በአርትራይተስ የሚሠቃዩ ሰዎች ያላቸው ተስፋ
በአርትራይተስ የሚሠቃዩ ሰዎች ያላቸው ተስፋ
“አርትራይተስ እንደ ካንሰርና እንደ ልብ ሕመም ዋነኛ ገዳይ በሽታ አይሁን እንጂ በሕይወት ጣዕም ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል” ይላሉ ዶክተር ፋቲማ ሚላይ። አርትራይተስ የማይነካው የሕይወት ዘርፍ የለም። በአርትራይተስ የሚሠቃዩ ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እነዚህን ችግሮችስ መቋቋም ይቻላል?
የ28 ዓመቷ ኢጣሊያዊት ካትያ * “በአርትራይተስ እንደተያዝኩ ከታወቀበት የ20 ዓመት ዕድሜዬ ጀምሮ መላው ሕይወቴ ተለውጧል። በሚሰማኝ ሕመም ምክንያት ሥራዬን ለመተውና እንደሙያዬ አድርጌ የያዝኩትን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለማቋረጥ ተገድጃለሁ” ብላለች። የአርትራይተስ ሕሙማን በሙሉ የሚጋሩት ችግር የሕመም ስሜት ነው። የ63 ዓመቱ እንግሊዛዊ አለን “መጠነኛ ሊሆን ይችላል እንጂ በአንድ የሰውነት ክፍል ሕመም የማይሰማበት ጊዜ የለም” ብሏል። ሌላው ተፈታታኝ ችግር ድካም ነው። የ21 ዓመቷ ሣራ “ሕመሙንና እብጠቱን መቋቋም ቢቻል እንኳን ድካሙን ፈጽሞ መቋቋም አይቻልም” ብላለች።
ስሜታዊ ሥቃይ
የ61 ዓመቷ ጃፓናዊት ሴትሱኮ በእያንዳንዱ ቀን ከከባድ ሕመም ጋር እየታገሉ መኖር “ስሜታዊም ሆነ አእምሯዊ አቅም ያሳጣል” ብላለች። እርሳስ መያዝ ወይም ስልክ ማንሳት እንኳን ከባድ ሥራ የሚሆንበት ጊዜ አለ! የ47 ዓመቷ ካዙሚ “ሕፃን ልጅ እንኳን ሊያደርጋቸው የሚችላቸው ቀላል ነገሮች አስቸጋሪ ሆነውብኛል” በማለት ታማርራለች። በሁለት እግሮቿ ቆማ መራመድ የተሳናት የ60 ዓመቷ ጃኒስ ደግሞ “ከዚህ በፊት አደርጋቸው የነበሩትን ነገሮች ማድረግ አለመቻሌ ተስፋ ያስቆርጠኛል” ብላለች።
እንደነዚህ ያሉት እክሎች ብስጭትና አሉታዊ ስሜት ሊያሳድሩ ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክር የሆነው የ27 ዓመቱ ጋኩ “በወንጌላዊነቱ ሥራ እንደልብ ለመካፈል አለመቻሌ ወይም በጉባኤ የሚሰጡኝን የሥራ ምድቦች አለማከናወኔ ዋጋ የሌለኝ ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል” ብሏል። ከሁለት ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ ከአርትራይተስ ጋር ስትታገል የኖረችው ፍራንቼስካ “ከቀን ወደ ቀን መውጫ በሌለው ተስፋ የመቁረጥ ባሕር ውስጥ እየሰጠምኩ እንዳለሁ ይሰማኛል” ብላለች። እንዲህ ያለው ተስፋ ማጣት መንፈሳዊ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። በደቡብ አፍሪካ የምትኖረው ጆይስ የተባለች የይሖዋ ምሥክር ራሷን ከክርስቲያን ጉባኤ ማግለል እንደጀመረች ተናግራለች። “ማንንም ሰው ለማየት ከማልችልበት ደረጃ ደርሼ ነበር” በማለት ታስረዳለች።
በተጨማሪም በዚህ በሽታ የተዋጠ ሰው በበርካታ ፍርሃቶች ይዋጣል። መንቀሳቀስ ያቅተኝና ሙሉ በሙሉ ሰው እጅ ላይ እወድቃለሁ ብሎ ይፈራል። አስታማሚ አጣለሁ ብሎ ይፈራል። እወድቅና አጥንቴ ይሰበራል ብሎ ይፈራል። ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን መተዳደሪያ ማግኘት ያቅተኛል ብሎ ይፈራል። የ52 ዓመቷ ዮኮ “የአንጓዎቼ ቅርጽ መበላሸት መጀመሩን ስመለከት እየተባባሰ ይሄድ ይሆናል ብዬ መስጋት ጀመርኩ” ብላ ሳትሸሽግ ተናግራለች።
የቤተሰብ አባሎችም በየቀኑ የሚወዱት ሰው ሲሠቃይ ሲመለከቱ እነርሱም በስሜት ይሠቃያሉ። እንዲያውም አንዳንድ
ባልና ሚስቶች ትዳራቸው ከባድ ችግር ላይ ይወድቅባቸዋል። በእንግሊዝ አገር የምትኖር ዴኒዝ የተባለች ሴት “ለ15 ዓመት በትዳር ካሳለፍን በኋላ ባለቤቴ ሕመምሽን መቋቋም አልቻልኩም ብሎ እኔንና የ5 ዓመት ልጄን ጥሎን ሄደ” ትላለች።ስለዚህ አርትራይተስ በታማሚዎቹም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ላይ ከባድ ችግር ያስከትላል። ቢሆንም ብዙዎቹ ያጋጠሟቸውን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ መቋቋም ችለዋል! ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ እንዴት መቋቋም እንደቻሉ እንመልከት።
ያለብህን የአቅም ውስንነት ተቀብለህ መኖር
በአርትራይተስ የምትሠቃይ ከሆነ በቂ እረፍት ማግኘት ያስፈልግሃል። የሚሰማህን የድካም ስሜት ይቀንስልሃል። እንዲህ ሲባል ግን አልጋ ላይ ውለህ ታድራለህ ማለት አይደለም። ቲሞቲ እንዲህ በማለት ያስረዳል “በአርትራይተስ ሙሉ በሙሉ ከተሸነፍክ ተቀምጠህ ሙሉ በሙሉ ሥቃይህን ብቻ ስለምታዳምጥ በሽታው እንዳይቆጣጠርህ መንቀሳቀስህን ማቆም የለብህም።” የማዮ ክሊኒክ ባልደረባ የሆኑት ሩማቶሎጂስቱ ዶክተር ዊልያም ጊንዘበርግ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “ሥራ በማብዛትና በበቂ መጠን ባለመንቀሳቀስ መካከል ያለው መለያ መስመር በጣም ቀጭን ነው። አንዳንድ ጊዜ ሕመምተኞቹን እንቅስቃሴያቸውን እንዲቀንሱና በሽታቸውን እንዲያዳምጡ ማሳሰብ አስፈላጊ ይሆናል።”
ይህም ላጋጠመህ የአቅም ውስንነት ያለህን አመለካከት መለወጥ ሊጠይቅብህ ይችላል። በደቡብ አፍሪካ የምትኖረው ዳፍኒ እንዲህ ትላለች:- “አቅሜን ማወቅና አንዳንድ ነገሮችን መሥራት ገና ያላቃተኝ ቢሆንም በጣም ቀስ ብዬ መሥራት እንደሚኖርብኝ እገነዘባለሁ። ተስፋ ከመቁረጥና ከመበሳጨት ይልቅ በአንድ ጊዜ ትንሽ ትንሽ ነገር ብቻ እሠራለሁ።”
በተጨማሪም አንዳንድ ሥራዎችን ለማከናወን ከሚያግዙ መሣሪያዎች ጋር መተዋወቅ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ሐኪምህን ማማከር ሊያስፈልግህ ይችላል። ኬይኮ እንዲህ ትላለች:- “ደረጃ የሚያስወጣ መሣሪያ አስገብተናል። የበር መክፈቻ እጀታ ማዞር የእጅ አንጓዬን ያሳምመኝ ስለነበር እጀታዎቹን ለወጥን። አሁን ሁሉንም በሮች በግንባሬ ገፋ በማድረግ መክፈት እችላለሁ። በውኃ ቧንቧዎች ላይ ወደታች በመጫን የሚከፈቱ መክፈቻ ስላስገጠምን ቢያንስ አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወን ችያለሁ።” ሌላዋ ጌይል የተባለች በአርትራይተስ የምትሠቃይ ሴት እንዲህ ትላለች:- “የመኪናዬና የቤቴ ቁልፎች ረዥም እጀታ ስላላቸው ለማዞር ቀላል ሆኖልኛል። ማበጠሪያዬና የጠጉር ብሩሼ ረዥምና በቀላሉ ሊዟዟር የሚችል እጀታ አላቸው።”
የቤተሰብ ድጋፍ ‘የብርታት ምንጭ ነው’
በብራዚል የምትኖረው ካርላ እንዲህ ትላለች:- “ባለቤቴ የሚሰጠኝ ድጋፍ በጣም ወሳኝ ሆኖልኛል። አብሮኝ ሐኪም ቤት መሄዱ ድፍረት ይጨምርልኛል። በሽታው በአካሌ ላይ ምን ለውጥ እንደሚያስከትል፣ የሕመሙ ምልክቶች ምን እንደሆኑና ምን ዓይነት ሕክምናዎች አስፈላጊ እንደሚሆኑ አብረን ተምረናል። ችግሬን እንደሚረዳልኝ ስለማውቅ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል።” አዎን፣ የትዳር ጓደኞቻቸውን የአቅም ውስንነት የሚቀበሉና ስለ ትዳር ጓደኛቸው ሕመም በቂ እውቀት ለማግኘት ፈቃደኛ የሚሆኑ ባሎች ወይም ሚስቶች ከፍተኛ ድጋፍና እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
ለምሳሌ ቤቲ ባለቤቷ በአርትራይተስ ምክንያት የሕንፃ ግንባታ ሥራውን እንዲተው በተገደደ ጊዜ የጽዳት ሥራ ጀመረች። የካዙሚ ባለቤት እሷን ከማስታመም በተጨማሪ እርሷ ልታከናውን ያልቻለችውን የቤት ውስጥ ሥራ ይሠራል። በተጨማሪም ልጆቻቸው የአቅማቸውን ያህል እንዲያግዙ አሠልጥኗቸዋል። ካዙሚ “ባለቤቴ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። እርሱ ባይረዳኝ ኖሮ በጣም በባሰ ሁኔታ ውስጥ እወድቅ ነበር” ብላለች።
በአውስትራሊያ የምትኖር ካሮል የተባለች ሴት የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ትሰጣለች:- “ፕሮግራማችሁ በብዙ ሥራዎች የተጣበበ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ከቤተሰቦቼ እኩል መንቀሳቀስ ሲያቅተኝ አቅመ ቢስ መሆኔ በይበልጥ ይሰማኛል።” የቤተሰብ ድጋፍ በትክክለኛ ማስተዋልና አሳቢነት ከተሰጠ ለታማሚዎች የጥንካሬና የብርታት ምንጭ ይሆናል።
መንፈሳዊ እርዳታ
ካትያ እንዲህ ትላለች:- “አንዲት ሴት እንዲህ ባለው ሕመም በምትሠቃይበት ጊዜ ሥቃይዋን የሚያውቅላት ሰው እንደሌለ ይሰማታል። በዚህ ምክንያት ይሖዋ አካላዊና ስሜታዊ ችግራችንን እንደሚረዳልን ተገንዝቦ ወደ እርሱ በጸሎት መቅረብ አስፈላጊ ይሆናል። (መዝሙር 31:7) ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረኝ ማድረጌ በሽታዬን በእርጋታ ተቀብዬ እንድኖርና የአእምሮ ሰላሜን እንድጠብቅ አስችሎኛል።” መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” እንደሆነ መናገሩ ፍጹም ተገቢ ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
ስለዚህ ሥር በሰደደ ሕመም ለሚሠቃይ ሰው ጸሎት ከፍተኛ ኃይል ያለው ማጽናኛ ያስገኝለታል። ካዙሚ እንዲህ ትላለች:- “በሕመሙ ምክንያት እንቅልፍ በማጣታቸው ረዥም ሌሊቶች ሥቃዬን በጽናት ለመቋቋም የሚያስችለኝን ጥንካሬና ችግሮቼን ለመወጣት የሚረዳኝን ጥበብ እንዲሰጠኝ በመለመን እያለቀስኩ ከልቤ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። እርሱም ጸሎቴን ይመልስልኛል።” ፍራንቼስካም በተመሳሳይ የአምላክን ፍቅራዊ ድጋፍ ለማግኘት ችላለች። “‘ኃይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ’ የሚሉትን የፊልጵስዩስ 4:13 [አ.መ.ት ] ቃላት እውነተኝነት በራሴ ለማየት ችያለሁ” ብላለች።
ብዙውን ጊዜ ይሖዋ አምላክ ድጋፍ የሚሰጠው በክርስቲያን ጉባኤ በኩል ነው። ለምሳሌ ጌይል ባለችበት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ካሉ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ስላገኘችው መንፈሳዊ እርዳታ ስትናገር “ፍቅራቸው በጭንቀት እንዳልዋጥ ረድቶኛል” ብላለች። ኬይኮም በተመሳሳይ “በሕይወቴ ውስጥ ያስደስተኛል ብለሽ የምታስቢው ነገር አለ?” ተብላ ስትጠየቅ “አዎን፣ በጉባኤ ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች የማገኘው ፍቅርና አሳቢነት ነው” ስትል መልሳለች።
በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የበላይ ተመልካቾች እንዲህ ያለውን ድጋፍ በመስጠት ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው ይገኛሉ። ሴትሱኮ “ሽማግሌዎች አንድን በሕመም የሚሠቃይ ሰው አዳምጠው ማጽናናታቸው እንዴት ያለ ግሩም ውጤት እንዳለው መግለጽ ያስቸግረኛል” ብላለች። ይሁን እንጂ ዳንኤል የተባለ የአርትራይተስ ታማሚ እንዳለው “መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሊረዱን የሚችሉት እንዲረዱን ከፈቀድንላቸው ብቻ ነው።” ስለዚህ ታማሚዎች ከክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጋር አዘውትረው መገናኘታቸውና አቅማቸው በፈቀደ መጠን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸው አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25) በነዚህ ስብሰባዎች ላይ ለመጽናት የሚረዳቸውን መንፈሳዊ ማበረታቻ ያገኛሉ።
ሥቃይ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል
የአርትራይተስ ታማሚዎች ለሕክምናው ሙያና እስካሁን ለተገኙት የሕክምና እድገቶች አመስጋኞች ናቸው። ይሁን እንጂ በጣም የተሻለ ነው የሚባለው ሕክምና እንኳን ፈጽሞ የተሟላ ፈውስ ሊያስገኝ አይችልም። የአምላክን የአዲስ ዓለም ተስፋ በመቀበል በእጅጉ ሊጽናኑ ይችላሉ። * (ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:3, 4) በዚያ ዓለም “አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል።” (ኢሳይያስ 35:6) አርትራይተስና የሰውን ልጆች ቀስፈው የያዙት ሌሎች በሽታዎች ለዘላለም ይወገዳሉ! በዚህ ምክንያት በወገብ አርትራይተስ የሚሠቃየው ፒተር “በዚህ በምጓዝበት የጨለመ ዋሻ ጫፍ ላይ ብርሃን ይታየኛል” ብሏል። ጁልያና የተባለች ክርስቲያን ሴትም በተመሳሳይ “የማሳልፈውን እያንዳንዱን ቀን እንደ አንድ የድል ውሎ እቆጥራለሁ። መጨረሻው የሚመጣበት ጊዜ በአንድ ቀን አጥሮልኛል ማለት ነው!” ብላለች። አዎን፣ የአርትራይተስ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዓይነት ሥቃይ ማብቂያ ተቃርቧል!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
^ አን.24 አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች እንዲነግርህ የምትፈልግ ከሆነ አቅራቢያህ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር ተገናኝ ወይም ለዚህ መጽሔት አዘጋጂዎች ጻፍ።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በአርትራይተስ የሚሠቃዩ ሰዎች ጠቃሚ ተግባራትን እንዲያከናውኑ የሚያግዙ በርካታ መሣሪያዎች አሉ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ፍቅራዊ እርዳታ ማግኘት ይቻላል