በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አውዳሚ ወራሪዎች

ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን “ባዕዳን ወራሪዎች በሽታዎችን ከማሠራጨትና በሥነ ምህዳራችን ላይ መጠነ ሰፊ ውድመት ከማድረስ አልፈው በዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ላይ በመቶ ቢልዮን ዶላር የሚገመት ኪሣራ በማስከተል ላይ ናቸው” ይላል። በትውልድ አገራቸው ይህ ነው የሚባል ጥፋት የማያስከትሉ የነበሩ በርካታ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወደ አዳዲስ አካባቢዎች በመወሰድ ላይ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የአውስትራሊያና የኢንዶኔዥያ ተወላጅ የሆነ አንድ ትሪ ስኔክ የሚባል የእባብ ዝርያ በጉዋም የሚኖሩ የደን ወፎችን አሟጥጦ ከጨረሰ በኋላ ጎማዎች ታጥፈው በሚገቡበት ጎድጓዳ የአውሮፕላን አካል ክፍል ውስጥ በመደበቅና በሌሎች መንገዶች የፓስፊክ ውቅያኖስን እየተሻገረ ነው። ካውለርፓ የተባለው የባሕር ተክልና የደቡብ አሜሪካው ወተር ሃያሲንት ከዚህ በፊት ወደማይታወቁባቸው ሥነ ምህዳሮች ተወስደው በጣም ሰፋፊ በሆኑ አካባቢዎች በሚኖሩ የውቅያኖስና የባሕር እንስሳትና እፅዋት ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል። ለጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎች ንጣፍ እንዲሆን ታስቦ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ቻይና የተወሰደ የሣር ዝርያ ለመቆጣጠር በማይቻል ፍጥነት በመዛመት ላይ ሲሆን ከመርከብ ጭነት ማሸጊያ እንጨት ጋር የገባ ሎንግሆርን ቢትልስ የተባለ የጥንዚዛ ዝርያ ደግሞ በሰሜን አሜሪካ ደኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል ላይ ነው። አውዳሚ ሆነው ከተገኙ የእንስሳትና እፅዋት ዝርያዎች መካከል ኢንድያን ሞንጉዝ፣ ዜብራ መሰል፣ ሚኮንያ ትሪ፣ ናይል ፐርች፣ የሰሜን አሜሪካ ግራጫ ስኩውረል፣ ዎኪንግ ካትፊሽ፣ ሮዚ ውልፍ ስኔይልና ክሬዚ አንትስ ይገኛሉ።

መኳኳያ ለልጆች

በጃፓን የመዋቢያ ቅባት ሠሪዎች በተለይ ለትናንሽ ልጆች የተዘጋጁ መኳኳያዎች አዘጋጅተው መሸጥ መጀመራቸውን ዘ ጃፓን ታይምስ ዘግቧል። ገና በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ ያልደረሱትን ጨምሮ ለጋ ወጣት ልጃገረዶች አገሪቷን በሙሉ ካጥለቀለቀው የመኳኳያ ሽሚያ እኩል ለመራመድ በማሰብ አብረቅራቂ ሊፕስቲኮችንና ባለቀለም የፊት ቅባቶችን ለመግዛት ወደ ገበያ አዳራሾች በመጉረፍ ላይ ናቸው። እንደ ጣዖት የሚያመልኳቸውን ዘፋኞችም ለመምሰል ይጣጣራሉ። ከዚህ በፊት ልጆች ሊፕስቲክ የሚቀቡት ለጨዋታ ያህል ብቻ ነበር። አሁን ግን ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ በርካታ ልጆች እንደ ሊፕስቲክ ያሉትን መዋቢያዎች ሆን ብለውና አስበውባቸው ከመቀባታቸውም በላይ እንዴት በመኳኳያዎች አማካኝነት የፊታቸውን መልክ ሊለውጡ ወይም ሊያሻሽሉ እንደሚችሉ ለማወቅ ይፈልጋሉ። የአንድ የልጆች መጽሔት አዘጋጅ “የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ልጆች ዕድሜ ዝቅ ብሏል። የዛሬዎቹ ልጆች ስለ ድክመቶቻቸው መገንዘብ የሚጀምሩት ከቀድሞዎቹ ልጆች ባነሰ ዕድሜ ላይ ነው” ብሏል። ይሁን እንጂ አንድ የንግድ ድርጅት በዚህ ሳይሸነፍ በአቋሙ በመጽናት እንዲህ ብሏል:- “የአንደኛና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመኳኳያና የመዋቢያ ቅባቶች መፈለጋቸው ለጃፓን ባሕል ፈጽሞ እንግዳ ነው። ለማኅበረሰቡ ሥነ ምግባራዊ ደህንነት ስንል የመዋቢያ ቅባቶችን አንሠራላቸውም።”

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የመንፈስ ጭንቀትን ሊቀንስ ይችላል

“ለመንፈስ ጭንቀት መድኃኒት ከመውሰድ ይልቅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለአንዳንድ ሕመምተኞች የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል” ዘ ሃርቫርድ ሜንታል ሄልዝ ሌተር በዩናይትድ ስቴትስ ዱክ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል የተደረገን አንድ ምርምር ጠቅሶ ተናግሯል። በሦስት ቡድን ለተከፈሉ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ለተያዙ 50 ሰዎች ለአራት ወር የሚቆይ የተለያየ ሕክምና ተሰጣቸው። በመጀመሪያው ቡድን ውስጥ ለሚገኙት ጭንቀት የሚያስታግስ መድኃኒት ተሰጣቸው። በሁለተኛው ቡድን ውስጥ የሚገኙት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ብቻ እንዲሠሩ ተደረገ። በሦስተኛው ቡድን ውስጥ የሚገኙት ደግሞ ሁለቱንም የሕክምና ዘዴ እንዲጠቀሙ ተደረገ። ከአራት ወር በኋላ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት በሦስቱም ቡድን ውስጥ የሚገኙ ሕመምተኞች “የነበረባቸው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ለቅቋቸዋል” በማለት ሄልዝ ሌተር ተናግሯል። ይሁን እንጂ ለስድስት ወራት በተደረገው ክትትል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሠሩ የተደረጉት ሕመምተኞች “በስሜትም ሆነ በአካል በተሻለ ሁኔታ ላይ የተገኙ ሲሆን በበሽታው እንደገና የመጠቃት ዕድላቸው ስምንት በመቶ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል።” ከዚህ ጋር ሲነፃፀር መድኃኒት እንዲወስዱ የተደረጉትና መድኃኒት እየወሰዱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሠሩ የተደረጉት ሕመምተኞች በበሽታው እንደገና የመጠቃት ዕድላቸው 38 እና 31 በመቶ ሆኖ ተገኝቷል።

ለልጅ ማንበብ የሚያስገኘው ወሮታ

“[ልጆች] እናታቸውና አባታቸው በፈቃደኝነት ተነሳስተው ሲያነብቡላቸው እነርሱን ለመምሰል ይሞክራሉ” በማለት ፕቺአቹካ የተባለው የፖላንድ ሳምንታዊ ጋዜጣ ተናግሯል። ቴሌቪዥን የሚመለከቱ ልጆች እየተበራከቱ በመጡበት በአሁኑ ዘመን ይላል ጽሑፉ፣ ለሁለት ዓመት ሕፃናት እንኳ ሳይቀር ሥዕሎችን እያሳዩና እያብራሩ ማንበብ ጠቃሚ ነው። ልጁ ወይም ልጅቷ የገባቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ወላጆች ያነበቡትን ወዲያው ሊጠይቋቸው ይችላሉ። “ልጁ የመሰልቸት ስሜት ካሳየ . . . ሕያው የሆነ የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግና ድምፅን በመለዋወጥ ንባቡን ማራኪ ለማድረግ ጥረት አድርጉ።” ወላጆች የልጃቸውን ፍላጎት እንዲያውቁና ስለዚህም ጉዳይ እንዲያነጋግሩት ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። “ልጅ በነበራችሁበት ጊዜ ትወዱት ስለነበረው መጽሐፍ ንገሯቸው፣ ጉጉት የሚፈጥሩ ርዕሶችን ጥቀሱላቸው። . . . ልጆች ማንበብ በሚችሉበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ለልጆቻችሁ ማንበባችሁን አታቁሙ” በማለት ፕቺአቹካ ይናገራል። “አንዳንድ ጊዜ የልጁን ፍላጎት ለመቀስቀስ ከመጀመሪያዎቹ ገጾች ጥቂቶቹን ማንበብ ብቻ ይበቃል። ከዚያ ልጁ ራሱ ደስ ብሎት ማንበቡን ይቀጥላል።”

የተጎዱ የማጣጣሚያ ቀንበጦች

የጆሮ፣ አፍንጫና ጉሮሮ ስፔሻሊስት የሆኑት ሂሮሺ ቶሚታ በሰጡት ግምት መሠረት በጃፓን ከምንጊዜውም የበለጠ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችን ጨምሮ በየዓመቱ ከ140, 000 የሚበልጡ ሰዎች የመቅመስ ችሎታቸውን ያጣሉ። መድኃኒቶችና የጤና እክሎች ችግሩን ሊፈጥሩ ቢችሉም እንኳ ይላል ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ ያወጣው ዘገባ፣ 30 በመቶ የሚሆነው ችግር በጣም አስፈላጊ ከሆነ ማዕድን ማለትም ከዚንክ እጥረት ጋር የተያያዘ ነው። ጽሑፉ ሲቀጥል “አዳዲስ የማጣጣሚያ ቀንበጦች ሕዋሳትን በማስገኘት ረገድ ዚንክ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን [የዚንክ] እጥረት የመቅመስ ችሎታ ቀስ በቀስ እንዲጠፋ ያደርጋል።” ጣፋጭና በፋብሪካ የሚዘጋጁ ምግ​ቦችን እየተመገቡ የተለያዩ ዓይነት ምግቦች አለመመገብ ለችግሩ መከሰት ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። “ተዘጋጅተው በሚሸጡ ምግቦች ውስጥ የሚጨመሩ እንደ ፎስፌት ያሉ ቅመሞች በሰውነት ውስጥ ያለውን የዚንክ መጠን የሚያመነምኑ ከመሆኑም በላይ ከሰውነት ጋር እንዳይዋሃድ እንቅፋት ይፈጥራሉ።” የምግብን ጣዕም መለ​የት የሚቸግራቸው ሰዎች በዚንክ የዳበሩ ምግቦችን እንዲመገቡ ቶሚታ ይመክራሉ። ከእነዚህ ውስጥም ኦይስተር፣ ትናንሽ ዓሦችና ጉበት ይገኙበታል። የተለያዩ ዓይነትና ጤናማ የሆኑ ምግቦች መመገብ የማጣጣሚያ ቀንበጦች እንዲያንሰራሩ ሊያደርግ ቢችልም ከበድ ያሉ ሁኔታዎች ሕክምና ሳይደረግላቸው ከስድስት ለሚበልጡ ወራት ከቆዩ እነዚህን ዘአካላት ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ ያለው አጋጣሚ እጅግ የመነመነ ይሆናል በማለት ቶሚታ ተናግረዋል።

በወተት ምርት ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘችው አገር

በአሁኑ ጊዜ ሕንድ በዓለም ግንባር ቀደሟ ወተት አምራች አገር ለመሆን በቅታለች በማለት ዘ ሂንዱስታን ታይምስ ዘግቧል። “በአካባቢ ጥናት ላይ ያተኮረው [በዋሽንግተን ዲ ሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው] ዎርልድዎች ኢንስትቲዩት የሕንድን የወተት አብዮት አወድሷል” በማለት ዘገባው ይገልጻል። “ከ1994 ጀምሮ ወተት የሕንድ ዋነኛ የግብርና ምርት ውጤት ሆኖ የቆየ ሲሆን በ1997 ደግሞ አገሪቱ ዩናይትድ ስቴትስን በመቅደም በዓለም ግንባር ቀደሟ ወተት አምራች አገር ለመሆን በቅታለች።” የዎርልድዎች ኢንስትቲዩት ሊቀ መንበር የሆኑት ሌስተር ብራውን እንዲህ ብለው መናገራቸው ተጠቅሷል:- “ሕንድ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለችው ከብቶችን እህል ከመመገብ ይልቅ የግብርና ተረፈ ምርቶችንና እንደ አገዳና ገለባ ያሉ ነገሮችን በመመገብ ነው። ሕንድ ሰዎች የሚመገቡትን እህል ለከብቶች ማቅረብ ሳያስፈልጋት የከብቶቹን መኖ የፕሮቲን ይዘት ማሳደግ ችላለች።”

“ሕፃናትን መወዝወዝ የሚያስከትለው የጤና ቀውስ

አንድን ሕፃን እጁን፣ እግሩን ወይም ትከሻውን ይዞ መወዝወዝ ከፍተኛ የጤና ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ኤል ዩኒቨርሳል የተባለው የሜክሲኮ ሲቲ ጋዜጣ ዘግቧል። “ትምህርት የመቅሰም ችግር ያለባቸው አንዳንድ ግለሰቦች ይህ ችግር የገ​ጠማቸው በሕፃንነታቸው በመወዝወዛቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ ዶክተሮች ያምናሉ።” የሕፃናት ሐኪም የሆኑት ኹዋን ሆሴ ራሞስ ሱዋሬዝ እንደሚሉት “በዚህ ምክንያት የሚደርሰው ጉዳት ከውጭ የሚታይ ምንም ዓይነት የጉዳት ምልክት ባያሳይም በአንጎል ውስጥ ደም እንዲፈስ ወይም በአንጎል ላይ ጉዳት እንዲደርስ ሊያደርግ ይችላል።” በማከልም የመስማት ችሎታ ማጣት፣ ዐይነ ስውርነት፣ የአከርካሪ አጥንት መጎዳት፣ ሽባነት፣ ማንቀጥቀጥና ከዚያም በላይ ሞት ሊያስከትል ይችላል ብለዋል። ይህን የሚያክል ጉዳት ሊደርስ የሚችልበት ምክንያት የአንድ ሕፃን የራስ ቅል ከሌላው የሰውነቱ ክፍል ጋር ሲወዳደር ከባድ ሲሆን አንገቱን ደግፈው የሚይዙት ጡንቻዎች ግን ገና ያልጠኑ በመሆናቸው በመወዝወዙ ምክንያት የሚደርስበትን ጫና መቋቋም ያቅተዋል። እርግጥ ነው፣ ሕፃን ልጅ ሲያለቅስ በጣም ሊያበሳጭ ይችላል። ቢሆንም ይህ ጋዜጣ ለሕፃናት አሳዳጊዎች “ሦስት ቀላል እርምጃዎችን በመፍትሔነት ያስቀምጣል:- (1) ቆም በል፣ (2) ተቀመጥ እንዲሁም (3) ዘና በል። በሕፃኑ ላይ በቁጣ ከመጮህ ይልቅ ስሜትህን ተቆጣጠር።” ከዚህ በኋላ ልጁን በመመገብ ወይም የሽንት ጨርቁን በመቀየር አለዚያም የሚያስደስተው ወይም የሚያጫውተው አንድ ነገር በማድረግ ለማባበል ሞክር።

የባሕር ላይ ዝርፊያ ተስፋፍቷል

ቫለር አክትዌል የተባለው የፈረንሳይ መጽሔት “የባሕር ላይ ዝርፊያ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ተስፋፍቷል” ሲል ዘግቧል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የባሕር ላይ ዝርፊያ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። በተለይ ደግሞ ሁኔታው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ቀውስ ምክንያት ወደ ወንጀለኛነት እንዲያመሩ በተገደዱባቸው በደቡብ ምሥራቅ እስያ አካባቢዎች በጣም ተባብሷል። ይሁን እንጂ የባሕር ላይ ዝርፊያ በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ የባሕር ጠረፎችም ጭምር ተስፋፍቷል። የፈረንሳይ የመርከብ ባለቤቶች ማዕከላዊ ኮሚቴ ተወካይ የሆኑት ኤድዋር በርሌ እንዳሉት “በ1998 የባሕር ላይ ዝርፊያ ያደረሰው ኪሣራ 16 ቢልዮን ዶላር ነበር። አንዳንድ መርከቦች ከነጭነታቸው ይጠፋሉ። መርከቦቹ ከተጠለፉና ጠፍተው ከቆዩ በኋላ ለዘራፊዎቹ አመቺ በሆኑ ወደቦች አመቺ ባንዲራ ተደርጎላቸው ይገኛሉ።” ዘራፊዎቹ ከፍተኛ ፍጥነት ባላቸው ጀልባዎችና በተራቀቁ የመገናኛ መሣሪያዎች የሚገለገሉ ሲሆን ከባድ መሣሪያ የታጠቁና ጉዳት ለማድረስም ወደኋላ የማይሉ ናቸው።