በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብረውኝ ለሚማሩት ልጆች መስበክ የምችለው እንዴት ነው?

አብረውኝ ለሚማሩት ልጆች መስበክ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

አብረውኝ ለሚማሩት ልጆች መስበክ የምችለው እንዴት ነው?

“እየሰበክሁ ሳለ ድንገት አንድ የማውቀው ሰው አጋጠመኝ። በድንጋጤ ክው ብዬ ቀረሁ! አብሮኝ ያገለግል የነበረው ሰው ጣልቃ ገብቶ በእኔ ፋንታ መናገር ነበረበት።”​አቤርቶ

“የክፍል ጓደኛዬ የሆነ ልጅ በዚህ አካባቢ እንደሚኖር ስላወቅሁ ሁሉንም ቤቶች ወንድሜ እንዲያንኳኳ አደረግሁ። በኋላ ግን ወንድሜ ትንሽ ስለበዛበት የሚቀጥለውን በር እኔ እንዳንኳኳ ጠየቀኝ። እንዳለኝ አደረግሁ፤ የፈራሁት አልቀረም፣ እሱ ራሱ ነበር! እንዴት እንደደነገጥኩ ልነግራችሁ አልችልም”!—ጄምስ

ብዙውን ጊዜ ወጣቶች ስለ ሃይማኖት መወያየት “አይጥማቸውም።” በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያሉ ወጣቶች ግን ከአምላክ ያገኙትን እምነታቸውን ለሌሎች የማካፈል መብት ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በመሆኑም በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው የስብከት ሥራ ይካፈላሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ይህንን ሥራ የሚሠሩት ትምህርት ቤት የሚያውቁት ሰው እንዳያገኙ እየፈሩ ነው። ጄኒፈር የተባለችው ወጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች የተወሰኑ ዓመታት ቢያልፉም “አሁንም ቢሆን አብሬያቸው የተማርኳቸውን ልጆች እንዳላገኝ እፈራለሁ” ትላለች።

አንተም ወጣት ክርስቲያን ከሆንክ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ይሰማህ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ሁላችንም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማጣት ያስፈራናል። ስለዚህ አብሮህ ከሚማር ልጅ ጋር ስለ ሃይማኖት መወያየት ትንሽ ቢያስፈራህ ምንም አያስደንቅም። * ይሁን እንጂ በፍርሃት የምትብረከረክበት ምንም ምክንያት የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የአርማትያሱ ዮሴፍ’ ብሎ የሚጠራውን ሰው ታስታውሰዋለህ? ከኢየሱስ በተማራቸው ነገሮች ያምን ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዮሴፍ ሲናገር “አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ” ይላል። (ዮሐንስ 19:38) ጓደኝነታችሁ በምስጢር እንዲያዝ የሚፈልግ ጓደኛ ቢኖርህ ምን ይሰማሃል? (ሉቃስ 12:8, 9) እንግዲያው አምላክ ክርስቲያኖች የሆኑ ሁሉ ስለ እምነታቸው “እንዲመሰክሩ” ቢጠብቅባቸው ምንም አያስገርምም። (ሮሜ 10:10) ይህም በትምህርት ቤታችሁ ላሉት ወጣቶች መመሥከርን ይጨምራል።

የአርማትያሱ ዮሴፍ ሌላው ቢቀር በተወሰነ መጠን ፍርሃቱን አሸንፎ የኢየሱስን አስከሬን ለመቅበር ፈቃድ ጠይቋል። አንተስ ፍርሃትህን ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?

ለመስበክ ጉጉት ማሳደር

ሐዋርያው ጳውሎስ እምነቱን ለሌሎች ማካፈል አያሳፍረውም ነበር። በሮሜ 1:​15 [አ.መ.ት] ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስበክ እንደሚጓጓ ተናግሯል! እንዲህ ዓይነት ጉጉት ሊያድርበት የቻለው ለምንድን ነው? በቁጥር 16 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው እንዲህ ብሏል:- “በወንጌል አላፍርም፤ ምክንያቱም ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ነው።” አንተስ? እውነትን ፈትነህ አውቀኸዋልን? (ሮሜ 12:2) የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት “ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል” መሆኑን በግልህ አምነህበታልን?

ከወላጆችህ ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ብቻውን በቂ አይደለም። ዴብራ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች:- “ወላጆችህ እንድትሄድ ስለሚነግሩህ ብቻ ወደ ስብሰባዎች መሄድ ቀላል ነው። ሆኖም ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ሲያቀርቡልኝ ምን ብዬ መመለስ እንዳለብኝ አላውቅም።” ሚ ያንግ የተባለች ወጣትም በተመሳሳይ “ይህ እውነት መሆኑን ራሳችንን ማሳመን አለብን” በማለት ሐቁን ተናግራለች።

የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህን ለሌሎች እንድታካፍል ምን ሊገፋፋህ ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስን በግልህ ማጥናት አለብህ። ሾን የተባለ ወጣት እንዲህ ይላል:- “በግልህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር እውነትን የራስህ ታደርገዋለህ። የምታጠናው ለራስህ ይሆናል።” እውነት ነው፣ ሁሉም ሰው በተፈጥሮው አንባቢ አይደለም። ሼቮን የተባለች ወጣት “ማንበብ አልወድም” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። “በመሆኑም መጀመሪያ ላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ማንበብ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ ያስቸግረኝ ነበር። ሆኖም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እንደዚያ ማድረግ ጀመርኩ።”

እንዲህ ያለው ትጋት የታከለበት ጥናት ምን ውጤት ያስገኛል? ሐዋርያው ጳውሎስ “እምነት ከመስማት ነው” ብሏል። (ሮሜ 10:17) እምነትህ እያደገ ሲሄድ አመለካከትህም እንደሚለወጥ ምንም ጥርጥር የለውም። ኤሊዛጄላ የተባለች ብራዚላዊት ወጣት የሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሳለች:- “ክርስቲያን መሆን የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር ነገር አይደለም።” በእርግጥም እምነትህ እያደገ ሲሄድ አብረውህ የሚማሩትን ልጆች ጨምሮ ለሌሎችም ለመመስከር ትገፋፋለህ። ጳውሎስ “እኛ . . . እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 4:13) ደግሞስ በየቀኑ ለምታገኛቸው ልጆች ሕይወት የሚያስገኘውን እውቀት ካልነገርካቸው እንዴት ከሌሎች “ደም ንጹሕ” መሆን ትችላለህ?​—⁠ሥራ 20:26, 27

ሆኖም አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች ለሌሎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመናገር በቂ ዝግጅት እንዳላደረጉ ይሰማቸዋል። ኢያሱ የተባለ ወጣት “ምን ማለት እንዳለብህ ካላወቅህ ለመስበክ መሞከር እምብዛም አስደሳች አይደለም” ብሏል። አሁንም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት መረዳትህ ብቃቱ እንዲኖርህ ያደርጋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ወጣቶች ወደ ጉባኤ ሽማግሌዎች ቀርበው የማስተማር ችሎታቸውን ለማዳበር በግል እርዳታ እንዲደረግላቸው መጠየቅ ይችላሉ። ማትያስ የተባለ ጀርመናዊ ወጣት እንዲህ ይላል:- “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲወስዱ በመጋበዝ ሳልወሰን ከሰዎች ጋር ውይይት ማድረግ ስጀምር መስበክ ያስደስተኝ ጀመር።”

በመጨረሻም በድፍረት ለመናገር እንዲረዳህ ወደ አምላክ መጸለይ ትችላለህ። (ሥራ 4:29) በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ በግሉ ከአምላክ እርዳታ አግኝቷል። በ1 ተሰሎንቄ 2:​2 ላይ እንዲህ ብሏል:- “በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን።” አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳስቀመጠው ከሆነ ይህ ዓረፍተ ነገር “አምላክ ፍርሃትን ከልባችን ውስጥ አውጥቶ ጣለልን” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። እንግዲያው አምላክ ፍርሃትን ከልብህ አውጥቶ እንዲጥልልህ ለምን በጸሎት አትጠይቀውም?

ማንነትህን አሳውቅ

ከጸሎትህ ጋር በሚስማማ መንገድ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ውሰድ። ሺክ የተባለች እንግሊዛዊት ወጣት “አብረውህ ለሚማሩት ልጆች ክርስቲያን እንደ ሆንክ ንገራቸው” ስትል ትመክራለች። ‘ኅቡዕ ደቀ መዝሙር’ መሆን አትፈልግም። ርብቃ የተባለች ወጣት በአንድ ወቅት በስብከቱ ሥራ ላይ እያለች የምታውቀው ሰው ማግኘት ያስፈራት እንደነበረ አምናለች። ይሁን እንጂ “ክርስቲያን እንደሆንክና ከቤት ወደ ቤት እንደምትሄድ ከነገርካቸው አንዳንድ ጊዜ ‘ወደ እኔ ቤትም ትመጣላችሁ?’ ብለው” እንደሚጠይቁ መገንዘቧን ተናግራለች።

ሆኖም በአጋጣሚ እስክትገናኙ ለምን ትጠብቃለህ? በትምህርት ቤት ስለ እምነትህ ለመናገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ፈልግ። ሐዋርያው ጳውሎስ ያነሳቸውን የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስታውስ:- “ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” (ሮሜ 10:14) አብረውህ የሚማሩት ልጆች ምሥራቹን እንዲሰሙ ለመርዳት ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ አለህ። ኢራይዳ የተባለች ወጣት “ትምህርት ቤት እኛ ብቻ ማገልገል የምንችልበት የስብከት ክልል ነው” ብላለች። በዚህም ምክንያት ብዙ ወጣቶች መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በመስጠት አጋጣሚውን ይጠቀሙበታል።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለማካፈል የሚያስችል አጋጣሚ የሚፈጥሩ የክፍል ሥራዎች ይሰጡሃል። ጄሚ የተባለች እንግሊዛዊት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “በሳይንስ ክፍለ ጊዜ ስለ ዝግመተ ለውጥ እየተወያየን ነበር፤ እምነቴን ስናገር ከተማሪዎቹ አንዱ አፌዘብኝ። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮች ዝቅተኛ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ስለሆኑ ትምህርት ቤት መግባት እንደሌለባቸው ተናገረ። ይሁን እንጂ ወዲያውኑ ሌሎቹ ተማሪዎች ለእኔ አገዙ።” በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በአርአያነቷ የምትጠቀስ ክርስቲያን በመሆን ያተረፈችው መልካም ስም ዋጋ አስገኝቷል። ጄሚ እንዲህ ስትል አክላ ተናግራለች:- “በውጤቱም ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ አለን? የተባለውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ አብራኝ ለምትማር ልጅ አበረከትኩ።” *

ሚኩ የተባለች በሩማንያ የምትኖር የ14 ዓመት ልጃገረድም ተመሳሳይ ተሞክሮ አላት:- “መምህሬ ስለ አልኮል መጠጦች፣ ትምባሆና ዕፆች በክፍል ውስጥ ውይይት እንደሚደረግ ተናገረች። ስለዚህ ‘ሲጋራ ማቆም የምትችልበት መንገድ’ የሚል ርዕስ ያለውን የሰኔ 2000 ንቁ! ይዤ ሄድኩ። አብራኝ የምትማር ልጅ መጽሔቱን አይታው ወሰደችውና ልትመልስልኝ አልፈለገችም። መጽሔቱን ካነበበች በኋላ ማጨስ ለማቆም እንደቆረጠች ተናገረች።”

ሁልጊዜ እንደዚህ ዓይነት አዎንታዊ ምላሽ አታገኝ ይሆናል። ሆኖም መክብብ 11:6 እንዲህ ሲል ያሳስበናል:- “ማናቸው እንዲበቅል . . . አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፣ በማታም እጅህን አትተው።” በትምህርት ቤት እምነትህን ለሌሎች ማካፈልህ ሌላው ቢቀር አንድ ቀን ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል አብሮህ የሚማር ልጅ ብታገኝ ይበልጥ አስደሳች የሆነ ውይይት ለመጀመር መንገድ ይጠርጋል። ጄሲካ የተባለች እንግሊዛዊት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “ቀድሞውኑም ትውውቅ ስላላችሁ በትምህርት ቤት ለምታውቋቸው ልጆች መመስከር እንዲያውም ቀላል ነው።” አብረውህ ከሚማሩት ልጆች አንዳንዶቹ ስለ እምነትህ ለማወቅ ምን ያህል እንደሚጓጉ ስታይ ትገረም ይሆናል።

እውነት ነው፣ ሁሉም በደግነት ላይቀበሉህ ይችላሉ። ሆኖም ኢየሱስ የሚከተለውን ተግባራዊ ምክር ሰጥቷል:- “ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፣ ከዚያ ቤት . . . ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።” (ማቴዎስ 10:14) በሌላ አባባል አንተን በግል እንዳልተቀበሉህ አድርገህ ማሰብ የለብህም። ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ትተሃቸው በመሄድ ለመስማት ይበልጥ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልግ። ይዋል ይደር እንጂ እውነትን የተራቡና ለመስማት ፈቃደኛ የሆኑ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ማግኘትህ አይቀርም። ከእነዚህ አንዱ አብሮህ የተማረ ልጅ ቢሆን የሚክስ አይሆንም? እንደዚያ ከሆነ አብረውህ ለሚማሩት ልጆች እምነትህን በማካፈል ረገድ የነበረህን ፍርሃት በማሸነፍህ ደስተኛ ትሆናለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 በመጋቢት 2002 እትማችን ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . ትምህርት ቤት የማውቀው ሰው ቢያጋጥመኝስ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.18 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በግልህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር እውነትን የራስህ ታደርገዋለህ።”​—ሾን

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን መሆንህን ለመናገር አትፍራ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብዛኛውን ጊዜ የክፍል ሥራዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለማካፈል አጋጣሚ ይሰጣሉ