መምህር የሚኮነው ለምንድን ነው?
መምህር የሚኮነው ለምንድን ነው?
“አብዛኞቹ መምህራን ወደ ማስተማር ሥራ የሚገቡት ሰዎችን የሚረዳ ሙያ በመሆኑ ነው። [መምህር መሆን] በልጆች ሕይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት ራስን መሥዋዕት ማድረግ ነው።”—ቲቸርስ፣ ስኩልስ፣ ኤንድ ሶሳይቲ
አንዳንድ መምህራን አስተማሪነት ቀላል ሙያ እንደሆነ አድርገው ለማሳየት ይሞክሩ እንጂ መምህርነት በርካታ እንቅፋቶችን መወጣት የሚጠይቅ ከባድ ሙያ ነው። በአንድ ክፍል ውስጥ ያሉ በርካታ ተማሪዎችን ማስተማር፣ በጣም ብዙ የወረቀት ሥራዎችን መሥራት፣ እንደ ልብ የማያሠራ የቢሮክራሲ ጫና መቋቋም፣ ግድ የለሽ ተማሪዎችን ማስተማር፣ የደመወዝ ማነስ ከከባዶቹ ችግሮች መካከል የሚቆጠሩ ናቸው። በማድሪድ፣ ስፔይን የሚኖር ፔትሮ የተባለ መምህር እንደሚከተለው አስቀምጦታል:- “መምህርነት ፈጽሞ ቀላል ሥራ አይደለም። በጣም ከፍተኛ መሥዋዕትነት ይጠይቃል። ሆኖም ችግሮች ይኑሩ እንጂ አሁንም ቢሆን መምህርነት በንግዱ ዓለም ከሚገኝ ሌላ ሙያ የበለጠ የሚያረካ ሥራ ነው እላለሁ።”
በአብዛኞቹ አገሮች ትላልቅ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ችግሩ በጣም የከፋ ሊሆን ይችላል። አደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች፣ ወንጀል፣ የሥነ ምግባር ልቅነት፣ አንዳንዴ ደግሞ የወላጆች ግድየለሽነት በትምህርት ቤት በሚኖረው መንፈስና ዲስፕሊን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራሉ። የዓመፀኝነት መንፈስ በጣም ተስፋፍቷል። ታዲያ ጥሩ ችሎታና ብቃት ያላቸው በርካታ ሰዎች መምህራን ለመሆን የሚመርጡት ለምንድን ነው?
ሊማሪዝና ዳያና በኒው ዮርክ ሲቲ በመምህርነት ሙያ ተሠማርተው ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ አሥር ዓመት ዕድሜ የሚደርሱ ልጆችን ያስተምራሉ። ሁለቱም ሁለት ቋንቋ ተናጋሪዎች ሲሆኑ (እንግሊዝኛና ስፓንኛ) በአብዛኛው የሚያስተምሯቸው ልጆች ከስፓንኛ ተናጋሪ ቤተሰቦች የመጡ ናቸው። ጥያቄያችን የሚከተለው ነበር:-
አንድን ሰው መምህር ለመሆን የሚያነሳሳው ምንድን ነው?
ሊማሪዝ እንዲህ ብላለች:- “እኔን ያነሳሳኝ ለልጆች ያለኝ ፍቅር ነው። አንዳንድ ልጆች ከእኔ በስተቀር ጥረታቸውን የሚደግፍላቸው ማንም እንደሌለ አውቃለሁ።”
ዳያና እንዲህ ትላለች:- “ትምህርት፣ በተለይም ማንበብ በጣም የሚከብደውን የወንድሜን የስምንት ዓመት ልጅ አስጠና ነበር። እሱም ሆነ ሌሎች እየተሻሻሉ ሲሄዱ ማየት በጣም የሚያስደስት ነበር! በዚህ ምክንያት መምህር የመሆን ፍላጎት አደረብኝና የባንክ ሥራዬን ትቼ ወጣሁ።”
ንቁ! በሌሎች አገሮች ለሚኖሩ መምህራንም ይህንኑ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የሚከተሉት ከተገኙት መልሶች ለናሙና ያህል የቀረቡ ናቸው።
በአርባዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ጣልያናዊው ጁልያኖ እንዲህ ይላል:- “ይህን ሙያ የመረጥኩት ተማሪ ሳለሁ እመኘው የነበረ ሥራ በመሆኑ ነው (በስተቀኝ)። አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር የሚያስችልና ሌሎችን ለማነሳሳት ጥሩ አጋጣሚ የሚሰጥ ሙያ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር። በመጀመሪያ የነበረኝ ግለትና ፍቅር በሥራዬ መጀመሪያ ላይ ያጋጠሙኝን ችግሮች ለመወጣት አስችሎኛል።”
በአውስትራሊያ ኒው ሳውዝ ዌልስ የሚኖረው ኒክ እንዲህ ይላል:- “ሰልጥኜበት በነበረው የኬሚካል ምርምር መስክ ብዙ የሥራ ዕድል አልነበረም። በትምህርት ዘርፍ ግን በርካታ የሥራ ዕድል ነበር። በሙያው ከተሰማራሁ ወዲህ ማስተማር የሚያስደስተኝ ሥራ ሆኗል። ተማሪዎቼም በማስተማር ችሎታዬ ደስ የሚላቸው ይመስላል።”
በርካታ ሰዎች የመምህርነት ሙያን እንዲመርጡ በምርጫቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረው የወላጆቻቸው አርዓያነት ነው። ኬንያዊው ዊልያም ላቀረብንለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “መምህር ለመሆን ባደረግኩት ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረው በ1952 አካባቢ መምህር የነበረው አባቴ ነው። በዚህ ሙያ ጸንቼ እንድቆይ ያስቻለኝ የወጣቶችን አእምሮ እንደምቀርጽ ማወቄ ነው።”
ሌላዋ ኬንያዊት ሮዝሜሪ እንዲህ ብላናለች:- “ከልጅነቴ ጀምሮ ችግረኛ የሆኑ ሰዎችን የመርዳት ፍላጎት ነበረኝ። ስለዚህ የነበረኝ ምርጫ ነርስ ወይም መምህር መሆን ነበር። በቅድሚያ የቀረበልኝ መምህር የመሆን ምርጫ ነበር። እኔም የልጆች እናት መሆኔ ደግሞ ለሙያው ያለኝን ፍቅር ጨመረልኝ።”
የዱረን፣ ጀርመን ነዋሪ የሆነውን ቤርቶልትን ለመምህርነት ያነሳሳው ምክንያት ለየት ያለ ነው። “ባለቤቴ ጥሩ መምህር ይወጣሃል በማለት አሳመነችኝ” ሲል ተናግሯል። በእርግጥም አልተሳሳተችም ነበር። በመቀጠልም “ባሁኑ ጊዜ ከሥራዬ ከፍተኛ ደስታ አገኛለሁ። አንድ መምህር ትምህርት ስላለው ከፍተኛ ዋጋ ከልብ የማያምንና ለወጣቶች ፍቅር የሌለው ከሆነ ጥሩ፣ የተዋጣለት፣ የሥራ ፍቅር ያለውና በሥራው የሚረካ መምህር ለመሆን ፈጽሞ አይችልም” ብሏል።
በናካትሱ ከተማ የሚኖረው ጃፓናዊው ማሳሂሮ እንደሚከተለው ይላል:- “መምህር እንድሆን ያነሳሳኝ በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ አጋጥሞኝ የነበረው ግሩም መምህር ነው። ከልቡ ያስተምረን ነበር። በዚህ ሙያ ለመቀጠል ያስቻለኝ ዋነኛ ምክንያት ለልጆች ያለኝ ፍቅር ነው።”
በአሁኑ ጊዜ 54 ዓመት የሆነው ጃፓናዊው ዮሺያ ጥሩ ደመወዝ የሚያስገኝ የፋብሪካ ሥራ ነበረው። ይሁን እንጂ ለዚህ ሥራውና ወደ ሥራው ለመመላለስ ለሚያደርገው ጉዞ ባርነት ያደረ ሆኖ ተሰማው። “አንድ ቀን ‘እንዲህ ባለው ኑሮ የምቀጥለው እስከ መቼ ድረስ ነው?’ ብዬ አሰብኩ። ከግዑዝ ማምረቻ መሣሪያ ጋር ሳይሆን ይበልጥ ከሰዎች ጋር የሚያገናኘኝ ሥራ ለመፈለግ ወሰንኩ። መምህርነት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሙያ ነው። የምትሠራው ከወጣቶች ጋር ነው። ሰብዓዊነት ያለው ሥራ ነው።”
የሴይንት ፒትስበርግ፣ ራሽያ ነዋሪ የሆነችው ቫለንቲናም ይኸኛውን የመምህርነት ልዩ ባሕርይ ታደንቃለች። እንዲህ ትላለች:- “መምህርነት ወድጄና መርጬ የተሰማራሁበት ሙያ ነው። ለ37 ዓመታት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሆኜ ሠርቻለሁ። ከልጆች ጋር፣ በተለይም ከሕፃናት ጋር መሥራት ያስደስተኛል። ሥራዬን በጣም እወደዋለሁ። እስካሁን ጡረታ ያልጠየቅኩትም በዚህ ምክንያት ነው።”
ራሳቸው መምህር የሆኑት ዊልያም አየርስ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “ሰዎች በመምህርነት ሥራ የሚሰማሩት ሕፃናትንና ወጣቶችን ስለሚወዱ፣ ወይም ከሕፃናትና ከወጣቶች
ጋር መሆን ስለሚወዱ፣ ማደጋቸውን፣ በዓለም ውስጥ ያላቸው ችሎታ፣ ብቃትና ሥልጣን እየጨመረ መሄዱን መመልከት ስለሚያስደስታቸው ነው። ሰዎች የሚያስተምሩት . . . ራሳቸውን ለሌሎች እንደተሰጡ ስጦታዎች አድርገው ስለሚቆጥሩ ነው። እኔ የማስተምረው ዓለምን የተሻለች መኖሪያ ለማድረግ እችል ይሆናል የሚል ተስፋ ስላለኝ ነው።”አዎን፣ በርካታ ችግሮችና እንቅፋቶች ቢኖሩም በሺህ የሚቆጠሩ ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው ያቀረቡ ወንዶችና ሴቶች ወደ ማስተማር ሙያ ይገባሉ። ከሚጋረጡባቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህንን ጥያቄ ይመረምራል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በመምህራንና በወላጆች መካከል የሚደረግ የሐሳብ ልውውጥ የሰመረ እንዲሆን የሚረዱ ሐሳቦች
✔ ከወላጆች ጋር ጥሩ ትውውቅ ይኑርህ። ለዚህ ጉዳይ የምታውለው ጊዜ በከንቱ የባከነ አይሆንም። የጋራ ጠቀሜታ በሚያስገኝ ጉዳይ ላይ የዋለ ጊዜ ነው። ከማንም የበለጠ ትብብር ሊያደርጉላችሁ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ሊያቀራርባችሁ የሚችል አጋጣሚ ነው።
✔ አነጋገርህ ከወላጁ የእውቀት ደረጃ ጋር የሚመጣጠን ይሁን። ካንተ ያነሰ የመረዳት ችሎታ ወይም እውቀት እንዳለው አድርገህ አትቁጠር። መምህራን ብቻ የሚጠቀሙባቸውን የሙያ ቃላት አትጠቀም።
✔ ስለ ልጆቹ በምትናገርበት ጊዜ ለጠንካራ ጎናቸው የበለጠ ትኩረት ስጥ። ማመስገን ከማውገዝ የበለጠ ውጤት ያስገኛል። ወላጆቹ ልጁን እንዴት ሊረዱ እንደሚችሉ ግለጽ።
✔ ወላጆቹ እንዲናገሩ አጋጣሚ በመስጠት ከልብ አዳምጣቸው።
✔ ልጁ የሚኖርበትን አካባቢና ሁኔታ ለማወቅ ሞክር። የሚቻል ከሆነ ቤቱን ጎብኝ።
✔ ለሚቀጥለው ውይይታችሁ የተወሰነ ቀን ቅጠር። ክትትል ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ልባዊና እውነተኛ ፍላጎት እንዳለህ ያሳያል።—ቲቺንግ ኢን አሜሪካ በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘አባቴም መምህር ነበር።’—ዊልያም፣ ኬንያ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ከልጆች ጋር መሥራት ያስደስተኛል።’—ቫለንቲና፣ ሩስያ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“መምህርነት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሙያ ነው። የምትሠራው ከወጣቶች ጋር ነው።”—ዮሺያ፣ ጃፓን