ቱሪዝም—ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪ
ቱሪዝም—ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪ
ባሃማስ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
‘አሁንስ ዕረፍት መውሰድ አለብኝ’ ብለህ ታውቃለህ? የዕለት ተዕለት ሥራህ ከሚያስከትልብህ ጫና ትንሽ አረፍ ማለት እንደሚያስፈልግህ ተሰምቶህ ይሆናል። ለዕረፍት ራቅ ወዳለ ቦታ ተጉዘህ ታውቃለህ? ይህን ታውቅ ኖሯል? ከአንድ መቶ ዓመት ከማይበልጥ ጊዜ በፊት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሰዎች አብዛኞቹ መደበኛ ዕረፍት አይወስዱም ነበር። በተጨማሪም አብዛኞቹ ሰዎች ከተወለዱበት አካባቢ ከጥቂት መቶ ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ክልል ውስጥ ተወስነው ይኖሩ ነበር። ለደስታም ሆነ ለትምህርት ራቅ ወዳለ አካባቢ መጓዝ ጀብደኛ ወይም ከበርቴ ለሆኑ ጥቂት ግለሰቦች የተወሰነ ቅንጦት ነበር። ዛሬ ግን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የገዛ አገራቸውን ከዚያም አልፎ ዓለምን ከላይ ታች ያቆራርጣሉ። እንዲህ ያለ ለውጥ ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?
ከኢንዱስትሪ አብዮት ወዲህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሸቀጦችን በማምረትና አገልግሎቶችን በማቅረብ ሥራ ላይ ተሰማሩ። ይህም ከፍተኛ ገቢ አስገኘላቸው። በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ምጥቀት አድካሚ የሆኑ ሥራዎችን ሊያከናውኑ የሚችሉ ማሽኖችን አስገኘ። በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ተጨማሪ ትርፍ ጊዜ አስገኘላቸው። በእነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት በ1900ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ብዙ ወጪ የማይጠይቁ የሕዝብ መጓጓዣዎች ሲስፋፉ ቱሪስቶች መጉረፍ ጀመሩ። በዚሁ ጊዜ አካባቢ የተፈለሰፈው የቴሌቪዥን ስርጭት ሩቅ አካባቢ ያሉ ቦታዎች ምስል በየሰዉ ቤት እንዲታይ በማድረግ በሰዎች ልብ ውስጥ የመጓዝ ፍላጎትን ቀሰቀሰ።
በውጤቱ በጣም እያደገ የሄደ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተፈጠረ። የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (ደብልዩ ቲ ኦ) ከአገር ወደ አገር የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር በ1997 ከነበረው 613 ሚልዮን ተነስቶ በ2020 1.6 ቢልዮን እንደሚደርስና እድገቱም ይቀንስ ይሆናል የሚያሰኝ ምንም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ እንደሌለ ተንብዮአል። ከቱሪዝም እድገት ጎን ለጎን ለቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ተቋሞች፣ መዝናኛ ቦታዎችና አገሮች ቁጥርም በዚያው መጠን ጨምሯል።
ወደ ቱሪዝም ገበያ የገቡ አገሮች ተበራክተዋል
ቱሪዝም ሁሉም ወገኖች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ኢንዱስትሪ ነው። ሸማቹ ከመደበኛ ሥራው ፋታ አግኝቶ ጥሩ መስተንግዶ፣ መዝናኛና ትምህርት ያገኛል። አስተናጋጆቹስ ምን ጥቅም ያገኛሉ? ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ጥሩ የውጭ ምንዛሪ ማፍሪያ ነው። አብዛኞቹ አገሮች የሚያስፈልጓቸውን ሸቀጦችና አገልግሎቶች ከውጭ አገሮች ለማስመጣት የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋቸዋል።
እንዲያውም አንድ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው “ዓለም አቀፍ ቱሪዝም የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ በአንደኛ ደረጃ የሚመደብ ሲሆን በበርካታ አገሮች የክፍያ ሚዛን አጠባበቅ ረገድ ወሳኝ ሚና አለው። ከዓለም አቀፍ ቱሪዝም በ1996 የተገኘው የውጭን ምንዛሪ ገቢ 423 ቢልዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን የነዳጅ ውጤቶችን፣ መኪናዎችን፣ የቴሌኮሙኒኬሽን መሣሪያዎችን፣
ጨርቃ ጨርቆችን ወይም ማንኛውንም ሌላ ሸቀጥ ወይም አገልግሎት ወደ ውጭ በመላክ ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በልጧል።” ይኸው ሪፖርት “ቱሪዝም ከማንኛውም የዓለም ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለ ኢንዱስትሪ ሲሆን ከዓለም ጠቅላላ ምርት 10 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይዟል” ብሏል። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ አገሮች፣ አንዳንዶቹን የቀድሞዎቹ የሶቪዬት ህብረት አገሮች ጨምሮ ከዓለም አቀፉ የቱሪስት ኢንዱስትሪ ድርሻቸውን ለማግኘት በመሯሯጥ ላይ ናቸው።መንግሥታት ከቱሪዝም በሚያገኙት ገቢ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና መንገድ የመሰሉትን ታህታይ መዋቅሮች ለማስፋፋት፣ የትምህርት ደረጃ ለማሻሻልና ሌሎች አንገብጋቢ ችግሮቻቸውን ለመወጣት እየተጠቀሙ ነው። ዜጎቹ በሙሉ ሥራ ማግኘታቸው የማያሳስበው መንግሥት የለም። ቱሪዝም የሚፈጥረው የሥራ ዕድል ይህን ቀዳዳ ይደፍናል።
ቱሪዝም በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ውጤት በምሳሌ ለማስረዳት በዩናይትድ ስቴትስ ከምትገኘው ከፍሎሪዳ እስከ ኩባ ደሴት በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ አፍ ላይ ተዘርተው የሚገኙትን የባሃማስ ደሴቶች ሁኔታ እንውሰድ። የባሃማስ ደሴቶች ሰፋፊ እርሻዎች የሌሏቸው ሲሆን አንድም የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ የላቸውም። ይሁን እንጂ እነዚህ ደሴቶች ሞቃታማ አየር፣ ገና ያልተበላሸ የባሕር ጠፈር፣ ከሩብ ሚልዮን የማይበልጡ ሰው ወዳድ ሕዝቦች ሲኖሯቸው ለዩናይትድ ስቴትስም በጣም ቅርብ ናቸው። እነዚህ ጠንካራ ጎኖች ተዳምረው ሞቅ ያለ የቱሪስት ኢንዱስትሪ አስገኝተዋል። ይሁን እንጂ ቱሪስቶች የሚፈልጉትን አስደሳችና ከማንኛውም ዓይነት አደጋ የተጠበቀ የዕረፍት ጊዜ ማቅረብ ምን ነገሮችን ይጠይቃል?
ዘመናዊ ዕረፍት ወሳጆችን ፍላጎት ማርካት
ዓለም አቀፍ ቱሪዝም በጀመረባቸው ዓመታት ረዥም ጉዞ ማድረግ በጣም አድካሚና ከባድ ቢሆንም ለብዙ ተጓዦች እንደ ብርቅ ነገር ይታይ ነበር። ዛሬ ግን መገናኛ ብዙሐን በመስፋፋታቸው ምክንያት ብዙ ሰዎች ከሞቀ ቤታቸው ሳይወጡ የሩቅ አካባቢዎችን ሁኔታ በቴሌቪዥን ማየት ችለዋል። በዚህ ምክንያት የመዝናኛ ሥፍራዎች ሊጎበኟቸው ለመጡ ሰዎች በቤቶቻቸው ያገኙት የነበረው ምቾት ሳይጓደልባቸው በጣም ልዩ የሆነ አስደሳች ጊዜ እንዲያሳልፉ የማስቻል ፈተና ገጥሟቸዋል። በተጨማሪም ብዙ ቱሪስቶች በርካታ ጉዞ ስለሚያደርጉ የቱሪስት ተቀባዮች የሚወዳደሩት በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው።
በዚህ ምክንያት በጣም አስደናቂ የሆኑ የቱሪስት መስህቦችና መዝናኛዎች ብቅ ብቅ ብለዋል። ለምሳሌ ያህል በባሃማስ የሚገኝ አንድ በጣም ትልቅ ሆቴል እንውሰድ። የሆቴሉ የድርጅት ማስፋፊያ ዲሬክተር የሆኑት በቨርሊ ሶንደርስ “ጠቅላላ ሕንጻው ማንም ሰው ሊረሳው የማይችል ትዝታ ይዞ እንዲሄድ ለማድረግ ታስቦ የተሠራ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህም አልፈን ለመሄድ እንፈልጋለን። ከአስተናጋጆቹ ጋር የነበራችሁ ግንኙነትም የማይረሳ ትዝታ ጥሎባችሁ እንዲያልፍ እንፈልጋለን” ብለዋል። እንደነዚህ ያሉት መዝናኛ ቦታዎች ለእንግዶቻቸው የሚያስፈልገውን መስተንግዶና እንክብካቤ የሚያቀርቡት እንዴት ነው?
በመዝናኛ ማዕከሎች ጓዳዎች የሚከናወኑ ሥራዎች
“ሁለት ሺህ ሦስት መቶ የሚያክሉት የሆቴላችን ክፍሎች በሙሉ በሚያዙበት ጊዜ በአንድ ጊዜ የምናስተናግዳቸው ከ7, 500 እስከ 8, 000 የሚደርሱ እንግዶች ይኖሩናል” ይላሉ በቨርሊ። “ይህ የሚፈጥረው የሎጅስቲክ ቅንጅት በጣም ከባድ ነው። እነዚህን እንግዶች በሙሉ ለማስተናገድ የሚያስፈልገው ድርጅትና ዝግጅት አንድ ከተማ ለማስተዳደር ከሚያስፈልገው ነገር ጋር እኩል ሲሆን እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። እንግዶቻችን አገራቸው ሳሉ የለመዷቸውን ዓይነት ምግቦች ማቅረብ ይኖርብናል። ይሁን እንጂ የማይረሳ ትዝታ ይዘው እንዲመለሱ ከተፈለገ አዲስ ዓይነት ምግብና መዝናኛ ማቅረብ ይኖርብናል። በብዙ የመዝናኛ ማዕከሎች ከድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች 50 በመቶ የሚሆኑት ለምግብና መጠጥ አቅርቦት የተመደቡ ናቸው።”
ይህም ሆኖ አይ ኬ ፕራድሃን “ሶሽዮ ካልቸራል ኢምፓክት ኦቭ ቱሪዝም ኢን ኔፓል” በተባለው ጽሑፋቸው ላይ “ለአንድ ተጓዥ የተሟላ ደስታና እርካታ ማግኘት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ነገሮች በሙሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለእንግዶች ከሚያሳዩት አቀባበልና እንግዳው ምንም ዓይነት የሚያሰጋ ነገር እንደማይገጥመው እርግጠኛ እንዲሆን ከማድረግ የበለጠ አስፈላጊ ነገር የለም” ብለዋል።
በዓለም ዙሪያ የተሳካ ውጤት ያገኙ የቱሪስት ማስተናገጃዎች በዚህ ረገድ የእንግዶቻቸውን ፍላጎት ለማርካት የጣሩት እንዴት ነው? የአንድ የባሃማስ እውቅ ሆቴል የሥልጠና ኃላፊ “ማስተማር፣ ተፈላጊዎቹን ባሕርያት መቅረጽ፣ ማሠልጠን፣ ማረም፣ ማስተካከል፣ ከፍተኛ የሆነ የጥራት ደረጃ ያለው አገልግሎት ለማቅረብ ያላሰለሰ ጥረት
ማድረግ ያስፈልጋል” በማለት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። “አብዛኞቹ ባሃማውያን በተፈጥሮአቸው ጨዋዎች ናቸው። ሁልጊዜ በሥራ ቦታ ላይ ተጫዋች፣ ፈገግተኛና ደግ መሆን ግን ያስቸግራል። ምንም ዓይነት ሥራ ቢሰጣቸው ከአንድ ዶክተር ወይም የሕግ ባለሞያ ወይም ከኢንሹራንስ ወኪል የሚፈለገውን ዓይነት የሞያ ብቃት ማሳየት እንደሚኖርባቸው ደጋግመን የምናሳስባቸው በዚህ ምክንያት ነው። በቱሪስቱ መስተንግዶ ውስጥ ለሚካተቱት ነገሮች በሙሉ ቁርጥ ያለና የጠበቀ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች አውጥተናል። እንደ አንድ ቡድን ተቀናጅተን እነዚህን ደረጃዎች ለማሟላት በጣርን መጠን የሥራ ውጤታችን ይበልጥ ከፍተኛና እንከን የለሽ ይሆናል።”ሌላው ገጽታ
ወደ ሌላ አገር ተጉዘህ ከነበረ ምንም ያህል ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ ብታወጣ ያልጠበቅኸው ወጪ ሳያጋጥምህ እንደማይቀር አልተገነዘብክም? የቱሪስት አስተናጋጆችም ተመሳሳይ ችግር እያጋጠማቸው ነው።
ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ፕራድሃን “የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በማደግ ላይ ለሚገኘው ማኅበረሰባችን ብዙ ጥቅሞች ያስገኛል” ብለዋል። ይሁን እንጂ ተገቢ ቁጥጥር ካልተደረገ “መድኃኒት የማይገኝላቸው ማኅበራዊ ችግሮች ሊያቆጠቁጡ ይችላሉ። ዘመናዊ ቱሪዝም የሚያስከትላቸውን የተለያዩ ጫናዎች ለመቋቋም ተገቢውን ግንዛቤ አግኝተን በቂ ዝግጅት ማድረግ አለብን” በማለት አክለዋል። የትኛውን ችግር ማመልከታቸው ነው?
“በርካታ ቁጥር ያላቸውን ቱሪስቶች የሚያስተናግዱ አገሮች ሁልጊዜ ለማለት ይቻላል፣ ሳያስቡት ባሕላዊ አኗኗራቸው በከባድ ሁኔታ ይበረዝባቸዋል። በአንዳንድ ቦታዎች የአካባቢው ባሕል ፈጽሞ ጠፍቷል።” የባሃማስ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ኮርደል ቶምሰን የቱሪዝም መስፋፋት የሚያስከትለውን አንድ መጥፎ ጎን የገለጹት እንዲህ በማለት ነበር። ቶምሰን ቱሪዝም ለአገራቸው ስላስገኛቸው በርካታ ጥቅሞች በኩራት ይናገራሉ። ሆኖም ብዙ ጊዜ ለዕረፍት የመጡ ሰዎች ከመደበኛ ነዋሪዎች ጋር በቁጥር እኩል ወይም የበለጡ በሚሆኑበት አገር መኖር ብዙ ያልታሰቡ ችግሮች ማስከተሉን አልካዱም።
ለምሳሌ ያህል ቱሪስቶችን ከሚያስተናግዱ መካከል አንዳንዶቹ ጎብኚዎቹ ሙሉ ጊዜያቸውን በዕረፍትና በመዝናናት ብቻ የሚያሳልፉ ይመስላቸዋል። የአገሬው ሰዎች ይህን አእምሮአቸው የፈጠረውን ዓይነት ኑሮ ለመኖር ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ እንዲህ ባለው አስተሳሰብ ባይነኩም አብዛኛውን የዕረፍት ጊዜያቸውን በጎብኚዎቹ መጫወቻ ቦታዎች ስለሚያሳልፉ ባሕላዊ አኗኗራቸውን እርግፍ አድርገው ይጥላሉ። አንዳንድ ጊዜ ለቱሪስቶች የተሠሩት መዝናኛ ቦታዎች በአገሬው ነዋሪዎች ይለመዱና የአገሬው ማኅበራዊ ማዕከሎች ቀስ በቀስ ተመናምነው እስከ መሞት ይደርሳሉ።
ብዙዎቹ የታወቁ ዓለም አቀፋዊ የቱሪስት ማዕከሎች በሁለት ተጻራሪ ፍላጎቶች ተወጥረው የተያዙ ናቸው። ከሚጎርፉት ጎብኚዎች የሚያገኙትን ገንዘብ ይፈልጋሉ። ሆኖም ጨዋነት የጎደላቸውን የቱሪስት ፍላጎቶች ለማርካት ታስበው የተቋቋሙ የንግድ ዓይነቶች በሚፈጥሩት ጫና ምክንያት በደረሰባቸው ማኅበራዊ ቀውስ በመታመስ ላይ ናቸው።
ዘላቂነት ያለው ቱሪዝም
ዘመናዊ ቱሪዝም ካስገኛቸው ታላላቅ ጥቅሞች አንዳንዶቹ የራሱን የቱሪዝምን ቀጣይነት አደጋ ላይ በመጣል ላይ በመሆኑ “ቀጣይነት ያለው ቱሪዝም” የሚለው ሐረግ አዘውትሮ የሚደመጥ ሆኗል። አንዳንዶቹ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዓይነቶች የአጭር ጊዜ ትርፍ የሚያስገኙ ቢሆኑም ‘የወርቅ እንቁላል የምትጥለውን ዶሮ የሚገድሉ’ መሆናቸውን መገንዘብ የጀመሩ ሰዎች አሉ። ኢንዱስትሪው ለረዥም ዘመን ቀጣይ እንዲሆን ከተፈለገ አንዳንድ ከባድ ችግሮች መፍትሔ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
ቱሪዝም በአካባቢና በአገሩ ባሕሎች ላይ የሚያሳድረው ጫና፣ ለትርፍ ብቻ በቆሙ ታላላቅ የቱሪስት ማዕከሎች ዓላማና በአስተናጋጅ አገሮች ብሔራዊ ዓላማዎች መካከል ያለው አለመጣጣም በመጪዎቹ ጊዜያት እርስ በርስ መመጣጠንና መስማማት ከሚያስፈልጋቸው ችግሮች አንዳንዶቹ እነዚህ ናቸው። ከቅርብ ወራት ወዲህ የተፈጠረው የአደጋ ሥጋት በጉዞ ኢንዱስትሪ ላይ ከፍተኛ ኪሣራ አስከትሏል። ይህም ውሎ አድሮ መፍትሔ ማግኘት ይኖርበታል። እነዚህ አሳሳቢ ሁኔታዎች በዘመናዊው የቱሪዝም እድገት ላይ ምን ዓይነት ጫና እንደሚያሳድር ወደፊት የሚታይ ነገር ነው።
ወደፊት ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገህ ትተህ ከመኖሪያ አካባቢህ ራቅ ብሎ ወደሚገኝ የመዝናኛ ቦታ ሄደህ እፎይ ለማለት ስትወስን ይህን ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ የቱሪስት ኢንዱስትሪ አቅልለህ አትመለከት ይሆናል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]