መምህርነት—ደስታውና እርካታው
መምህርነት—ደስታውና እርካታው
“በመምህርነት ሥራዬ እንድቀጥል ያስቻለኝ ምንድን ነው? ማስተማር አስቸጋሪና አድካሚ ቢሆንም በዚሁ ሥራ እንድቀጥል የሚገፋፋኝ ልጆች ያላቸውን የመማር ጉጉትና የሚያደርጉትን እድገት መመልከት መቻሌ ነው።”—ሊማሪስ፣ የኒው ዮርክ ከተማ መምህርት
በሚልዮን የሚቆጠሩ መምህራን ምንም ዓይነት ፈተና፣ እንቅፋትና ብስጭት ቢገጥማቸውም በመረጡት ሙያ ላይ ጸንተዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ይህ ነው የሚባል እውቅና እንደማያገኙ እያወቁ አስተማሪ ለመሆን እንዲጣጣሩ የሚያነሳሳቸው ፍላጎት ምንድን ነው? ተስፋ ሳይቆርጡ እንዲቀጥሉ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
ኢና የተባለችው ሩሲያዊት መምህርት እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “ተማሪዎቻችሁ የነበሩ ልጆች አድገው ትልቅ ሰው ሲሆኑና ከእናንተ የተማሩት ነገር በጣም እንደጠቀማቸው ሲናገሩ መስማት በጣም ያስደስታል። ከእናንተ ጋር ያሳለፉት ጥሩ ጊዜ ሁልጊዜ ትዝ እንደሚላቸው ሲናገሩ መስማት በጣም ያበረታታል።”
በቀደሙት ርዕሶች ላይ የተጠቀሰው ጁልያኖ እንዲህ ይላል:- “በጣም ከሚያረካችሁ ነገር አንዱ ተማሪዎቹ ስለ አንድ ትምህርት ያላቸውን የማወቅ ጉጉት እንዳነሳሳችሁ ማወቃችሁ ነው። ለምሳሌ፣ ስለ አንድ የታሪክ ትምህርት ከገለጽኩ በኋላ አንዳንድ ተማሪዎች ‘እባክህ አታቁም። ተጨማሪ ነገር ንገረን’ አሉኝ። እንደነዚህ ያሉት የልጆችን ልብ ፈንቅለው የሚወጡ አስተያየቶች በልጆቹ ላይ አዲስ የሆነ ስሜት እንዲፈጠር ማድረግ መቻላችሁን ስለሚያሳውቃችሁ ሙሉው የሥራ ቀን ብሩሕ ሆኖ እንዲታያችሁ ያደርጋል። አንድን ርዕሰ ትምህርት በሚገባ ለመረዳት ስለቻሉ ዓይናቸው ሲበራ ማየት በጣም ያስደስታል።”
በኢጣሊያ በመምህርነት የምትሠራው ኤሌና “እርካታ የሚገኘው ብዙ ጊዜ በማያጋጥሙ ታላላቅ ውጤቶች ሳይሆን ተማሪዎቹ በሚያገኟቸው ጥቃቅን የዕለት ተዕለት ውጤቶች ይመስለኛል” ስትል ገልጻለች።
በ30ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው አውስትራሊያዊቷ ካኒ “በመምህርነትና በተማሪነት ተሳስራችሁ የነበረ አንድ ተማሪ ጊዜ ወስዶ የምስጋና ደብዳቤ ሲልክላችሁ በጣም ደስ ያሰኛል” ብላለች።
በሜንዶዛ፣ አርጀንቲና የሚኖረው ኦስካር ይህንኑ ስሜት ይጋራል:- “ተማሪዎቼ መንገድ ላይ ወይም አንድ ሌላ ቦታ አግኝተውኝ ላስተማርኳቸው ነገሮች ያላቸውን አድናቆት ሲገልጹልኝ ድካሜ ሁሉ አለዋጋ አልቀረም የሚል ስሜት ይሰማኛል።” የማድሪድ፣ ስፔይን ነዋሪ የሆነው አንገልም እንዲህ ብሏል:- “ሕይወቴን በከፊል ለዚህ ድንቅ፣ ግን አስቸጋሪ ሙያ በመሠዋቴ የማገኘው ትልቅ እርካታ ያስተማርኳቸው ወጣቶች በከፊል እኔ ባደረግኩት ጥረት የተነሣ ጥሩ ወንዶችና ሴቶች ሆነው ለማየት መቻሌ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።”
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ሊማሪስ “መምህራን ልዩ ሰዎች እንደሆኑ ይሰማኛል። በተጨማሪም እንዲህ ያለውን ታላቅ ኃላፊነት ለመሸከም በመምረጣችን እኛም ትንሽ ችግር ያለብን ይመስለኛል። ይሁን እንጂ በአሥር ልጆችም ይሁን በአንድ ልጅ ላይ አንድ ዓይነት ለውጥ ማምጣት ከቻልን ግዳጃችንን ተወጥተናል ማለት ነው። ከዚህ የበለጠ የሚያስደስት
ስሜት ሊኖር አይችልም። ተግባርህን በደስታ ታከናውናለህ ማለት ነው።”መምህሮችህን አመስግነህ ታውቃለህ?
ተማሪ ወይም ወላጅ ከሆንክ መምህሩ ለሠዋው ጊዜ፣ ጥረትና አሳቢነት አመስግነኸው ታውቃለህ? ወይም አመስጋኝነትህን የሚገልጽ ማስታወሻ ወይም ደብዳቤ ልከህለት ታውቃለህ? የናይሮቢ፣ ኬንያ ነዋሪ የሆነው አርተር “መምህራንም የሚሰጣቸው ምስጋና በጣም ያበረታቸዋል። መንግሥት፣ ወላጆችና ተማሪዎች ለእነርሱም ሆነ እነርሱ ለሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ግምት መስጠት ይኖርባቸዋል” በማለት ተገቢ የሆነ አስተያየት ሰጥቷል።
መምህርና ደራሲ የሆኑት ሉአን ጆንሰንም እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “ስለ አንድ መምህር ለሚደርሰኝ ለእያንዳንዱ አሉታዊ ደብዳቤ መቶ የሚያክሉ አዎንታዊ ደብዳቤዎች ይደርሱኛል። ይህም ከመጥፎዎቹ መምህራን ይልቅ ጥሩዎቹ በጣም ብዙ በሆነ እጥፍ ይበልጣሉ የሚለውን እምነቴን አጠናክሮልኛል።” እንዲያውም ብዙ ሰዎች “የቀድሞ መምህራቸውን ፈልጎ የሚያገኝላቸው” መርማሪ እስከመቅጠር ደርሰዋል። “መምህሮቻቸውን አግኝተው ለማመስገን የሚፈልጉ ሰዎች በርካታ ናቸው።”
የአንድን ሰው ትምህርት አስፈላጊ መሠረት የሚጥሉት መምህራን ናቸው። በጣም እውቅ በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ በጣም ጎበዝ ፕሮፌሰሮች እንኳን ጊዜያቸውንና ጥረታቸውን ሠውተው ትምህርት፣ እውቀትና ማስተዋል የመቅሰም ፍላጎታቸውን ያዳበሩላቸው መምህራኖቻቸው ውለታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። የናይሮቢው አርተር “በመንግሥትም ሆነ በግል የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ታላላቅ ባለሥልጣናት በሙሉ በአንድ ወቅት ተማሪዎች ነበሩ” ይላል።
የማወቅ ፍላጎታችንን ላነሳሱት፣ ልባችንንና አእምሮአችንን ለቀሰቀሱት፣ ለእውቀትና ለማስተዋል ያለንን ጥማት የምናረካበትን መንገድ ላሳዩን ለእነዚህ ወንዶችና ሴቶች ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል!
በምሳሌ 2:1-6 ላይ የሚገኙትን ቃላት በመንፈሱ ላስጻፈው ለታላቁ መምህር ለይሖዋ አምላክ ደግሞ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባናል! “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ።”
በዚህ የሚያመራምር ጥቅስ ውስጥ ‘እንዲህ ብታደርግ’ በሚል ሐሳብ የቀረቡትን ነጥቦች ልብ በል። ይህን ማሳሰቢያ ለመቀበል ፈቃደኛ ብንሆን ‘የአምላክን እውቀት ለማግኘት እንችላለን’ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ተወዳዳሪ ሊገኝለት የማይችል ትልቅ እውቀት ነው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ደስ የተሰኘች ወላጅ
የሚከተለው ለአንድ የኒው ዮርክ ከተማ መምህር የተላከ ደብዳቤ ነው:-
“ለልጆቼ ላደረግህላቸው እገዛ ከልቤ በጣም ላመሰግንህ እፈልጋለሁ። በአንተ እንክብካቤ፣ ደግነትና ችሎታ ምክንያት አንተን ባያገኙ ኖሮ ሊደርሱ ከማይችሉበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርሱ ችለዋል። በልጆቼ እንድኮራ አስችለኸኛል። ይህ ፈጽሞ ልረሳው የማልችለው ነገር ነው። ያንተው፣ ኤስ. ቢ። ”
አንተስ ልታበረታታው የምትችል መምህር አለ?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ተማሪዎቹ አንድን ርዕሰ ትምህርት ለመረዳት በመቻላቸው ዓይናቸው ሲበራ ማየት በጣም ትልቅ ነገር ነው።’—ጁልያኖ፣ ኢጣሊያ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
‘አንድ ተማሪ ጊዜ ወስዶ አድናቆቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ሲልክ በጣም ያስደስታል። ’— ካኒ፣ አውስትራሊያ