መምህራን በጣም የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው?
መምህራን በጣም የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው?
“አንድ ሺህ ቀናት ለብቻ አቀርቅሮ ከማጥናት አንድ ቀን ከጥሩ መምህር ጋር ማጥናት ይሻላል።”—የጃፓናውያን ምሳሌ
ተማሪ ሳለህ በሕይወትህ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረ መምህር ነበረህ? አሁንም በመማር ላይ ከሆንክ ደግሞ በጣም የምትወደው መምህር አለህ? ከኖረህስ ለምን ወደድከው?
ጥሩ መምህር ተማሪዎቹ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያድርባቸው ከማድረግ በተጨማሪ መማር ደስ የሚያሰኝ ሥራ እንዲሆን ያደርጋል። አንድ በ70 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ እንግሊዛዊ አዛውንት በበርሚንግሃም ተማሪ ሳሉ ያስተማራቸውን የእንግሊዝኛ መምህር በፍቅር ያስታውሳሉ። “ሚስተር ክልውሊ እንደነበረኝ የማላውቀውን ችሎታ እንዳውቅ አስችሎኛል። ዐይነ አፋርና ቁጥብ ልጅ የነበርኩ ቢሆንም በትምህርት ቤቱ የድራማ ውድድር እንድካፈል አበረታታኝ። በዚያ ትምህርት ቤት በቆየሁበት የመጨረሻ ዓመት ለድራማ የሚሰጠውን ሽልማት ለመሸለም በቃሁ። እርሱ ባያበረታታኝ ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ አልችልም ነበር። ከዚያ ወዲህ አግኝቼው ለተማሪዎቹ ያሳይ ስለነበረው ያልተቆጠበ ጥረት ላመሰግነው አለመቻሌ በጣም ያሳዝነኛል።”
በ50ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የምትገኘውና በሙኒክ፣ ጀርመን የምትኖረው ማርጊት እንዲህ ትላለች:- “በጣም የምወዳት አንዲት መምህር ነበረች። በጣም ከባድና ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑ ትምህርቶችን ቀለል አድርጋ የማስረዳት ልዩ ችሎታ ነበራት። አንድን ነገር መረዳት ሲያስቸግረን ጥያቄ እንድንጠይቅ ታበረታታን ነበር። ተጫዋች ነበረች እንጂ ቁጥብ ወይም በቀላሉ የማትቀረብ አልነበረችም። በዚህም ምክንያት የምትሰጠው ትምህርት በጣም የሚያስደስት ሊሆን ችሏል።”
ፒተር የተባለ አንድ አውስትራሊያዊ ደግሞ የሂሣብ መምህሩን ያስታውሳል። እንዲህ ይላል:- “ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምሳሌዎችን በመስጠት የምንማረው ነገር ምን ተጨባጭ ጥቅም ሊኖረው እንደሚችል ያስረዳን ነበር። ትሪግኖሜትሪ በምንማርበት ጊዜ አንድን ሕንጻ በእጃችን እንኳን መንካት ሳያስፈልገን የትሪግኖሜትሪ ሕጎችን በመጠቀም የሕንጻውን ከፍታ እንዴት ማግኘት እንደምንችል አሳይቶናል። ‘ይህ በእርግጥም ትልቅ ነገር ነው!’ ብዬ እንደነበረ አስታውሳለሁ።”
የሰሜን እንግሊዟ ፖሊን “ሂሳብ በጣም ይከብደኛል” በማለት ለመምህሯ ሐቁን ትናገራለች። መምህሩም “ማሻሻል ትፈልጊያለሽ?” ብሎ ከጠየቃት በኋላ “ልረዳሽ እችላለሁ” በማለት ቃል ይገባላታል። ታሪኳን በመቀጠል “በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ልዩ ክትትል አደረገልኝ። ከትምህርት ሰዓት ውጭ ሳይቀር ይረዳኝ ነበር። እንደሚያስብልኝና እንዲሳካልኝ እንደሚፈልግ አውቅ ነበር። ይህን ማወቄ በርትቼ እንድሠራ ስላነሳሳኝ ለመሻሻል ቻልኩ” ብላለች።
በአሁኑ ጊዜ በ30ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው ስኮትላንዳዊቷ አንጂ የታሪክ መምህሯን ሚስተር ግራምን ታስታውሳለች። “የታሪክ ትምህርቱን በጣም አስደሳች አድርጎ የማቅረብ ችሎታ ነበረው። የተፈጸሙትን ክንውኖች እንደ ተረት አድርጎ የመተረክ ችሎታ የነበረው ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱን ትምህርት በጋለ ስሜት ያቀርብ ነበር። ሕያው ያደርገው ነበር።” አረጋዊት የነበረችውን የአንደኛ ክፍል መምህሯን ሚስስ ሂዩትንም በፍቅር ታስታውሳለች። “ደግና በጣም አሳቢ ነበረች። አንድ ቀን ክፍል ውስጥ አንድ ጥያቄ ልጠይቃት ወደ እርሷ ተጠጋሁ። ብድግ አድርጋ አቀፈችኝ። በእርግጥ እንደምታስብልኝ እንዲሰማኝ አድርጋለች።”
በደቡባዊ ግሪክ የሚኖረው ቲሞቲ ያለውን ከፍተኛ አድናቆት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “የሳይንስ መምህሬን ዛሬም አስታውሳለሁ። በዙሪያዬ ስላለው ዓለምም ሆነ ስለ ሕይወት ያለኝ አጠቃላይ አመለካከት እንዲለወጥ አድርጎልኛል። በክፍል ውስጥ የአድናቆትና የመገረም መንፈስ እንዲሰፍን ያደርግ ነበር። በውስጣችን የማወቅና የመረዳት ጥማት እንዲፈጠር ያደርግ ነበር።”
ሌላዋ ምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ ካሊፎርኒያ የምትኖረው ራሞና ነች። እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “የሁለተኛ ደረጃ መምህሬ እንግሊዝኛ በጣም ትወድ ነበር። ለትምህርቱ የነበራት ፍቅር ወደ ሌሎች ሊጋባ የሚችል ነበር። በጣም ከባድ የሆኑትን ክፍለ ትምህርቶች እንኳን ቀላል የማስመሰል ችሎታ ነበራት።”
ካናዳዊቷ ጄን ስለ አካል ብቃት መምህሯ በከፍተኛ አድናቆት ትናገራለች። “አዳዲስ የማስተማሪያና የመዝናኛ ሐሳቦችን ይፈጥር ነበር። ወደ ውጭ ወስዶ የበረዶ ሸርተቴና ከበረዶ በታች ባለ ውኃ ውስጥ ዓሣ ማጥመድ አስተምሮናል። ሌላው ቀርቶ ራሳችን ባያያዝነው እሳት ላይ ባኖክ የተባለውን የሕንዳውያን ባሕላዊ ዳቦ እንዴት እንደምንጋግር አሳይቶናል። ይህ ሁሉ አብዛኛውን ጊዜዋን ከቤት ሳትወጣ መጽሐፍ ላይ
አቀርቅራ ለምትውል እንደኔ ያለች ልጃገረድ በጣም የሚያስደስት ተሞክሮ ነው።”ሔለን በሻንግሃይ ተወልዳ በሆንግ ኮንግ የተማረች ዐይነ አፋር ወይዘሮ ናት። እንዲህ በማለት ትዝታዋን ትተርካለች:- “አምስተኛ ክፍል ሳለሁ አካላዊ ብቃትና ሥዕል ያስተምረን የነበረ ሚስተር ቻን የተባለ አንድ መምህር ነበረን። አቅም ስላልነበረኝ መረብ ኳስና ቅርጫት ኳስ መጫወት ይከብደኝ ነበር። ሆኖም በዚህ እንድሸማቀቅ አላደረገም። ለእኔ ይበልጥ ተስማሚ የሆኑትን እንደ ባድሜንተን ያሉ ሌሎች ጨዋታዎች እንድጫወት ይፈቅድልኝ ነበር። አሳቢና ደግ ሰው ነበር።
“ሥዕልን በተመለከተም ቢሆን ሰዎችንና ዕቃዎችን በመሳል ረገድ ጎበዝ አልነበርኩም። ከዚያ ይልቅ ቅርጾችንና ጌጦችን በመሳል ረገድ የተሻለ ችሎታ ስለነበረኝ እነዚህን ሥዕሎች እንድስል ይፈቅድልኝ ነበር። ከሌሎቹ ተማሪዎች በዕድሜ አንስ ስለነበረ ያን ክፍል ደግሜ እንድማር አበረታታኝ። ይህም በትምህርት ቤት ሕይወቴ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ሆነልኝ። በራሴ ለመተማመንና ዕድገት ለማድረግ ቻልኩ። ምንጊዜም ሳመሰግነው እኖራለሁ።”
ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉት የትኞቹ መምህራን ናቸው? ዊልያም አየርስ ቱ ቲች—ዘ ጀርኒ ኦቭ ኤ ቲቸር በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ በማለት ይመልሳሉ:- “ጥሩ አስተማሪነት ከሁሉ በላይ የሚጠይቀው አሳቢነትን፣ ራስን ለተማሪዎች ሕይወት መሥዋዕት ማድረግን ነው። . . . ጥሩ አስተማሪነት አንድ የተወሰነ ቴክኒክ ወይም ስልት፣ ዘዴ ወይም እቅድ የመከተል ጉዳይ አይደለም። . . . ጥሩ አስተማሪነት በዋነኛ ደረጃ ፍቅር የማሳየት ጉዳይ ነው።” እንግዲያው የተሳካለት ጥሩ መምህር የሚባለው እንዴት ያለው ነው? እንዲህ በማለት ይመልሳሉ:- “ልብህን የነካው መምህር፣ በትክክል ማንነትህን የተረዳው ወይም ስላንተ በግል ያሰበልህ መምህር፣ ለሙዚቃ፣ ለሂሣብ፣ ለላቲን፣ ለወላንዶ ወይም ለማንኛውም ነገር ያለውን ፍቅር ወደ ተማሪዎቹ ሊያስተላልፍና እነርሱንም ለማነሳሳት የቻለ መምህር ነው።”
በርካታ መምህራን ከተማሪዎቻቸውና ከተማሪዎች ወላጆች ጭምር የአድናቆትና የምስጋና ቃላት እንደደረሳቸውና ይህም የሚያጋጥሟቸውን እንቅፋቶች በሙሉ ተቋቁመው በማስተማር ሥራቸው እንዲቀጥሉ እንዳበረታታቸው ጥርጥር የለውም። እነዚህን የአድናቆት አስተያየቶች በሙሉ አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ባሕርይ መምህሩ ለተማሪዎቹ ያሳየው ልባዊ አሳቢነትና ደግነት ነው።
እርግጥ፣ ሁሉም መምህራን ይህን ባሕርይ አሟልተው ይገኛሉ ለማለት አይቻልም። ከዚህም በላይ መምህራን ለተማሪዎቻቸው ሊያደርጉ የሚችሏቸውን ነገሮች የሚገድቡባቸው በርካታ ችግሮች አሉ። ይህም ሰዎች እንዲህ ወዳለው አስቸጋሪ ሙያ የሚገቡት ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሣ ያደርገናል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ጥሩ አስተማሪነት በአንደኛ ደረጃ ፍቅር የማሳየት ጉዳይ ነው”