የብሪቲሽ ሙዚየም አዲስ ገጽታ
የብሪቲሽ ሙዚየም አዲስ ገጽታ
ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ለንደን የሚገኘው የብሪቲሽ ሙዚየም በየዓመቱ ወደ ስድስት ሚልዮን የሚደርሱ ጎብኚዎችን ያስተናግዳል። ከአንድ ዓመት በፊት ገደማ ሙዚየሙ እነዚህን ጎብኚዎች ለማስተናገድ የሚያስችል 40 በመቶ የሚሆን ተጨማሪ ቦታ አግኝቷል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
የብሪቲሽ ሙዚየም ቤተ መጻሕፍትም ሆነ የብሪቲሽ ሙዚየም ለሕዝብ ክፍት የሆኑት በ1759 ነው። ቤተ መጻሕፍቱንና ሙዚየሙን የያዘው አሁን ያለው ሕንፃ ተገንብቶ የተጠናቀቀው በ1852 ነበር። ይሁንና ብሪቲሽ ላይብረሪ በመባል የሚታወቀው ቤተ መጻሕፍት በ1997 በአቅራቢያው ወደሚገኝ አዲስ ቦታ የተዛወረ ሲሆን 12 ሚልዮን መጻሕፍት፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎችና ማህተሞች ወደዚያው ተወስደዋል። ይህ የቦታ ለውጥ የብሪቲሽ ሙዚየም ለ150 ዓመታት ያህል ለሕዝብ ዝግ የነበረውን በመካከለኛ ቦታ ላይ የሚገኘውን አዳራሽ በመክፈት አገልግሎቱን እንዲያሰፋ አስችሎታል!
ታላቁ አዳራሽ ተብሎ የሚጠራው አሁን የተለቀቀው ባለ ጉልላት የማንበቢያ ክፍሉ ትኩረት የሚስብ ነው። ይህ የማንበቢያ ክፍል ሥራ ከጀመረበት ከ1857 አንስቶ ከዓለም ዙሪያ ለሚመጡ ጥናት ለሚያካሂዱ ሰዎች አመቺ ቦታ ሆኖላቸዋል። ፀጥታ በሰፈነበት በዚህ ስመ ጥር ቤተ መጻሕፍት ከተጠቀሙት የታወቁ ሰዎች መካከል ሞሃንዳስ ጋንዲ፣ ቻርለስ ዳርዊንና ካርል ማርክስ ጥቂቶቹ ናቸው። ይህ ክፍል ለመላው ሕዝብ ክፍት የሆነው አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። በአሁኑ ጊዜ የሙዚየሙ ንብረት የሆኑ 25, 000 መጻሕፍት በውስጡ ይገኛሉ።
የዚህ ታሪካዊ የጉልላት ክፍል ዕደሳ ተደርጎለታል። የማንበቢያ ክፍሉን ጨምሮ ታላቁ አዳራሽ 800 ቶን በሚመዝን እጅግ ማራኪ በሆነ ኮርኒስ ተሸፍኗል። የኮርኒሱ አውታር ከአረብ ብረት የተሠራ ሲሆን ብዛታቸው 3, 312 በሚሆኑ ሦስት መዓዘን ቅርጽ ባላቸው መስተዋቶች ተገጥሟል። የእያንዳንዱ መስተዋት መጠን እኩል እንዲሆን በጥንቃቄ በኮምፒውተር ተለክቷል።
በማንበቢያ ክፍሉ በአሁኑ ጊዜ ብሪቲሽ ሙዚየም በዋጋ የማይተመኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎቹን በኮምፒውተር ውስጥ ማግኘት እንዲቻል አድርጓል። በለንደን የሚታተመው ዘ ታይምስ መጽሔት በአዲስ መልክ የተሠራውን ይህን ሕንፃ ከፍተኛ ጥበብ የተንጸባረቀበት ታላቅ ቅርስ በማለት ጠርቶታል። ጎብኚዎችም በዚህ አባባል ይስማማሉ!
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ የሥዕሎቹ ምንጮች]
ከላይ መሃል እና ከታች:- Copyright The British Museum የቀሩት:- Copyright Nigel Young/The British Museum