ከአስማት ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች መጠቀም ምን ጉዳት አለው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ከአስማት ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች መጠቀም ምን ጉዳት አለው?
በአሥራዎቹ ዕድሜ ለሚገኙ ልጆች የአስማት ድርጊቶች በእርግጥ ይስቧቸዋል? አንድ የተመራማሪዎች ቡድን በ115 መለስተኛና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ ተማሪዎች ላይ ጥናት በማካሄድ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሞክረዋል። ጥናቱ የሚከተለውን ግንዛቤ የሚያሰፋ አኃዛዊ መረጃ ይፋ አድርጓል:- ጥናቱ ከተካሄደባቸው መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት (54 በመቶ) አስማታዊና ተአምራዊ ድርጊቶች ቀልባቸውን እንደሚስቡት፣ አንድ አራተኛ (26 በመቶ) የሚሆኑት ደግሞ “በከፍተኛ ትኩረት እንደሚከታተሉ” ተናግረዋል።
በአንኮሬጅ የሚገኘው የአላስካ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች “ጋዜጦችና መጽሔቶች የሰይጣናዊ አምልኮ መስፋፋትን አስመልክተው የሚያወጡት ዜና . . . ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ አሸን ፈልቷል” ሲሉ ጽፈዋል። ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ በወጣቶች ዘንድ የሰይጣን አምልኮ በእጅጉ ተስፋፍቶ ይገኛል የሚለውን አባባል የሚደግፍ ያን ያህል ተጨባጭ ማስረጃ የለም። ይሁን እንጂ ወጣቶች አልፎ አልፎ ቢሆንም እንኳ ከሰይጣን አምልኮና ከአስማት ድርጊት ጋር ግንኙነት ላላቸው ነገሮች ፍላጎት ማሳየታቸው አልቀረም።
ከዚህም የተነሳ አንዳንድ ወጣቶች ‘ከአስማት ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች መጠቀም ምን ጉዳት አለው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። የዚህን መልስ ለማግኘት ወጣቶች ወደ አስማት ድርጊቶች የሚሳቡባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።
የአስማት ድርጊት ያለው መስህብ
ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “በዛሬው ጊዜ ልጆችና በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ግራ ለሚያጋቡና አብዛኛውን ጊዜ አእምሮ ለሚረብሹ በርካታ ምስሎችና መረጃዎች የተጋለጡ ከመሆኑም በላይ እነዚህን ነገሮች በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ምስሎችና መረጃዎች ከ20 ዓመት በፊት እንኳ ፈጽሞ የማይታሰቡ ነበሩ” ይላል። ብዙ ወጣቶች ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሳ አስማታዊ ድርጊቶች በጉልህ የሚንጸባረቁባቸውን መጻሕፍትና መጽሔቶች ያነብባሉ፣ ቪዲዮዎች ይመለከታሉ ወይም በኢንተርኔት ዌብ ሳይቶችን ይቃኛሉ።
ቢ ቢ ሲ በኢንተርኔት ያሰራጨው ዜና እንዳለው ከሆነ ጥንቆላና ጣረሞት የሚያሳዩ ተወዳጅ የሆኑ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች “ልጆች በጥንቆላ ድርጊቶች እንዲማረኩ ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል።” በተመሳሳይ አንዳንድ ሄቪ ሜታል ሙዚቃዎች የዓመፅ ወይም አጋንንታዊ መልእክት ያስተላልፋሉ። በቶሮንቶ የሚታተመው ዘ ሰንዴይ ስታር የተባለው ጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ የሆኑት ቶም ሃርፐር የሚከተለውን ጽፈዋል:- “[በሙዚቃው ዓለም] እየታየ ስላለው ነገር በተቻለ መጠን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ መስጠት እፈልጋለሁ። . . . እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም። ዘፈኖቹ በእብደት፣ በርኩስ መንፈስ ተጽእኖ፣ በአጋንንት፣ በደም መፋሰስ፣ በእርግማን እንዲሁም የግዳጅ ወሲብን፣ የገዛ ራስን ሰውነት መተልተልን፣ ግድያንና የራስን ሕይወት ማጥፋትን ጨምሮ በተለያየ ዓይነት የጭካኔ ድርጊቶች ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥኑ ናቸው። መልእክታቸው ሞትና እልቂት፣ የጥፋት ትንቢቶች፣
ጥሩ ነገሮችን ባጠቃላይ መጥላትን እንዲሁም አሰቃቂና መጥፎ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ መውደድን የሚያጎሉ ናቸው።”እንዲህ ዓይነት ሙዚቃ ማዳመጥ ጎጂ ባሕርይ ሊያስከትል ይችላል? ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳይ ቢያንስ አንድ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንድ የ14 ዓመት ልጅ እናቱን በስለት ከገደለ በኋላ የራሱን ሕይወት አጥፍቷል። የመኝታ ክፍሉ ግድግዳ በሄቪ ሜታል የሮክ ዘፋኞች ፎቶግራፍ የተሞላ ነበር። ሁኔታው ከተፈጸመ በኋላ አባትየው “ወላጆች ልጆቻቸው ምን ዓይነት ሙዚቃ እንደሚያዳምጡ በንቃት እንዲከታተሉ አሳስቧቸው” ሲል ተማጽኗል። ልጁ እናቱን ከመግደሉ ከአንድ ሳምንት በፊት “ስለ ደም መፋሰስና እናትን ስለመግደል” የሚናገር የሮክ ሙዚቃ ደጋግሞ ይዘፍን እንደነበር አባትየው ተናግሯል።
ከዚህም በላይ በአፈ ታሪክ የሚታወቁ ገጸ ባሕርያትን ለብሰው የሚተውኑበት ጨዋታ አለ። ከእነዚህ ጨዋታዎች አንዳንዶቹ ተሳታፊዎቹ የጠንቋዮችንና የሌሎች አስማተኞችን ገጸ ባሕርያት ወክለው እንዲጫወቱ የሚያደርጉ ናቸው። ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል አብዛኞቹ አጋንንታዊ የሆኑ የኃይል ድርጊቶች ይንጸባረቁባቸዋል። *
ይሁን እንጂ ሚዲያስኮፕ የተባለው የምርምር ተቋም የሚከተለውን ሪፖርት አውጥቷል:- “ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሄቪ ሜታል ሙዚቃ አፍቃሪ መሆን ራስን የማግለል፣ ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች የመውሰድ፣ ሥነ አእምሯዊ ችግሮች፣ የራስን ሕይወት የማጥፋት አደጋ . . . ወይም በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሕይወት አስጊ የሆኑ ነገሮችን የማድረግ ባሕርይ ጉልህ ጠቋሚ ቢሆንም ሙዚቃ የእነዚህ ባሕርያት መንስኤ አይደለም። አስቀድሞም ከእነዚህ ችግሮች ጋር እየታገሉ ያሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ግጥሙ የሚሰማቸውን ጭንቀት የሚገልጽ በመሆኑ የሄቪ ሜታል ሙዚቃ እንደሚማርካቸው ይገመታል።”
ሰይጣናዊ ሙዚቃ ማዳመጥ አደጋ እንዳለው ሁሉም ተመራማሪዎች በአንድ ድምፅ አይስማሙ ይሆናል። ሆኖም የኃይል ድርጊትን አሊያም የራስን ሕይወት ማጥፋትን የሚያበረታቱ ቪዲዮዎችን፣ ሙዚቃዎችን ወይም ጨዋታዎችን መከታተል ምንም ዓይነት ጉዳት የለውም ሊባል ይችላል? ለክርስቲያኖች ደግሞ ከአስማት ድርጊቶች ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች መጠቀማቸው ይበልጥ አስከፊ የሆነ አደጋ ይጋርጥባቸዋል።
አምላክ ለአስማታዊ ድርጊት ያለው አመለካከት
አንደኛ ቆሮንቶስ 10:20 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም” ሲል አስጠንቅቋቸዋል። ለመሆኑ አጋንንት እነማን ናቸው? ከእነሱ ጋር ግንኙነት መፍጠር ያን ያህል አደገኛ የሆነውስ ለምንድን ነው? በቀላል አነጋገር አጋንንት ሰይጣን ዲያብሎስን መከተል የመረጡ መላእክት የነበሩ ፍጡራን ናቸው። ሰይጣን “ተቃዋሚ” ማለት ሲሆን ዲያብሎስ ደግሞ “ስም አጥፊ” ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው በፊት የአምላክ ልጅ የነበረው ይህ መልአክ በአምላክ ላይ ለማመፅ በመምረጡ ራሱን ተቃዋሚና ስም አጥፊ አደረገ። ከጊዜ በኋላ ሌሎች መላእክትም በዓመፅ አካሄዱ እንዲተባበሩት ለማድረግ አሳታቸው። በመሆኑም እነዚህ ተባባሪዎቹ አጋንንት ሆኑ።—ዘፍጥረት 3:1-15፤ 6:1-4፤ ይሁዳ 6
ኢየሱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ሲል ጠርቶታል። (ዮሐንስ 12:31) ሰይጣንና አጋንንቱ ጥፋታቸው እየቀረበ በመምጣቱ ‘ታላቅ ቁጣ’ አድሮባቸዋል። (ራእይ 12:9-12) ከአጋንንት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች አጋንንት ጨካኝ መሆናቸውን መገንዘባቸው ምንም አያስደንቅም። በመናፍስት ሥራ በተጠመደ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች በሱሪናም የምትኖር አንዲት ሴት አጋንንት “አልታዘዝ ያሏቸውን ሰለባዎቻቸውን ማሰቃየት እንደሚያስደስታቸው” በገዛ ዓይኗ መመልከት ችላለች። * በመሆኑም ከእነዚህ ጨካኝ መንፈሳዊ ፍጡራን ጋር ማንኛውንም ዓይነት ግንኙነት መፍጠር በጣም አደገኛ ነው!
በዚህም ምክንያት አምላክ የጥንት ሕዝቦቹ የነበሩት እስራኤላውያን ማንኛውንም አስማታዊ ድርጊት እንዲያስወግዱ አዟቸው ነበር። ዘዳግም 18:10-12 “ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው” ሲል ያስጠነቅቃል። ‘አስማተኛዎች’ በአምላክ እጅ እንደሚጠፉ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ራእይ 21:8) ሌላው ቀርቶ ከአስማት ድርጊቶች ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች መጠቀም በአምላክ ዘንድ የተወገዘ ተግባር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ርኩስንም አትንኩ” ሲል ያዝዛል።—2 ቆሮንቶስ 6:17
ከአስማት ድርጊቶች መላቀቅ
ከአስማት ድርጊቶች ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች ተጠቅመህ ታውቃለህ? ከሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ከተማ የተፈጸመውን ነገር ተመልከት። በዚያ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች “አስማተኞች” ነበሩ። ሆኖም አንዳንዶች ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ባከናወናቸው አስደናቂ ሥራዎች በጥልቅ ተነኩ። ውጤቱስ ምን ሆነ? “ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ። እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር።”—ሥራ 19:11-20
ይህ ምን ያስገነዝበናል? አንድ ሰው ከአጋንንት ተጽዕኖ መላቀቅ ከፈለገ ከሰይጣናዊ አምልኮ ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውንም ነገር ማስወገድ ይኖርበታል! ይህም ማንኛውንም ዓይነት መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ ሥዕሎች፣ የቀልድ መጻሕፍት፣ ቪዲዮዎች፣ ክታቦች (“ጥበቃ” ለማግኘት የሚደረጉ ነገሮች) እና ከኢንተርኔት የተወሰዱ አጋንንታዊ ጽሑፎችን ያጠቃልላል። (ዘዳግም 7:25, 26) እንደ አውደ ነገሥት ያሉ ከጥንቆላ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ አስወግድ። በተጨማሪም ሰይጣናዊ መልእክት የሚያስተላልፉ ሙዚቃዎችንና ቪዲዮዎችን አስወግድ።
እንዲህ ዓይነት ቆራጥ እርምጃ ለመውሰድ ድፍረትና ቁርጥ ውሳኔ ይጠይቃል። ሆኖም ከፍተኛ ጥቅሞች ያስገኛል። ጂን * የምትባል አንዲት ክርስቲያን ሴት መጀመሪያ ላይ ጉዳት የሌለው የሚመስል አንድ የኮምፒውተር ጨዋታ ገዛች። በኋላ ግን ጨዋታውን አንድ በአንድ መጫወት ስትጀምር መናፍስታዊ ይዘት እንዳለው ተረዳች። ብዙም ሳይቆይ አስፈሪ ቅዥት ማየት ጀመረች። “በውድቅት ሌሊት ከእንቅልፌ ተነስቼ ጨዋታው ያለበትን ሲዲ ሰባበርኩት” ትላለች ጂን። ውጤቱስ? “ከዚያ በኋላ እረፍት አገኘሁ።”
ከአጋንንት ተጽዕኖ ለመላቀቅ ቆርጠህ ከተነሳህ ይሳካልሃል። ዲያብሎስ እንዲሰግድለት ኢየሱስን ለማባበል በሞከረ ጊዜ ኢየሱስ የወሰደውን ቆራጥ አቋም አስታውስ። “ኢየሱስ:- ሂድ፣ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው። ያን ጊዜ ዲያብሎስ ተወው።”—ማቴዎስ 4:8-11
ብቻህን አትጋፈጥ
ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች ‘በሰማያዊ ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ተጋድሎ’ እንዳለባቸው አሳስቦናል። (ኤፌሶን 6:12) ሆኖም ሰይጣንና አጋንንቱን ብቻህን ለመጋፈጥ አትሞክር። ፈሪሃ አምላክ ካላቸው ወላጆችህና ባለህበት ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካሉት ሽማግሌዎች እርዳታ አግኝ። ከአስማታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ባላቸው ነገሮች ትጠቀም እንደነበር መናገር ሊያሳፍርህ ቢችልም እንዲህ ማድረግህ በጣም ጠቃሚ እርዳታ ሊያስገኝልህ ይችላል።—ያዕቆብ 5:14, 15
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” እንደሚል አስታውስ። (ያዕቆብ 4:7, 8) አዎን፣ ይሖዋ አምላክ ይደግፍሃል! ከአስማታዊ ድርጊቶች ወጥመድ እንድትላቀቅ ይረዳሃል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.10 በነሐሴ 22, 1999 የንቁ! (እንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . በአፈ ታሪክ የሚታወቁ ገጸ ባሕርያትን አስመስሎ መጫወት አደጋ አለው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.15 የይሖዋ ምሥክሮች በሚያሳትሙት የዚህ መጽሔት ተጓዳኝ በሆነው የመስከረም 1, 1987 መጠበቂያ ግንብ (የእንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “ከመናፍስትነት ቀንበር መላቀቅ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.20 ስሟ ተቀይሯል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሰይጣናዊ አምልኮ ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ አስወግድ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መናፍስታዊ ሥራዎችን ከሚያስፋፉ ዌብ ሳይቶች ራቅ