በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕልሜ እውን የሆነልኝ እንዴት ነው?

ሕልሜ እውን የሆነልኝ እንዴት ነው?

ሕልሜ እውን የሆነልኝ እንዴት ነው?

አሌና ዥትኒኮቫ እንደተናገረችው

ገና ልጅ ሳለሁ የሶቪዬት አጋር በሆነችው በቺኮዝሎቫክያ ይኖር የነበረው ቤተሰባችን ኮምኒዝም ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ሰላማዊ ዓለም በናፍቆት ይጠብቅ ነበር። ሆኖም ኮምኒዝም አንድነት ያለው ደስተኛ ኅብረተሰብ ለመፍጠር የነበረው ሕልም በ1991 ሶቪዬት ኅብረት በፈራረሰች ጊዜ አከተመ። ይህ ሕልሜ በሌላ መንገድ እንዴት እውን እንደሆነ ልግለጽ።

ስከረም 12 ቀን 1962 ሆርኒ ቤኔሶቭ ተብሎ በሚጠራ ከፕራግ 290 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ አንድ መንደር የኮምኒዝም ፍጹም ተከታይ ከሆኑ ቤተሰቦች ተወለድኩ። አባቴ በኮምኒስት ፍልስፍና የሚያምንና የሚመራ ሰው ነበር። ሁለት ወንድሞቼን፣ እህቴንና እኔን ያሳደገንም በዚህ ፍልስፍና ኮትኩቶ ነበር። ጠንክሮ በመሥራትና የጨዋነት ኑሮ በመምራት የተሻለ ኅብረተሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ልናበረክት እንደምንችል ያስተምረን ነበር። ከኮምኒዝም የተሻለ አስተዳደር ሊኖር እንደማይችል ያምንና በንቃትም ይደግፍ ነበር።

አባቴ ብዙ ጊዜ ለኮምኒዝም ከፍተኛ ግምት በሚሰጥባቸው ስብሰባዎች ይገኛል። በአብያተ ክርስቲያናት ግብዝነት ምክንያት ለሃይማኖት ከፍተኛ ንቀት የነበረው ከመሆኑም በላይ አምላክ የለም ብሎም ያምንና ያስተምር ነበር። ቤትና በቂ ምግብ ለሁሉ ሰው ከተዳረሰ የሰው ዘር በሰላምና በተሻለ ሁኔታ ሊኖር ይችላል የሚል እምነት ነበረው። ተስፋው በጣም አጓጊ ከመሆኑ የተነሳ እያደግኹ ስሄድ በተደጋጋሚ እሰማው ነበር። አባቴ ያስተማረንን ሁሉ ስላመንኩ ኮምኒዝምን ከልቤ ለመደገፍ ቆርጬ ተነሳሁ።

ገና ትንሽ ልጅ እያለሁ የወጣት ኮምኒስት ሕዝባዊ ድርጅት አባሎች ይጠሩ እንደነበረው አቅኚ ለመሆን ተዘጋጀሁ። የኮምኒስት አቅኚዎች ጥሩ ጥሩ ባሕርያት እንዲኮተኩቱና ጠንካራ የአገር ፍቅር እንዲኖራቸው ማሳሰቢያ ይሰጣቸው ነበር። ዘጠኝ ዓመት እንደሆነኝ የአቅኚነት መሐላ ፈጸምኩና የምለብሰው ቀይ ያንገት ሻሽ ተሰጠኝ። በተጨማሪም በልዩ ቀናት የአቅኚዎች የደንብ ልብስ እንድለብስ ተፈቀደልኝ። ጥሩ አቅኚ ሆኜ ለመገኘት እጣጣር ነበር። የትምህርት ቤት ጓደኞቼ የብልግና ቃላት ሲናገሩ እንዲህ ያለ ቃል አቅኚ ከሆኑ ልጃገረዶች አፍ አይወጣም እያልኩ እገስጻቸው ነበር።

ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ኮምኒስት ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች የኮምኒዝምን ምግባሮች እንደማያከብሩ መገንዘብ ጀመርኩ። የስግብግብነትንና የምቀኝነትን ሰብዓዊ ዝንባሌ ከመቃወም ይልቅ የሕዝብ ንብረቶችን ይሠርቃሉ። ብዙዎቹ ሌሎች ሰዎች ጠንክረው እንዲሠሩ ቢቀሰቅሱም እነርሱ ግን እንደዚያ አያደርጉም ነበር። እንዲያውም “የማይሠርቅ ከገዛ ቤተሰቦቹ ይሠርቃል” የሚለው አባባል እጅግ የተለመደ ሆነ። ‘ይህን ያህል ግብዝነት የበዛው ለምንድን ነው? የኮምኒዝምን ግሩም ዓላማዎች ለመደገፍ የሚጣጣሩት ሰዎች ይህን ያህል ጥቂቶች የሆኑት ለምንድን ነው? የሚደረጉት ጥረቶች ሁሉ በአብዛኛው የማይሳኩት ለምንድን ነው?’ እያልኩ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ።

ራስን የመመርመሪያ ጊዜ

በአሥራዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ የበጋ ዕረፍት ጊዜዬን በከፊል አሌና ከምትባለው የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ጋር አሳለፍኩ። አንድ ቀን ምሽት የአሌና ወዳጅ የሆነች ታንያ የተባለች ትልቅ ሴት መጣች። “በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አንድ ጉዳይ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ” አለችን። “አምላክ እንዳለ አምኛለሁ።” እንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ መደረስዋ በጣም አስገረመን። የመገረም ስሜታችን እንዳለፈልን ጥያቄዎች አዥጎደጎድንባት። “ምን ማስረጃ አገኘሽ?” “መልኩ ምን ይመስላል?” “የሚኖረው የት ነው?” “ዝም ያለውስ ለምንድን ነው?”

ታንያ ጥያቄዎቻችንን አንድ በአንድ መለሰችልን። የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ የሰው ልጅ ገነት በሆነች ምድር እንዲኖር እንደነበረና ይህ ዓላማውም ወደፊት ፍጻሜውን እንዴት እንደሚያገኝ ገለጸችልን። ምድር ጸድታ ጤነኛ በሆኑና እርስ በርሳቸው በሚተሳሰቡ ጥሩ ሰዎች እንደምትሞላ የሚገልጸውን ተስፋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ስታሳየን ይህ ተስፋ አምነው ከነበረው የኮምኒዝም ተስፋ ጋር እንደሚመሳሰል ተገነዘብኩ። ይሁን እንጂ እነዚህ አስደናቂ ነገሮች እውን የሚሆኑት በኮምኒዝም ሳይሆን በአምላክ መንግሥት እንደሆነ አባቴ ቢሰማ ደስ እንደማይለው እርግጠኛ ነበርኩ።

ምናልባት ስድስት ወይም ሰባት ዓመት እንደሆነኝ አንዲት የጎረቤት ልጅ ወላጆቼ ሳያውቁ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስዳኝ እንደ ነበር ትዝ ይለኛል። ቄሱ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ተረኩልንና ታሪኩ በጣም ደስ ስላለኝ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ፈለግኩ። ጥቂት ሃይማኖታዊ ጽሑፎችንም ሰጡኝና ወሰድኩ። ለወላጆቼ ስናገር ዳግመኛ ቤተ ክርስቲያን እንዳልሄድ አጥብቀው ከለከሉኝ። እንዲያውም ይዣቸው የመጣኋቸውን ጽሑፎች በሙሉ አጠፉብኝ። ከዚያም አልፎ ዳግመኛ እንዳይለምደኝ አባቴ ገረፈኝ።

ከዚያ በኋላ አምላክ የሚል ቃል በቤታችን ተነስቶ አያውቅም። በአምላክ የሚያምኑት ያልሰለጠኑና ያልተማሩ ሰዎች ብቻ እንደሆኑና ሃይማኖትም ሰው የፈለሰፈው ነገር እንደሆነ አምን ነበር። ልንረዳቸው የማንችላቸው ነገሮች ስላሉ ሰዎች አምላክ አለ የሚለውን ሐሳብ እንደ ፈጠሩ የሚገልጽ ትምህርት በትምህርት ቤት ተሰጥቶን ነበር። አሁን ግን የተማረች፣ እንዲያውም መምህር የሆነች ታንያ የምትባል በአምላክ የምታምን ሴት ተገኘች! ‘አንድ ነገር መኖር አለበት’ ብዬ አሰብኩ።

ታንያ ትናገር የነበረው በእርግጠኝነት ስለሆነ የምትናገረው ሁሉ ከልብ የምታምንበትን እንደሆነ እርግጠኞች ነበርን። በዚህም ምክንያት “ታንያ፣ በእርግጥ አምላክ እንዳለ ያሳመነሽ ነገር ምንድን ነው?” ብለን ጠየቅናት።

“መጽሐፍ ቅዱስ ነው” ስትል መለሰችልን። “የጠየቃችሁኝ ጥያቄዎች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመልሰዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ለመረዳት ትፈልጋላችሁ?”

መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ብጀምር ወላጆቼ ደስ እንደማይሰኙ አውቅ ነበር። ቢሆንም ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት በጣም ፈለግኩ። ስለዚህም ታንያ ከቤታችን አቅራቢያ በሆርኒ ቤኔሶቭ የምትኖረውን የሉድሚላን አድራሻ ሰጠችኝ። ከሉድሚላ ጋር ሆኜ አምላክ የሰጠውን የምድራዊ ገነት ተስፋ በምመረምርበት ጊዜ ‘ይህ ነገር እንደሚፈጸም ምን ዋስትና አለኝ?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር።

ሉድሚላ በአምላክና በተስፋዎቹ እንዳምን ስለ አምላክ ተጨማሪ እውቀት ማግኘት እንደሚያስፈልገኝ ነገረችኝ። ምድርና በምድር ላይ የሚኖሩት የተወሳሰቡ ሕያዋን ፍጥረታት እንዲያው በአጋጣሚ የተገኙ ሊሆኑ እንደማይችሉ ከጥናታችን ለማረጋገጥ ቻልኩ። በጣም ከፍተኛ ጥበብ ያለው አንድ ፈጣሪ መኖር አለበት ብዬ ለመቀበል ተገደድኩ። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፣ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው” ብሎ ሲናገር ምን ያህል ምክንያታዊ እንደሆነ ተገነዘብኩ።​—⁠ዕብራውያን 3:​4

ቤተሰቦቼ እነዚህን ነገሮች እንዲያውቁ ፈለግኩ። ሆኖም አይፈልጉ ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ ሳልነግራቸው ቆየሁ። አንድ ቀን ግን እናቴ ተሰጥቶኝ ከነበረ አሮጌ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገንጥሎ የወደቀ አንድ ገጽ ከዕቃዎቼ መካከል አገኘች። ወላጆቼ በጣም ተረበሹ።

ከአባቴ ጋር የተደረገ ውይይት

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደምገናኝ አባቴ የነበረው ጥርጣሬ እውነት መሆኑ ሲረጋገጥ አብረን በእግር ረዥም መንገድ እንድሄድ ጠራኝ። “ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያለሽን ግንኙነት አሁኑኑ ማቋረጥ አለብሽ” አለኝ። “ካላቋረጥሽ የመንደራችን ከንቲባ ሆኜ በማገልገል ልቀጥል አልችልም። ሥራዬን ታበላሽብኛለሽ። ቢሮዬን ለቅቄ ቀድሞ እሠራበት ወደነበረው ፋብሪካ ለመመለስ እገደዳለሁ። በመላው ቤተሰብ ላይ እፍረት ታመጪያለሽ።”

“ግን አባዬ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታዊ መጽሐፍ ነው። ስለ ኑሮ በጣም ግሩም የሆኑ ምክሮች ይሰጣል” ስል ተማጸንኩት።

“አይሆንም አሌንካ፣ ያለ አምላክም ሆነ ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ደስተኛ ሆኜ ኖሬያለሁ። ሁሉን ነገር በእነዚህ በእጆቼ አሳክቼያለሁ። ማንም የረዳኝ የለም። እንዲህ ያለውን የማይረባ ነገር ማመን መቻልሽ በጣም አስደንቆኛል። ትዳር ይዘሽና ልጆች ወልደሽ እውነተኛ ሕይወት መኖር አለብሽ። ያን ጊዜ ያለ አምላክ ደስ ብሎሽ ልትኖሪ እንደምትችይ ትገነዘቢያለሽ” አለኝ።

የአባቴ ውትወታ ተጽዕኖ አሳደረብኝ። ጠንካራ መሠረት ያልነበረውን እምነቴን ወዲያው ተጠራጠርኩ። ከይሖዋ ምሥክሮች በፊት ለበርካታ ዓመታት የማውቀው አባቴን ነው። በቤታችን የነበረው ኑሮዬም በጣም የተረጋጋ ነበር። አባቴ እንዲህ የተናገረው ለኔ አስቦ እንደሆነ እርግጠኛ ነበርኩ። እንደሚወደኝ አውቃለሁ። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት አቆማለሁ ብዬ ቃል ገባሁለት። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ 18 ዓመት ሞላኝና ትምህርት ጨርሼ ሥራ ለመቀጠር የአገራችን ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ፕራግ ሄድኩ።

የፕራግ ኑሮዬ

በአንድ ባንክ ሥራ አገኘሁና አባቴ በኮምኒዝም አማካኝነት ይገኛል ስላለው እውነተኛ ሕይወት ይበልጥ ለማወቅ በጉጉት ተነሳሳሁ። ይሁን እንጂ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከተማ የሚኖሩ ሰዎችም ከገጠሮቹ የተሻለ ደስታ እንደሌላቸው ተመለከትኩ። እንዲያውም ብልግና፣ ግብዝነት፣ ራስ ወዳድነትና ሰካራምነት የተለመዱ ነገሮች ናቸው።

ከጊዜ በኋላ ፕራግን ለመጎብኘት መጥቶ የነበረ ቤታችን አቅራቢያ በሆርኒ ቤኔሶቭ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር ከምሥክሮች ጋር እንድገናኝ አደረገች። በዚህ መንገድ ኢቫ ከምትባል ሴት ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን እንደገና ጀመርኩ። አጥንተን በጨረስን ቁጥር ኢቫ “በሚቀጥለው ሳምንት እንድመጣ ትፈልጊያለሽ?” እያለች ትጠይቀኝ ነበር። በእኔ ቦታ ብትሆን ምን እንደምታደርግ የጠየኳት ጊዜያቶች ቢኖሩም የራሷን አስተሳሰብ እንድቀበል አስገድዳኝ አታውቅም።

“እኔ ብሆን ምን እንደማደርግ ልነግርሽ አልችልም” ትለኛለች። ከዚያም ውሳኔ ላይ እንድደርስ የሚረዳኝ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሳየኛለች። ትልቁ አሳሳቢ ነገር ከወላጆቼ ጋር ያለኝ ዝምድና በመሆኑ ከእነርሱ ጋር ያለኝን ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርብኝ እንደሆነ ጠየቅኳት። ኢቫ ዘጸአት 20:​12ን አወጣችና ወላጆቻችንን ማክበር እንደሚኖርብን ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየችኝ። ከዚያም “ሆኖም ከወላጆቻችን ልናስበልጠው የሚገባ ይኖራል?” ስትል ጠየቀችኝ።

መልሱን በእርግጠኝነት ስላላወቅኩ መጽሐፍ ቅዱስ ገልጣ “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃላት አሳየችኝ። (ማቴዎስ 10:​37) በዚህ መንገድ ወላጆቼን ማክበር ቢኖርብኝም ኢየሱስና የኢየሱስ ሰማያዊ አባት የበለጠ አክብሮት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተገነዘብኩ። ኢቫ ሁልጊዜ አግባብነት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ለመጠቆም ትሞክርና ውሳኔውን ግን ለእኔ ትተው ነበር።

የፍላጎት መጋጨት

ከጊዜ በኋላ በመስከረም 1982 በፕራግ የሚገኝ አንድ ኮሌጅ ተቀበለኝና የግብርና ትምህርት መከታተል ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ግን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ የምፈልገውን ያህል ጊዜ እየሰጠሁ የኮሌጅ ትምህርቴን ለመከታተል እንደማልችል ተነገዘብኩ። ስለዚህም ትምህርቴን ለማቋረጥ እንዳሰብኩ ለአንዲት አስተማሪዬ ነገርኩ። “ችግርሽን ተረድቶ ሊረዳሽ ወደሚችል ሰው እልክሻለሁ” አለችኝ። የኮሌጁ ዲን እንዲያነጋግረኝ አደረገች።

ዲኑ ጥሩ አቀባበል ካደረገልኝ በኋላ “በጣም ጥሩ ተማሪያችን ትምህርቷን ለማቋረጥ የፈለገችው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ።

“ለምፈልገው ሌላ ጉዳይ በቂ ጊዜ ማግኘት ስላልቻልኩ ነው” ስል መለስኩለት። የይሖዋ ምሥክሮች በቼኮዝሎቫክያ የታገዱበት ጊዜ ስለነበረ ትምህርቴን ለማቋረጥ የወሰንኩበትን ምክንያት ለመናገር አልፈለግኩም ነበር። ለሁለት ሰዓት ያህል ካነጋገርኩት በኋላ ግን እምነት ሊጣልበት የሚችል ሰው ነው ብዬ አሰብኩ። ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ እያጠናሁ እንደሆነ ነገርኩት።

“መጽሐፍ ቅዱስንም ማርክስንም አጥኚና ከዚያ በኋላ ምርጫሽን ትወስኚያለሽ” አለኝ። መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ያበረታታኝ ይመስል ነበር።

ሴራው ከሸፈ

በማግስቱ ግን እርሱና አስተማሪዬ እስከ ትውልድ መንደሬ ድረስ ሄደው ወላጆቼን አነጋገሩ። አደገኛ ከሆነና ከታገደ ሃይማኖታዊ ኑፋቄ ጋር እንደምገናኝና ከኮሌጅም መውጣት እንደምፈልግ ነገሯቸው። ዲኑ ለአባቴ “ልጅህ ትምህርቷን ለማቋረጥ ከወሰነች በፕራግ ፈጽሞ ሥራ እንዳታገኝ እናደርጋለን። ያን ጊዜ ወደ እናንተ ለመመለስ ስለምትገደድ ከዚህ ኑፋቄ ጋር ያላትን ግንኙነት ታቋርጣለች” ሲል ነገረው።

በጥር ወር 1983 ትምህርቴን አቋረጥኩ። መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ የምትገኝ ጓደኛዬ ከአንዲት በዕድሜ የገፉ ሴት ቤት እንድከራይ ረዳችኝ። ዲኑ ቤተሰቦቼን ስለማነጋገሩም ሆነ ለአባቴ ስለገባለት ቃል ያወቅኩት ነገር ስላልነበረ ሥራ ለማግኘት ያደረግኩት ጥረት ሁሉ መና መቅረቱ ሊገባኝ አልቻለም። ቤት ያከራዩኝም ሴት የኔ ሁኔታ ስለከነከናቸው ለእኔ ሳይነግሩኝ ወደ ኮሌጁ ዲን ሄዱና ትምህርት ያቋረጥኩበትን ምክንያት ጠየቁት።

“ተጠንቀቁ” በማለት አስጠነቀቃቸው። “አደገኛ የሆነው የይሖዋ ምሥክሮች ኑፋቄ አባል ነች። ትምህርት ያቋረጠችውም በዚህ ምክንያት ነው። ወደ ወላጆቿ መመለስና ይህን ግንኙነቷን ማቆም አለባት። በፕራግ ውስጥ ምንም ዓይነት ሥራ እንዳታገኝ አደርጋለሁ!” አላቸው።

ሴትዮዋ ያን ዕለት ማታ ቤት እንደተመለሱ ጠሩኝና “አሌንካ፣ ዛሬ ኮሌጅሽ ሄጄ ነበር” አሉኝ። ያኔውኑ ሻንጣዬን ጠቅልዬ የምወጣ መስሎኝ ነበር። ይሁን እንጂ “ዲኑ ያደረገውን አልደግፍም። የፈለግሽውን ማመን ትችያለሽ። ዋናው አስፈላጊ ነገር ጠባይሽ ነው። ሥራ እንድታገኚ እረዳሻለሁ” አሉኝ። ያን ዕለት ማታ ይሖዋ ስላደረገልኝ እርዳታ በጸሎት አመሰገንኩት።

ወዲያውም አባቴ ይዞኝ ሊሄድ ወደ ፕራግ መጣ። በዚህ ጊዜ ግን ያቀረበልኝ ምክንያት አላሳመነኝም። አሁን በይሖዋና በተስፋዎቹ ላይ ያለኝ እምነት ጠንከር ብሏል። በመጨረሻ አባቴ ብቻውን ለመመለስ ተገደደ። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያለቅስ አየሁት። በከፍተኛ ምሬት ተላቅሰን ብንለያይም በይበልጥ ከይሖዋ ጋር እንድቀራረብ አደረገኝ። የይሖዋ ንብረት ለመሆንና እርሱንም ለማገልገል ፈለግኩ። በመሆኑም ኅዳር 19 ቀን 1983 በፕራግ በሚገኝ አንድ አፓርተማ በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ በመጠመቅ ሕይወቴን ለይሖዋ መወሰኔን አሳየሁ።

ውሳኔዬ ተባረከ

ከጊዜ በኋላ ታግዶ የነበረውን የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፍ በማዘጋጀት ሥራ መካፈል ጀመርኩ። ባለ ሥልጣኖች ቀደም ሲል በዚሁ ሥራ ይካፈሉ የነበሩ አንዳንዶችን አስረው ስለነበረ ሥራው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነበር። የመጀመሪያው ሥራዬ በቼክ ቋንቋ የተተረጎመ መጠበቂያ ግንብ በታይፕ መገልበጥ ነበር። እነዚህ የታይፕ ቅጂዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸው እንዲጠቀሙባቸው ለይሖዋ ምሥክሮች ይታደሉ ነበር።

በኋላ ደግሞ በፕራግ በሚገኝ አፓርተማ ውስጥ ተገናኝቶ መጻሕፍት ከሚያዘጋጅ አንድ ቡድን ጋር አብሬ እንድሠራ ተጋበዝኩ። በአንድ ክፍል ውስጥ የነበሩ ዕቃዎች በአብዛኛው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ከክፍሉ መሐል ለመሐል በተቀመጠ ትልቅ ጠረጴዛ ላይ አንዳንድ ነጠላ ገጾች እየለቀምን እናነባብራለን። በኋላም እነዚህ ገጾች ይጠረዙና መጻሕፍት ይሆናሉ። ይህን ሥራ ሙሉውን ጊዜዬን ብሠራ እንዴት ጥሩ ይሆን ነበር እያልኩ ብዙ ጊዜ አስብ ነበር።

በኮምኒስት ወጣቶች ድርጅት ውስጥ አቅኚ በነበርኩ ጊዜ ሕፃናት የተሻሉ ሰዎች እንዲሆኑ ለማስተማር ሞክሬ ነበር። የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ በኋላ ደግሞ ከወጣቶች ጋር በመሥራት ብዙዎቹ የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሆኑ ለመርዳት ችያለሁ። ከቤተሰቦቼ መካከል እስካሁን የይሖዋ ምሥክር የሆነ ሰው ባይኖርም መጽሐፍ ቅዱስ በገባው ቃል መሠረት በርካታ መንፈሳዊ አባቶችና እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች አግኝቻለሁ።​—⁠ማርቆስ 10:​29, 30

በ1989 በአገራችን የነበረው የኮምኒስት መንግሥት በዲሞክራሲያዊ መንግሥት ተተካ። ይህ ለውጥ ለይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ነጻነት በማስገኘቱ በይፋ ተሰብስበን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት፣ እንታሠራለን ብለን ሳንፈራ ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ፣ ወደ ውጭ አገሮች ተጉዘን በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ችለናል። ከዚህም በላይ ምርመራ፣ እስራት ወይም ማስፈራሪያ ይደርስብናል ብለን መስጋት ቀርቶልናል!

ከባለቤቴ ጋር ማገልገል

በ1990 ክርስቲያን ባልደረባዬ የሆነውን ፔትርን አገባሁ። በሚያዝያ ወር 1992 ሁለታችንም አቅኚ ለመሆን የነበረንን ግብ አሳካን። (የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ የተሰማሩትን ሰዎች አቅኚ ብለው ይጠራሉ።) በኋላም በሰኔ ወር 1994 በፕራግ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንድንሠራ ተጋበዝን። አሁን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን በድብቅ ማዘጋጀታችን ቀርቶ በመላይቱ የቼክ ሪፑብሊክ የሚኖሩ ሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት በይፋ እንንቀሳቀሳለን።

ከጥቂት ዓመታት በፊት 60 ከሚያክሉ ሌሎች የቅርንጫፍ ቢሮ አባላት ጋር የምንኖርበትንና የምንሠራበትን ቦታ እንዲጎበኙልን ያቀረብንላቸውን ግብዣ ወላጆቼ በመቀበላቸው እኔና ፔትር ደስ ተሰኝተናል። ቤታችንንና መሥሪያ ቤታችንን ከጎበኙ በኋላ አባቴ “በእርግጥ በመካከላችሁ እውነተኛ ፍቅር ያለ ይመስለኛል” ብሏል። ከአባቴ አፍ ይህን የመሰለ ቃል በመውጣቱ በጣም ተደስቻለሁ።

ኮምኒዝም አስገኛለሁ ይላቸው በነበሩ ነገሮች መደሰት

በኮምኒዝም አማካኝነት የተሻለ ዓለም እንደሚመጣልን የነበረን ተስፋ ከንቱ ሕልም ሆኖ ከመቅረት አላለፈም። የሰው ልጆች ያደረጉት ጥረት ሁሉ ጽድቅ የሰፈነበት ኅብረተሰብ ሊያስገኝ እንዳልቻለ የሰው ልጅ ታሪክ ይመሰክራል። የሰው ልጅ ያለ አምላክ እርዳታ ደስታ የሰፈነበት ኑሮ ሊኖር እንደማይችል የሚገነዘቡ በርካታ ሰዎች ገና እንደሚኖሩ አምናለሁ።​—⁠ኤርምያስ 10:​23

አባቴ ኮምኒዝም ያመጣልናል ብሎ ያስተማረንን “እውነተኛ ሕይወት” እንዳገኝ ይመኝ እንደነበረ ብዙ ጊዜ አስታውሳለሁ። ሆኖም የሰው ልጆች ሊተማመኑበት የሚችሉት እርግጠኛና ብቸኛ ተስፋ መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ሕይወት” ብሎ የሚጠራው በአምላክ አዲስ የጽድቅ ዓለም ውስጥ የሚገኘው ሕይወት እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ለመገንዘብ ችያለሁ። (1 ጢሞቴዎስ 6:​18, 19) እንዲህ የምልበት ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በሕይወታቸው ሥራ ላይ ለማዋል ልባዊ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች የኃጢአትና የሰብዓዊ አለፍጽምና ተገዥዎች ቢሆኑም እንኳ አስደናቂ በሆነ ሰላም አብረው ለመኖር መቻላቸውን በማየቴ ነው። አንድነታቸውን ለማናጋት ወይም ከአምላካቸው ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለመበጠስ የተደረጉትን ሙከራዎች በሙሉ በአሸናፊነት ተወጥተዋል።

ይህን በይበልጥ ልገነዘብ የቻልኩት እኔና ባለቤቴ ግንቦት 19 ቀን 2001 በዩክሬይን፣ በልቮቭ አቅራቢያ የተሠራው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለይሖዋ አገልግሎት በተወሰነበት ሥነ ሥርዓት ላይ ከተገኙት እንግዶች መካከል የመሆን መብት ባገኘን ጊዜ ነበር። እዚያም ቀደም ሲል የኮምኒስት ወጣቶች ድርጅት አቅኚዎች ከነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት ችያለሁ። እነርሱም ልክ እንደ እኔ ኮምኒዝም ለመላው የሰው ዘር ሰላምና አንድነት ያመጣል ብለው ተስፋ ያደርጉ ነበር። ባሁኑ ጊዜ ከባለቤቱ ጋር በሩሲያ ቅርንጫፍ በማገልገል ላይ የሚገኘው ቭላዲሚር ግሪጎርየቭ የኮምኒስት ወጣቶች አቅኚ ነበር።

አሁን የይሖዋ ምሥክሮች አዲሱን ቅርንጫፍ ቢሯቸውን የኮምኒስት ወጣት አቅኚዎች የበጋ መንደራቸው አድርገው በሚጠቀሙበት ቦታ ላይ መሥራታቸው የሚያስገርም ነገር ነው። በቅርንጫፉ በቂ ቦታ ባለመኖሩ ሕንጻው ለይሖዋ አገልግሎት በተወሰነበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሊገኙ የቻሉት ከ35 አገሮች የመጡ 839 ሰዎች ብቻ ነበሩ። ይሁን እንጂ በማግስቱ ጧት 30, 881 የሚያክሉ ሰዎች በልቮቭ የእግር ኳስ ስታድየም ተገኝተው ባለፈው ቀን የተከናወነውን ፕሮግራም በድጋሚ አዳምጠዋል። * ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ እዚህ ሊገኙ የቻሉት ስድስት ሰዓት ያህል ተጉዘው ነበር።

እነዚህ ሁሉ አዲሱን የቅርንጫፍ ሕንጻ ለመጎብኘት የሚያስችል ዝግጅት እንደተደረገ ሲያውቁ ወዲያው ወደ ስታድየም አምጥተዋቸው በነበሩ በርካታ አውቶብሶች ላይ ተሳፈሩ። ቀትር ላይ አውቶቡሶቹ የቅርንጫፉ ሕንጻ ወደ ተሠራበት ቦታ መድረስ ጀመሩና በእግር እየተዘዋወሩ መጎብኘት ጀመሩ። እኔና ባለቤቴ ሌሊቱን እዚያው በእንግድነት የማሳለፍ መብት አግኝተን ነበር። በዚያው ዕለት ምሽት ከእነዚህ ውድ የእምነት ባልንጀሮቻችን መካከል ከ16, 000 የሚበልጡ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ወደየቤቶቻቸው ለመመለስ ለአንዳንዶቹ በጣም ረዥም የነበረውን ጉዞ ለመጀመር በየአውቶቡሶቻቸው ተሳፈሩ።

በዩክሬይንም እንደ ሌሎቹ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ሰላም የሰፈነበት አዲስ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ከኮምኒዝም የተሻለ ተስፋ የለም ብለው ያምኑ የነበሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ነበሩ። ዛሬ ግን በዩክሬይን ብቻ ስለ አምላክ መንግሥት ለሰዎች በመናገር ሥራ ላይ የተጠመዱ 120, 000 ሰዎች አሉ። በእርግጥም ኮምኒስቶች የነበርን በርካታ ሰዎች በሰው ልጆች መካከል እውነተኛ ወንድማማችነትና ሰላም ለማስፈን የሚችለው ይህ የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ አምነናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.51 ሌሎች 41, 143 የሚያክሉ ደግሞ በተመሳሳይ ሰዓት 500 ኪሎ ሜትር በሚያክል ርቀት ላይ በምትገኘው በኪዬቭ በአንድ ስታድየም ውስጥ ተሰብስበው ሕንጻው ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰነበትን ዝግጅት በድጋሚ ተከታትለዋል። በድምሩ የተሰበሰቡት 72, 024 ሰዎች ሲሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬይን ይህን በሚያክል ብዛት ሲሰበሰቡ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገና በአሥር ዓመቴ የወጣት ኮምኒስቶች አቅኚ ከሆንኩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከፔትር ጋር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዩክሬይን ቅርንጫፍ ለይሖዋ አገልግሎት በተወሰነበት ሥነ ሥርዓት ላይ ያገኘሁት የቀድሞ ኮምኒስት አቅኚ ቭላዲሚር

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከ30,000 የሚበልጡ ሰዎች ሕንጻው ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰነበትን ሥነ ሥርዓት ፕሮግራም በድጋሚ አዳምጠዋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከ16,000 የሚበልጡ ሰዎች የቅርንጫፉን ሕንጻዎች ጎብኝተዋል