በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመላእክት አለቃ ሚካኤል ማን ነው?

የመላእክት አለቃ ሚካኤል ማን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የመላእክት አለቃ ሚካኤል ማን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ መላእክታዊ ፍጥረታት አሉ። (ዳንኤል 7:9, 10፤ ራእይ 5:11) ከአምላክ ጎን በታማኝነት ስለቆሙ መላእክት የሚናገሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ መግለጫዎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት መካከል በስም የተጠቀሱት ሁለቱ ብቻ ናቸው። አንደኛው መላእኩ ገብርኤል ሲሆን እርሱም 600 በሚያክሉ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከይሖዋ የተቀበለውን መልእክት ለሦስት የተለያዩ ሰዎች አድርሷል። (ዳንኤል 9:20-22፤ ሉቃስ 1:8-19, 26-28) ሌላው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስም የተጠቀሰው መልአክ ሚካኤል ነው።

በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ሚካኤል ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው መልአክ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ሚካኤል ስለ ይሖዋ ሕዝቦች ከክፉ መናፍስት ጋር እንደተዋጋ ተገልጿል። (ዳንኤል 10:13፤ 12:1) በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በይሁዳ ደብዳቤ ላይ ስለ ሙሴ ሥጋ በተነሳ ክርክር ሚካኤል ከሰይጣን ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጧል። (ይሁዳ 9) የራእይ መጽሐፍ ሚካኤል ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር እንደተዋጋና ከሰማይ አውጥቶ እንደጣላቸው ይገልጻል። (ራእይ 12:7-9) በአምላክ ጠላቶች ላይ የዚህን ያህል ታላቅ ኃይልና ሥልጣን እንዳለው ተደርጎ የተገለጸ ሌላ አንድም መልአክ የለም። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ሚካኤልን “የመላእክት አለቃ” ብሎ መጥራቱ ምንም አያስደንቅም፤ “አለቃ” የሚለው ቃል “መሪ” ወይም “ዋና” የሚል ትርጉም አለው።

የሚካኤልን ማንነት በተመለከተ የተነሳው ውዝግብ

የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶችም ሆኑ የአይሁድ እምነት እንዲሁም እስልምና መላእክትን በተመለከተ እርስ በእርስ የሚጋጩ ሐሳቦች አሏቸው። አንዳንዶቹ ማብራሪያዎች ድፍንፍን ያሉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንዲህ ይላል:- “የሁሉም የበላይ የሆነ አንድ መልአክ እና/ወይም (ባብዛኛው አራት ወይም ሰባት) የመላእክት አለቆችን ያቀፈ አንድ አነስተኛ ቡድን ይኖር ይሆናል።” ዚ ኢምፔርያል ባይብል ዲክሽነሪ እንደሚለው ከሆነ ደግሞ ሚካኤል “ከሰው በላይ ኃይል ያለው አካል መጠሪያ ሲሆን ስለ ማንነቱም እርስ በርስ የሚጋጩ ሁለት አጠቃላይ አመለካከቶች ተሰንዝረዋል፤ እነሱም ወይ የአምላክ ልጅ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው አሊያም ከሰባቱ የመላእክት አለቆች መካከል አንዱ ነው የሚሉ ናቸው።”

በአይሁዳውያን ወግ መሠረት እነዚህ ሰባቱ የመላእክት አለቆች ገብርኤል፣ ጀርምኤል፣ ሚካኤል፣ ራጉኤል፣ ሩፋኤል፣ ሰራኤል እና ኡራኤል ናቸው። በሌላ በኩል እስልምና ጂብሪል፣ ሚካል፣ ኢዝራይል እና ኢስራፊል የተባሉ አራት የመላእክት አለቆች እንዳሉ ያምናል። የካቶሊክ እምነትም ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል እና ኡራኤል በሚባሉ አራት የመላእክት አለቆች ያምናል። መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? በርካታ የመላእክት አለቆች አሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚካኤል በቀር የመላእክት አለቃ እንደሆነ ተደርጎ የተጠቀሰ ሌላ መልአክ ካለመኖሩም በላይ ቅዱሳን ጽሑፎች “የመላእክት አለቃ” የሚለውን ሐረግ በብዙ ቁጥር አይጠቀሙበትም። መጽሐፍ ቅዱስ ሚካኤልን “የመላእክት አለቃ የሆነው” ብሎ መጥራቱ ይህ መጠሪያ የሚገባው እሱ ብቻ መሆኑን ያመለክታል። (ይሁዳ 9 አ.መ.ት) እንግዲያው ይሖዋ አምላክ ከሰማያዊ ፍጥረታቱ መካከል በሁሉም መላእክት ላይ ሙሉ ሥልጣን የሰጠው ለአንዱ ብቻ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይሆናል።

ከራሱ ከፈጣሪ ሌላ መላእክት እንደሚገዙለት የተነገረለት አንድ ታማኝ አካል ብቻ ሲሆን እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ማቴዎስ 13:41፤ 16:27፤ 24:31) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ “ጌታ ኢየሱስ” እና ስለ “ሥልጣኑ መላእክት” ለይቶ ተናግሯል። (2 ተሰሎንቄ 1:​6, 7) ጴጥሮስ ደግሞ ትንሣኤ ስላገኘው ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።”​—⁠1 ጴጥሮስ 3:22

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ኢየሱስ እንደሆነ በቀጥታ የሚናገር ሐሳብ ባይኖርም ኢየሱስ የመላእክት አለቅነት ሥልጣን እንዳለው የሚናገር አንድ ጥቅስ አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፣ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ”። (1 ተሰሎንቄ 4:16) በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ የአምላክ መሲሐዊ ንጉሥ በመሆን ሥልጣኑን እንደያዘ ተደርጎ ተገልጿል። ይሁን እንጂ የሚናገረው ‘በመላእክት አለቃ ድምፅ’ ነው። ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለውም ልብ በል።

ኢየሱስ ሰው ሆኖ ምድር በነበረበት ጊዜ በርካታ ትንሣኤዎችን ፈጽሟል። ይህንንም ሲያደርግ ድምፁን የትእዛዝ ጥሪ ለማሰማት ተጠቅሞበታል። ለምሳሌ ያህል፣ በናይን ከተማ የአንዲትን መበለት ልጅ ከሞት ሲያስነሳ “አንተ ጐበዝ፣ እልሃለሁ፣ ተነሣ” ብሎታል። (ሉቃስ 7:14, 15) ቆይቶም ጓደኛውን አልዓዛርን ከማስነሳቱ በፊት ኢየሱስ “በታላቅ ድምፅ:- አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ።” (ዮሐንስ 11:43) ይሁን እንጂ በእነዚህ ጊዜያት ኢየሱስ ያሰማው ድምፅ የፍጹም ሰው ድምፅ ነበር።

ኢየሱስ ራሱ ከሞት ከተነሳ በኋላ መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ “ከፍ” ያለ ቦታ አግኝቷል። (ፊልጵስዩስ 2:9) አሁን ሰው ስላልሆነ የመላእክት አለቃ ድምፅ አለው። ስለዚህ ‘በክርስቶስ የሞቱትን’ ለሰማያዊ ሕይወት ለማስነሳት የአምላክ መለከት ሲነፋ ኢየሱስ “ትእዛዝ” አሰምቷል፤ በዚህ ጊዜ ግን የተናገረው ‘በመላእክት አለቃ ድምፅ’ ነው። ‘በመላእክት አለቃ ድምፅ’ የሚናገረው የመላእክት አለቃ ብቻ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።

እርግጥ ነው እንደ ሱራፌሎችና ኪሩቤሎች ያሉ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው መላእክትም አሉ። (ዘፍጥረት 3:24፤ ኢሳይያስ 6:2) ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች የሁሉም መላእክት የበላይ ማለትም የመላእክት አለቃ ሚካኤል እንደሆነ የሚናገሩለት ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።