በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መምህርነት የሚጠይቀው መሥዋዕትነትና ዋጋ

መምህርነት የሚጠይቀው መሥዋዕትነትና ዋጋ

መምህርነት የሚጠይቀው መሥዋዕትነትና ዋጋ

“ከመምህርነት ሙያ የሚጠበቀው ግዴታ በጣም ብዙ ቢሆንም በየትምህርት ቤቶቻችን ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው የሚሠሩት አስተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ለሚያደርጉት ጥረት . . . ከሕዝብ የሚያገኙት ምሥጋና እጅግ አነስተኛ ነው።”—ኬን ኤልቲስ፣ የሲድኒ ዩኒቨርሲቲ፣ አውስትራሊያ

“በጣም አስፈላጊ የሆነ ሙያ” ተብሎ የሚጠራው ይህ የመምህርነት ሙያ ከደመወዝ ማነስ እስከ ክፍል ውስጥ ሁኔታዎች አለመሟላት፣ ከወረቀት ሥራዎች መብዛት እስከ ተማሪዎች ብዛት እንዲሁም ከአክብሮት መጥፋትና ከዓመፅ እስከ ወላጆች ግድየለሽነት የተለያዩ በርካታ ችግሮች የተጋረጡበት መሆኑ ሊካድ አይችልም። አንዳንድ አስተማሪዎች እነዚህን ችግሮች እንዴት እየተወጧቸው ነው?

የአክብሮት መጥፋት

በኒው ዮርክ ከተማ የሚኖሩ አራት መምህራን ዋነኛ ችግራቸው ምን እንደሆነ ተጠይቀው ነበር። ሁሉም በአንድ ቃል “የአክብሮት መጥፋት” ነው ሲሉ መልሰዋል።

የኬንያው ዊልያም እንዳለው በዚህ ረገድ በአፍሪካም ያለው ሁኔታ ተለውጧል። እንደሚከተለው ይላል:- “የልጆቹ ዲሲፕሊን በማሽቆልቆል ላይ ነው። ልጅ በነበርኩባቸው ዓመታት [አሁን በ40ዎቹ ዓመታት ውስጥ ይገኛል] በአፍሪካ ኅብረተሰብ ውስጥ መምህራን ከፍተኛ አክብሮት ይሰጣቸው ነበር። መምህሩ በወጣቶችም ሆነ በአረጋውያን ዘንድ እንደ ጥሩ አርዓያ ተደርጎ ይታይ ነበር። ይህ አክብሮት እየጠፋ መጥቷል። የምዕራባውያኑ ባሕል በአፍሪካ ገጠሮች ሳይቀር በወጣቶች ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ነው። ፊልሞች፣ ቪድዮዎችና ሥነ ጽሑፎች ባለሥልጣናትን ማቃለል ጀብዱ እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ።”

በኢጣሊያ የሚያስተምረው ጁልያኖ “በመላው ኅብረተሰብ ውስጥ ሥር የሰደደው የዓመፅ፣ ያለመገዛትና ያለመታዘዝ መንፈስ በልጆችም ላይ ተጽእኖ አሳድሯል” በማለት ያማርራል።

አደገኛ ዕፆችና ዓመፅ

አደገኛ ዕፆች በትምህርት ቤቶች ውስጥ በጣም አሳሳቢ የሆነ ችግር በመፍጠራቸው ምክንያት የዩናይትድ ስቴትስ መምህርና ደራሲ የሆኑ ሉአን ጆንሰን “የአደገኛ ዕፅ ሱሰኛ ከመሆን ስለመራቅ የሚሰጠው ትምህርት ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ [በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።] የሚሰጥ የሁሉም ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ክፍል ሆኗል ማለት ይቻላል። ልጆች ስለ አደገኛ ዕፅ ያላቸው እውቀት . . . ከአብዛኞቹ ትላልቅ ሰዎች ይበልጣል” ብለው እስከ መጻፍ ደርሰዋል። በማከልም “በራሳቸው የማይተማመኑ፣ በቂ ፍቅር ያላገኙ፣ ብቸኛ የሆኑ፣ የተሰላቹ ወይም ያልተረጋጉ ተማሪዎች አደገኛ ዕፆችን የመሞከር ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው” ብለዋል።​—⁠ቱ ፓርትስ ቴክስትቡክ፣ ዋን ፓርት ላቭ

በአውስትራሊያ የሚያስተምረው ኬን “መምህሮቻችን የገዛ ወላጆቹ አለማምደውት የዕፅ ሱሰኛ የሆነን የዘጠኝ ዓመት ልጅ የማስተማር ችግር ሊወጡ የሚችሉት እንዴት ነው?” በማለት ጠይቋል። በ30ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ የሚገኘው ሚካኤል በጀርመን አገር በአንድ አጠቃላይ ትምህርት ቤት ያስተምራል። እርሱም “አብዛኛውን ጊዜ ሳይታወቅ በድብቅ የሚካሄድ ይሁን እንጂ የአደገኛ ዕፆች ዝውውር እንደሚካሄድ እናውቃለን” ሲል ጽፏል። አስተያየቱን በመቀጠል ዲሲፕሊን እየጠፋ መምጣቱ “በልጆቹ የአውዳሚነት ባሕርይ ላይ በግልጽ ይታያል። ጠረጴዛዎችና ግድግዳዎች ይሞጫጨርባቸዋል፣ በዕቃዎችም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል። ከተማሪዎቼ አንዳንዶቹ ከሱቅ ዕቃ ሲሠርቁ ወይም ይህን የመሰለ ወንጀል ሲሠሩ በፖሊሶች እጅ ከፍንጅ እስከ መያዝ ደርሰዋል። በትምህርት ቤቶች ሥርቆት እየበረከተ መሄዱ አያስደንቅም።”

አሚራ የምታስተምረው በሜክሲኮ፣ በጉዋናዋቶ ክፍለ ሀገር ነው። እንዲህ ብላለች:- “ልጆቹ በሚኖሩባቸው ቤተሰቦች ውስጥ የኃይል ድርጊትንና የዕፅ ሱሰኛነትን የመሳሰሉ ችግሮች ያጋጥሙናል። ይህ በልጆቹ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። የሚኖሩበት አካባቢ አስነዋሪ አነጋገሮችንና ሌሎች ብልግናዎችን ያስተምራቸዋል። ሌላው ከፍተኛ ችግር ድህነት ነው። እዚህ አገር ትምህርት የሚሰጠው በነጻ ቢሆንም ወላጆች ደብተር፣ እርሳስና ሌሎች የጽሕፈት መሣሪያዎች መግዛት ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ምግብ ነው።”

በትምህርት ቤትም ጠመንጃ?

በቅርብ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ትምህርት ቤቶች የተፈጸሙ የተኩስ አደጋዎች በዚህች አገር በጠመንጃ አጋዥነት የሚፈጸሙ ወንጀሎች በቀላሉ የሚታዩ አለመሆናቸውን አረጋግጠዋል። አንድ ሪፖርት እንደሚለው “በየቀኑ 87, 125 ወደሚያክሉት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚገቡት ሽጉጦችና ጠመንጃዎች ቁጥር 135, 000 እንደሚደርስ ይገመታል። ወደ ትምህርት ቤቶች የሚገቡትን የጦር መሣሪያዎች ቁጥር ለመቀነስ ባለሥልጣኖች ኤሌክትሮኒክ በሆኑ ጠቋሚ መሣሪያዎች፣ በስለላ ካሜራዎች፣ የጦር መሣሪያዎችን አነፍንፈው በሚያገኙ የሠለጠኑ ውሾች ይጠቀማሉ። የተማሪዎችን ዕቃ ማስቀመጫ ሣጥኖች ይፈትሻሉ። መታወቂያ ካርዶችን እንዲይዙ ያስገድዳሉ። የመጻሕፍት ቦርሳ ይዞ መግባትም ከልክለዋል።” (ቲቺንግ ኢን አሜሪካ ) ይህን ሁሉ ቁጥጥር የተመለከተ ሰው እየተናገርን ያለነው ስለ ትምህርት ቤት ነው ወይስ ስለ እስር ቤት ብሎ መጠየቁ አይቀርም። ሪፖርቱ በማከል 6, 000 የሚያክሉ ተማሪዎች የጦር መሣሪያ ይዘው በመግባታቸው ከትምህርት ቤት እንደተባረሩ ይገልጻል!

በኒው ዮርክ ከተማ በመምህርነት የምትሠራው አይሪስ ለንቁ! እንዲህ ብላለች:- “ተማሪዎቹ የጦር መሣሪያ ደብቀው ወደ ትምህርት ቤት ያስገባሉ። መፈተሻ መሣሪያዎቹ ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠሩ አልቻሉም። ሆን ብሎ ንብረት ማበላሸትና ማውደምም ሌላው ዋነኛ የትምህርት ቤቶች ችግር ነው።”

ትጉህ የሆኑ መምህራን ለተማሪዎቻቸው ትምህርትና ጥሩ የሥነ ምግባር እሴቶችን ለማስተላለፍ ከፍተኛ ተጋድሎ የሚያደርጉት እንዲህ ባለው ሥርዓት አልበኝነት የሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነው። በርካታ መምህራን በመንፈስ ጭንቀትና በከፍተኛ ድካም መሸነፋቸው አያስደንቅም። በጀርመን የቱሪንጂያ ግዛት መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ሮልፍ ቡሽ “በጀርመን አገር ከሚገኙት አንድ ሚልዮን መምህራን መካከል ሲሶ የሚሆኑት በውጥረት ምክንያት ይታመማሉ። በከፍተኛ ድካም ይሸነፋሉ።”

ባለ ልጅ የሆኑ ልጆች

ሌላው ዋነኛ ችግር ወደ ጉርምስና ዕድሜ የደረሱ ልጆች የሚፈጽሙት ወሲባዊ ግንኙነት ነው። ቲቺንግ ኢን አሜሪካ የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ጆርጅ ኤስ ሞሪሰን ስለዚያች አገር ሲናገሩ “በየዓመቱ 1 ሚልዮን የሚያክሉ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች (ከ15 እስከ 19 ዓመት ከሆናቸው ልጃገረዶች መካከል 11 በመቶ የሚሆኑት) ያረግዛሉ” ብለዋል። ከበለጸጉ አገሮች በሙሉ ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛውን የአፍላ ወጣቶች እርግዝና ቁጥር ይዛለች።

አይሪስም ይህንኑ ሁኔታ አረጋግጣልናለች። እንዲህ ትላለች:- “ጉርምስና ዕድሜ ላይ የደረሱት ልጆች የሚያወሩት ሁሉ ስለ ወሲብና ስለ ፓርቲ ብቻ ነው። አእምሮአቸው በሙሉ የተያዘው በዚህ ነው። አሁን ደግሞ በትምህርት ቤት ኮምፒውተሮች ከኢንተርኔት ጋር እንዲገናኙ ተደርጓል። ይህ ደግሞ በኢንተርኔት አማካኝነት የወሬ ጓደኞች ማፍራትና የብልግና ሥዕሎችን መመልከት ይቻላል ማለት ነው።” በማድሪድ፣ ስፔይን የሚኖረው አንገል “በተማሪዎች ዘንድ የጾታ ብልግና የታወቀ የሕይወት ክፍል ሆኗል። በጣም ትናንሽ የሆኑ ተማሪዎች ያረገዙበት ሁኔታ አጋጥሞናል” ሲል ሪፖርት አድርጓል።

“ከበሬታ የተሰጣቸው የሕፃናት አጫዋቾች”

አንዳንድ መምህራን የሚያሰሙት ሌላው እሮሮ ብዙ ወላጆች የገዛ ልጆቻቸውን የማሠልጠንና የማስተማር ኃላፊነታቸውን የማይወጡ መሆናቸው ነው። ወላጆች የልጆቻቸው የመጀመሪያ አስተማሪዎች መሆን እንደሚገባቸው መምህራን ያምናሉ። ጨዋነትና መልካም ጠባይ መጀመር ያለበት ከቤት ነው። የአሜሪካ መምህራን ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ሳንድራ ፌልድማን “መምህራን . . . እንደ ማንኛውም ባለሙያ እንጂ ከበሬታ እንደተሰጣቸው የሕፃናት አጫዋቾች መታየት የለባቸውም” እስከ ማለት መድረሳቸው የሚያስደንቅ አይደለም።

አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች በትምህርት ቤት ለሚሰጠው ዲሲፕሊን ድጋፍ አይሰጡም። ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ሊማሪስ ለንቁ! በሰጠችው ሐሳብ ላይ “ጥፋተኛውን ልጅ ለዲሬክተሩ ሪፖርት ብታደርግ ወዲያው ወላጆቹ ሊጣሉህ ይመጣሉ” ብላለች። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ቡሽ አስቸጋሪ ስለሆኑ ልጆች አያያዝ ሲናገሩ “የቤተሰብ አስተዳደግ እየጠፋ መጥቷል። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ልጆች ጥሩና ምክንያታዊ የሆነ የቤተሰብ አስተዳደግ ያገኙ ናቸው ብሎ መገመት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል” ብለዋል። በአርጀንቲና፣ ሜንዶዛ የምትኖረው ኤስቴላ እንዲህ ብላለች:- “እኛ መምህራን ተማሪዎቹን እንፈራለን። ዝቅተኛ ማርክ ብንሰጣቸው ድንጋይ ይወረውሩብናል፣ ወይም ሊደበድቡን ይነሳሉ። መኪና ካለን ይሰባብሩብናል።”

ታዲያ በበርካታ አገሮች የመምህራን እጥረት መኖሩ ያስደንቃል? የኒው ዮርክ ካርኔጊ ኮርፖሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት ቫርታን ግሪጎርያን “ትምህርት ቤቶቻችን [የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች] በሚቀጥለው አሥር ዓመት እስከ 2.5 ሚልዮን የሚደርሱ አዳዲስ መምህራን ያስፈልጓቸዋል” በማለት አስጠንቅቀዋል። ትላልቆቹ ከተሞች “ከሕንድ፣ ከዌስት ኢንዲስ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከአውሮፓና ጥሩ መምህራን ሊገኙ ከሚችሉባቸው ሌሎች አገሮች መምህራን በማፈላለግ ላይ ናቸው።” ይህ ማለት ደግሞ እነዚህ አገሮች በተራቸው የመምህራን እጥረት ያጋጥማቸዋል ማለት ነው።

የመምህራን እጥረት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?

የ32 ዓመት ልምድ ያካበተው ጃፓናዊው መምህር ዮሺኖሪ “መምህርነት ጥሩ ካሳ ያለው የተከበረ ሥራ ነው። በጃፓናውያን ኅብረተሰብ ውስጥም ትልቅ ግምት ይሰጠዋል” ብሏል። የሚያሳዝነው ግን በርካታ ባሕሎች ይህን የመሰለ ከበሬታ የማይሰጡ መሆናቸው ነው። ቀደም ብለን የጠቀስናቸው ግሪጎርያን መምህራን “ለሙያቸው ተመጣጣኝ የሆነ ከበሬታ፣ እውቅናና ክፍያ አያገኙም። . . . በአብዛኞቹ [የዩናይትድ ስቴትስ] ክፍለ ግዛቶች ለመምህራን የሚከፈለው ደመወዝ የባችለር ወይም የማስተር ዲግሪ ከሚጠይቁ ሌሎች ሞያዎች ሁሉ ያነሰ ነው” ብለዋል።

በመግቢያችን ላይ የጠቀስናቸው ኬን ኤልቲስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “መምህራን በጣም ያነሰ ብቃት የሚጠይቁ በርካታ ሥራዎች ከማስተማር የበለጠ ደመወዝ እንደሚያስገኙ ሲያውቁ ምን ሁኔታ ይፈጠራል? ወይም ከአሥራ ሁለት ወራት በፊት ተማሪዎቻቸው የነበሩ ልጆች . . . አሁን ወይም ከአምስት ዓመት በኋላ እነርሱ ከሚያገኙት ደመወዝ የበለጠ ሲያገኙስ? አንድ መምህር ይህን ማየቱ ስለራሱ ያለው ግምት ዝቅ እንዲል ያስገድደዋል።”

ዊልያም አየርስም እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “የመምህራን ደመወዝ ዝቅተኛ ነው። . . . በአማካይ የሚከፈለን ለሕግ ባለሞያዎች የሚከፈለውን አንድ አራተኛ፣ የሂሣብ ሠራተኞች የሚከፈላቸውን ግማሽ ሲሆን የከባድ መኪና ሾፌሮችና የመርከብ ጥገና በሚካሄድበት ቦታ የሚሠሩ ሰዎች ከሚከፈላቸው ደመወዝም ያነሰ ነው። . . . የመምህርነትን ያህል ብዙ ድካም የሚጠይቅና አነስተኛ ክፍያ የሚያስገኝ ሥራ የለም።” (ቱ ቲች —⁠ዘ ጀርኒ ኦቭ ኤ ቲቸር) የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጃነት ሪኖ በኅዳር ወር 2000 እንዲህ ብለው ነበር:- “ሰዎችን ወደ ጨረቃ መላክ እንችላለን። . . . ለአትሌቶቻችን ከፍተኛ ደመወዝ እንከፍላለን። ለመምህሮቻችን ግን የተሻለ ክፍያ መስጠት ያቃተን ለምንድን ነው?”

ሊማሪስ “በአጠቃላይ የመምህራን ደመወዝ አነስተኛ ነው። ያን ሁሉ ዓመት በትምህርት አሳልፌ በዚህ በኒው ዮርክ ሲቲ በትልቅ ከተማ መኖር የሚያስከትለውን ውክቢያና ውጥረት ችዬ የማገኘው ዓመታዊ ደመወዝ በጣም ዝቅተኛ ነው” ብላለች። በሴይንት ፒተርስበርግ፣ ሩስያ በመምህርነት የምትሠራው ቫለንቲና “በክፍያ ረገድ መምህርነት የማይረባ ሥራ ነው። ደመወዙ ምንጊዜም ቢሆን ከዝቅተኛ ደረጃ ወጥቶ አያውቅም” ብላለች። በአርጀንቲና፣ ቹቡት የምትኖረው ማርሊንም ይህንኑ በማስተጋባት እንዲህ ብላለች:- “የደመወዛችን ማነስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ እየተሯሯጥን ሁለት ወይም ሦስት ቦታ እንድንሠራ ያስገድደናል። ይህ ደግሞ ውጤታማነታችንን በእጅጉ ይቀንሰዋል።” በናይሮቢ፣ ኬንያ የሚያስተምረው አርተር ለንቁ! ሲናገር “ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ በሄደ መጠን የመምህርነት ኑሮዬ ከባድ እየሆነብኝ መጥቷል። ብዙዎቹ የሥራ ባልደረቦቼ እንደሚስማሙበት የክፍያው ማነስ ብዙ ሰዎች በእኛ የሙያ መስክ እንዳይሰማሩ እንቅፋት ሆኗል” ብሏል።

በኒው ዮርክ ከተማ የምታስተምረው ዳያና መምህራንን ለበርካታ ሰዓቶች አስሮ ስለሚይዘው የወረቀት ሥራ መብዛት አማርራለች። ሌላው መምህር “አብዛኛው የቀኑ ክፍል የሚያልቀው አሰልቺ የሆኑ የተለመዱ ተግባራትንና ሥነ ሥርዓቶችን በተደጋጋሚ በማከናወን ነው” ሲል ጽፏል። አንዱ ለከፍተኛ ምሬት ምክንያት የሆነው ነገር “ሙሉ ቀን አሰልቺ የሆኑ ቅጾችን ሲሞሉ መዋል ነው።”

ተማሪዎች ከመጠን በላይ በዝተዋል፣ በቂ መምህራን ግን የሉም

በዱረን ጀርመን የሚኖረው ቤርቶልት የገለጸው በየጊዜው ሲነገር የሚሰማ ሌላ እሮሮ አለ። “በእያንዳንዱ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በጣም ብዙ ናቸው። በአንዳንድ ክፍሎች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች እስከ 34 ይደርሳሉ። ይህ ማለት ደግሞ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች በቂ ትኩረት ለመስጠት አንችልም ማለት ነው። ልብ አንላቸውም። የግለሰብ ችግሮች ችላ ተብለው ይታለፋሉ።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሊማሪስ “ባለፈው ዓመት ግድ የለሽ ከሆኑ ወላጆች ሌላ ትልቁ ችግሬ የነበረው በክፍሌ ውስጥ 35 ተማሪዎች መኖራቸው ነበር። በስድስት ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ 35 ሕፃናት ማስተማር ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት ይቻላል” ስትል ገልጻለች።

አይሪስ ደግሞ እንዲህ ብላለች:- “እዚህ ኒው ዮርክ ውስጥ የመምህራን፣ በተለይ የሂሣብና የሳይንስ መምህራን እጥረት አለ። ሌላ ቦታ የተሻለ ሥራ ሊያገኙ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት የከተማው አስተዳደር በርካታ የውጭ አገር መምህራን ለመቅጠር ተገዷል።”

መምህርነት ብዙ መሥዋዕትነት የሚጠይቅ ሙያ እንደሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ መምህራን በሙያቸው ላይ እንዲቆዩ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው? ችግሩን በሙሉ ተቋቁመው የሚዘልቁት ለምንድን ነው? የመጨረሻው ጽሑፋችን እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ትምህርት ቤቶች በየቀኑ የሚገቡት ሽጉጦችና ጠመንጃዎች ቁጥር 135, 000 እንደሚደርስ ይገመታል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንድን መምህር ጥሩ መምህር የሚያሰኘው ምንድን ነው?

ጥሩ መምህር ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ ልጅ የተማረውን ሁሉ በቃል ሸምድዶ ፈተና እንዲያልፍ የሚያስችል መምህር ነው? ወይስ የመጠየቅ፣ የማሰብና የማገናዘብ ችሎታው እንዲዳብር የሚያስችል? አንድን ልጅ የተሻለ ዜጋ እንዲሆን የሚረዳው የትኛው ነው?

“በመምህርነታችን ከተማሪዎቻችን ጋር ረዥም በሆነውና ውጣ ውረድ በበዛበት የሕይወት ጉዞ አብረን ተጓዦች መሆናችንን ከተገነዘብን፣ ሰብዓዊ ፍጥረታት መሆናቸውን አምነንና ተቀብለን ለሰብዓዊነታቸው የሚገባውን ክብር ከሰጠን ጥሩ መምህራን ለመሆን በሚያስችለን ጎዳና ላይ ነን ማለት ነው። ነገሩ የዚህን ያህል ቀላልም ከባድም ነው።”​—⁠ቱ ቲች —⁠ዘ ጀርኒ ኦቭ ኤ ቲቸር

ጥሩ መምህር የእያንዳንዱን ተማሪ እምቅ ችሎታ ያውቃል፣ እንዴት እንዲያድግና እንዲያብብ ማድረግ እንደሚችልም ያውቃል። ዊልያም አየርስ እንዲህ ብለዋል:- “የተሻለ ዘዴ፣ በጠንካራ ጎኖች፣ በተሞክሮዎች፣ በችሎታዎችና በክህሎት ላይ የተመሠረተ ዘዴ ማግኘት ይኖርብናል። . . . የአምስት ዓመት ወንድ ልጁ ‘የመማር ችሎታው ዘገምተኛ ነው’ የተባለበት የአንድ የአሜሪካ ሕንዳዊ ወላጅ ሁኔታ ትዝ ይለኛል። ዊንድ-ዉልፍ ከአርባ የሚበልጡ አእዋፍን ስምና ከአገር ወደ አገር የመዘዋወር ልማድ ያውቃል። አንድ ንሥር አሥራ ሦስት የጭራ ላባዎች እንዳሉት ያውቃል። ያስፈልገው የነበረው አቅሙንና ችሎታውን የሚያውቅለት መምህር ነበር።”

መምህሩ እያንዳንዱ ልጅ ያለውን እምቅ ችሎታ እንዲያዳብር ለመርዳት ፍላጎቱን ወይም ስሜቱን የሚቀሰቅሱትን ነገሮች ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም ለሙያው ያደረ መምህር ልጆችን መውደድ ይኖርበታል።

[ምንጭ]

United Nations/Photo by Saw Lwin

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መማር ሁልጊዜ ጨዋታ መሆን ይኖርበታል?

መምህር ዊልያም አየርስ ማስተማርን በተመለከተ ሰዎች ያሏቸውን አሥር የተሳሳቱ አመለካከቶች ዘርዝረዋል። ከእነዚህ አንዱ “ጥሩ መምህራን የሚያስተምሩት እንደ ቀልድ አድርገው ነው” የሚለው ነው። በመቀጠልም እንዲህ ብለዋል:- “ቀልድ ትኩረት ይከፋፍላል፣ ያዝናናል። ቀልደኞች ተጫዋቾች ናቸው። ቀልዶች አስደሳች ሊሆኑ ይችላሉ። ትምህርት ደግሞ ሙሉ ትኩረት የሚጠይቅ፣ የሚመስጥ፣ የሚያስገርምና ግራ የሚያጋባ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜም ውስጣዊ የሆነ የደስታ ስሜት ይፈጥራል። ትምህርቱ በጨዋታና ቀልድ መልክ ሊሰጥ የሚችል ከሆነ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ የግድ በጨዋታ መልክ መቅረብ አለበት ማለት አይደለም።” አክለውም “ማስተማር በጣም ሰፊ የሆነ የእውቀት አድማስ፣ ችሎታ፣ ክህሎት፣ ማስተዋልና ማመዛዘን ይጠይቃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አሳቢ ሰው መሆንን ይፈልጋል” ብለዋል።​—⁠ቱ ቲች፣ ዘ ጀርኒ ኦቭ ኤ ቲቸር

በጃፓን የናጎያ ከተማ ነዋሪ የሆነው ሱሚዮ በተማሪዎቹ ላይ ይህን ችግር አስተውሏል። “ብዙዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከቀልድና ከጨዋታ ሌላ ለምንም ነገር ደንታ የላቸውም። ጥረት የሚጠይቅ ምንም ነገር ማድረግ አይፈልጉም።”

በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የተማሪዎች አማካሪ የሆነችው ሮሳ እንዲህ ብላለች:- “ተማሪዎች በአጠቃላይ ትምህርት አሰልቺ ነው የሚል አመለካከት አላቸው። መምህሩም አሰልቺ ነው። ሁሉ ነገር ጨዋታና ቀልድ መሆን አለበት ብለው ያስባሉ። ከትምህርት የሚያገኙት ውጤት በሚያደርጉት ጥረት ላይ የተመካ መሆኑን መገንዘብ ይሳናቸዋል።”

የወጣቶች ትኩረት ያረፈው በቀልድና ጨዋታ ላይ ብቻ መሆኑ ከፍተኛ ጥረት እንዳያደርጉና መሥዋዕትነት እንዳይከፍሉ እንቅፋት ሆኗል። “ዋናው ችግር” ይላል ከላይ የጠቀስነው ሱሚዮ፣ “አርቀው ለማየት አለመቻላቸው ነው።” አሁን በርትተው ቢሠሩ ወደፊት ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው የሚያስቡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳያና፣ ዩ ኤስ ኤ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘የአደገኛ ዕፆች ዝውውር በግልጽ አይታወቅ እንጂ በጣም ተስፋፍቷል።’​—⁠ሚካኤል፣ ጀርመን

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘በቤተሰብ ውስጥ የኃይል ድርጊትና የዕፅ ሱስ ችግሮች ያጋጥሙናል። ’—⁠አሚራ፣ ሜክሲኮ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“መምህራን . . . እንደ ማንኛውም ባለሙያ እንጂ ከበሬታ እንደተሰጣቸው የሕፃናት አጫዋቾች መታየት የለባቸውም።”—⁠ሳንድራ ፌልድማን፣ የአሜሪካ መምህራን ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት