በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በማኅፀኔ የነበረው ልጄ ጨነገፈ

በማኅፀኔ የነበረው ልጄ ጨነገፈ

በማኅፀኔ የነበረው ልጄ ጨነገፈ

ዕለቱ ሰኞ፣ ሚያዝያ 10, 2000 ነው። ሞቅ ያለና ፀሐያማ ቀን ስለነበር ወጣ ብዬ አንዳንድ ነገሮች ለማከናወን እቅድ አወጣሁ። ከፀነስኩ ልክ አራተኛ ወሬን መያዜ ሲሆን ብዙም ብርታት ባይሰማኝም እንኳ ወደ ውጭ በመውጣቴ ደስ ብሎኝ ነበር። ከዚያም አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ገንዘብ ለመክፈል ተራ እየጠበቅሁ ሳለሁ አንድ ዓይነት የጤንነት መታወክ ተሰማኝ።

ወደ ቤት እንደመጣሁ የፈራሁት ነገር ደረሰ። ከዚህ በፊት ባሳለፍኳቸው ሁለት የእርግዝና ወቅቶች ያላጋጠመኝ ነገር ነበር፤ ደም እየፈሰሰኝ መሆኑን ሳውቅ በጣም ደነገጥኩ! ለዶክተሬ ደውዬ ብነግረውም በነጋታው ቀጠሮ ስለነበረኝ እስከዚያ ድረስ እንድጠብቅ ነገረኝ። የዚያን ቀን ማታ እኔና ባለቤቴ ሁለቱን ልጆቻችንን ከማስተኛታችን በፊት ይሖዋ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት በማንኛውም መንገድ ብርታት እንዲሰጠን በመጠየቅ አብረን ጸለይን። በኋላ ተኛሁ።

ሆኖም ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ገደማ ከባድ ውጋት ከእንቅልፌ አስነሳኝ። ቀስ በቀስ ውጋቱ የቀነሰልኝ ቢሆንም ገና እንዳሸለበኝ መልሶ ያገረሸብኝ ሲሆን ያዝ ለቀቅ እያደረገ ይመላለስብኝ ጀመር። የሚፈስሰኝ ደም የጨመረ ከመሆኑም በላይ የጡንቻ መኮማተር ተሰማኝ። ለዚህ መንስኤ የሚሆን ያደረግሁት ነገር ካለ በሚል ባወጣ ባወርድም ተሳስቼ ያደረግሁት አንድም ነገር ትዝ ሊለኝ አልቻለም።

ከሌሊቱ አሥራ አንድ ሰዓት ሲሆን ወደ ሆስፒታል መሄድ እንዳለብኝ ወሰንኩ። እኔና ባለቤቴ እዚያ እንደደረስን በጣም ደግ፣ ተባባሪና አሳቢ የሆኑ የድንገተኛ ክፍል ሠራተኞች እርዳታ በማግኘታችን ከፍተኛ እፎይታ ተሰማን። ከዚያም ከሁለት ሰዓት በኋላ ዶክተሩ የፈራነውን ነገር አረዳን፤ በማኅፀኔ የነበረው ልጄ ጨንግፏል።

አስቀድሞ ካጋጠሙኝ የሕመም ምልክቶች የተነሳ ይህ እንደሚደርስ ጠብቄ ስለነበር ውጤቱ ሲነገረኝ ብዙም አልደነገጥኩም። በተጨማሪም ባለቤቴ በዚህ ሁሉ ጊዜ ከአጠገቤ ያልተለየኝ ሲሆን ከፍተኛ ድጋፍም ሰጥቶኛል። ሆኖም ወደ ቤት የምንመለሰው ልጅ ሳንይዝ በመሆኑ ለሁለቱ ልጆቻችን ማለትም ለስድስት ዓመቷ ኬትሊንና ለአራት ዓመቱ ዴቪድ ምን ብለን እንደምንነግራቸው ጨነቀን።

ለልጆቻችን ምንድን ነው የምንላቸው?

ልጆቻችን ወደ መኝታቸው ሲሄዱ አንድ ችግር እንደተፈጠረ ተሰምቷቸዋል፤ ሆኖም ትንሹ ወንድማቸው ወይም እህታቸው መሞቱን(ቷን) የምንነግራቸው እንዴት ነው? ጉዳዩን ሳናድበሰብስ በግልጽ ለመናገር ወሰንን። በዚህ ረገድ እናቴ ሕፃኑ ከእኛ ጋር እንደማይመጣ ለልጆቹ በመንገር ተባበረችን። ቤት ስንደርስ ሮጠው መጥተው እቅፍ አድርገው ሳሙን። የመጀመሪያ ጥያቄያቸው “ሕፃኑ ደህና ነው?” የሚል ነበር። እኔ የምለው ጠፋኝ፤ ባለቤቴ ግን ሁላችንንም ሰብሰብ አድርጎ ይዞ “ሕፃኑ ሞቷል” አለ። እርስ በርስ ተያይዘን አለቀስን፤ ይህም ሐዘኑ ቀስ በቀስ እንዲወጣልን ረድቶናል።

ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ በልጆቻችን ላይ ያየነው የስሜት ለውጥ ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነበር። ለምሳሌ ያህል ፅንሱ ከጨነገፈብኝ ከሁለት ሳምንት በኋላ እኛ ባለንበት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ያሉ የቤተሰባችን የቅርብ ወዳጅ የሆኑ አንድ አረጋዊ ምሥክር ማረፋቸው በማስታወቂያ ተነገረ። የአራት ዓመቱ ልጃችን ዴቪድ ስቅስቅ ብሎ በማልቀሱ ባለቤቴ ወደ ውጭ ይዞት ወጣ። ዴቪድ ማልቀሱን ካቆመ በኋላ አረጋዊ ወዳጁ ለምን እንደሞቱ ጠየቀ። ከዚያም ሕፃኑ ለምን እንደሞተ ጠየቀ። በመቀጠልም አባቱን “አንተም ትሞታለህ?” ሲል ጠየቀው። ከዚህም በላይ ይሖዋ አምላክ እስካሁን ድረስ ሰይጣንን ያላጠፋውና “ሁኔታዎችን ማስተካከል” ያልጀመረው ለምን እንደሆነ ማወቅ ፈለገ። በጨቅላ አእምሮው ውስጥ ምን ያህል ሐሳብ ይጉላላ እንደነበር ማወቃችን በጣም አስገረመን።

ኬትሊንም ብዙ ጥያቄዎች ትጠይቅ ነበር። በአሻንጉሊቶቿ ስትጫወት አብዛኛውን ጊዜ አንዷ እንደታመመች፣ ሌሎቹ ደግሞ አስታማሚዎች ወይም የቤተሰብ አባሎች እንደሆኑ አድርጋ ትጫወት ነበር። በካርቶን የአሻንጉሊት ሆስፒታል ትሠራና አንዳንዴ አንደኛዋ አሻንጉሊት እንደሞተች ታስመስል ነበር። ልጆቻችን የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና የሚጫወቷቸው ጨዋታዎች ስለ ሕይወትና መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች እንዴት ተቋቁመን ማሳለፍ እንደምንችል እንደሚረዳን ጠቃሚ ትምህርቶች እንድንሰጣቸው የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎች ከፍተውልናል። እንዲሁም አምላክ ሞትን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ሥቃይና መከራ በማስወገድ ምድርን ውብ ገነት ለማድረግ ያለውን ዓላማ መለስ ብለው እንዲያስቡበት አደረግናቸው።​—⁠ራእይ 21:​3, 4

ሐዘኑን መቋቋም የቻልኩበት መንገድ

መጀመሪያ ከሆስፒታል ወደ ቤት እንደተመለስኩ ደንዝዤና ግራ ተጋብቼ ነበር። ቤት ውስጥ ብዙ ሥራ ይጠብቀኝ የነበረ ቢሆንም በየትኛው እንደምጀምር መላ ቅጡ ጠፋኝ። ተመሳሳይ ችግር ያሳለፉ አንዳንድ ጓደኞቼ ጋር ስልክ የደወልኩ ሲሆን እነሱም በጣም አጽናኑኝ። በጣም የምቀርባት አንዲት ጓደኛዬ አበባ የላከችልን ከመሆኑም በላይ ልጆቹ ከሰዓት በኋላ አብረዋት እንዲውሉ ሐሳብ አቀረበች። ልባዊ አሳቢነቷንና ተግባራዊ እርዳታዋን በጣም ነበር ያደነቅሁት!

የቤተሰባችንን ፎቶግራፎች መልክ እያስያዝኩ አልበም ውስጥ ከተትኩ። ለሕፃኑ የተገዙትን ልብሶች አየሁና አንስቼ ያዝኳቸው። የሞተብኝን ልጅ የሚያስታውሰኝ ነገር ቢኖር ይህ ብቻ ነው። ለበርካታ ሳምንታት ከፍተኛ የስሜት መቃወስ ገጠመኝ። ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ድጋፍ ያደርጉልኝ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ቀን በጣም አለቅስ ነበር። አንዳንድ ጊዜ አእምሮዬን የምስት ይመስለኝ ነበር። በተለይ ነፍሰ ጡር ከሆኑ ጓደኞቼ ጋር በምሆንበት ጊዜ እረበሽ ነበር። ከዚህ በፊት የፅንስ መጨንገፍ በሴት ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥም እንዲያው በቀላሉ ልንረሳው የምንችል “ጊዜያዊ ችግር” እንደሆነ አድርጌ አስብ ነበር። ምንኛ ተሳስቻለሁ! *

ፍቅር​—⁠ፍቱን መድኃኒት

ጊዜ እያለፈ መሄዱ ከሚያበረክተው እርዳታ በተጨማሪ ባለቤቴና ክርስቲያን ወዳጆቼ ያሳዩኝ ፍቅር ፍቱን መድኃኒት ሆኖልኛል። አንዲት የይሖዋ ምሥክር እራት አዘጋጅታ ይዛልን መጣች። አንድ የጉባኤ ሽማግሌና ሚስቱ አበባና ካርድ ይዘው መጥተው ምሽቱን ከእኛ ጋር አሳለፉ። ሥራ በጣም እንደሚበዛባቸው ስለምናውቅ አሳቢነታቸው ልባችንን ነካው። ሌሎች በርካታ ወዳጆቻችን ካርዶች አሊያም አበባ ልከውልናል። “ምንጊዜም እናስባችኋለን” የሚሉት አጭር ቃላት ከፍተኛ ትርጉም ነበራቸው! አንዲት የጉባኤያችን አባል እንዲህ ስትል ጻፈችልን:- “ለሕይወት ያለን አመለካከት ከይሖዋ የተለየ አይደለም፤ በጣም ክቡር አድርገን እንመለከተዋለን። ይሖዋ አንዲት ድንቢጥ ስትሞት የሚያውቅ ከሆነ አንድ ሽል በሚጨነግፍበት ጊዜም ማወቁ እንደማይቀር የተረጋገጠ ነው።” የአጎቴ ልጅ ሚስት “ልጅ መውለድና ሕይወት በጣም አስገራሚ ተአምር የሚሆንብንን ያህል የፅንስ መጨንገፍም ፈጽሞ የማንጠብቀው ነገር ነው” ስትል ጻፈችልን።

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መንግሥት አዳራሽ ውስጥ እያለሁ እንባ ተናነቀኝና ልክ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ወደ ውጭ ለመውጣት ተገደድኩ። በጣም የምወዳቸው ሁለት ጓደኞቼ እያለቀስኩ ስወጣ አይተው ተከተሉኝና መኪና ውስጥ አብረውኝ ተቀምጠው እጄን ይዘው እያዋሩ አሳቁኝ። ብዙም ሳንቆይ ሦስታችንም ተመልሰን ገባን። “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ” ጓደኛ ማግኘት እንዴት ያስደስታል!​—⁠ምሳሌ 18:​24

ወሬው እየተዳረሰ ሲሄድ ብዙ ምሥክሮች ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሟቸው እንደነበር ሳውቅ በጣም ተገረምኩ። ሌላው ቀርቶ በፊት ብዙም የማልቀርባቸው አንዳንዶች ከፍተኛ ማጽናኛና ማበረታቻ ሰጥተውኛል። ችግር ላይ እያለሁ የሰጡኝ ፍቅራዊ ድጋፍ “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል አስታውሶኛል።​—⁠ምሳሌ 17:​17

የአምላክ ቃል የሚሰጠው ማጽናኛ

ፅንሱ ከጨነገፈብኝ ከአንድ ሳምንት በኋላ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ደረሰ። አንድ ቀን ማታ ኢየሱስ በሕይወት ያሳለፋቸውን የመጨረሻ ቀኖች የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ስናነብ ‘ይሖዋ ልጁን በሞት ስላጣ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን ያውቃል!’ የሚለው ሐሳብ ድንገት ወደ አእምሮዬ መጣ። ይሖዋ በሰማይ የሚኖር አባታችን በመሆኑ የወንዶችም ሆኑ የሴቶች አገልጋዮቹን ሁኔታ ምን ያህል መረዳት እንደሚችልና ምን ያህል ርኅራኄ እንደሚያሳያቸው አንዳንድ ጊዜ እዘነጋለሁ። በዚህ ቅጽበት ግን ከፍተኛ የእፎይታ ስሜት ተሰማኝ። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንደቀረብኩ ተሰማኝ።

እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱ ጽሑፎች በተለይ ደግሞ የሚወዱትን ሰው በሞት ስለማጣት ከሚናገሩ በፊት ከወጡ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ከፍተኛ ማጽናኛ አግኝቻለሁ። ለምሳሌ ያህል የነሐሴ 8, 1987 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እትም ላይ “የልጅ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም” በሚል ርዕስ የወጣው ጽሑፍም ሆነ የምትወዱት ሰው ሲሞት * የተባለው ብሮሹር በጣም ጠቅመውኛል።

ሐዘን የሚወገድበት ጊዜ

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በደለኛነት ሳይሰማኝ መሳቅ ስጀምርና የጨነገፈብኝን ልጅ ጉዳይ ሳላነሳ መጫወት ስችል ሐዘኑን እየረሳሁት እንደሆነ ተገነዘብኩ። ይህም ሆኖ የደረሰብኝን ሐዘን ያልሰሙ ጓደኞቼን ሳገኝ ወይም ጨቅላ ሕፃን የያዙ ቤተሰቦች ወደ መንግሥት አዳራሻችን ሲመጡ አልፎ አልፎ የስሜት መረበሽ ያጋጥመኝ ነበር።

ከዚያም አንድ ቀን ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ በመጨረሻ ደመናው ከላዬ የተገፈፈ ሆኖ ተሰማኝ። ገና ዓይኔን እንኳ ሳልገልጥ ከደረሰብኝ የመንፈስ ስብራት እንዳገገምኩና ለወራት ያህል የራቀኝን ሰላምና መረጋጋት መልሼ እንዳገኘሁ ተሰምቶኝ ነበር። ሆኖም ልጁ ከጨነገፈብኝ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ነፍሰ ጡር መሆኔን ሳውቅ እንደገና ቢያስወርደኝስ የሚለው ሐሳብ ወደ አእምሮዬ መጣ። ደስ የሚለው ነገር ጥቅምት 2001 ላይ ጤናማ የሆነ ወንድ ልጅ ወለድኩ።

አሁንም ቢሆን የጨነገፈብኝ ልጅ ያስከተለብኝ ሐዘን አልወጣልኝም። ሆኖም የተከሰተው ሁኔታ በአጠቃላይ ለሕይወት፣ ለቤተሰቤና ለክርስቲያን ጓደኞቼ እንዲሁም መጽናኛ ለሚሰጠን አምላክ ያለኝን አድናቆት አሳድጎልኛል። እንዲሁም የደረሰብኝ ሁኔታ አምላክ ልጆቻችንን እንደማይወስድ ከዚህ ይልቅ “ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ [ሁላችንንም] እንደሚገናኘን” የሚገልጸውን መራራ እውነት በተጨባጭ አስገንዝቦኛል።​—⁠መክብብ 9:​11 NW

አምላክ የፅንስ መጨንገፍ የሚያስከትለውን አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ስቃይ ጨምሮ ሐዘንን፣ ጩኸትንና ስቃይን በሙሉ የሚያስወግድበትን ጊዜ በከፍተኛ ጉጉት እጠባበቃለሁ! (ኢሳይያስ 65:​17-23) በዚያ ጊዜ ታዛዥ የሰው ልጆች በአጠቃላይ “ሞት ሆይ፣ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፣ መንደፊያህስ የት አለ?” ማለት ይችላሉ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​55 አ.መ.ት፤ ኢሳይያስ 25:​8—⁠ተጽፎ የተላከልን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.13 እያንዳንዱ ሰው ለፅንስ መጨንገፍ የሚሰጠው ምላሽ ፈጽሞ የተለያየ መሆኑን ጥናታዊ ምርምሮች ያሳያሉ። አንዳንዶች ግራ ይጋባሉ፣ ሌሎች ይበሳጫሉ፣ ሌሎች ደግሞ በከባድ ሐዘን ይዋጣሉ። ተመራማሪዎች ሐዘን እንደ ፅንስ መጨንገፍ በመሳሰሉ ሁኔታዎች ውድ የሆነን ነገር በማጣት የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ስሜት እንደሆነና ሁኔታው ካስከተለው የስሜት መረበሽ ለመላቀቅ የሚቻልበት ሂደት አካል እንደሆነ ይናገራሉ።

^ አን.20 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የፅንስ መጨንገፍ ሊከሰት የሚችልበት መጠንና መንስኤዎቹ

ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ “ምርመራ ተደርጎላቸው ነፍሰ ጡር መሆናቸው ከተረጋገጠው ውስጥ ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት እንደሚጨነግፉ ጥናቶች ይጠቁማሉ” ይላል። “ሆኖም ከፅንስ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ፅንሱ ሊጨነግፍ የሚችልበት አጋጣሚ ከፍተኛ ሲሆን በዚህ ጊዜ አብዛኞቹ ሴቶች መፀነሳቸውን እንኳ አያውቁም።” አንድ ሌላ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ፅንሶች የሚጨነግፉት በተፀነሱ በመጀመሪያዎቹ 12 ሳምንታት ውስጥ” ሲሆን ከዚህ ውስጥ ቢያንስ ግማሹ በሽሉ ክሮሞሶም ላይ በሚፈጠር እክል ሳቢያ እንደሚከሰት ይገመታል ሲል ገልጿል። እነዚህ እክሎች በእናትየው ወይም በአባትየው ክሮሞሶም ውስጥ ካሉ ተመሳሳይ እክሎች የሚመነጩ አይደሉም።

ፅንስ እንዲጨነግፍ የሚያደርጉ ሌሎች መንስኤዎች ከእናትየው የጤንነት ሁኔታ ሊመነጩ ይችላሉ። የሕክምና ባለሙያዎች ከሆርሞን ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የሰውነት የበሽታ መከላከያ መቃወስ፣ ኢንፌክሽኖችና በእናትየው የማኅፀን አፍ ወይም ማኅፀን ውስጥ የሚፈጠሩ የተዛቡ ሁኔታዎች መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሐሳብ ሰንዝረዋል። እንደ ስኳር በሽታ (ተገቢው ጥንቃቄና ክትትል የማይደረግለት ከሆነ) እና የደም ግፊት የመሳሰሉ ሥር የሰደዱ በሽታዎችም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።

የሕክምና ጠበብት እንደሚሉት የፅንስ መጨንገፍ የግድ በአካል እንቅስቃሴ፣ ከባድ ዕቃዎችን በማንሳት ወይም የፆታ ግንኙነት በመፈጸም የሚከሰት ነገር አይደለም። መውደቅ፣ ቀላል የሆነ ምት ወይም ድንጋጤ የፅንስ መጨንገፍ ማስከተሉ አጠራጣሪ ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ጉዳቱ በራስሽ ሕይወት ላይ ስጋት የሚፈጥር እስካልሆነ ድረስ በሽሉ ላይ ጉዳት ያደርሳል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።” የማኅፀን ንድፍ ጥበበኛና አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ ለመኖሩ እንዴት ያለ ጠንካራ ማስረጃ ነው!​—⁠መዝሙር 139:​13, 14

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ቤተሰቦችና ጓደኞች እርዳታ መስጠት የሚችሉበት መንገድ

አንድ የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ የፅንስ መጨንገፍ ሲያጋጥመው አንዳንድ ጊዜ ምን ማለት ወይም ማድረግ እንደሚቻል ማወቅ ያስቸግራል። ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲገጥማቸው የሚሰጡት ምላሽ የተለያየ በመሆኑ ማጽናኛ ወይም እርዳታ መስጠት የሚቻልበት አንድ ወጥ የሆነ ደንብ የለም። ይሁን እንጂ ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት። *

እርዳታ መስጠት የምትችልባቸው ተግባራዊ መንገዶች:-

በዕድሜ ከፍ ያሉትን ልጆች ለተወሰነ ጊዜ ለመውሰድ ሐሳብ ማቅረብ።

ምግብ ሠርቶ በመሄድ ቤተሰቡን መጠየቅ።

ለአባትየውም ጭምር ድጋፍ መስጠት። አንድ አባት እንዳለው “ይህ ሁኔታ ለደረሰባቸው አባቶች ታስበው የተዘጋጁ ካርዶች የሉም።”

በሚከተሉት መንገዶች የሚያጽናኑ ቃላት መናገር ይቻላል፦

“የገጠመሽን ሁኔታ ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት።”

እነዚህ አጭር ቃላት ከፍተኛ ትርጉም ያዘሉ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ አጽናኝ ቃላት ለመናገር በር ሊከፍቱ ይችላሉ።

“ማልቀስሽ ምንም ጥፋት የለውም።”

ፅንሱ ከጨነገፈ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አልፎ ተርፎም ወራት አንዲት ሴት በቀላሉ ሆድ ሊብሳት ይችላል። ስሜቷን ገልጣ ስላወጣች ለእሷ ያላችሁ ግምት እንደማይቀንስ አረጋግጡላት።

“እንዴት እንደሆንሽ ለማወቅ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሜ ልደውልልሽ?”

መጀመሪያ ላይ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች የሚያስተዛዝኑ በርካታ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሐዘናቸው ገና ሳይወጣላቸው ሌሎች እንደረሷቸው ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። የምትሰጧቸው ድጋፍ ቀጣይነት እንዳለው ማወቃቸው ጠቃሚ ነው። ያደረባቸው ሐዘን ለሳምንታት ወይም ለወራት ሊቆይ ይችላል። በተሳካ ሁኔታ ፅንስ ከያዙም በኋላ እንኳ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊያገረሽ ይችላል።

“ምን ብዬ እንደማጽናናሽ አላውቅም።”

ዝም ከማለት እንዲህ ብሎ መናገሩ የተሻለ ነው። ሐቀኝነታችሁም ሆነ ለማጽናናት መምጣታችሁ አሳቢነታችሁን ያሳያል።

መባል የሌለበት ነገር:-

“በፈለግሽው ጊዜ ሌላ ልጅ መውለድ ትችያለሽ።”

ይህ ትክክል ሊሆን ቢችልም እንኳ አዘኔታ አለማሳየት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ወላጆቹ ማግኘት የፈለጉት እንዲሁ ማንኛውንም ልጅ ሳይሆን ያንን ልጅ ነበር። ሌላ ልጅ ስለመውለድ ማሰብ ከመጀመራቸው በፊት የሞተባቸው ልጅ ሐዘን እንዲወጣላቸው ይፈልጉ ይሆናል።

“ምናልባት አንድ ዓይነት እክል ይኖርበት ይሆናል።”

ይህ ትክክል ሊሆን ቢችልም እንኳ ያን ያህል የሚያጽናና አባባል አይደለም። እናትየው ሆድዋ ውስጥ ጤናማ ሕፃን እንደያዘች ነው የምታስበው።

“ቢያንስ ሕፃኑን አለማየትሽ አንድ ነገር ነው። የሞተው ከተወለደ በኋላ ቢሆን ኖሮ የባሰ አሳዛኝ ይሆን ነበር።”

ብዙ ሴቶች በማኅፀናቸው ውስጥ ካለው ሕፃን ጋር ትስስር የሚፈጥሩት ገና ከጅምሩ ነው። በመሆኑም ሕፃኑ ሲሞት በሐዘን እንደሚደቆሱ የሚጠበቅ ነገር ነው። ሕፃኑን የእናትየውን ያህል “የሚያውቀው” ሌላ ሰው አለመኖሩ ሐዘኑን ያባብሰዋል።

“ደግነቱ ሌሎች ልጆች አሉሽ።”

በሐዘን ለተደቆሱት ወላጆች እንዲህ ብሎ መናገር አንድ እጁን ላጣ ሰው “ቢያንስ አንድ እጅ ቀርቶልሃል” ከማለት ላይተናነስ ይችላል።

እርግጥ ነው፣ በጣም አሳቢና ቅን የሆኑ ሰዎችም ሳይቀር አልፎ አልፎ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሊናገሩ እንደሚችሉ መቀበል ያስፈልጋል። (ያዕቆብ 3:​2) በመሆኑም ፅንስ የጨነገፈባቸው አስተዋይ የሆኑ ሴቶች ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየት የሚፈልጉ ከመሆኑም በላይ እነሱን ለመጥቀም አስበው እያለ ጥበብ በጎደለው መንገድ የሚናገሩ ሰዎች በሚሰጡት ሐሳብ ቅያሜ አያሳድሩም።​—⁠ቆላስይስ 3:​13

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.36 በኒው ዚላንድ፣ ዌሊንግተን የሚገኘው ሚስካሪጅ ሰፖርት ግሩፕ የተባለው ማኅበር ካዘጋጀው ኤ ጋይድ ቱ ኮፒንግ ዊዝ ሚስካሪጅ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።