በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአርትራይተስን ምንነት መረዳት

የአርትራይተስን ምንነት መረዳት

የአርትራይተስን ምንነት መረዳት

“ማታ፣ ማታ ቅርጻቸው የተበላሸውን እግሮቼንና እጆቼን አይና አለቅሳለሁ።”​—⁠ሚዶሪ፣ ጃፓን

ርትራይተስ የሰው ልጆችን ማሰቃየት ከጀመረ ብዙ መቶ ዓመታት አልፈዋል። በሽታው ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ እንደነበረ በግብፅ እንዳይፈርሱ ተደርገው ከቆዩ አስከሬኖች ማስረጃ ተገኝቷል። አገር አሳሹ ክርስቶፎር ኮሎምበስ በዚሁ በሽታ ይሠቃይ እንደነበር ሊታወቅ ችሏል። ዛሬም ቢሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚሁ በሽታ ይሠቃያሉ። ይህ ሰውነትን የሚያሽመደምድ በሽታ ምንድን ነው?

“አርትራይተስ” የሚለው ቃል “የበገኑ አንጓዎች” የሚል ትርጉም ካላቸው የግሪክኛ ቃላት የተወሰደ ሲሆን ከ100 ከሚበልጡ የተለያዩ የቁርጥማት በሽታ ዓይነቶች ጋር ተዛማጅነት ያለው ነው። * እነዚህ በሽታዎች አንጓዎችን ብቻ ሳይሆን አንጓዎቹን ደግፈው የሚይዙትን ጡንቻዎች፣ አጥንቶች እንዲሁም አጥንትን ከጡንቻና አጥንትን ከአጥንት የሚያገናኙ ጅማቶችን ጭምር ያጠቃሉ። አንዳንድ የአርትራይተስ ዓይነቶች ቆዳን፣ የውስጥ አካል ክፍሎችንና፣ ዓይንን ሳይቀር ሊያጠቁ ይችላሉ። ከአርትራይተስ ጋር የቅርብ ትስስር ባላቸው ሁለት ሕመሞች ማለትም ሩማቶይድ አርትራይተስ (RA) እና ኦስትዮአርትራይተስ (OA) በሚባሉት ላይ ትኩረት እናድርግ።

የአንጓዎች አፈጣጠር

አንጓ የሚባለው ሁለት አጥንቶች የሚገናኙበት ቦታ ነው። በሲኖቪያል አንጓ ዙሪያ ከአደጋ የሚጠብቀውና ደግፎ የሚይዘው በከዳ (capsule) የተባለ ጠንካራ ገለፈት ይገኛል። (ገጽ 4 ላይ የሚገኘውን ሥዕል ተመልከት።) የአንጓው በከዳ በሲኖቪያል ገለፈት ይሸፈናል። ይህ ገለፈት የሚያሙለጨልጭ ፈሳሽ ያመነጫል። በአንጓው በከዳ ውስጥ የሁለቱ አጥንቶች ጫፍ የመለጠጥ ባሕርይ ባለው ካርትሌጅ የሚባል ህብረህዋስ ይሸፈናል። ይህም አጥንትህ እርስ በርሱ እንዳይፋተግና እንዳይፋጭ ይከላከላል። በተጨማሪም ካርቲሌጅ በአጥንቶችህ ጫፎች መካከል እንደ ትራስ ሆኖ በማገልገል ንዝረትን የሚቀንስ ከመሆኑም ሌላ በአጥንቶችህ ላይ የሚያርፈው ጭነት ለመላ አጥንቶችህ እኩል እንዲዳረስ ያስችላል።

ለምሳሌ ያህል በምትራመድበት፣ በምትሮጥበት ወይም በምትዘልበት ጊዜ በዳሌዎችህና በጉልበቶችህ ላይ የሚያርፈው ጭነት የሰውነትህን ክብደት ከአራት እስከ ስምንት እጥፍ ሊያደርስ ይችላል! ከዚህ ጭነት አብዛኛው ክፍል በአካባቢው ባሉ ጡንቻዎችና ጅማቶች የሚዋጥ ቢሆንም ካርቲሌጅ እንደ ስፖንጅ በመጨመቅ አጥንቶችህ ይህን ጭነት እንዲሸከሙ ያግዛቸዋል።

ሩማቶይድ አርትራይተስ

በሽታው ሩማቶይድ አርትራይተስ በሚሆንበት ጊዜ የሰውነት መድህን በራሱ አንጓዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ይከፍታል። በውል በማይታወቅ ምክንያት ሰውነትን ከበሽታ በመከላከል ረገድ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱትን ቲ ሴሎች ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የደም ሴል ወደ አንጓዎች ይጎርፋል። ይህ ደግሞ የተለያዩ የኬሚካል ሂደቶች እንዲካሄዱ ስለሚያደርግ አንጓው ይቆጣል። ሲኖቪያል ሴሎች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መጠን መራባት ይጀምሩና ፓነስ የሚባል እጢ መሳይ ነገር ይፈጠራል። ፓነሱ በተራው በካርቲሌጁ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ኢንዛይሞች ያመነጫል። በዚህ ጊዜ የአጥንት ጫፎች እርስ በርሳቸው ስለሚያያዙ እንደ ልብ መንቀሳቀስ አይቻልም፤ ኃይለኛ ሕመምም ይፈጥራል። ይህ ጎጂ ውጤት ያለው ሂደት አጥንትን ከአጥንትና ጡንቻን ከአጥንት የሚያያይዙትን ጅማቶችና ጡንቻዎች ስለሚጎዳ አንጓው ደካማና በከፊል የወለቀ ይሆናል። ብዙ ጊዜም ቅርጹ የተበላሸ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ሩማቶይድ አርትራይተስ የሚያጠቃው የግራውንና የቀኙን የሰውነት ክፍል በአንድ ላይ ሲሆን ቁርጭምጭሚቶችን፣ ጉልበቶችንና እግሮችን ይጎዳል። ሩማቶይድ አርትራይተስ እንደያዛቸው በምርመራ ከታወቀላቸው ሰዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከቆዳቸው ሥር ትናንሽ እባጭ ወይም ዕጢ መሳይ ነገር ይፈጠርባቸዋል። አንዳንዶቹ የደም ማነስ፣ የዓይን መድረቅና መቆጥቆጥ እንዲሁም የጉሮሮ ሕመም ይኖራቸዋል። ድካም እንዲሁም እንደ ትኩሳትና የጡንቻዎች ሕመም የመሳሰሉ የኢንፍሉዌንዛ ዓይነት የሕመም ስሜት ይሰማቸዋል።

ሩማቶይድ አርትራይተስ በሚያስከትለው ውጤት፣ በአጀማመሩም ሆነ በበሽታው ዕድሜ ረገድ የተለያየ ዓይነት አለው። በአንዳንድ ሰው ላይ ሕመሙና የጡንቻዎቹ ግትርነት (stiffness) ቀስ ብሎ ይጀምርና በሳምንታት እንዲያውም በዓመታት ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ እየበረታና እየተባባሰ ይመጣል። በሌሎች ላይ ደግሞ በድንገት ሳይታሰብ ይጀምራል። በአንዳንድ ሰዎች ላይ ሩማቶይድ አርትራይተስ ለጥቂት ወራት ብቻ ይቆይና የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ይተዋል። ሌሎች ደግሞ አንድ ወቅት ላይ በአጣዳፊ ሁኔታ ካመማቸው በኋላ ሻል ብሏቸው ይሰነብታል። በሽታው ለበርካታ ዓመታት ፋታ ሳይሰጥ የሚቆይባቸውና ለአካለ ጉዳት እስከመዳረግ የሚያደርሳቸውም ሰዎች አሉ።

በሩማቶይድ አርትራይተስ የመያዝ ሰፊ አጋጣሚ ያላቸው እነማን ናቸው? ዶክተር ማይክል ሺፍ “በመካከለኛ ዕድሜ ላይ በሚገኙ ሴቶች ላይ በብዛት ይታያል” ብለዋል። ይሁን እንጂ ሺፍ “ሕፃናትንና ወንዶችን ጨምሮ በማንኛውም እድሜ የሚገኝን ሰው ሊያጠቃ ይችላል” በማለት አክለው ተናግረዋል። ሩማቶይድ አርትራይተስ ያለባቸው ዘመዶች ያሏቸው ሰዎች በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ማጨስ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረትና ደም መውሰድ ለበሽታው የሚያጋልጡ ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑ በበርካታ ጥናቶች ተረጋግጧል።

ኦስትዮአርትራይተስ

ዌስተርን ጆርናል አቭ መዲስን “ኦስትዮአርትራይተስ በብዙ መንገዶች ሁኔታው ከአየር ጋር ይመሳሰላል። በሁሉም ቦታ የሚገኝ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት አይሰጠውም። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጣም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ያስከትላል” ብሏል። ኦስትዮአርትራይተስ እንደ ሩማቶይድ አርትራይተስ ሁልጊዜ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን የሚያዳርስ ሳይሆን አንድ ወይም ጥቂት አንጓዎችን የሚፈረፍር ነው። ካርቲሌጅ ቀስ በቀስ እየተፈረፈረ ሲሄድ የአጥንቶቹ ጫፎች እርስ በርሳቸው መፋጨት ይጀምራሉ። ከዚሁ ጋር ኦስትዮፋይትስ የሚባሉ እንደ ትርፍ አጥንት የመሰሉ ነገሮች ይፈጠራሉ። ሲስት (cyst) ዓይነት ነገር ሊፈጠር ስለሚችል ከሥር ያለው አጥንት ይደነድንና ቅርጹ ይበላሻል። የአንጓዎች ማበጥ፣ መፋጨትና መንቋቋት እንዲሁም የጡንቻዎች መኮማተር፣ ግትርነትና እንደ ልብ አለመታዘዝ ሌሎቹ የበሽታው ምልክቶች ናቸው።

ቀደም ባሉት ዓመታት ኦስትዮአርትራይተስ እርጅና ከሚያስከትላቸው ውጤቶች አንዱ እንደሆነ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ የሳይንስ ሊቃውንት በዚህ በቆየ አባባል ማመኑን እየተዉ መጥተዋል። ዚ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሜዲሲን እንዲህ ይላል:- “ለተለመዱት አካላዊ ጭነቶችና ተግባራት የተጋለጠ ጤነኛ አንጓ በአንድ ሰው የዕድሜ ዘመን ውስጥ ከጥቅም ውጭ እንደሚሆን የሚጠቁም ማስረጃ የለም።” ታዲያ ኦስትዮአርትራይተስ የሚመጣበት ምክንያት ምንድን ነው? ዘ ላንሴት የተባለው የብሪታንያ መጽሔት እንደሚለው የበሽታውን ትክክለኛ ምክንያት ለመረዳት የተደረገው ጥረት “ብዙ ውዝግብ አስነስቷል።” አንዳንድ ተመራማሪዎች የበሽታው መንስኤ እንደ አነስተኛ ስብራት ያለ በአጥንት ላይ የሚደርስ ጉዳት ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ። ይህ ዓይነቱ ጉዳት በተራው ትርፍ አጥንት እንዲበቅልና ካርቲሌጅ የሚባለው የአንጓዎች ሽፋን እንዲጎዳ ያደርጋል። ሌሎች ደግሞ ኦስትዮአርትራይተስ የሚጀምረው በራሱ በካርቲሌጅ ውስጥ ነው ይላሉ። በካርቲሌጁ ላይ ጉዳትና መጋጋጥ ሲደርስ ከሥር ባሉት አጥንቶች ላይ የሚደርሰው ጭነት ይጨምራል። ሰውነት የተጎዳውን ካርቲሌጅ ለመጠገን ጥረት በሚያደርግበት ጤናማ ያልሆኑ ለውጦች ይከሰታሉ።

በኦስትዮአርትራይተስ የመያዝ ሰፊ አጋጣሚ ያላቸው እነማን ናቸው? ዕድሜ ብቻውን የበሽታው ምክንያት ባይሆንም የአንጓ የካርቲሌጅ መጎዳት አብዛኛውን ጊዜ የሚባባሰው ከዕድሜ መግፋት ጋር ነው። አንጓ ላይ አጥንቶቻቸው በሚገናኙበት መንገድ ጉድለት ያለባቸው ወይም ደካማ የሆኑ የእግርና የጭን ጡንቻዎች ያሏቸው፣ የቅልጥማቸው ርዝማኔ የተለያየ፣ ወይም የአከርካሪ አጥንት መዛባት የደረሰባቸው ሰዎችም በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ከሆኑ ሰዎች የሚመደቡ ናቸው። በተጨማሪም በአደጋ ወይም በተደጋጋሚ እንቅስቃሴ ወይም ሥራ ምክንያት በአንጓ ላይ የሚደርስ ጉዳት ኦስትዮአርትራይተስ የሚመጣበትን ሁኔታ ያመቻቻል። በዚህ ዓይነት የጀመረው ጉዳት በሰውነት ክብደት መጨመር ይባባሳል።

ዶክተር ቲሞ ስፔክተር “ኦስትዮአርትራይተስ በግልጽ የሚታወቁ ውጪያዊ ምክንያቶች ያሉት የተወሳሰበ በሽታ ቢሆንም ከፍተኛ የሆነ በዘር ውርሻ ለበሽታው የመጋለጥ አጋጣሚም አለ” ይላሉ። በተለይ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙና ከዚያም ጠና ያሉ በበሽታው የተያዘ የቅርብ ዘመድ ያላቸው ሴቶች በኦስትዮአርትራይተስ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ኦስትዮፓሮሲስ ከተባለው በሽታ በተለየ መንገድ ከኦስትዮአርትራይተስ በፊት የሚቀድመው የአጥንት መሳሳት ሳይሆን የአጥንት መደንደን ነው። በተጨማሪም አንዳንድ ተመራማሪዎች ያልተጣመረ ኤሌክትሮን ባላቸው የኦክስጅን አተሞች ምክንያት የሚደርስ ጉዳትን፣ የቫይታሚን ሲ እና ዲ እጥረትን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

ሕክምና

የአርትራይተስ ሕክምና አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ መድኃኒቶች መውሰድን፣ አካላዊ እንቅስቃሴና የአኗኗር ለውጥ ማድረግን ያጠቃልላል። አንድ ፊዚካል ቴራፒስት ጤናን ለማሻሻል የሚረዳ የሰውነት እንቅስቃሴ ያሠራህ ይሆናል። ይህም ጡንቻዎች እንዲሳሳቡና እንዲለጠጡ የሚያደርግ (isometric)፣ ክብደት እንደማንሳት ያሉትን (isotonic) እና የኤይሮቢክ እንቅስቃሴዎችን ሊያካትት ይችላል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች እንደ አንጓ ሕመምና እብጠት፣ ድካም፣ መጥፎ ስሜት እንደመሰማትና ጭንቀት ያሉትን የሕመም ስሜቶች እንደሚቀንሱ ታውቋል። የአካላዊ እንቅስቃሴ ጥቅም በጣም ባረጁ ሰዎች ላይ ሳይቀር ታይቷል። በተጨማሪም አካላዊ እንቅስቃሴ የሚደርሰውን የአጥንት መሳሳት ያስወግዳል። አንዳንዶች ደግሞ በሙቀትና በቅዝቃዜ በሚሰጡ የተለያዩ ሕክምናዎችና በአኩፓንክቸር ከሕመማቸው ፋታ እንዳገኙ ይናገራሉ። *

ክብደት መቀነስ የአንጓ ሕመሞችን በከፍተኛ መጠን ስለሚቀንስ የአመጋገብ ለውጥ ማድረግ ለአርትራይተስ ከሚደረጉት ጥንቃቄዎች ዋነኛውን ቦታ ሊይዝ ይችላል። ጠቆር ያለ አረንጓዴ ቀለም ያላቸውን በካልስየም የበለጸጉ ቅጠላ ቅጠሎችን፣ ትኩስ ፍራፍሬዎችን፣ ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ የሚባለው ንጥረ ምግብ የሚገኝባቸውን የቀዝቃዛ አካባቢዎች ዓሣ አዘውትሮ መመገብና በፋብሪካዎች በመዘጋጀታቸው ምክንያት የተፈጥሮ ባሕርያቸውን ያጡና የቅባት ክምችት ያላቸውን ምግቦች መቀነስ ክብደት ለመቀነስ ከመርዳቱ በተጨማሪ የሕመም ስሜትን በእጅጉ ይቀንሳል። እንዴት? አንዳንዶች እንዲህ ያለው አመጋገብ የአጥንት ብግነቱን ሂደት ያግዳል ይላሉ። ሥጋ፣ የወተት ውጤቶች፣ ስንዴና እንደ ቲማቲም፣ ድንች፣ ቃሪያና ደበርጃን ያሉትን አትክልቶች አለመመገብ እንደረዳቸው የሚናገሩ አሉ።

አርትሮስኮፒ የሚባለውን ቀዶ ሕክምና መውሰድ የሚመከርበት ሁኔታም አለ። ይህ ሕክምና በሚሰጥበት ጊዜ መሣሪያው አንጓ ውስጥ እንዲገባ ይደረግና የቀዶ ሕክምና ባለሙያው ጉዳት የሚያስከትሉ ኢንዛይሞች የሚያመነጨውን ሲኖቭያል ህብረህዋስ ያስወግዳል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ አንጓው ተመልሶ ስለሚቆጣ ይህ ዓይነቱ ቀዶ ሕክምና የሚያስገኘው ጥቅም በጣም ውስን ነው። ከዚህ ይበልጥ ከባድ የሆነው ሕክምና አርትሮፕላስቲ ይባላል። በዚህ ሕክምና መላው አንጓ (አብዛኛውን ጊዜ የዳሌ ወይም የጉልበት አንጓ) ይወገድና በቦታው ሰው ሠራሽ አንጓ ይተካል። ይህ ሕክምና ከ10 እስከ 15 ዓመት ሊያቆይ ሲችል ሕመም በማስወገድ ረገድ በጣም ውጤታማ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዶክተሮች ይበልጥ ቀለል ያሉ እንደ ቪስኮከስፕልሜንተሽን የመሰሉ ሕክምናዎችን ሞክረዋል። በዚህ ሕክምና ሃያሉሮኒክ የሚባለው ቅባትነት ያለው ፈሳሽ አንጓ ውስጥ ይጨመራል። ይህ የሚደረገው አብዛኛውን ጊዜ በጉልበት አንጓዎች ላይ ነው። አንዳንድ በአውሮፓ የተደረጉ ጥናቶች ደግሞ ካርቲሌጅ እንዲጠገን የሚያደርጉ (ኮንዶፕሮቴክቲቭ) ቅመሞችን መውጋት መጠነኛ ውጤት እንዳስገኘ ጠቁመዋል።

አርትራይተስን ጨርሶ የሚያድን መድኃኒት ባይገኝም የሕመም ስሜቶችንና የአንጓ ብግነትን የሚያስታግሱ በርካታ መድኃኒቶች አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ የበሽታውን መባባስ እንደሚያዘገዩ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች፣ ኮርቲኮስቲሮይድ መድኃኒቶች፣ ከስቴሮይድ ነፃ የሆኑ ብግነትን የሚከላከሉ መድኃኒቶች፣ (NSAIDs) በበሽታው ባሕርይ ላይ ለውጥ የሚያመጡ የቁርጥማት መድኃኒቶች፣ (DMARDs) የሰውነትን መከላከያ ኃይል የሚያዳክሙ መድኃኒቶች፣ በሰውነት ተፈጥሯዊ ምላሽ ላይ ለውጥ የሚያስከትሉ እንዲሁም የሰውነትን መከላከያ ኃይል ባሕርይ የሚለውጡ መድኃኒቶች የሚያሽመደምደውን የአርትራይተስ በሽታ ለመዋጋት ጥቅም ላይ የዋሉ መሣሪያዎች ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ የመድኃኒት ዓይነቶች በሙሉ ከባድ የሆኑ ተጓዳኝ ጉዳት ስላላቸው ከሕመሙ ፋታ ለማግኘት ሲባል ከባድ ዋጋ መክፈል ሊያስፈልግ ይችላል። መድኃኒቱ የሚያስከትለውን ጉዳትና ያለውን ጥቅም ማመዛዘን ለሐኪሙም ሆነ ለበሽተኛው ከባድ ሊሆን ይችላል።

አርትራይተስ ጉዳት ያደረሰባቸው አንዳንድ ሰዎች ይህን ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል ሕመም ተቋቁመው ሊኖሩ የቻሉት እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ከእነዚህ መካከል ኦስትዮአርትራይተስ፣ ሩማቶይድ አርትራይተስ፣ ሲስተሚክ ሉፐስ ኤራይቲማቶሰስ፣ ጁቨናይል ሩማቶይድ አርትራይተስ፣ ጋውት፣ በርሳይተስ፣ ሩማቲክ ፊቨር፣ ላይም በሽታ፣ ካርፐል ታነል ሲንድሮም፣ ፋይብሮማያልጂያ፣ ሪይተርስ ሲንድሮም እና አንክሎሲንግ ስፖንዲላይተስ ይገኙበታል።

^ አን.18 ንቁ! ለማንኛውም ዓይነት ሕክምና፣ መድኃኒት ወይም ቀዶ ሕክምና የተለየ ድጋፍ አይሰጥም። በታወቁት መርጃዎች አማካኝነት አመዛዝኖ የሚበጀውን ሕክምና መምረጥ የእያንዳንዱ ታማሚ ኃላፊነት ነው።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ ማጨስና ደም መውሰድ አንድን ሰው ለሩማቶይድ አርትራይተስ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያጋልጠው ይችላል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አማራጭ ሕክምናዎች

አንዳንድ መድኃኒቶች ከባሕላዊ መድ​ኃኒቶች ይበልጥ አስተማማኝ እንደሆኑና የሚያስከትሉትም ጉዳት እንደሚያንስ ይታሰባል። ከእነዚህ መካከል ተመራማሪዎች በሩማቶይድ አርትራይተስ ምክንያት የሚደርሰውን ሕመምና የአንጓ እብጠት እንደሚቀንስ የሚናገሩለት በአፍ የሚወሰደው ታይፕ II ኮላጂን ይገኝበታል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ኢንተርሉኪን-1 እና ቱሞር ኒክሮሲስ ፋክተር አልፋ የሚባሉትን ሥቃይ አስከታይና አጥፊ ተጽእኖ ያላቸው ሳይቶኪንስ የተባሉ ቅመሞች በመቆጣጠር ነው። እነዚህን ጎጂ ቅመሞች እንደሚቆጣጠሩ የተደረሰባቸው ተፈጥሮአዊ ንጥረ ምግቦችም እንዳሉ ሪፖርት ተደርጓል። ቫይታሚን ኤ፣ ቫይታሚን ሲ፣ ናያ​ሲንአማይድ፣ አይኮሳፔይንታኖይክ አሲድ [EPA] በብዛት የሚገኝባቸው የዓሣ ዘይቶች፣ ጋማሊኖሌይኒክ አዲስ [GLA] በራጅ እና ኢቭኒንግ ፕሪሞሮስ ከሚባሉት ዕፅዋት የሚገኝ ዘይት ከነዚህ የሚመደቡ ናቸው። በቻይና ትሪፕቴርግየም ዊልፎርዳይ የተባለው ሐረግ መሳይ ዕፅ ለበርካታ ዓመ​ታት አገልግሎት ላይ ውሏል። ሩማ​ቶይድ አርትራይተስ የሚያስከትለውን ሥቃይ በመቀነስ ረገድም መጠነኛ ውጤት እንዳስገኘ ይነገርለታል።

[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጤነኛ አንጓ

ቡርሳ

ጡንቻ

ካርቲሌጅ

ጅማት

የአንጓ በከዳ

ሲይኖቪያል ገለፈት

ሲይኖቪያል ፈሳሽ

አጥንት

ሩማቶይድ አርትራይተስ ያጠቃው አንጓ

የክፍተት መጥበብ

በአጥንቱና በካርቲሌጁ ላይ የደረሰ ጉዳት

የተቆጣ ሲይኖቫል ገለፈት

ኦስቲዮአርትራይተስ ያጠቃው አንጓ

የሚንሳፈፉ የካርቲሌጅ ፍርፋሪዎች

በካርቲሌጅ ላይ የደረሰ ጉዳት

የአጥንት ስፐር

[ምንጭ]

ምንጭ:- Arthritis Foundation

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አርትራይተስ በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኝን ሰው ሊያጠቃ ይችላል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የአካል እንቅስቃሴ ማድረግና የተመጣጠነ አመጋገብ በተወሰነ መጠን ሥቃይን ሊያስታግሥ ይችላል