቦች ለይታችሁ እስክታውቁ ድረስ ብትቆዩ የተሻለ ይሆናል። ከዚህም በላይ ዕድሜያችሁ ትዳር የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች ለመሸከም የሚያስችል መሆን ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል አንድ ባል የቤተሰቡን አካላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት እንዲያሟላ ይሖዋ ይጠብቅበታል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት ልጅ ከሆንክ ሥራ ይዘህ ሚስትና ምናልባትም ልጆች ለማስተዳደር ተዘጋጅተሃል? መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀው መኖር እንዲችሉ መርዳት በምትችልበት ሁኔታ ላይ ነህ? ወጣት ልጃገረድ ከሆንሽስ? አንዲት ሚስት ባሏን ማፍቀርና ማክበር ይኖርባታል፤ የሚያደርጋቸውን ውሳኔዎችም መደገፍ አለባት። ይህንን ለዘለቄታው ለማድረግ ተዘጋጅተሻል? በየዕለቱ የቤት ውስጥ ጉዳዮችን ለማከናወን ማለትም ምግብ ለማብሰል እንዲሁም ልጆችን ለመንከባከብስ ዝግጁ ነሽ?​—⁠ኤፌሶን 5:22-25, 28-31፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8

በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- በምዕራባውያን አገሮች ወጣት ልጆች የቤተሰቦቻቸውን መኪና ለመንዳት ይጓጓሉ። ይሁን እንጂ አንድ ወጣት ወይም አንዲት ወጣት የቤተሰባቸውን መኪና ለመንዳት ፈቃድ ከማግኘታቸው በፊት ምን እንዲያደርጉ ይፈለግባቸዋል? በብዙ አገሮች የመንጃ ፈቃድ ከማግኘታችሁ በፊት ሥልጠና መውሰድና መፈተን ይኖርባችኋል። ለምን? ምክንያቱም መኪና መንዳት ከባድ ኃላፊነት ነው። መሪውን ስትጨብጡ የራሳችሁም ሆነ የሌሎች ሰዎች ደህንነት ያለው በእናንተ እጅ ነው ማለት ነው። ትዳርም በጣም ከባድ ኃላፊነት ነው! በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኙ ወጣቶች ከሆናችሁ ይህንን ኃላፊነት ለመሸከም አልደረሳችሁ ይሆናል። እንዲያ ከሆነ ደግሞ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ እንድትጫወቱ የሚደርስባችሁን ፈተና መቋቋማችሁ ጥበብ ይሆናል። ምክንያቱም ተቀጣጥሮ መጨዋወት የትዳር ጓደኛ ለማግኘት የሚወሰድ እርምጃ ነው። በቀላል አነጋገር ለማግባት ካልደረሳችሁ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ መጫወት የለባችሁም።

በዚህ ረገድ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ለማድረግ እንድትችሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሶ የሚገኘው ‘እውቀትና ልባምነት’ ያስፈልጋችኋል። (ምሳሌ 1:4 አ.መ.ት ) እንግዲያው በዕድሜ ከሚበልጣችሁ ሰው እውቀትና ተሞክሮ ለመጠቀም መሞከራችሁ ጥሩ ይሆናል። ለጋብቻ መድረስ አለመድረሳችሁን እንድታመዛዝኑ በመርዳት ረገድ ከማንም የተሻለ ሁኔታ ያላቸው ክርስቲያን ወላጆች ናቸው። ከጎለመሱ የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም ምክር ለማግኘት ትፈልጉ ይሆናል። ወላጆቻችሁ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ እንድትጫወቱ የማይፈልጉ ከሆነ ከነሱ ጋር መስማማታችሁ መልካም ይሆናል። የነሱ ፍላጎት ‘ከኀዘን እንድትርቁ’ መርዳት ነው።​—⁠መክብብ 11:10

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ ለመጫወት እንዳልደረሳችሁ ከተሰማቸው እስከዛው ድረስ ትኩረታችሁን በአንድ ሰው ላይ ብቻ ከማድረግ ይልቅ ከብዙ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት እንድትሞክሩ ሐሳብ ያቀርቡላችሁ ይሆናል። ነጠላ ከሆኑና ካገቡ፣ በዕድሜ ከገፉና ከወጣቶች፣ እንዲሁም በእናንተ ዕድሜ ከሚገኙ ሰዎች ጋር መቀራረባችሁ የግል ባሕርያችሁን ለማዳበር እንዲሁም ስለ ሕይወትና ስለ ጋብቻ የተስተካከለ አመለካከት ለመያዝ ይረዳችኋል።

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ ለመጫወት እስክትደርሱ መጠበቁ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም ይህንን ማድረጉ የሚክስ ነው። ‘አፍላ የጉርምስና ዕድሜያችሁን’ የጎለመሰና ኃላፊነት የሚሰማው ትልቅ ሰው ወደ መሆን ደረጃ ለማደግ ከተጠቀማችሁበት ራሳችሁን ከብዙ ችግሮች ታድናላችሁ። ትዳር የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶችና ጫናዎች ለመሸከም የምትችሉ ዓይነት ሰዎች ሆናችሁ ትገኛላችሁ። አጋጣሚውን መንፈሳዊ ሰው ሆናችሁ ለመገኘትም ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ። በዚህ መንገድ መጨረሻ ላይ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥራችሁ ለመጫወት ስትደርሱ ሌሎች ሰዎች በቅርበት ለማወቅ የሚጓጉላችሁ ዓይነት ሰዎች ትሆናላችሁ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.14 ዝሙት የሚል ትርጉም ያለው የመጀመሪያው የግሪክኛ ቃል ፖርኒያ ነው። ቃሉ በጋብቻ ያልተሳሰሩ ሁለት ሰዎች የጾታ ብልቶቻቸውን ለፆታ ድርጊት መጠቀማቸውን ያመለክታል። ይህም የሌላውን ሰው የጾታ ብልት ሆን ብሎ ማሻሸትንና በአፍ የሚደረግ ወሲብንም ይጨምራል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፍቅር መግለጫዎች ብዙውን ጊዜ ወደ ችግር ይመራሉ