የሜዳ አህያ—ለማዳ ያልሆነው የአፍሪካ ፈረስ
የሜዳ አህያ—ለማዳ ያልሆነው የአፍሪካ ፈረስ
አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በሺህ የሚቆጠሩ የሜዳ አህዮች በተንጣለለው የአፍሪካ መስክ ላይ እንደ ልብ ይፈነጫሉ። ባለ ሽንትር ዳሌያቸውን ወደ ላይ አቅንተው፣ ዘንፈል ብሎ የወረደውን ጋማቸውን ከሶምሶማ ግልቢያቸው ጋር አስማምተው ጎንበስ ቀና እያደረጉ ይሮጣሉ። ፀሐይ ያከረረውን መሬት የሚጎደፍረው የኮቴያቸው ድምፅ ከሩቅ ይሰማል። ከኋላቸው ቦለል እያለ የሚወጣው የቀይ አቧራ ጉም ከብዙ ርቀት ይታያል። ከዚህ ተመለሱ የሚላቸው ሳይኖር እንደልባቸው በነጻነት ይሮጣሉ።
ወዲያው አንድ የማይታይ ምልክት የተሰጣቸው ይመስል ዝግ ካሉ በኋላ ቀጥ ብለው ይቆማሉ። ችምችም ባለው ጠንካራ ጥርሳቸው የደረቀውን ሣር ጋጥ ጋጥ ያደርጋሉ። መንጋው አካባቢውን በንቃት ይከታተላል። በየጊዜው ቀና ብሎ በመመልከት ያዳምጣል፣ አየሩን ያነፈንፋል። ከሩቅ የሚነፍሰው ነፋስ ይዞት የመጣው የአንድ አንበሳ ግሳት ተሰማቸውና በተጠንቀቅ ቆሙ። ድምፁን በሚገባ ያውቁታል። የሜዳ አህዮቹ ጆሮአቸውን ቀስረውና ነጭተው በአፋቸው የያዙትን ሣር ማኘክ ትተው የሚያስገመግመው ድምፅ ወደመጣበት አቅጣጫ ተመለከቱ። የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ካረጋገጡ በኋላ አንገታቸውን ጎንበስ አድርገው ሣራቸውን መጋጥ ቀጠሉ።
የቀኑ ፀሐይ እየከረር ሲመጣ እንደገና ጉዟቸውን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ እነዚህ ለማዳ ያልሆኑ ፈረሶች የውኃ ሽታ እያነፈነፉ ወንዝ ፍለጋ ይጓዛሉ። በወንዙ ዳርቻ ላይ ይቆሙና በቀስታ የሚወርደውን ድፍርስ ውኃ እየተመለከቱ ደረቁን አቧራ እየጎደፈሩ ያናፋሉ። ፀጥ ብሎ ከሚፈሰው ወንዝ ግርጌ አደጋ ይኖር ይሆናል ብለው ስለሚጠረጥሩ ቆም ይላሉ። ቢሆንም የያዛቸው ጥም ከባድ ስለሆነ አንዳንዶቹ ተጋፍተው ወደፊት ያመራሉ። አንዱ በድፍረት ወደፊት ሲሄድ ሁሉም ተንጋግተው ወደ ወንዙ ጠርዝ ይሮጣሉ። ተራ በተራ እስኪበቃቸው ከጠጡ በኋላ ወደተንጣለለው መስካቸው ይመለሳሉ።
መሸት ሲል መንጋው ቀስ ብሎ እያዘገመ በረዣዥሙ ሣር ውስጥ ያልፋል። በቀይ ቀለም የጋመችው ፀሐይ ልትጠልቅ ስትል የምትጥልባቸው ጥላ ከአፍሪካ ዱር ጋር ተነጻጽሮ ሲታይ በጣም ያምራል።
ባለሽንትሮችና ማህበራዊ ኑሮ ወዳዶች
የሜዳ አህዮች የሚያከናውኗቸው የየዕለት ተግባራት አንድ ዓይነት ናቸው። ምግብና ውኃ ፍለጋ ስለሚዘዋወሩ ሁልጊዜ በጉዞ ላይ ናቸው። የሜዳ አህዮች በገላጣ መስኮች ላይ ሲግጡ ለሚያያቸው ንጹሕና ወፋፍራም ናቸው፣ በባለ ሽንትር ቆዳ የተሸፈነ ፈርጠም ያለ ገላ አላቸው። የሜዳ አህያ ሽንትሮች የተለያዩ በመሆናቸው የሚመሳሰል አንድም ሽንትር እንደሌለ የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ነጭና ጥቁር ሽንትራቸው ከሌሎቹ የዱር እንስሳት የተለዩ ሆነው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል። ቢሆንም መልካቸው ከማማሩም በላይ ገና ካልተገራው የአፍሪካ ምድር ጋር በእጅጉ ይስማማል።
የሜዳ አህዮች ማኅበራዊ ኑሮ ወዳዶች ናቸው። እያንዳንዱ የሜዳ አህያ ከመንጋው ጋር ለዕድሜ ልክ የሚጸና ትስስር ይመሠርታል። በአንድ ትልቅ መንጋ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ እንስሳት ቢኖሩም እያንዳንዳቸው በርካታ ባዝራዎችና አንድ አውራ በሚገኝባቸው በርካታ ቤተሰቦች ይከፋፈላል። ይህ ትንሽ የቤተሰብ አሃድ አባሎቹን በየማዕረግ በመለያየት ሥርዓት ያስከብራል። የቤተሰቡን እንቅስቃሴዎች የምትወስነው የበላይነት ያላት እንስት የሜዳ አህያ ናት። ከፊት ትቀድምና ሌሎቹ ባዝራዎችና ውርንጭላዎቻቸው እንደየደረጃቸው ተከታትለው በአንድ መስመር ይጓዛሉ። የመጨረሻው ተቆጣጣሪ ግን አውራው የሜዳ አህያ ነው። ቤተሰቡ መንገዱን እንዲቀይር ከፈለገ ፊት ሆና ወደምትመራው ባዝራ ይጠጋና ወደ አዲሱ አቅጣጫ ጎሸም ያደርጋታል።
የሜዳ አህዮች ገላቸውን ማሰማመር ይወዳሉ። አንዳቸው የሌላውን ጀርባ፣ ትከሻና ዳሌ ሲልሱና ሲያክኩ ይታያሉ። በእያንዳንዱ እንስሳ መካከል ያለውን ትስስር የሚያጠነክረው አንዳቸው የሌላውን ገላ ማሰማመራቸው ሳይሆን አይቀርም። ይህም የሚጀምረው ግልገሎቹ ገና የጥቂት ቀናት ዕድሜ እያላቸው ነው። የሜዳ አህዮች የሚያክላቸው የቤተሰብ አባል በማያገኙበት ጊዜ መሬት ላይ በመንከባለል ወይም ከዛፍ ወይም ከጉንዳን ኩይሳ ወይም ከማይነቃነቅ ከማንኛውም ነገር ጋር በመታከክ የመታከክ ፍላጎታቸውን ይወጣሉ።
ለመኖር የሚደረገው ትግል
የሜዳ አህያ ሕይወት ለብዙ አደጋዎች የተጋለጠ ነው። አንበሶች፣ ተኩላዎች፣ ጅቦች፣ ነብሮችና አዞዎች 250 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን የሜዳ አህያ አድነው ይቀራመታሉ። የሜዳ አህያ በሰዓት እስከ 55 ኪሎ ሜትር መሮጥ ይችላል። ቢሆንም አድፍጠው በድንገት ጉብ በሚል አዳኝ አራዊት መያዙ አይቀርም። አንበሶች ደፈጣ አድርገው ይጠባበቃሉ፤ አዞዎች በደፈረሰ ወንዝ ውስጥ ተሰውረው ያደባሉ፤ ነብሮች ደግሞ ጨለማን ተገን አድርገው ያድናሉ።
የሜዳ አህያ ራሱን ሊከላከል የሚችለው ንቁ በመሆንና የመንጋው አባላት በሚያደርጉት ጥበቃ ነው። ማታ፣ ማታ አብዛኞቹ እንቅልፍ ሲተኙ አንዳንዶቹ ነቅተው እያዳመጡ ዘብ ይጠብቃሉ። አንድ የሜዳ አህያ አዳኝ አውሬ እንደመጣ ካየ መላውን መንጋ የሚቀሰቅስ ድምፅ ያሰማል። አብዛኛውን ጊዜ አንድ የመንጋ አባል ታምሞ ወይም አርጅቶ ከሌሎቹ እኩል መጓዝ
በሚያቅተው ጊዜ አገግሞ እኩል መጓዝ እስከሚችል ድረስ ሌሎቹ ቀስ ብለው አብረውት ይጓዛሉ ወይም ከመንጋው ጋር እስኪቀላቀል ድረስ ቆመው ይጠብቁታል። አደገኛ ሁኔታ ከፊት ለፊት ፈጥጦ በሚመጣበት ጊዜ አውራው የሜዳ አህያ በድፍረት በአዳኙና በባዝራዎቹ መካከል ቆሞ ጠላቱን እየተናከሰና እየተራገጠ መንጋው የሚያመልጥበት ጊዜ እንዲያገኝ ያደርጋል።የተፈጥሮ ተመራማሪ የሆኑት ሁጎ ቫን ላቪክ ለዚህ የቤተሰብ ትስስር ምሳሌ የሚሆን አፍሪካ በሚገኘው በሴሬንጌቲ ሜዳ የተከሰተ ሁኔታ ተመልክተዋል። አንድ የተኩላዎች መንጋ አንድ የሜዳ አህዮችን መንጋ እንዴት እንዳባረረ ሲተርኩ ተኩላዎቹ አንዲት ሴት የሜዳ አህያና ግልገልዋን እንዲሁም አንድ ሌላ ዓመት የሞላው ውርንጭላ ከመንጋው መነጠል እንደቻሉ ይናገራሉ። ሌሎቹ የሜዳ አህዮች ጋልበው ሲያመልጡ እናቲቱና የአንድ ዓመቱ ውርንጭላ ተኩላዎቹን በድፍረት ተከላከሉ። ወዲያው ተኩላዎቹ በጣም እያየሉ ሲመጡ ባዝራዋና የአንድ ዓመቱ ውርንጭላ መድከም ጀመሩ። መጨረሻቸው የቀረበ መስሎ ታየ። ቫን ላቪክ ተስፋ ቢስ መስሎ የታየውን ትርዒት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “በድንገት መሬቱ ሲነቃነቅ ተሰማኝና ዙሪያዬን ስመለከት አሥር የሜዳ አህዮች በፍጥነት እየጋለቡ ሲመጡ አየሁ። ወዲያው ባዝራይቱንና ሁለቱን ግልገሎች ከብበው ፊታቸውን እያዞሩ በመከላከል ወደመጡበት አቅጣጫ መጋለብ ጀመሩ። ተኩላዎቹ 50 ሜትር ያህል ካባረሯቸው በኋላ መንጋውን ሰንጥቀው መግባት ባለመቻላቸው ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ።”
ልጆች ማሳደግ
አዲስ ግልገል ሲወለድ የምትጠብቀው እንስቷ የሜዳ አህያ ስትሆን መጀመሪያ
ላይ ከሌሎቹ መንጋዎች ነጥላ ትጠብቀዋለች። ተነጥለው በሚቆዩበት በዚህ ወቅት በእናትና ልጅ መካከል ጠንካራ ትስስር ይፈጠራል። ግልገሉ የእናቱን የተለየ የነጭና የጥቁር ሽንትር ቅንብርና አቀማመጥ ያጠናል። ከዚያ በኋላ የእናቱን የጥሪ ድምፅ፣ ጠረንና ሽንትር ለይቶ ስለሚያውቅ ማንኛዋንም ሌላ እንስት አይቀበልም።የሜዳ አህያ ግልገሎች ገና እንደተወለዱ የወላጆቻቸው ዓይነት ጥቁርና ነጭ ሽንትር አይኖራቸውም። ሽንትራቸው ቀላ ያለ ቡናማ መልክ ያለው ሲሆን ዕድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ ይጠቁራል። በትልቁ መንጋ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቤተሰቦች ግልገሎች አንድ ላይ ተሰባስበው ይጫወታሉ። እየተሯሯጡ አንዳቸው ሌላውን ያባርራሉ። እየተራገጡና እየተሯሯጡ በትላልቆቹ መካከል ሲያልፉ አንዳንድ ጊዜ ትላልቆቹም አብረዋቸው መጫወት ይጀምራሉ። ግልገሎቹ በቀጫጭን እግሮቻቸው እየሮጡ ወፎችንና ትናንሽ እንስሳትን በማባረር ይጫወታሉ። ረዣዥምና ቀጫጭን እግሮች፣ ትላልቅ ጥቁር ዐይኖችና የሚያብረቀርቅ ፀጉራም ጀርባ ያሏቸው የሜዳ አህያ ግልገሎች በጣም ያምራሉ።
ለማዳ ያልሆኑና የሚያስደንቁ
ዛሬም የሜዳ አህያ መንጋዎች በተንጣለሉት የአፍሪካ መስኮች እንደልባቸው ሲጋልቡና ሲሯሯጡ ማየት ይቻላል። በጣም የሚያስደንቅ ትዕይንት ነው።
አንዱ ከሌላው የማይመሳሰል ነጭና ጥቁር ሽንትር ያለው፣ ለቤተሰቡ ሙት የሆነውና እንደልቡ በነጻነት የሚቦርቀው የሜዳ አህያ በእርግጥም በጣም አስደናቂና ባለ ታላቅ ግርማ እንስሳ መሆኑን ማን ሊክድ ይችላል? እንደዚህ ስላለው እንስሳ ማወቅ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ቀርቦ ለነበረው “ለሜዳ አህያ ነጻነት የሰጠው ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ያስገኛል። (ኢዮብ 39:5 NW ) መልሱ ግልጽ ነው። የሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሜዳ አህያ ሽንትር የኖረው ለምንድን ነው?
በአዝጋሚ ለውጥ የሚያምኑ ሰዎች የሜዳ አህያ ሽንትር ሊኖረው የቻለው ለምን እንደሆነ ምክንያት መስጠት ያስቸግራቸዋል። አንዳንዶች ለማስጠንቀቂያነት ያገለግላል የሚል ሐሳብ አላቸው። ይሁን እንጂ አንበሶችም ሆኑ ሌሎች ትላልቅ አዳኝ አራዊት በሜዳ አህያዎች ሽንትር ቅንጣት ያህል እንደማይደነግጡ የታወቀ ነው።
ሌሎች ደግሞ ሽንትሮቹ ተባዕቱና እንስቷ የሜዳ አህያ እንዲሳሳቡ ያስችላል የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም የሜዳ አህዮች ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ ሽንትር ስላላቸው ይህ ሐሳብ የሚመስል ነገር አይደለም።
ሌላው መላ ምት ደግሞ ጥቁርና ነጭ ሽንትር ሊኖራቸው የቻለው የአፍሪካን ሐሩር ለመቋቋም እንዲችሉ ነው ይላል። እንዲህ ከሆነ ሌሎች እንስሳትና አራዊት ሽንትር ያልኖራቸው ለምንድን ነው?
ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ሌላ መላ ምት ደግሞ የሜዳ አህዮች በአዝጋሚ ለውጥ አማካኝነት ሽንትር የኖራቸው ለመሰወሪያ ስለሚያገለግላቸው ነው ይላል። የአፍሪካ ፀሐይ እየከረረ ሲሄድ የሜዳ አህዮች ገጽ ስለሚያጭበረብር ከርቀት አጣርቶ ለማየት አስቸጋሪ እንዲሆን እንደሚያደርገው ሳይንቲስቶች ተገንዝበዋል። ይሁን እንጂ የሜዳ አህያ ዋነኛ ጠላት የሆነው አንበሳ የሚያድነው በቅርበት አድፍጦ ስለሆነ ከርቀት ለመታየት አለመቻላቸው የሚጠቅማቸው ነገር አይኖርም።
በተጨማሪም የሜዳ አህዮች ከአደጋ ለማምለጥ በሚጋልቡበት ጊዜ ሽንትራቸው የሚፈጥረው ትርምስ አዳኝ አንበሶቹ በማደናገር በአንድ የተወሰነ የሜዳ አህያ ላይ እንዳያተኩሩ ይከለክላቸዋል ተብሎ ይታሰባል። ሆኖም በዱር አራዊት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንዳረጋገጡት አንበሶች የሜዳ አህዮችን በሚያድኑበት ጊዜ ከሌሎች ታዳኝ እንስሶች የተለየ ምንም ችግር አይገጥማቸውም።
ይበልጥ ግራ የሚያጋባው ደግሞ ሽንትሮቹ ለሜዳ አህዮች ችግር ፈጣሪ የሚሆኑባቸው ጊዜያት መኖራቸው ነው። የሜዳ አህዮች ሌሊት ሜዳ ላይ ሆነው የጨረቃ ብርሃን በሚያርፍባቸው ጊዜ ሽንትሮቻቸው አንድ ዓይነት ቀለም ካላቸው እንስሳት ይበልጥ ደምቀው ይታያሉ። አንበሶች አብዛኛውን ጊዜ የሚያድኑት በማታ ስለሆነ የሜዳ አህዮች በይበልጥ ለአደጋ የተጋለጡ ይሆናሉ።
ታዲያ የሜዳ አህዮች ሽንትራቸውን ያገኙት ከየት ነው? ይህን ለመረዳት የሚያስችለን ቁልፍ “የእግዚአብሔር እጅ ይህን [አ]ደረገ” በሚለው ቃል ውስጥ ይገኛል። (ኢዮብ 12:9) አዎን፣ የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ ሊገነዘበው ባይችልም እንኳ ፈጣሪ የምድርን ፍጥረታት ለይተው የሚያሳውቋቸውን የተለያዩ ባሕርያትና ችሎታዎች አላብሶ ፈጥሯቸዋል። የሕያዋን ፍጥረታት አስደናቂ አሠራር ለሌላም ዓላማ ያገለግላል። ለሰው ልጆች ልብ ተድላ፣ ፍስሐና ደስታ ያስገኛል። እንዲያውም በዘመናችን የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በፍጥረታት ውበት ተማርከው በጥንት ዘመን እንደነበረው እንደ ዳዊት ተሰምቷቸዋል። “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች።”—መዝሙር 104:24