በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በኒው ዚላንድ ዶልፊኖችን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ

በኒው ዚላንድ ዶልፊኖችን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ

በኒው ዚላንድ ዶልፊኖችን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ

ኒው ዚላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“ሰውን በሰውነቱ የሚወድ ብቸኛ ፍጡር ነው” ሲል ፕሉታርክ የተባለ ግሪካዊ ደራሲ ጽፏል። ስለ ማን እየተናገረ ነበር? ከዓሣ ነባሪ ጋር የቅርብ ዝምድና ስላለው አጥቢ እንስሳ ስለ ዶልፊን መናገሩ ነበር።

ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዳለው ከሆነ “ዶልፊኖች እንደ ቺምፓንዚዎችና ውሻዎች ካሉ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ካላቸው እንስሳት ጎን እንደሚመደቡ ብዙ ሳይንቲስቶች ያምናሉ።” ሆኖም ፕሉታርክ እንደጠቀሰው ዶልፊኖች ሰውን የሚጠጉት ምግብ ፍለጋ አይደለም። ከዚያ ይልቅ አብዛኞቹ እንዲሁ ከእኛ ጋር መሆን የሚያስደስታቸው ይመስላል። ሚስትሪስ ኦቭ ዘ ዲፕ የተባለው መጽሐፍ “ምንም እንኳ ዶልፊን ከሰው የሚያገኘው ጥቅም ላይኖር ቢችልም የማወቅ ጉጉት ያለውና እኛ አስቂኝ እንቅስቃሴውን በማየት የምንደሰተውን ያህል እሱም የእኛን እንቅስቃሴ በማየት የሚደሰት ይመስላል” ሲል ተናግሯል። በባሕር ውስጥ ከሚኖሩት 32 የዶልፊን ዝርያዎች መካከል 4ቱ በኒው ዚላንድ ይገኛሉ። እነዚህም ኮመን ዶልፊን፣ ቦትል ኖዝድ ዶልፊን፣ ደስኪ ዶልፊንና በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ አነስተኛ የሆነው ሄክተርስ ዶልፊን ናቸው። *

የደሴቶች የባሕር ወሽመጥ በሚባለው ማራኪ ገጽታ ያለው የኒው ዚላንድ የባሕር ዳርቻ አካባቢ ዶልፊኖች በገፍ ይገኛሉ። ይህን ቦታ ለማየት ጓጉተን ስለነበር ራስል ከሚባለው ከተማ በጀልባ ተነሳን። አስጎብኚያችን ከቦትል ኖዝድና ከኮመን ዶልፊኖች በተጨማሪ የዶልፊን ወገን የሆኑትን ኪለር ዌልስና ፓይለት ዌልሶችን የማየት አጋጣሚ ሊኖረን እንደሚችል ነገረችን። እነሱን ለመለየት አናታቸው ላይ ያለውን መተንፈሻ ወይም ከኋላቸው ያለውን ክንፍ ለማየት መጣር እንዳለብን ጠቆመችን። “አንዳንድ ጊዜ አስቀድመው የሚያዩን እነሱ ናቸው!” አለች።

ከዶልፊኖች ጋር መዋኘት

ብዙም ሳይቆይ፣ እስከ 4 ሜትር የሚደርስ ርዝመትና ግዙፍ ሰውነት ያላቸውን ቦትል ኖዝድ ዶልፊኖችን ከፊት ለፊታችን ያየን ሲሆን የኋላ ክንፋቸው ሞገዱን ያለ ችግር ሰንጥቆ ያልፋል። በሚቦርቁበት ጊዜ ጀልባው የሚፈጥረው ሞገድ እየገፋ ይወስዳቸው ነበር። ጀልባዋ ከቆመች በኋላ እኔና አስጎብኚዋ ለማዳ ያልሆኑት ዶልፊኖች አብረናቸው እንድንዋኝበት ወደፈቀዱልን አረንጓዴ መልክ ወዳለው የታችኛው የውኃው ክፍል ቀስ ብለን እየዋኘን ወረድን።

በዶልፊኖቹ የኋላ ክንፍ ተከብቤና መጀመሪያ ወዴት እንደማይ ግራ ተጋብቼ ከስሬ በሚዋኙት አመድማ መልክ ያላቸው አካላት በጣም በመገረም በረጅሙ ተንፍሼ አፍጥጬ ቀረሁ። አንድ ዶልፊን ማንነቴን ለማወቅ ከታች ከመጣ በኋላ በመጠኑ ተገልብጦ ሲሄድ ሆዱ ላይ ያለውን ነጭ የሰውነቱን ክፍል አየሁ። ዶልፊኖቹ ራቅ ብለው የሚዋኙ ቢሆንም እንኳ የሚያሰሙት ድምፅ ጥርት ብሎ ይሰማል። ዶልፊኖቹ የእነሱን ዓይነት ድምፅ ለማሰማት ላደረግሁት ጥረት ምንም ትኩረት ሳይሰጡ ከአካባቢው ርቀው ከሄዱ በኋላ ተመልሰው መጥተው ዙሪያዬን ከበቡኝ።

ዓሣ ማጥመድና ጨዋታ

ተመልሰን ጀልባው ላይ ከተሳፈርን በኋላ ጀልባዋ ዶልፊኖቹን እየተከተለች መጠለያ ወዳለበት ባሕረ ሰላጤ አመራች። እዚያ ስንደርስ እየዘለሉ የሚንቦጫረቁ ለቁጥር የሚታክቱ ብዙ ዶልፊኖች አካባቢውን አጥለቅልቀውት አየን! ዓሣ በማጥመድ ላይ ነበሩ። ዶልፊኖች በአብዛኛው የሚመገቡት ስኩዊድ የተባለ የባሕር እንስሳ፣ ዓሣና ሸርጣን አስተኔን ነው። ከዚህም በላይ ዓሣ የማጥመድ ትምህርት ሲሰጥ ተመለከትን። እናትየው በድምፅዋ ያስበረገገችውን አንድ ትንሽ ዓሣ ልጅዋ በጭራው እየመታ ለመያዝ ጥረት ያደርጋል። ትንሹ ዶልፊን ተጨማሪ ትምህርት ሳያስፈልገው አይቀርም!

ዶልፊኖች አብዛኛው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በመጫወትና አብረው በመሆን ነው። አንድ ዶልፊን የኋላ ክንፉ ላይ የያዘውን የባሕር ውስጥ ተክል እያሳየ በኩራት ያልፋል። አስጎብኚያችን የባሕር ውስጥ ተክል ዶልፊኖች በጣም የሚወዱት መጫወቻ እንደሆነና ክንፋቸው ወይም አፍንጫቸው ላይ አስቀምጠው ለረጅም ጊዜ እንደሚጫወቱበት ነገረችን። አንድ ዶልፊን ሲጫወት ቆይቶ ተክሉን ሲጥለው ሌላው አንስቶ ይጫወትበታል።

‘በድምፅ አማካኝነት የሚፈጠሩ ምናባዊ ምስሎች’

ዶልፊኖች ከውኃ በታች ያለውን አካባቢያቸውን “ማየት” እንዲችሉ የአልትራሳውንድ መሣሪያ ከሚሠራበት የድምፅ ሞገድ ድግግሞሽ ጋር ተመሳሳይ አሠራር ባለው የገደል ማሚቶ ይጠቀማሉ። ዶልፊኖች ድምፅ ካሰሙ በኋላ ተመልሶ የሚመጣላቸው “ምስል” ቀለባቸው እንዲሁም ሰውን ጨምሮ ሌሎች ትኩረታቸውን የሚስቡ ነገሮች ያሉበትን ቦታ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። ዶልፊኖች እርስ በርሳቸው ሐሳብ የሚለዋወጡት ቀጭን ፉጨት በማሰማት ሲሆን ይህ ድምፅ ከሰው ንግግር በአሥር እጥፍ የሚበልጥ የሞገድ ድግግሞሽና ከአራት ከግማሽ በላይ ፍጥነት አለው። ዶልፊኖች እኛ በምናውቀው መልኩ በቋንቋ ከመጠቀም ይልቅ ‘የድምፅ ምስሎች’ የሚፈጥሩ ይመስላል።

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ስለ ዶልፊኖች ገና ብዙ የምንማረው አለ። የሚያስቡበትን መንገድ በተመለከተና ስለ እኛ ምን ብለው እንደሚያስቡ የተሟላ ግንዛቤ የምናገኝበት ቀን ይመጣ ይሆናል። በአድናቆትና በፍቅር ስሜት ተሞልተን በጭጋግ የተሸፈነ ተራራና ነጭ አሸዋ የለበሰ የባሕር ዳርቻ ያለውን ይህን የሚያምር ጭር ያለ ባሕረ ሰላጤ ለዶልፊኖቹ ትተን ሄድን። ለእነዚህ ፍጡራን በፊት ያልነበረን ጥልቅ የአድናቆት ስሜት ያደረብን ከመሆኑም በላይ ለፈጣሪያቸው ያለን አክብሮታዊ ፍርሃትም ጨምሯል።​—⁠ራእይ 4:​11

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 አልፎ አልፎ ኒው ዚላንድ አካባቢ ከሚገኙት ሌሎች ዝርያዎች መካከል አወርግላስ ዶልፊንና ፊንለስ ሳውዘርን ራይት ዌል ዶልፊን ይገኙበታል።

[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ልጅ ማሳደግ

ዶልፊኖች የሚመደቡት ከዓሣ ሳይሆን ከአጥቢ እንስሳት ወገን ነው። በመሆኑም አንድ ትንሽ ዶልፊን በእናቱ ሰውነት ውስጥ የሚዘጋጀውን ወተት ይጠባል። እናትየው እንክብካቤ በምታደርግለት የሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሕይወት ለመቆየት ማወቅ የሚያስፈልገውን ነገር ለልጅዋ ታስተምረዋለች። ለምሳሌ ያህል እያንዳንዱን “ዓረፍተ ነገር” የሚደመድምበትን ልዩ “ምልክት” ጨምሮ በገደል ማሚቶ በመጠቀም አንድ ነገር ያለበትን ቦታ እንዴት ማወቅ እንደሚችል ታስተምረዋለች። በተጨማሪም ዓሣ እንዴት እንደሚያጠምድ፣ እንዴት ተራክቦ እንደሚፈጽምና ከሌሎች ዶልፊኖች ጋር እንዴት አብሮ መኖር እንደሚችል ታስተምረዋለች።

ዶልፊን ሲወለድ በጭራው በኩል የሚወጣ ሲሆን እናቱ ሆድ ውስጥ እያለ ግማሽ ለግማሽ ታጥፎ ነው የሚቀመጠው። አዲስ የተወለዱ ዶልፊኖች ታጥፈው የነበሩበትን ቦታ የሚያሳይ በግልጽ የሚታይ ከላይ ወደታች ቀጥ ያለ መስመር አላቸው። ግልገሉ ዶልፊን እናቱ ውኃውን እየሰነጠቀችለት ስትሄድ ከእርሷ ጋር ተጣብቆ እየዋኘ ይጠባል።

[ምንጭ]

© Jeffrey L. Rotman/CORBIS

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኒው ዚላንድ

የደሴቶች የባሕር ወሽመጥ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቦትልኖዝድ ዶልፊን

[ምንጭ]

© Jeff Rotman

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሄክተርስ ዶልፊን

[ምንጭ]

Photo by Zoe Battersby

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደስኪ ዶልፊን

[ምንጭ]

Mark Jones

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮመን ዶልፊንስ

[ምንጭ]

© R.E. Barber/Visuals Unlimited