በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መስመሩን ማቋረጥ

መስመሩን ማቋረጥ

መስመሩን ማቋረጥ

የሰው ልጅ ቀደም ባለው ዘመን ውስጥ እንደገና ለመኖርም ሆነ የወደፊቱን ጊዜ ለማየት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ጊዜን አቋርጦ ለመጓዝ ሲመኝ ቆይቷል። ታዲያ ሰዎች በሆነ መንገድ በየቀኑ ጊዜን አቋርጠው እንደሚጓዙ ብታውቅ ትገረማለህ? ለስብሰባ ከቶኪዮ ወደ ኒው ዮርክ በአውሮፕላን የሚጓዘውን ነጋዴ ሁኔታ ተመልከት። እኩለ ቀን ላይ በረራ ጀምሮ ያለ ማቋረጥ የዓለምን እኩሌታ ከተጓዘ በኋላ በዚያው ዕለት ጠዋት እንዲያውም ከተነሳበት አስቀድሞ ያሰበበት ቦታ ይደርሳል።

ከረጅም ርቀት ጉዞ በኋላ ከተነሳህበት ጊዜ በፊት መድረስ በእርግጥ ይቻላል? ፈጽሞ አይቻልም። ሆኖም በመካከላቸው ከፍተኛ ርቀት ያላቸው ከተሞች የሚገኙት በተለያየ የጊዜ ሰቅ ውስጥ ነው። እንዲያውም በምድር ሉል ላይ ያለውን ሐሳባዊ መስመር ማለትም ዓለም አቀፉን ዕለተ መስመር ማቋረጥ ማለት ቅምር ቀኖችን የሚለያየውን በስምምነት የተዘረጋውን ወሰን ማቋረጥ ማለት ነው። በእርግጥ ይህ ግራ ያጋባል! በምትጓዝበት አቅጣጫ መሠረት በድንገት አንድ ቀን የማትረፍ ወይም የማጣት ጉዳይ ነው።

የቶኪዮው ነጋዴ በመልስ ጉዞው ላይ ከኒው ዮርክ ማክሰኞ ምሽት ላይ ተነሳ እንበል። ከ14 ሰዓት ገደማ በረራ በኋላ ከአውሮፕላን ሲወርድ ጃፓን ውስጥ ቀኑ ሐሙስ ሆኖ ይጠብቀዋል። አንድ ሙሉ ቀን መዝለል እንዴት ግር ይላል! ብዙ ጊዜ ከአገር አገር የምትጓዝ አንዲት ሴት ዓለም አቀፉን ዕለተ መስመር ያቋረጠችበትን የመጀመሪያ ጉዞዋን በማስታወስ “የተዘለለው ቀን የት እንደገባ ሊገባኝ አልቻለም ነበር። በጣም ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው” ስትል ተናግራለች።

ዕለተ መስመሩ መንገደኞችን ግራ ሊያጋባ ስለሚችል አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት ወሰን ለምን ተዘረጋ ብለው ያስቡ ይሆናል።

የመርከበኞች ግኝት

የፈርዲናንድ ማጄላን መርከበኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለምን ዞረው ወዳጠናቀቁበት ወደ 1522 ከተመለስን የዕለተ መስመር አስፈላጊነት በግልጽ ይገባናል። በባሕር ላይ ለሦስት ዓመታት ሲጓዙ ከቆዩ በኋላ እሁድ፣ መስከረም 7 ስፔይን ደረሱ። ይሁን እንጂ በመርከቡ ዕለታዊ መዝገብ መሠረት ቀኑ ቅዳሜ፣ መስከረም 6 ነበር። ልዩነት የተፈጠረው ለምንድን ነው? መርከበኞቹ የፀሐይን አቅጣጫ ተከትለው በምድር ዙሪያ ሲጓዙ ከስፔይን ነዋሪዎች በተለየ አንድ ቀን የፀሐይን መውጣት ሳያዩ ቀርተዋል።

ደራሲው ጁልዝ ቬርን አራውንድ ዘ ወርልድ ኢን ኤይቲ ዴይስ በተባለው ልብ ወለድ መጽሐፋቸው ላይ ይህን ክስተት በተቃራኒው በመጠቀም ታሪኩን ባልታሰበ መንገድ ደምድመዋል። የመጽሐፉ ዋነኛ ገጸ ባሕርይ ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት ለማግኘት በ80 ቀን ውስጥ ዓለምን ዞሮ መጨረስ ይጠበቅበት ነበር። ጉዞውን ያጠናቀቀው ከፍተኛ ሽልማት ሊያገኝ ከሚችልበት ጊዜ በአንድ ቀን ዘግይቶ ስለነበር በጣም አዘነ። በሌላ አነጋገር አንድ ቀን እንደዘገየ አድርጎ አስቦ ነበር። ይሁንና በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ መድረሱን ሲያውቅ በጣም ተደነቀ። “ፊሊየስ ፎግ ከመነሻው እስከ መድረሻው ድረስ በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ስለተጓዘ ብቻ ምንም ሳያውቀው አንድ ቀን ሊያተርፍ ችሏል” ሲል መጽሐፉ ይገልጻል።

ዓለም አቀፉ ዕለተ መስመር የሚስተር ቬርን ታሪክ አስደሳች መደምደሚያ እንዲኖረው ያስቻለ ቢመስልም ይህ ተወዳጅ ልብ ወለድ በታተመበት በ1873 ዕለተ መስመሩ አሁን ባለው መልኩ አይታወቅም ነበር። በዚያን ዘመን የነበሩ የመርከብ ካፒቴኖች ፓስፊክ ውቅያኖስን ሲያቋርጡ መቁጠሪያቸውን በአንድ ቀን ያስተካክሉ ነበር። ሆኖም ይጠቀሙበት የነበረው ካርታ አሁን ያለውን ዕለተ መስመር አያሳይም። ይህም ዓለም አቀፍ የጊዜ ሰቅ ሥርዓት ከመውጣቱ በፊት መሆኑ ነው። በመሆኑም አላስካ የሩስያ ግዛት በነበረችበት ወቅት በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ከሞስኮ ነዋሪዎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ ቀን መቁጠሪያ ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን በ1867 ዩናይትድ ስቴትስ አላስካን ከሩስያ ስትገዛ ነዋሪዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ የቀን መቁጠሪያ መጠቀም ጀመሩ።

ታሪካዊ እድገት

በ1884 የጊዜ አቆጣጠርን በተመለከተ ግራ መጋባት ሰፍኖ በነበረበት ወቅት ከ25 ብሔራት የተውጣጡ ተወካዮች በዓለም አቀፉ መነሾ ዋልቴ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ዋሽንግተን ዲ ሲ ውስጥ ተሰበሰቡ። ተሰብሳቢዎቹ 24 የጊዜ ሰቆች ያሉት ዓለም አቀፍ ሥርዓት ያቋቋሙ ከመሆኑም በላይ በእንግሊዝ ግሪንዊች የሚያልፈው የኬንትሮስ መስመር መነሾ ዋልቴ እንዲሆን ስምምነት ላይ ደረሱ። * ይህ መስመር በምድር ሉል ላይ በስተ ምሥራቅም ሆነ ምዕራብ ያሉ ቦታዎችን ለመለካት የሚያገለግል መነሻ ሆነ።

ከግሪንዊች ተነስቶ የምድር ክበብ ግማሽ ላይ ማለትም በምሥራቅ ወይም በምዕራብ አቅጣጫ 12 የጊዜ ሰቆች ሲታለፍ የሚገኘው ቦታ ዓለም አቀፍ ዕለተ መስመር የሚያርፍበት ተስማሚ ቦታ ሆኖ ተገኘ። በ1884 በተደረገው ጉባኤ ላይ ባለ 180 ዲግሪው ዋልቴ በይፋ የጸደቀ ባይሆንም እንኳ ዕለተ መስመሩ በየትኛውም አህጉር ላይ እንዳያልፍ የሚያደርግ በመሆኑ በጣም አመቺ ቦታ ላይ እንደሚገኝ ተቆጥሮ ተቀባይነት አገኘ። አንተ በምትኖርበት አገር ግማሹ ክፍል እሁድ ቢሆንና የተቀረው ግማሽ ደግሞ ሰኞ ቢሆን ምን ዓይነት ዝብርቅ ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ትችላለህ?

የዓለም አትላስ ወይም ሉል የተመለከትክ እንደሆነ 180 ዲግሪ ያለው ዋልቴ የሚገኘው ከሃዋይ በስተ ምዕራብ በኩል ነው። ዓለም አቀፉ ዕለተ መስመር ሙሉ በሙሉ ዋልቴውን ተከትሎ እንደማይሄድ ወዲያውኑ መገንዘብ ትችላለህ። ዕለተ መስመሩ በየብስ ላይ እንዳያልፍ ሲባል ጠመዝማዛ መስመር ይዞ ፓስፊክ ውቅያኖስን እንዲያቋርጥ ተደርጓል። ደግሞም ዕለተ መስመሩ የተቋቋመው በዓለም አቀፍ ውል ሳይሆን በጋራ ስምምነት ላይ ስለሆነ በየትኛውም አገር ምርጫ ሊቀየር ይችላል። ለምሳሌ ያህል በ1995 ኪሪባቲ እንደ ሰንሰለት በተያያዙት ደሴቶች ላይ የሚያቋርጠው ዓለም አቀፉ ዕለተ መስመር ከዚያ ጊዜ አንስቶ በስተ ምሥራቅ ጫፍ በሚገኘው የአገሪቱ ደሴት በኩል ዞሮ እንደሚያልፍ አሳውቃለች። ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ያሉ ዘመናዊ ካርታዎች የኪሪባቲ ደሴቶች በሙሉ ከመስመሩ በአንድ ወገን እንዳሉ ያሳያሉ። በመሆኑም ደሴቶቹ ተመሳሳይ የቀን መቁጠሪያ ሊኖራቸው ችሏል።

ዕለተ መስመሩ የሚሠራበት መንገድ

ዕለተ መስመሩን ስናቋርጥ አንድ ቀን የሚቀንስበትን ወይም የሚጨምርበትን ምክንያት ለመረዳት ዓለምን በመርከብ እየዞርክ እንዳለህ አስብ። የምትጓዘው ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ነው እንበል። ላይታወቅህ ቢችልም እንኳ እያንዳንዱን የጊዜ ሰቅ ባቋረጥህ ቁጥር አንድ ሰዓት እንደምትጨምር ይታሰባል። በመጨረሻ ዓለምን ዞረህ ስትጨርስ 24 የጊዜ ሰቆችን አቋርጠሃል ማለት ነው። ዓለም አቀፍ ዕለተ መስመር ባይኖር ኖሮ ከደረስክበት ቦታ የቀን አቆጣጠር በአንድ ቀን እንደቀደምክ ተደርጎ ይቆጠራል። ዓለም አቀፉ ዕለተ መስመር እንዲህ ዓይነት ልዩነት እንዳይፈጠር ይረዳል። በመጠኑ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፣ አይደል? የማጄላን መርከበኞችና በልብ ወለድ መጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሰው ፊሊየስ ፎግ ዓለምን ዞረው ያጠናቀቁበትን ቀን ሲቆጥሩ መሳሳታቸው ምንም አያስደንቅም!

አዎን፣ መስመሩን ያቋረጡ ሰዎች በድንገት አንድ ሙሉ ቀን ማጣት ወይም ማግኘት የሚፈጥረውን ያልተለመደ ስሜት አሳምረው ያውቁታል። ሆኖም ዓለም አቀፉ ዕለተ መስመር ባይኖር ኖሮ በዓለም ላይ የሚደረግ ጉዞ ከዚያ የባሰ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ይሆን እንደነበር አሌ አይባልም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 የጊዜ ሰቅንና የኬንትሮስ መስመሮችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የመጋቢት 8, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ጠቃሚ የሆኑት ሐሳባዊ መስመሮች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

መጋቢት | መጋቢት

2 | 1

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ:- የግሪንዊች ሮያል የምርምር ተቋም

በስተ ቀኝ፡- በዚህ የድንጋይ ንጣፍ ላይ የሚታየው መስመር መነሾ ዋልቴው የሚያልፍበትን ቦታ ያመለክታል