ጋብቻ ዘላቂ ትስስር መሆን ይኖርበታል
ጋብቻ ዘላቂ ትስስር መሆን ይኖርበታል
በርካታ ፊልሞች በደረሱበት ድምዳሜ መሠረት ጋብቻ የሚፈለግ ነገር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ወንድዬውና ሴቷ በመጨረሻ ይገናኛሉ፣ ይጋባሉ፣ “ከዚያ በኋላ የደስታ ኑሮ” ይኖራሉ። አብዛኛውን ጊዜ የፊልም ትረካዎች በዚሁ ያቆማሉ።
በገሐዱ ዓለም ግን የሠርጉ ቀን ተጋቢዎች አብረው የሚያሳልፉት አዲስ ሕይወት መጀመሪያ እንጂ መደምደሚያ አይደለም። መክብብ 7:8 እንደሚለው “የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው” የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ ይደረጋል።
ዘላቂ የሆነ ትስስር
አርቆ ተመልካች መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ጋብቻ ዘላቂና እርካታ የሚገኝበት እንዲሆን ከተፈለገ በጠንካራ መሠረት ላይ መመስረት ይኖርበታል። ካልሆነ ግን ከሠርጉ በኋላ የሚኖረው ውጥረት ከሠርጉ በፊት ከነበረው በጣም የጠነከረ ይሆናል። አንድ ክርስቲያን ‘ቢሆን ይሆናል፣ ካልሆነ መፋታት ነው’ የሚል አስተሳሰብ ይዞ ወደ ጋብቻ ዘው ሊል አይችልም። ጋብቻ ዘላቂ ትስስር ሆኖ መታየት ይኖርበታል።
ኢየሱስ ስለ ፍቺ ቀርቦለት ለነበረው ጥያቄ በሰጠው መልስ ጋብቻ ዘላቂ መሆን እንደሚገባው በግልጽ ተናግሯል። “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፣ አለም:- ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” ብሏል።—ማቴዎስ 19:4-6
ከሠርጉ ቀን በኋላ
በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ራስን ለአምላክ ከመወሰን ቀጥሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጋብቻ ነው ተብሎ በትክክል ተነግሯል። ራሱን ለአምላክ መወሰኑ ከፈጣሪ ጋር ለዘላለም የሚያስተሳስረው ሲሆን ይህም በጥምቀት አማካኝነት ለሰዎች ይፋ ይደረጋል። ጋብቻ ደግሞ ከአንድ ሌላ ሰው ጋር ለዘላለም የተደረገን ቃል ኪዳን ለሕዝብ ይፋ የሚደረግበት ነው። ስለዚህ አንድ ዓይነት ገደብ ወይም ቅሬታ ይዞ ራስን ለአምላክ መወሰን ወይም በጋብቻ ሰንሰለት መተሳሰር ሊታሰብ የማይችል ነገር ነው። ስለዚህ ለማግባት የሚያስቡ ሁሉ የትዳር ጓደኛቸው የሚሆነውን ሰው እምነት፣ ግብ፣ ዝንባሌና ጠባይ በጥንቃቄ ቢመረምሩ ጥሩ ይሆናል።
ተጋቢዎቹ ለሠርጉ ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ አንዳቸው ለሌላው ደግ፣ አሳቢና ተባባሪ መሆናቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። የተሳካ ትዳር በመመሥረት ረገድ እነዚህ ባሕርያት ከሠርጉ ቀን በኋላ መታየታቸው ይበልጥ አስፈላጊ ነው። 1 ቆሮንቶስ 13:5, 8) ፍቅር በሰፈነበት ሁኔታ የመንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን እንደ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ የዋህነት፣ ራስን መግዛት ያሉትን ባሕርያት ማሳየት አስቸጋሪ አይሆንም። እነዚህ ባሕርያት ለተሳካ ትዳር በጣም አስፈላጊዎች ናቸው።—ገላትያ 5:22, 23
አዲሱ ተጋቢዎች እርስ በርሳቸው ይዋደዳሉ። ከጋብቻቸው ቀን በኋላ ግን በየቀኑ ‘ፍቅር የራሱን እንደማይፈልግ’ ለማስታወስ ይገደዳሉ። ፍቅር አላንዳች ማሰለስ ከዓመት እስከ ዓመት ተግባር ላይ በሚውልበት ጊዜ ደግሞ ‘ፍቅር ለዘወትር የማይወድቅ መሆኑ’ ይረጋገጣል። (ከባድ የሚሆነው እነዚህን ባሕርያት ከሠርጉ ቀን በኋላ ለዘለቄታው እያሳዩ መቀጠሉ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህን ግሩም ባሕርያት እያሳዩ ለመቀጠል ቁልፉ እነሆ:- ያገባኸውን/ሃትን ሰው መውደድና መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን።
ኢየሱስ ለሰዎች ከተሰጡት ትእዛዛት በሙሉ ትልቁ ይሖዋን መውደድ እንደሆነና ሁለተኛው ትልቅ ትእዛዝ ደግሞ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” የሚለው እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:39) ለአንድ ያገባ ሰው ከትዳር ጓደኛው የቀረበ ጎረቤት ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ሁለት ግለሰቦችን የጋብቻን ያህል አንድ አድርጎ ሊያስተሳስር የሚችል ምንም ነገር የለም።
ይሁን እንጂ አካላዊ አንድነት ብቻውን የስሜት አንድነት እንዲኖር ዋስትና አይሆንም። የሁለት አካሎች አንድነት ሁልጊዜ የሁለት አእምሮዎችን አንድነት አያስገኝም። የሩካቤ አንድነትም ቢሆን ከፍተኛ እርካታ እንዲያስገኝ ከተፈለገ ሁለተኛው ዓይነት አንድነት፣ ማለትም የልብና የፍላጎት አንድነት መኖር አለበት። አብዛኛውን ጊዜ ትዳርን የተሳካ ለማድረግ ለትዳር ጓደኛ ጥቅም መሥዋዕት መክፈል አስፈላጊ ይሆናል። ታዲያ መሥዋዕት መክፈል የሚኖርበት የትኛው ወገን ነው? ባልዬው ወይስ ሚስትዬዋ?
ፍቅርና አክብሮት ማሳየት
የአምላክ ቃል “እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ” ይላል። (ሮሜ 12:10 የ1980 ትርጉም፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ከቻልክ የትዳር ጓደኛህ ጥያቄ ከማቅረቡ በፊት መሥዋዕት አድርግ። ከብዙ ጉትጎታ በኋላ የተገኘ ነገር ዋጋውን በከፊል ማጣቱ አይቀርም። ከዚህ ይልቅ ባልም ሆነ ሚስት በራሳቸው ተነሳስተው ለትዳር ጓደኛቸው አክብሮት የማሳየት ልማድ ማዳበር ይገባቸዋል።
ለምሳሌ ያህል ባሎች “ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:7) አንድ ባል ሚስቱን በአክብሮት ካልያዘ ለአምላክ የሚያቀርበው ጸሎት እንኳን ሊታገድበት ይችላል። ታዲያ ሚስትን በአክብሮት መያዝ ማለት ምን ማለት ነው? ሁልጊዜ ለእርሷ ማሰብ፣ ሐሳቧን ማዳመጥ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ረገድ አብዛኛውን ጊዜ የርሷን ምርጫ ማክበር ማለት ነው። ሚስቲቱም ተባባሪ ረዳት በመሆን በተመሳሳይ መንገድ ለባልዋ አክብሮት ልታሳይ ትችላለች።—ዘፍጥረት 21:12፤ ምሳሌ 31:10-31
የአምላክ ቃል “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለ ሆንን፣ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፣ ይመግበዋል ይከባከበውማል” ይላል። ክርስቶስ ለተከታዮቹ የነበረው ፍቅር ምን ያህል ነበር? ሊሞትላቸው እንኳን ፈቃደኛ ነበር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ [ባል] የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት” ይላል። (ኤፌሶን 5:28-33) እንዲሁም “የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ፣ ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ . . . ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ” የአምላክ ቃል ለሚስቶች ይናገራል።—ቲቶ 2:4, 5
ስህተቶችን ማለፍ
ሁሉም ሰው ሲወለድ ፍጽምና የጎደለው ስለሆነ ስህተት ይሠራል። (ሮሜ 3:23፤ 5:12፤ 1 ዮሐንስ 1:8-10) ስህተቶችን ከማጋነን ይልቅ “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተሉ። (1 ጴጥሮስ 4:8) ጥቃቅን ስህተቶችን ችላ ብሎ ማለፍ የተሻለ ይሆናል። ከበድ ያሉ ስህተቶችም ቢሆኑ ሊታለፉ ይችላሉ። ቆላስይስ 3:12-14 “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት” ይላል።
የትዳር ጓደኛችንን ተራ ስህተቶችና ጉድለቶች ይቅር የምንለው ስንት ጊዜ ነው? ጴጥሮስ ኢየሱስን “ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን?” ሲል ጠይቆ ነበር። ኢየሱስ ግን “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም” ሲል መልሶለታል። (ማቴዎስ 18:21, 22) ኢየሱስ ይህን የተናገረው በጋብቻ ሰንሰለት ስላልተሳሰሩ ሰዎች ከሆነ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርስ ይቅር መባባላቸው ምን ያህል ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናል!
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጋብቻ ተቋም ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰ ያለ ቢሆንም የጋብቻን ተቋም ያቋቋመው አምላክ በመሆኑና እርሱ የመሠረተው ነገር ሁሉ ደግሞ “እጅግ መልካም” በመሆኑ በመጨረሻ ድል መንሳቱ አይቀርም። (ዘፍጥረት 1:31) ዘመን አያልፍበትም። በተለይ የአምላክን ትእዛዛት በሚያከብሩና በሚጠብቁ ዘንድ ደግሞ የተሳካ ይሆናል። ይሁን እንጂ ፈተናው ሁለቱ ግለሰቦች እርስ በርሳቸው እንደሚዋደዱና አንዳቸው ሌላውን እንደሚንከባከቡ በሠርጋቸው ዕለት የገቡትን ቃል ጠብቀው ይኖሩ ይሆን የሚለው ነው። ይህ በእርግጥም ከባድ ፈተና ሊሆን ይችላል። በድል አድራጊነት ለመወጣትም ብርቱ ትግል ማድረግ ይኖርባችሁ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሚገኘው ውጤት ማንኛውም ጥረት ሊደረግለት የሚገባው ነው!
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መፋታትና መለያየት
አምላክ ጋብቻን የመሠረተው ዘላለማዊ ጥምረት እንዲሆን አስቦ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ፈትቶ ሌላ ሊያገባ የሚችልበት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ይኖራል? ኢየሱስ የሚከተለውን በማለት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፣ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል።” (ማቴዎስ 19:9፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ንጹሕ የሆነው ወገን ሊፈታና ሌላ ለማግባት ነጻ ለመሆን የሚችልበት ብቸኛው ምክንያት የትዳር ጓደኛው በፆታ ታማኝነቱን ካጎደለ ነው።
በተጨማሪም 1 ቆሮንቶስ 7:10-16 ባልና ሚስት አብረው እንዲኖሩ ቢያበረታታም ሊለያዩ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ይገልጻል። አንዳንዶች ትዳራቸውን ከመፍረስ ለማዳን የቻሉትን ሁሉ ካደረጉ በኋላ ከመለያየት ሌላ ምንም ምርጫ እንደሌላቸው ተሰምቷቸዋል። እንዲህ ያለውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ሊኖር ይችላል?
አንድ ሰው ሆን ብሎ ለቤተሰቡ መተዳደሪያ ላያቀርብ ይችላል። አንድ ባል በሚያገባበት ጊዜ ሚስቱና ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ ግዴታ ይገባል። ለሕይወት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሆነ ብሎ የማያቀርብ ሰው “ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ስለዚህ እንዲህ ያለው ሁኔታ ለመለያየት ሊያበቃ ይችላል።
ሌላው ምክንያት ደግሞ በአካል ላይ የሚደርስ ከፍተኛ ጥቃት ነው። አንድ ባል በሚስቱ ላይ አካላዊ ጥቃት የሚሰነዝር ከሆነ ሚስቱ ልትለይ ትችላለች። (ገላትያ 5:19-21፤ ቲቶ 1:7) “ዐመፃን የሚወዱትን ግን፤ ነፍሱ [የአምላክ] ትጠላቸዋለች።”—መዝሙር 11:5 አ.መ.ት
ሌላው ለመለያየት የሚያበቃ ምክንያት ደግሞ የአንድን አማኝ መንፈሳዊነት ፈጽሞ አደጋ ላይ በመጣል ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና እንዲበላሽ ማድረግ ነው። የትዳር ጓደኛ ተቃውሞ፣ (የእንቅስቃሴ ገደብ መጣልን ሊጨምር ይችላል) አንድ አማኝ እውነተኛ አምልኮ የሚጠይቅበትን እንዲያከናውን ፈጽሞ የማያስችለው በሚሆንበትና መንፈሳዊነቱን አደጋ ላይ የሚጥልበት በሚሆንበት ጊዜ መለያየት አስፈላጊ እንደሆነ የተሰማቸው አማኞች አሉ። *—ማቴዎስ 22:37፤ ሥራ 5:27-32
ይሁን እንጂ እንደነዚህ ባሉት ምክንያቶች ፍቺ ከተፈጸመ አዲስ ጋብቻ ለመመሥረት ነጻ ሊሆኑ አይችሉም። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ለመፋታትና ሌላ ለማግባት የሚቻልበት ብቸኛ ምክንያት “ዝሙት” ወይም ምንዝር ብቻ ነው።—ማቴዎስ 5:32
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.27 መለያየትን በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኅዳር 1, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 22-3 ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጋብቻ ዘላቂ ዝግጅት እንደሆነ ተደርጎ መታየት ይኖርበታል
በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት” ይቅር ማለት እንደሚገባን ተናግሯል