በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓሣ ቆዳ የሚሠራ ጫማ

ኤል ኮሜርስዮ የተባለው የሊማ ጋዜጣ እንደዘገበው በፔሩ በሚገኙት የአንዲስ ተራራዎች ከዓሣ ቆዳ ጫማ የመሥራት አዲስ ኢንዱስትሪ ተጀምራል። ከዓሣ እርባታ ጣቢያዎች የሚገኙ የዓሣ ቆዳዎች ከታጠቡና ከጸዱ በኋላ ከተፈጥሮ በሚገኙት የማልፊያ ቅመሞች እንዲለሰልሱ ይደረጋል። ከዚያም በዘይት ከለፉ በኋላ እንደ እርድ፣ ኮክኒል ወይም አችዮት ባሉት ከተፈጥሮ የሚገኙ ቀለሞች እንዲቀልሙ ይደረጋል። እንዲህ ያለው የቆዳ አዘገጃጀት በቆዳዎቹ ላይ ያሉትን ባለ አልማዝ ቅርጾች ስለማያጠፋ ቆዳዎቹን “ለሳንቲም መያዣ ቦርሣ፣ ለገንዘብ ቦርሣ፣ ለሰዓት ማሠሪያ፣ ለሞባይል ስልክ ማህደር” መጠቀም ይቻላል። ይህን ፕሮጀክት በግንባር ቀደምትነት የመሩት የኢንዱስትሪ መሐንዲስ የሆኑት ባርባራ ሊዮን “ዋናው አስፈላጊ ነገር እንደ ክሮምየም ያሉትን ሰው ሠራሽ የማልፊያ ቅመሞች አለመጠቀም ነው። ይህም ብክለትን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ የዓሣ ቆዳ ሥነ ምህዳርን የማይጻረር ምርት እንዲሆን ያስችላል” ብለዋል።

አሁንም ከሳቅ የተሻለ መድኃኒት አልተገኘም

“በቀን አንድ ጊዜ ለአራት ሳምንታት በተከታታይ አስቂኝ ቀልድ መስማት የመንፈስ ጭንቀት የሕመም ምልክቶችን በእጅጉ እንደሚቀንስ ተደርሶበታል” ሲል የለንደኑ ዚ ኢንዲፐንደንት ዘግቧል። “በቀን ለ30 ደቂቃ ያህል በኮሜድያኖች የተዘጋጁ ክሮችን እንዲሰሙ ከታዘዙ በሽተኞች መካከል አንዳንዶቹ ከሕመማቸው ፈጽመው የዳኑ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ሕመማቸው በግማሽ ያህል ቀንሶላቸዋል።” በዩናይትድ ስቴትስ የተደረጉ ከ100 የሚበልጡ ጥናቶች ቀልድ ሰምቶ መሳቅ ጠቃሚ መሆኑን አረጋግጠዋል። የመንፈስ ጭንቀት የያዛቸው ብቻ ሳይሆኑ አለርጂ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት መዳከም፣ ካንሰርና ሩማቶይድ አርትራይተስ ያለባቸው ሳይቀር ጥሩ መሻሻል አሳይተዋል። ሳቅ ጤንነት እንደሚያሻሽል ከታወቀ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ቢሆንም እንዴት ሊያሻሽል እንደሚችል ግን እስካሁን በግልጽ አይታወቅም። ይሁን እንጂ ዶክተር ኤድ ዱንክልብላው የተባሉት ሳይኮቴራፒስት የሰጡት ማስጠንቀቂያ አለ። “የስድብና የሽሙጥ ቀልዶች መወገድ አለባቸው። ከመጠን በላይ ቀልደኛ መሆንም ጥሩ አይደለም። አለበለዚያ በሽተኛው ሕመሙ ከቁም ነገር እንዳልተቆጠረለት ሊሰማው ይችላል።”

‘ሃይማኖት ሁለተኛ ደረጃ ተሰጥቶታል’

በቅርቡ ጎልማሳ በሆኑ የብራዚል ከተማ ድሃ ኗሪዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት 67 በመቶ የሚሆኑት ካቶሊኮች እንደሆኑ ቢናገሩም በኢየሱስ፣ በማርያምና በቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ ትምህርቶች እናምናለን የሚሉት ግን ከ35 በመቶ እንደማይበልጡ ገልጧል። በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን ሄደው የሚያስቀድሱት ደግሞ ከዚህ ያነሱ ሲሆኑ እንዲያውም 30 በመቶ ብቻ ናቸው። በብራዚላውያን ጳጳሳት ብሔራዊ ጉባኤ ትእዛዝ የተካሄደው ይህ ጥናት ብዙዎች ከጋብቻ በፊት ስለሚፈጸም ወሲብ (44 በመቶ)፣ ስለ ፍቺ (59 በመቶ)፣ ፈትቶ ስለማግባት (63 በመቶ) እንዲሁም የወሊድ መቆጣጠሪያ ስለመጠቀም (73 በመቶ) ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምታስተምረው ትምህርት ጋር አይስማሙም። የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ሴቬሪኖ ቪሴንቴ እንዳሉት ቤተ ክርስቲያን የቀሳውስት ቁጥር ማነሱ፣ በብራዚል የትምህርት ሥርዓት ላይ የነበራት ሥልጣን መመናመኑ፣ ስለ መሠረተ ትምህርቶች የምትሰጠው ትምህርት ጥልቀት የሌለው መሆኑ የነበራትን ቦታ እያጣች እንድትሄድ እንዳደረጓት ተናግረዋል። “አዲሱ የካቶሊካውያን ትውልድ እውነት አንፃራዊ ነው በሚል አስተሳሰብ ተኮትኩተው ያደጉ ሲሆኑ ለሃይማኖት የሚሰጡት አስፈላጊነት ሁለተኛ ደረጃ ነው” ብለዋል።

በገዛ ቤት ውስጥ የሚያጋጥም አደጋ!

የብሪታንያ የንግድና ኢንዱስትሪ መሥሪያ ቤት ለ1999 ዓመት ባወጣው የሆስፒታል ስታትስቲክስ “በየሳምንቱ በቤት ውስጥ ባጋጠሙ አደጋዎች ምክንያት 76 ሰዎች እንደሞቱና ይህም አኃዝ በመንገድ ላይ በሚከሰት አደጋ ከሞቱት እንደሚበልጥ” የለንደን ዘ ጋርድያን ዘግቧል። በጣም ከተደጋገሙት የሞት ምክንያቶች መካከል “የእጅ መሣሪያዎች፣ ደረጃዎች፣ ምንጣፎችና የፈላ ውኃ ያለባቸው ጀበናዎች ይገኛሉ።” በየዓመቱ ከ3, 000 የሚበልጡ ሰዎች የቆሸሹ ልብሶች የተጠራቀሙበት ቅርጫት አደናቅፏቸው በመውደቅ፣ ከ10, 000 የሚበልጡ ሰዎች ካልሲያቸውን ወይም ጠባብ ሱሪያቸውን ለማጥለቅ ሲሞክሩ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት፣ ከ13, 000 የሚበልጡ አትክልቶችን ሲያዘጋጁ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ሆስፒታል ይገባሉ። ከአንድ መቶ ሺህ የሚበልጡት ጉዳቶች ከአልኮል ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ናቸው። የአደጋዎች መከላከያ ማኅበር ቃል አቀባይ “በሥራ ቦታና በመንገዶች ላይ ጠንቃቆች ነን። እቤታችን ስንሆን ግን እንዘናጋለን። የፈላ ውኃ ያለበትን ጀበና ክዳን ለመክፈት ስትሞክሩ ጀበናውን ከነፈላው ውኃ እግራችሁ ላይ ብትጥሉት ከባድ ጉዳት ሊደርስባችሁ ይችላል” ብለዋል።

የጭስ ጭጋግ ለልብ ድካም ያጋልጣል

የካናዳው ናሽናል ፖስት ጋዜጣ እንደዘገበው “ብዙዎቹን የካናዳ ከተሞች በበጋ ወራት የሚሸፍነው ጥቁር ጭጋግ በሁለት ሰዓት ጊዜ ውስጥ የልብ ድካም ሕመም ሊቀሰቅስ ይችላል።” በጭስ ጭጋግ ውስጥ በአብዛኛው ከመኪናዎች፣ ከኃይል ማመንጫዎችና ከማገዶ እንጨቶች የሚወጡ ጥቃቅንና በዐይን ሊታዩ የማይችሉ በካይ ቅንጣቶች ይኖራሉ። “እንደ ስኳር ሕመምተኞች፣ እንደልብ ታማሚዎችና እንደ አረጋውያን ባሉ ቀድሞውንም ቢሆን የልብ ድካም ምልክት ያለባቸው ሰዎች በካይ ቅንጣቶች ላሉበት ጭጋግ በተጋለጡ በሁለት ሰዓት ጊዜ ውስጥ በልብ ድካም የመያዝ ዕድላቸው በ48 በመቶ ጨምሯል” ይላል ጋዜጣው። “አደጋው በ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ 62 በመቶ ጨምሯል።” የጭስ ጭጋግ መኖሩ ማስጠንቀቂያ በሚሰጥበት ጊዜ “በተቻለ መጠን ከቤት ሳይወጡ መቆየትና የአየር ማጣሪያ መሣሪያውን ክፍት አድርጎ ማቆየት” እንደሚበጅ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሙረይ አሳስበዋል። “እነዚህ ቅንጣቶች በጣም ደቃቅ በመሆናቸው ወደ ቤት ሾልከው ቢገቡም የአየር ማጣሪያ መሣሪያው አጣርቶ ያወጣቸዋል።”

ሸለብታ ያለው ኃይል

ስለ እንቅልፍ በርካታ ጥናት ያደረጉትና የላፍባሮው ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ብሪታንያዊው ፕሮፌሰር ጂም ሆርን ከሰዓት በኋላ የሚሰማንን ድብታ ለማጥፋት “ከአሥር ደቂቃ ሸለብታ የሚበልጥ መድኃኒት እንደማይኖር” መናገራቸውን የለንደኑ ታይምስ ዘግቧል። ሆርንስ “ሸለብታ እንደማንኛውም ሕክምና ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው ገና ችግሩ እንደጀመረ ሲወሰድ ነው” ብለዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ አንዳንድ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው የሚያሸልቡባቸው አልጋዎች፣ ብርድ ልብሶች፣ ትራሶች የተዘጋጁባቸውና እንቅልፍ የሚያስወስዱ ሙዚቃዎችና በየ20 ደቂቃ የማንቂያ ደወል የሚሰማባቸው ክፍሎች አዘጋጅተዋል። ይሁን እንጂ ፕሮፌሰር ሆርን የእንቅልፉ ጊዜ ከረዘመ ለምሳሌ ያህል ለ25 ደቂቃ ከቆየ፣ ከእንቅልፍ ስትነቃ የመጫጫን ስሜት ሊሰማህ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። “ከአሥር ደቂቃ በላይ ከተኛህ ሰውነት ማታ የሆነ ይመስለውና ሙሉው የእንቅልፍ ሂደት እንዲጀምር ያደርጋል።”

ከልክ ያለፈ ውፍረትና ካንሰር

የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት እንደዘገበው “በምዕራቡ ዓለም ለማያጨሱ ሰዎች ዋነኛው ሊወገድ የሚችል የካንሰር ምክንያት ውፍረት ነው።” ለሃምሳ ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች ወፍራም ከሆኑ ክብደት መቀነስን ጨምሮ የአኗኗር ለውጥ ማድረግ አጫሽ ላልሆኑ ሰዎች በካንሰር የመያዝን ዕድል በግማሽ እንደሚቀንስ አመልክቷል። “አጫሽ ካልሆንክ የሚያሳስቡህ ሁለት ነገሮች ውፍረትና የሆድ ዕቃና የማህጸን ካንሰር መንስዔ የሆኑት ቫይረሶች ናቸው” ይላሉ የብሪታንያ ካንሰር ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ጁልያን ፔቶ። “የአመጋገብ ቁጥጥር በተደረገባቸው እንስሳት ላይ የተደረጉ ሙከራዎች ለካንሰር የመጋለጥ ዕድል በእጅጉ ቀንሶ መገኘቱን አመልክተዋል።” በሕክምና መመዘኛዎች መሠረት አንድ ሰው ወፍራም ነው የሚባለው ለዕድሜው፣ ለጾታው፣ ለቁመቱና ለቁመናው ትክክል ነው ተብሎ ከሚታሰበው የሰውነት ክብደት 20 በመቶ በልጦ ሲገኝ ነው።

ከመጋባት በፊት አብሮ መኖር

“ከመጋባታቸው በፊት አብረው ይኖሩ የነበሩ ወላጆች በፍቺ የመለያየታቸው ዕድል ከሌሎቹ በእጥፍ ይበልጣል” ሲል የካናዳው ናሽናል ፖስት ዘግቧል። ስታትስቲክስ ካናዳ አድርጎት የነበረው ጥናት ተባባሪ አዘጋጅ የሆኑት ሄዘር ጁቢ እንዳሉት ተመራማሪዎች ልጅ መውለድ ወላጆችን የሚያስተሳስር መስሏቸው ነበር። “ይሁን እንጂ ሳይጋቡ አብረው ለመኖር ቅር ያላላቸው ባልና ሚስቶች ለመፋታትም ይበልጥ ፈጣኖች ሆነው ተኝተዋል” ሲሉ ገልጸዋል። አጥኚዎቹ ከመጋባታቸው በፊት አብረው ይኖሩ ከነበሩ ባልና ሚስቶች መካከል 25.4 በመቶ የሚሆኑት የተለያዩ ሲሆን ከመጋባታቸው በፊት አብረው ካልኖሩት መካከል ግን የተለያዩት 13.6 በመቶ የሚሆኑት ናቸው። “ሳይጋቡ አብረው ለመኖር የማይከብዳቸው ሰዎች የጋብቻን ቃል ኪዳን አክብደው የማይመለከቱ ሊሆኑ ስለሚችሉ አብረው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሚመሰርቱት ጋብቻ በቀላሉ የሚፈርስ ሆኖ ተገኝቷል” ይላሉ ጁቢ።

ወጣት ጠጪዎች

ሱድ ዶቸ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ “በአውሮፓ የሚሰክሩ ወጣቶች የዕድሜ ጣሪያ እያነሰ ከመሄዱም በላይ ብዛታቸውም ጨምሯል” ሲል ዘግቧል። ይህ አስደንጋጭ አዝማሚያ ለአውሮፓ ህብረት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሮች ቀርቦ ነበር። ችግሩ ምን ያህል የከፋ ነው? በ1998 የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአንዳንድ አገሮች በ15 ዓመት ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ወንድ ልጆች መካከል 40 እና 50 በመቶ የሚሆኑት አዘውትረው ቢራ የሚጠጡ ሲሆን በዚሁ የዕድሜ ክልል የሚገኙ የእንግሊዝ፣ የስኮትላንድና የዌልስ ልጃገረዶች በወይን ጠጅና በጠንካራ የአልኮል መጠጦች ፍጆታቸው ወንዶቹን በልጠው ተገኝተዋል። በዴንማርክ፣ በፊንላንድና በብሪታንያ በ15 ዓመት ዕድሜ ክልል ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከአንድ ጊዜ በላይ በጣም ሰክረው ያውቃሉ። በአውሮፓ ኅብረት አገሮች ከ15 እስከ 29 ዓመት ዕድሜ ለሚገኙ በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መሞት ሰበቡ አልኮል ነው። የሚኒስትሮቹ ምክር ቤት ወጣቶች መጠጥ መጠጣት የሚያስከትለውን ጉዳት የሚያሳውቅ ስለ አልኮል ትምህርት እንዲሰጥ ሐሳብ አቅርበዋል።