በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሠርግ ቀን አድካሚ ቢሆንም ያስደስታል

የሠርግ ቀን አድካሚ ቢሆንም ያስደስታል

የሠርግ ቀን አድካሚ ቢሆንም ያስደስታል

የመጀመሪያውን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ያስፈ ጸመው ከማንም ይበልጥ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ የሚያውቀው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። ጋብቻን የመሠረተው ትዳር የሰብዓዊው ኅብረተሰብ መሠረት እንዲሆን ነበር። (ዘፍጥረት 2:​18-​24) ስለዚህ ሠርግ ለማዘጋጀት በምናስብበት ጊዜ በመንፈስ በተጻፈው በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መመሪያ ሆነው ሊያገለግሉን የሚችሉ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶች እናገኛለን።

ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ክርስቲያኖች ‘የቄሣርን ለቄሣር ማስረከብ እንዳለባቸው’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:​21) ስለዚህ ለአገሩ ሕግ መታዘዝ አለባቸው ማለት ነው። ሕጋዊ ብቃቶችን አሟልቶ የተመሠረተ ጋብቻ የተጋቢዎቹን መብቶችና ግዴታዎች ያስጠብቃል። ልጆች (መተዳደሪያንና ትምህርትን ጨምሮ) የሚያስፈልጓቸው ነገሮች እንዲሟሉላቸውና የውርስ መብቶች እንዲጠበቁ ያደርጋል። በተጨማሪም የቤተሰብ አባላት ግፍ እንዳይፈጸምባቸውና ጉልበታቸው አላግባብ እንዳይበዘበዝ ጥበቃ የሚያደርጉ ሕጎችም አሉ። *

ዝግጅቱ

አንድ ወንድና ሴት ለመጋባት ከቆረጡና ጋብቻውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ሕግና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲሁም ከአገሩ ሕጎች ጋር መስማማት እንደሚኖርበት ከተወሰነ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ምን ተግባራዊ ነገሮች ይኖራሉ? ከእነዚህ ውስጥ ጋብቻው የሚፈጸምበት ቀንና የጋብቻው ሥነ ሥርዓት ዓይነት ይገኙበታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የተጻፈ አንድ መጽሐፍ “ተጋቢዎቹ የሚፈልጉትና ወላጆቻቸው የሚፈልጉት ይለያይና ከራሳቸው ፍላጎትና ከቤተሰቦቻቸው ወግና ልማድ የትኛውን እንደሚመርጡ ይቸገሩ ይሆናል” ይላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ሲያጋጥም ምን ማድረግ ይቻላል? “ዘዴኛ ሆኖ ከማዳመጥ፣ ችግሩን ተወያይቶ ከመፍታትና እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሐሳቦችን ለማቻቻል ከመጣር የቀለለ አጭር መፍትሔ የለም። ለሁሉም ቀላል የማይባል ስሜታዊ ጫና የሚያስከትል ሁኔታ በመሆኑ አርቆ ተመልካች መሆንና የሌላውን አስተሳሰብ ለመረዳት መሞከር ዝግጅቱን በማቅለል ረገድ የሚኖረው ድርሻ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።”​—⁠ዘ ኮምፕሊት ዌድንግ ኦርጋናይዘር ኤንድ ሪከርድ

አፍቃሪ ወላጆች የሠርጉ ቀን የተሳካ እንዲሆን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በቀላሉ የማይታይ ቢሆንም የራሳቸውን አመለካከት በሙሽሮቹ ላይ እንዲጭኑ የሚገፋፋቸውን ፍላጎት መቃወም ይኖርባቸዋል። በሌላው በኩል ደግሞ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያደርጉት ሙሽሮቹ ቢሆኑም በቅን አሳቢነት የሚሰጣቸውን ምክር ማዳመጥ ይገባቸዋል። ተጋቢዎቹ የትኞቹን ምክሮች እንደሚቀበሉና እንደማይቀበሉ በሚወስኑበት ጊዜ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ቢያስታውሱ ጥሩ ይሆናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​23, 24

የሠርጉ ዝግጅት የጥሪ ወረቀቶችን ከመላክ አንስቶ ድግሱን እስከማሰናዳት የሚደርሱ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ያጠቃልላል። ኤች ባውማን ማሬጅ ፎር ሞደርንስ በተባለው መጽሐፋቸው “ዝግጅቱ ይበልጥ ሥርዓታማ በሆነና አርቆ ተመልካችነትና ጥሩ እቅድ የታከለበት በሆነ መጠን የሚጠይቀው ድካምና ውጥረት የቀነሰ ይሆናል” ብለዋል። በመቀጠልም “ሁሉ ነገር በተመቻቸበት ሁኔታ እንኳን ድካም መኖሩ ስለማይቀር ማንኛውንም አድካሚ ሁኔታ ለመቀነስ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ተገቢ ነው” ይላሉ።

መላላክ የሚጠይቁ ሁኔታዎችና መስተናገድ የሚኖርባቸው እንግዶች ይኖራሉ። በዚህ ረገድ ሊረዱ የሚችሉ ወዳጆች ወይም የቤተሰብ አባሎች ይኖራሉ? ሙሽራው ወይም ሙሽራይቱ የግድ መሠራት የማይኖርባቸውና ለሌላ ሰው ሊሰጡ የሚችሉ ሥራዎች ይኖራሉ?

ወጪዎቹ

ምክንያታዊ የሆነ ባጀት ማውጣት አስፈላጊ ነው። ተጋቢዎቹ ወይም የተጋቢዎቹ ወላጆች ዕዳ ገብተው ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሠርግ እንዲደግሱ መጠበቅ ምክንያታዊም ፍቅራዊም አይሆንም። ድል ያለ ሠርግ ለመደገስ አቅም ያላቸውም ቢሆኑ ሠርጋቸውን ልከኛ ለማድረግ መርጠዋል። ያም ሆነ ይህ አንዳንድ ተጋቢዎች ያጋጥመናል ብለው ለሚገምቷቸውና በትክክል ላጋጠሟቸው ወጪዎች አስቀድመው ዝርዝር ማዘጋጀታቸው ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በተጨማሪም መዘጋጀት ለሚኖርባቸው ነገሮች የቀን ገደብ ማውጣትና መዝግቦ መያዝ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የተቆረጡትን የቀጠሮ ቀናት በቃል ለመያዝ መሞከር ውጥረት ሊያስከትል ይችላል።

የሠርጉ ዝግጅት ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል? ዋጋዎች ከአገር አገር የሚለያዩ ቢሆንም የትም ኖርክ የት ‘ላቀድናቸው ነገሮች ሁሉ የሚበቃ ገንዘብ አለን? በእርግጥ አስፈላጊ ናቸው?’ ብለህ ራስህን ብትጠይቅ ጥሩ ይሆናል። ቲና የተባለች አንዲት ሙሽራ “በወቅቱ ‘የግድ አስፈላጊ’ መስሎ የታየን ነገር በኋላ ፈጽሞ የማያስፈልግ ሆኖ ተገኝቷል” ብላለች። ኢየሱስ የተናገረውን ልብ በል:- “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?” (ሉቃስ 14:​28) ለምትፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ የሚበቃ ገንዘብ ከሌለህ አንዳንዶቹን አስቀር። አቅሙ ያለህ ቢሆንም እንኳ ዝግጅቱን ቀለል ለማድረግ ትፈልግ ይሆናል።

በኢጣሊያ የሠርግ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ አንድ የንግድ ትርዒት አንዲት በመካከለኛ ደረጃ የምትታይ ሙሽራ ምን ያህል ገንዘብ ልታወጣ እንደምትችል የሚያሳይ የወጪ ዝርዝር አቅርቦ ነበር። መኳኳያና የፀጉር ሥራ 4, 000 ብር፤ የሙሽራ መኪና መከራያ 2, 500 ብር፤ ቪዲዮ ማንሻ 5, 000 ብር፤ የሠርጉ ቀን አልበም (ፎቶግራፎችን ሳይጨምር) ከ1, 000 እስከ 4, 000 ብር፤ አበባ ከ5, 000 ብር በላይ፤ ምሣ ወይም ራት በእያንዳንዱ ሰው ከ400 እስከ 800 ብር፤ የሙሽራ ልብስ 10, 000 ብር። ለዕለቱ የሚሰጠውን ከፍተኛ ቦታ ግምት ውስጥ ስናስገባ ለየት ያለ ነገር ለማድረግ መፈለግ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ የሚደረስበት ማንኛውም ዓይነት ውሳኔ ሚዛኑን የሳተ መሆን አይኖርበትም።

አንዳንዶች ከፍተኛ ንብረት ለሠርግ ሲከሰክሱ ሌሎቹ ደግሞ ምንም ምርጫ ስለሌላቸው ቁጥብ ለመሆን መርጠዋል። አንዲት ሙሽራ “ሁለታችንም አቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን) ስለነበርን ምንም ገንዘብ አልነበረንም። በዚህም ምክንያት አልተጨነቅንም። አማቴ ጨርቅ ገዛችና በጓደኛዋ አሰፍታ ለሠርጉ የምለብሰውን ልብስ ስጦታ አድርጋ ሰጠችኝ። የጥሪውን ወረቀት ባለቤቴ ራሱ በእጁ ሲጽፍ አንድ ክርስቲያን ወዳጃችን መኪናውን አዋሰን። ለድግሱ የሚያስፈልጉትን ምግቦች እኛ ስንገዛ ወይን ጠጁን ሌላ ሰው ሰጠን። የተቀናጣ ሠርግ አይሁን እንጂ በቂ ነበር” ብላለች። አንድ ሙሽራ እንዳለው ቤተሰቦችና ወዳጆች ተግባራዊ ድጋፍ ሲሰጡ “ወጪዎቹ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳሉ።”

ክርስቲያን ተጋቢዎች ምንም ዓይነት የገንዘብ አቅም ይኑራቸው ከልክ ያለፈ፣ ዓለማዊና የልታይ ባይነትን መንፈስ ለማስወገድ ይፈልጋሉ። (1 ዮሐንስ 2:​15-17) አንድ ሰው ሠርግን በመሰለ አስደሳች ወቅት ምክንያት ከልክ በላይ በመብላት፣ በመጠጣት ወይም አንድን ሰው ‘ተነቃፊ’ ሊያደርጉት ከሚችሉ ማናቸውም ሌሎች ነገሮች እንዲርቅ ቅዱሳን ጽሑፎች ልከኝነትን በማስመልከት የሚናገሩትን መሠረታዊ ሥርዓቶችን ቢተላለፍ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል!​—⁠ምሳሌ 23:​20, 21፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:​2

ከሌሎች የተሻለና የበለጠ ሠርግ ሊኖረኝ ይገባል የሚለውን አዝማሚያ አስወግድ። በአንድ አገር ሁለት ሙሽሮች የለበሱትን የቬሎ ተጎታች ተመልከት። አንደኛው የቬሎ ተጎታች መሐል ለመሐል ርዝመቱ 13 ሜትር የሚያክል ሲሆን ክብደቱ 220 ኪሎ ግራም ነበር። የሌላኛው ቁመት 300 ሜትር የሚያክል ርዝመት ያለው ሲሆን ዘርፉን ለመያዝ 100 ሚዜዎች አስፈልገዋል። እንደዚህ ያለውን የይታይልኝ ትርዒት ለመኮረጅ መሞከር ምክንያታዊ ሁኑ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር ይስማማል?​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​5 NW

ባሕልን መከተል የግድ አስፈላጊ ነው?

ጋብቻን የሚመለከቱ ወጎችና ልማዶች ከአገር ወደ አገር ስለሚለያዩ ስለ ሁሉም መናገር አይቻልም። ተጋቢዎች አንድን ዓይነት ባሕል ለመከተል ወይም ላለመከተል ሲወስኑ እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች ቢጠይቁ ጥሩ ይሆናል። ‘ትርጉሙ ምንድን ነው? ጥሩ ገድ ወይም ለመራባት የሚረዳ ሥርዓት ተብሎ ሙሽሮቹ ላይ ሩዝ እንደመበተን ያለ ከአጉል እምነት ጋር ተዛማጅነት ያለው ባሕል ነው? ከሐሰት ሃይማኖት ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ከተወገዙ ሌሎች ልማዶች ጋር ዝምድና ያለው ነው? ምክንያታዊነት ወይም ፍቅር የጎደለው ነው? ሌሎችን ሊያሳፍር ወይም ሊያደናቅፍ የሚችል ነው? የተጋቢዎቹን ፍላጎትና ዓላማ ጥያቄ ላይ የሚጥል ነው? ጨዋነት የጎደለው ነው?’ ከእነዚህ ነጥቦች በአንዱ ላይ እንኳን ጥርጣሬ ከኖረ እንዲህ ካለው ባሕልና ልማድ መራቅና አስፈላጊ ከሆነም ለተጋባዦቹ አስቀድሞ ማሳወቅ የተሻለ ይሆናል።

ደስታና የስሜት ግንፋሎት

በዚህ ታላቅ ቀን ከመፈንደቅ አንስቶ እስከ ማልቀስ የሚደርስ የስሜት መለወጥ ሊደርስ ይችላል። አንዲት ሙሽራ “የተሰማኝ ደስታ በጣም ታላቅ ስለነበረ በሕልም ያለሁ ይመስለኝ ነበር” ብላለች። አንድ ሙሽራ ግን “በሕይወቴ እንደዚያ ቀን መጥፎም ጥሩም ቀን አጋጥሞኝ አያውቅም። አማቶቼ የበኩር ልጃቸውን ልወስድባቸው ስለሆነ እንባቸው እንደ ጎርፍ ይወርድ ነበር። ባለቤቴም ወላጆቿ ሲያለቅሱ ስታይ መንሰቅሰቅ ጀመረች። በመጨረሻ እኔም ይህን ሁሉ መቋቋም አቅቶኝ በልቅሶ ፈነዳሁ” ብሏል።

እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ መደንገጥ አይገባም። በውጥረት ምክንያት የሚፈጠር የስሜት መለዋወጥ ነው። አንዳንድ ጊዜ በቤተሰብ ዝምድናዎች ሌላው ቀርቶ በተጋቢዎቹም ጭምር መካከል ውጥረት ቢፈጠር ሊያስደንቅ አይገባም። “አንድ ላይ ሆነው ሠርግን የሚያክል ትልቅ ዝግጅት ሲያዘጋጁ የመጀመሪያቸው በመሆኑ በዚህ ምክንያት በሚፈጠረው መደናገጥ ምክንያት የእርስ በርስ ዝምድናቸው መነካቱ አይቀርም” ይላል ዘ ኮምፕሊት ዌድንግ ኦርጋናይዘር ኤንድ ሪከርድ። “ነገሮች በታሰበው ዓይነት ባለመሄዳቸው መበሳጨት የሚፈይደው ነገር አይኖርም። እንዲህ ባለው ወቅት የሌሎችን ምክርና ድጋፍ መጠየቅ በጣም ጠቃሚ ነው።”

አንድ ሙሽራ “በኖረኝ ኖሮ ብዬ የማስበውና ባለማግኘቴም የሚቆጨኝ አንድ ነገር ቢኖር ምሥጢረኛዬ የሚሆንና የልቤን አውጥቼ የምነግረው አማካሪ ነው” ብሏል። እንዲህ ያለውን ተግባር ከአንድ የጎለመሰ ወዳጅ ወይም ዘመድ ወይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚገኝ ተሞክሮ ካለው ከአንድ ግለሰብ ሌላ ማን ሊያከናውን ይችላል?

ወላጆች ልጃቸው ከቤተሰባቸው እቅፍ ተነጥሎ መውጣቱን ሲመለከቱ የደስታ፣ የኩራት፣ የናፍቆትና የሥጋት ስሜት ሊፈራረቁባቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ራስ ወዳድ ባለመሆን ልጃቸው ፈጣሪ እንደወሰነው ‘አባቱንና እናቱን ትቶ’ ከትዳር ጓደኛው ጋር “አንድ ሥጋ” የሚሆንበት ጊዜ መድረሱን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (ዘፍጥረት 2:​24) አንዲት እናት የበኩር ልጅዋ ሲያገባ ተሰምቷት ስለነበረው ስሜት ስትናገር “አለቅስ ነበር። ለቅሶዬ ግን የሐዘን ብቻ ሳይሆን በእርግጥ የምትወደድ ምራት በማግኘቴ የደስታ ለቅሶ ጭምር ነበር” ብላለች።

የሠርጉን ወቅት አስደሳችና የሚያንጽ ለማድረግ እንደ ሙሽራውና ሙሽሪት ሁሉ ወላጆችም የክርስትና መለያ ባሕርያት የሆኑትን መተባበርን፣ እርጋታን፣ ራስ ወዳድ አለመሆንንና ቻይነትን ማንጸባረቅ ይኖርባቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​4-8፤ ገላትያ 5:​22-24፤ ፊልጵስዩስ 2:​2-4

አንዳንድ ሙሽሮች በሠርጋቸው ቀን የሚያሰናክል አንድ ችግር ያጋጥመን ይሆናል ብለው ይሰጋሉ። ጎማ ተንፍሶ ግብዣው ላይ በሰዓቱ ሳንደርስ ብንቀር፣ መጥፎ የአየር ጠባይ ቢያጋጥመን ወይም መጨረሻው ሰዓት ላይ የሠርጉ ልብስ እንደማይሆን ሆኖ ቢበላሽ ብለው ያስባሉ። እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይደርስ ይሆናል። ቢሆንም ምክንያታዊ መሆኑ ጥሩ ነው። ሁሉም ነገር ልክ እንደታሰበው በትክክል ላይፈጸም ይችላል። እክሎች ቢያጋጥሙ ተቀብሎ ማለፍ ይገባል። (መክብብ 9:​11) ችግር ሲያጋጥማችሁ ከመጠን በላይ አትበሳጩ። አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ። አንድ ነገር ቢከሰት በወደፊቶቹ ዓመታት ለሰው እያወራችሁ የምትስቁበት ነገር እንደሚሆን አስታውሱ። ጥቃቅን እክሎች ከሠርጋችሁ የምታገኙትን ደስታ እንዲሰርቅባችሁ አትፍቀዱለት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በዚህ ረገድ በርካታ አገሮች በጋብቻ ላይ ጋብቻ መፈጸምን፣ የቅርብ ዘመድ ማግባትን፣ ማታለልን፣ በትዳር ጓደኛ ላይ ዓመፅ መፈጸምንና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጆች ጋብቻን ይከለክላሉ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በወቅቱ የግድ አስፈላጊ መስሎ የታየን ነገር በኋላ ፈጽሞ የማያስፈልግ ሆኖ ተገኝቷል።”​—⁠ሙሽሪት ቲና

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ለናሙና የቀረበ የሠርግ ዝግጅት ዝርዝር *

6 ወር ወይም ከዚያም ቀደም ብሎ

❑ እቅዶቹን ከወደፊቱ ባል ወይም ሚስት ጋር እንዲሁም ከአማቶችና ከወላጆች ጋር መወያየት

❑ ስለሚደረገው የሠርግ ዓይነት ውሳኔ ላይ መድረስ

❑ ባጀት ማውጣት

❑ ሕግ ነክ ጉዳዮችን ማጣራት

❑ ሠርጉ የሚደረግበትን ቦታ መከራየት

❑ ፎቶ ግራፍ ከሚያነሳው ጋር መነጋገር

4 ወር

❑ ለሠርጉ የሚሆን ልብስ (ካሉ ልብሶች መካከል) መምረጥ፣ መግዛት ወይም መስፋት

❑ አበባ ማዘዝ

❑ የጥሪ ወረቀት መምረጥና ማዘዝ

2 ወር

❑ የጥሪ ወረቀት ማደል

❑ ቀለበት መግዛት

❑ አስፈላጊ ሰነዶችን ማውጣት

1 ወር

❑ የሠርግ ልብሶችን መሞከር

❑ የታዘዙ ዕቃዎችንና ቀጠሮዎችን ደግሞ ማረጋገጥ

❑ እስካሁን ለደረሱ ስጦታዎች የምስጋና ደብዳቤ መጻፍ

2 ሳምንት

❑ የግል ዕቃዎችን ወደ አዲሱ ቤት መውሰድ መጀመር

1 ሳምንት

❑ ረዳቶች በሙሉ ምን እንደሚፈለግባቸው የሚያውቁ መሆኑን ማረጋገጥ

❑ በኪራይ ወይም በውሰት የመጡ ዕቃዎች የሚመለሱበትን ሁኔታ ማዘጋጀት

❑ በተቻለ መጠን ሁሉንም ሥራ ማከፋፈል

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.31 ከአካባቢው ሕግና የግል ሁኔታ ጋር ለማስማማት እንደ ሁኔታው ሊስተካከል ይችላል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው”