በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኮልፖርተሮች—ተንቀሳቃሾቹ የመጻሕፍት መደብሮች

ኮልፖርተሮች—ተንቀሳቃሾቹ የመጻሕፍት መደብሮች

ኮልፖርተሮች—ተንቀሳቃሾቹ የመጻሕፍት መደብሮች

ፈረንሳይ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በደቡብ ምሥራቅ ፈረንሳይ ከደዛልፕ የበረዶ ላይ ጨዋታዎች መዝናኛ ስፍራ ከፍ ብሎ በሚገኘው በዣንድሪ ግላሲዬር ጉብታ ግርጌ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የተከፈተ አንድ ትንሽ “ቤተ መዘክር” አለ። በቤተ መዘክሩ ውስጥ ለእይታ ከቀረቡት የበረዶ ቅርጻ ቅርጾች መካከል ጥንታዊ የሆነውን የተራራማ አገር ንግድ የሚያስታውስ የኮልፖርተር ምስል ይገኛል።

ለበርካታ መቶ ዓመታት ኮልፖርተሮች ሸቀጦቻቸውን በአንገታቸው ላይ (በፈረንሳይኛ ኮል) አነግተው (በፈረንሳይኛ ፖርቴ) ከገበያ ወደ ገበያ እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት እያዞሩ ይለውጡ ነበር። ዛሬ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ስለ እነዚህ ነጋዴዎች ሰምተው አያውቁም። ከአሁን ቀደም ስለ እነርሱ የሰሙትም ቢሆኑ ጥቃቅን ዕቃዎችን የሚሸጡ ምስኪን ነጋዴዎች እንደሆኑ ያስቡ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኮልፖርተሮች እስከ ዛሬም ድረስ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የነካ ቅርስ ትተው አልፈዋል።

የኮልፖርተሮች ሥራ ሲቃኝ

አብዛኞቹ ኮልፖርተሮች በአውሮፓ ውስጥ ሰፊ የንግድ መረብ ዘርግተው አዳዲስ ሸቀጦችን የሚያከፋፍሉ በደንብ የተደራጁ ነጋዴዎች እንጂ ተሯሩጠው የሚያድሩ ምስኪኖች አልነበሩም። ይሁን እንጂ ቁሳዊ ትርፍ ለማግኘት ብለው ይሠሩ የነበሩት ሁሉም ኮልፖርተሮች አይደሉም። አንዳንዶቹ ይህንን ሥራ ይሠሩ የነበረው ጽኑ እምነቶቻቸውን ለማሰራጨት ሲሆን በዚህ ምክንያት ሕይወታቸውንም ያጡ አሉ።

የኮልፖርተሮች ሥራ የጀመረው በመካከለኛው ዘመን መገባደጃ አካባቢ ይመስላል። የመጀመሪያዎቹ ኮልፖርተሮች የግማሽ ጨረቃ ቅርጽ ባለው የአልፕስ ተራሮች አካባቢ፣ በፒሬኒስ እና በስኮትላንድ ደጋማ ቦታዎች የሚኖሩ የተራራማ አገር ሰዎች ነበሩ። አብዛኞቹ መከሩ ከተሰበሰበ በኋላ ተጓዥ ነጋዴ የሚሆኑ ገበሬዎች ናቸው።

ከነዚህ ተጓዥ ነጋዴዎች መካከል ዠአን ግራቪዬ የተባለ ፈረንሳዊ ይገኝበታል። በ16ኛው መቶ ዘመን ግራቪዬና ቤተሰቡ ላ ግራቭ ተብሎ በሚጠራ ተራራማ ቦታ ይኖሩ ነበር። ግራቪዬ ማሳው ፍሬያማ ስላልሆነ መሆን አለበት በሸለቆው ውስጥ ያሉት ከተሞች የሚፈልጓቸውን እንደ እንጨት፣ ቆዳ፣ ሱፍ እና ጨው ያሉ በተራራማው አገር የሚመረቱ ነገሮች ማዞር ጀመረ። እንደ ግራቪዬ ያሉ ኮልፖርተሮች እነዚህን ምርቶች ወደ ከተማ ያመጡና በወንዶች ልብሶች፣ ማበጠሪያዎች፣ መነጽሮች፣ መጽሐፎች፣ መድኃኒቶች፣ ትምባሆ እና ቅርጻ ቅርጾች ይለውጧቸዋል። እነዚህ ዕቃዎች ደግሞ በትናንሽ ከተሞች ለሚኖሩ ሰዎች ወይም ከሱቆች በጣም ርቀው ለሚኖሩ ገበሬዎች ይሸጣሉ። አንዳንድ ኮልፖርተሮች በቀን እስከ 20 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት ይጓዙ ነበር! እነሱ በማይኖሩበት ጊዜ ዘመዶቻቸው እርሻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ይንከባከቡላቸዋል።

ግራቪዬ ግን ትናንሽ ዕቃዎችን ብቻ በመሸጥ አልተወሰነም። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በንዋ ሪጎ ለተባለ አታሚ ዕዳ ነበረበት። እንደ ሌሎች ብዙ ኮልፖርተሮች ሁሉ ግራቪዬም በመጻሕፍት ንግድ ተሰማርቶ እንደነበር ከዚህ መረዳት ይቻላል። በወቅቱ አውሮፓ ኪነ ጥበብና ሳይንሳዊ ግኝቶች እንደገና ባቆጠቆጡበት የሽግግር ዘመን ላይ የነበረች ሲሆን የመጻሕፍት ንግድም ተስፋፍቶ ነበር። ከ1500 እስከ 1600 ባሉት ጊዜያት በአውሮፓ ውስጥ ከ140 እስከ 200 ሚልዮን የሚደርሱ መጻሕፍት ታትመዋል። ከነዚህ መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት የሚታተሙት በፈረንሳይ ነበር። በአልፕስ ተራሮች ግርጌ የምትገኘውና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ማዕከል የነበረችው ሊዮን፣ በአውሮፓ የሚካሄደው የኅትመት ሥራ ግምባር ቀደም ተዋናይና በፈረንሳይኛ የሚዘጋጁ መጻሕፍት ዋነኛ አሳታሚ ነበረች። ስለዚህ ግራቪዬ ለንግድ እንቅስቃሴው በቂ አቅርቦት ነበረው። እንደ ግራቪዬ ያሉ ሰዎች መጻሕፍት ይሸጡ የነበረው ትርፍ ለማግኘት ቢሆንም ለሃይማኖታዊ ዓላማ ሲሉ ብቻ መጻሕፍት የሚያሰራጩ ሌሎች ኮልፖርተሮችም ተነሱ።

የእምነት ኮንትሮባንድ’

የኅትመት መሣሪያዎች መፈልሰፍ ሰዎች ሃይማኖታዊ መጽሐፎችን፣ ብሮሹሮችንና ትራክቶችን በጉጉት እንዲያነቡ አነሳሳቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ በላቲን በኋላም በተራው ሕዝብ ቋንቋ ታተመ። በጀርመን በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅጂዎች የታተሙ ሲሆን ኮልፖርተሮችም በገጠር አካባቢ ለሚኖረው ሕዝብ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በፍጥነት በማሰራጨት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል። ሆኖም ይህን ስርጭት የደገፈው ሁሉም ሰው አልነበረም።

በ1525 የፈረንሳዩ ፓርላማ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ፈረንሳይኛ እንዳይተረጎም ከለከለ። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ በፈረንሳይኛ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ መያዝም ተከለከለ። ያም ሆኖ ግን በሺዎች የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶች መታተማቸውን ቀጥለው ነበር። እንዲሁም ቆራጥ ለነበሩት ኮልፖርተሮች ምስጋና ይድረሳቸውና ብዙዎቹ ቅጂዎች በመላው ፈረንሳይ በድብቅ ይሰራጩ ነበር። ከነዚህ ደፋር ኮልፖርተሮች አንዱ ፒዬር ሻፖ የተባለ ወጣት ነበር። በ1546 ታሰረና ተገደለ።

በመጨረሻ በ1551 ካቶሊካዊቷ ፈረንሳይ ኮልፖርተሮች መጻሕፍት እንዳይሸጡ በማገድ ጠንከር ያለ እርምጃ ወሰደች። ምክንያቱም ኮልፖርተሮቹ “ከጄኔቫ” ማለትም ከፕሮቴስታንቶች የሚመጡ መጻሕፍትን “በድብቅ” ያሰራጩ ነበር። ሆኖም ይህ ጎርፉን አላስቆመውም። መጽሐፍ ቅዱሶች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወደ ፈረንሳይ ይጎርፉ ነበር። ባብዛኛው ትናንሽ መጠን ያላቸው ስለነበሩ ከታች በኩል ለመደበቅ እንዲያመቹ ሆነው በተሠሩ የወይን በርሜሎች፣ በለውዝ በርሜሎችና ከጀልባዎች ወለል ሥር ባለው ክፍት ቦታ ተደብቀው ይገቡ ነበር። ደኒ ለ ቬር የተባለ ደፋር ሰው በርሜል ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያጓጉዝ ተይዞ እሱም ተገደለ። አንድ በወቅቱ የነበረ ኮልፖርተሮችን የሚጠላ ካቶሊክ በነሱ ምክንያት “ፈረንሳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፈረንሳይኛ አዲስ ኪዳን እትሞች እንደተሞላች” ሳይሸሽግ ተናግሯል።

አንድ ጸሐፊ ‘እምነትን በኮንትሮባንድ የሚያስገቡ’ ያሏቸው የእነዚህ ሰዎች የ16ኛው መቶ ዘመን ሕይወት በስጋት የተሞላ ነበር። ብዙ ኮልፖርተሮች ይያዙ፣ ይታሰሩ ወይም የመርከብ ቀዛፊ ባሪያ ይደረጉ፣ ከአገር ይባረሩ አሊያም ይገደሉ ነበር። አንዳንድ ኮልፖርተሮች ከነመጽሐፎቻቸው ተቃጥለዋል። ታሪክ የሚጠቅሰው የጥቂቶቹን ስም ብቻ ቢሆንም አብዛኛው የፕሮቴስታንት ቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እንዲያገኝ ያስቻሉት ሁሉም ደፋር ግለሰቦች ሊመሰገኑ ይገባል።

ተንቀሳቃሽ መጻሕፍት ቤቶች

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በ17ኛው መቶ ዘመንም ተራው ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንዳያገኝ መከላከሏን ቀጥላ ነበር። አማኞች በመጽሐፍ ቅዱስ ፋንታ የጸሎት መጻሕፍትና የቅዱሳንን ገድል የያዙ መጻሕፍት ይሰጧቸው ነበር። እነዚህ ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱስን ሊተኩ የሚችሉ መጻሕፍት አይደሉም! * በተቃራኒው ደግሞ ጃንሰኒስቶች ተብለው የሚጠሩት “መናፍቃዊ” አመለካከት ያላቸው ካቶሊኮች ቅዱሳን መጻሕፍት መነበብ እንዳለባቸው ያስተምሩ ነበር። በመሆኑም ኮልፖርተሮች ለ ሜስትር ደ ሳሲ የተረጎመውንና በቅርብ ተዘጋጅቶ የወጣውን የጃንሴኒስቶች የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች (“አዲስ ኪዳን”) ትርጉም ያሰራጩ ጀመር።

በዚሁ ጊዜ ኮልፖርተሮቹ በጀርባቸው በሚያዝሉት ቦርሳ መጠነኛ ዋጋ ያላቸውን ሌሎች ጽሑፎችም ማዞር ጀመሩ። እነዚህ መጻሕፍት በ19ኛው መቶ ዘመን እስከጠፉበት ጊዜ ድረስ በፈረንሳይ ያሉ ብዙ ሰዎችን እያስተማሩና እያዝናኑ ማንበብ እንዲችሉ ረድተዋቸዋል። በሽፋናቸው ቀለም ምክንያት ፈረንሳዮች ቢብሊዮቴክ ብለ ማለትም ሰማያዊው ቤተ መጻሕፍት ብለው ሲጠሯቸው በእንግሊዝ ቻፕቡክስ በስፔይን ደግሞ ፕሊዬጎስ ደ ኮርዴል ተብለው ይጠሩ ነበር። መጽሐፎቹ የመካከለኛው መቶ ዘመን የጦር መኳንንትን ታሪኮች፣ ትውፊቶች፣ የቅዱሳንን ገድሎችና የመሳሰሉትን የያዙ ነበሩ። አንድ ኮልፖርተር ከፒሬኒስ አካባቢ እንደሚመጡት በበጋ ወይም ከዶፊኔ ተራሮች እንደሚመጡት በክረምት ሊመጣ ይችላል። መቼም ይምጣ መቼ በጉጉት ይጠበቅ እንደነበረ መገመት አያዳግትም።

ኮልፖርተሮች የተማረውንም ሆነ ያልተማረውን ሰው ፍላጎት ያሟሉ የነበረ መሆኑ ያስገርማል። በደቡብ ምሥራቅ ፈረንሳይ በጊየን ክልል ይኖሩ ስለነበሩ ገበሬዎች በ18ኛው መቶ ዘመን የተካሄደ ጥናት እንዲህ ይላል:- “ረዣዥም በሆኑት የክረምት ምሽቶች [ገበሬዎቹ] የቅዱሳንን ገድሎች ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ምዕራፍ ለቤተሰባቸው አባላት ለግማሽ ሰዓት ያህል ያነቡላቸው ነበር። . . . ሌላ የሚነበብ ነገር በማይኖርበት ጊዜ ደግሞ ሰማያዊውን ቤተ መጻሕፍት እና ኮልፖርተሮች በየዓመቱ ወደ ገጠሩ ክፍል የሚያመጧቸውን ሌሎች እርባና የሌላቸው ጽሑፎች . . . ያነባሉ።” ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ተወዳጅ ስለነበር በተራ ገበሬ ቤት እንኳን ሳይቀር ይገኝ ነበር።

የተቀናጀ የንግድ መረብ

ኮልፖርተሮች በፈረንሳይና በኢጣሊያ የአልፕስ ተራሮች፣ በፒሪኒስ እንዲሁም በሰሜናዊ ምዕራብ ፈረንሳይ በሚገኘው በኖርማንዲ መረባቸውን ዘርግተው ነበር። ከዶፊኔ የአልፕስ ተራራ የሚመጡት ኮልፖርተሮች ብቻ ሩቡን የደቡብ አውሮፓ የመጻሕፍት ገበያ ተቆጣጥረውት ነበር። በዚያ ዘመን በጄኔቫ መጻሕፍት ይሸጥ የነበረ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል:- “በስፔይንና በፖርቹጋል እንዲሁም በብዙ የኢጣሊያ ከተሞች የነበረው የመጻሕፍት ንግድ . . . በዶፊኔ የአልፕስ ተራሮች ከሚገኙት ከነዚያው መንደሮች በመጡ ፈረንሳውያን እጅ ነበረ።”

ኮልፖርተሮች ከቤተሰቦቻቸው፣ ከመንደራቸውና ከሃይማኖታቸው አባላት ጋር የነበራቸው የቀረበ ትስስር “ብርቱና ታታሪ ሠራተኞች እንዲሁም በጣም አስተዋዮች” ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ ለስኬታቸው አስተዋጽኦ አድርጓል። አብዛኞቹ ፕሮቴስታንቶች ሲሆኑ በስደቱ ወቅት ወደ ግዞት ከተወሰዱት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አላቋረጡም ነበር። በዚህም ምክንያት አውሮፓን የሚያቆራርጠውን የተቀናጀ የንግድ መረብ የሚያንቀሳቅሱት ዘመዳሞች፣ የአንድ አገር ልጆች እና ተመሳሳይ ሃይማኖት የነበራቸው ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል የግራቪዬ ቤተሰቦች ፈረንሳይን፣ ስፔይንንና ኢጣሊያን የሚያጠቃልል የመጻሕፍት ሽያጭ መረብ ነበራቸው። ሌሎች መረቦች ደግሞ እስከ ፋርስና አሜሪካ ሳይቀር ተዘርግተው ነበር።

የኮልፖርተሮች ሥራ እንደገና አንሰራራ

በ19ኛው መቶ ዘመን የኢንዱስትሪው አብዮት ሲጀምር ከትውልድ ትውልድ ሲወራረስ የቆየው የኮልፖርተሮች የቤተሰብ ንግድ አከተመለት። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት መቋቋም የመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን እንደገና እንዲስፋፋ አድርጓል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግን አሁንም የመጽሐፍ ቅዱስን ስርጭት መቃወሟን አላቋረጠችም። እስከ 1800ዎቹ መገባደጃ ድረስ ኮልፖርተሮች ይንገላቱና እየተከሰሱ ፍርድ ቤት ይቀርቡ ነበር። ያም ሆኖ ግን ከ1804 እስከ 1909 ባለው ጊዜ ውስጥ በፈረንሳይ ውስጥ ብቻ በሙሉም ይሁን በከፊል ስድስት ሚልዮን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን አሰራጭተዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች የማስተማሩ ሥራ ግን በዚህ አላበቃም። በ1881 የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ (የታተመው በዩናይትድ ስቴትስ ነው) የተሰኘው መጽሔት ክርስቲያኖች የወንጌላዊነቱን ሥራ እንዲሠሩ ጥሪ አቀረበ። ዓላማቸው ምን ነበር? “ሰዎች እንዲያነቡ በማድረግ እውነትን ማሰራጨት” ነበር። በ1885 ወደ 300 የሚሆኑ ወንጌላውያን ለጥሪው ምላሽ ሰጥተው በመስኩ ላይ ተሰማሩ። አንዳንዶቹ እንደ ሆንዱራስ፣ በርማ (የአሁኗ ማያንማር)፣ ባርባዶስ፣ ኤል ሳልቫዶር፣ ጓቴማላ እና ፊንላንድ ወዳሉ ራቅ ያሉ ቦታዎች በስፋት ተሰማርተዋል። አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ እነዚህ ወንጌላውያን በስዊድን፣ በስዊዘርላንድ፣ በቻይና፣ በኒውዚላንድ፣ በኖርዌይ፣ በእንግሊዝ፣ በኮስታሪካ፣ በጀርመን፣ በፈረንሳይና በፖላንድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አሰራጭተው ነበር።

ቀደም ባሉት ዓመታት ከነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (አሁን የይሖዋ ምሥክሮች በመባል ይታወቃሉ) መካከል የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑት ኮልፖርተሮች ተብለው ይጠሩ እንደነበረ ማወቁ ትኩረት የሚስብ ነው። ሆኖም ቃሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮቹ የሚሠሩትን ሥራ ዋነኛ ዓላማ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ የማስተማሩን ተግባር በትክክል ስለማይገልጽ ይህን ቃል መጠቀም አቆሙ። (ማቴዎስ 28:19, 20) በተጨማሪም ቃሉ ለትርፍ ብለው የሚሠሩ አለመሆናቸውን የሚገልጽ አልነበረም። ስለዚህ ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አቅኚዎች ተብለው ይጠራሉ።

ባለፈው ዓመት ከ800, 000 በላይ አቅኚዎች መጽሐፍ ቅዱሶችንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ያለክፍያ አሰራጭተዋል። ይህንን የሚያደርጉት የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት አይደለም፤ ‘በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላኩ በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነው ይናገራሉ።’ (2 ቆሮንቶስ 2:17) ስለዚህ ዛሬ ያሉት አቅኚ አገልጋዮች ከተንቀሳቃሽ መጻሕፍት ቤቶቹ የላቀ ተግባር እያከናወኑ ነው። ያም ሆኖ ግን የቅንዓትና የድፍረት ምሳሌ የተዉላቸው እነዚያ የጥንቶቹ ኮልፖርተሮች ባለውለታዎቻቸው ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.16 የጸሎት መጽሐፍ በይፋ በሚታወቅ የተወሰነ ሰዓት ላይ ለማርያም ውዳሴ የሚቀርቡ ጸሎቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው።

[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኮልፖርተሮች አዳዲስ ዕቃዎችን ሰዎች ቤት ድረስ ያመጡ ነበር

ኮልፖርተሮች በጉጉት ይጠበቁ ነበር

[ምንጭ]

© Cliché Bibliothèque nationale de France, Paris

[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለ ሜስትር ደ ሳሲ ያዘጋጀው “አዲስ ኪዳን” እና ከሰማያዊው ቤተ መጻሕፍት የተወሰደ መጽሐፍ

[ምንጭ]

በስተግራ ጥግ:- © Cliché Bibliothèque nationale de France, Paris በስተግራ:- © B.M.V.R de Troyes/Bbl.390/Photo P. Jacquinot

[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንጌላውያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አሰራጭተዋል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዛሬ ያሉ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ያስተምራሉ