የበደለኛነት ስሜት ሁልጊዜ መጥፎ ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የበደለኛነት ስሜት ሁልጊዜ መጥፎ ነው?
ዛሬ ያሉ ብዙ ሰዎች የበደለኛነት ስሜት መጥፎ እንደሆነ ይሰማቸዋል። “የበደለኛነት ስሜት የሰውን ልጅ ካሸነፉት በሽታዎች ሁሉ የከፋው ነው” ብሎ ከተናገረው ጀርመናዊ ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒይትሽ ጋር የሚመሳሰል አመለካከት አላቸው።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ተመራማሪዎች ከዚህ የተለየ መደምደሚያ ላይ እየደረሱ ነው። ዶክተር ሱዛን ፎርዋርድ የተባሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ ቴራፒስትና ደራሲ እንዲህ ይላሉ:- “የበደለኛነት ስሜት አሳቢ የሆነና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ሊኖረው የሚገባ አስፈላጊ ባሕርይ ነው። የሕሊና ክፍል ነው።” እንግዲያው የበደለኛነት ስሜት በአጠቃላይ መጥፎ ነውን? የበደለኛነት ስሜት ጠቃሚ ሊሆን የሚችልባቸው ሁኔታዎች ይኖሩ ይሆን?
የበደለኛነት ስሜት ምንድን ነው?
አንድ የምንወደውን ሰው እንዳሳዘንን ስንረዳ አሊያም ልንመራበት እንደሚገባን የምናስበውን የአቋም ደረጃ ሳናሟላ ስንቀር የበደለኛነት ስሜት ይፈጠራል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው በደለኛነት “አንድ ሰው ማድረግ የሚገባውን ባለማድረጉ፣ ሌሎችን በማስቀየሙ አለዚያም ወንጀል ወይም ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት የሚሰማው የባለ ዕዳነት ስሜት” ነው።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በደለኛነት አንድ እስራኤላዊ ከአምላክ ሕግ ጋር ተስማምቶ መኖር ካለመቻሉ ጋር ተዛምዶ የተገለጸ ሲሆን ቃሉ ከተጠቀሰባቸው ቦታዎች መካከል አብዛኞቹ የሚገኙት በዘሌዋውያንና በዘኁልቁ መጽሐፍ ውስጥ ነው። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥም በተመሳሳይ የበደለኛነት ጽንሰ ሐሳብ በአምላክ ላይ ከባድ ኃጢአት መሥራትን ያመለክታል።—ማርቆስ 3:29 NW ፤ 1 ቆሮንቶስ 11:27 NW
የሚያሳዝነው ግን በደለኞች ሳንሆን የበደለኛነት ስሜት ሊሰማን የሚችል መሆኑ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ፍጽምናን የሚጠብቅ ከሆነና ለራሱ ምክንያታዊ ያልሆኑ መሥፈርቶች የሚያወጣ ከሆነ ያወጣውን መሥፈርት ማሟላት ሳይችል በቀረ ቁጥር ተገቢ ያልሆነ የበደለኛነት ስሜት ሊሰማው ይችላል። (መክብብ 7:16) ወይም ደግሞ ስህተት ሠርተን የተሰማን ተገቢ ጸጸት የኃፍረት ስሜት እንዲሰማን እንዲያደርገንና ራሳችንን አላግባብ ወደ መቅጣት እንዲያደርሰን እንፈቅድ ይሆናል። እንግዲያው የበደለኛነት ስሜት ምን ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል?
የበደለኛነት ስሜት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል
የበደለኛነት ስሜት ቢያንስ በሦስት መንገዶች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ተቀባይነት ያላቸውን መሥፈርቶች እንደምናውቅ ያመለክታል። የሚሠራ ሕሊና እንዳለን ያሳያል። (ሮሜ 2:15) እንዲያውም በአሜሪካ የሥነ አእምሮ ማኅበር የታተመ አንድ መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ የበደለኛነት ስሜት አለመኖር ለኅብረተሰቡ አስጊ የሆነ ባሕርይ ነው። ሕሊናቸው የቆሸሸ ወይም የደነዘዘ ሰዎች ትክክልና ስሕተት በሆነው መካከል ያለውን ልዩነት ማየት ያስቸግራቸዋል፤ ይህ ደግሞ አደገኛ ነው።—ቲቶ 1:15, 16
በሁለተኛ ደረጃ፣ የበደለኛነት ስሜት መጥፎ ድርጊቶችን ለማስወገድ ይረዳናል። አካላዊ ሕመም የጤና ችግር እንዳለን እንደሚያመለክት ሁሉ ከበደለኛነት ስሜት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ስሜታዊ ስቃይም ትኩረታችንን የሚሻ ሥነ ምግባራዊ ወይም መንፈሳዊ ችግር እንዳለ ይጠቁመናል። አንድ ጊዜ ድክመታችንን ካወቅን በኋላ ራሳችንን፣ የምንወዳቸውን ሰዎች ወይም ሌሎችን ደግመን ላለመጉዳት ይበልጥ እንጠነቀቃለን።—ማቴዎስ 7:12
በመጨረሻም፣ በደልን መናዘዝ በደለኛውንም ሆነ በደል የተፈጸመበትን ሰው ይጠቅማል። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ዳዊት የፈጸመው በደል ከባድ የስሜት ሥቃይ አስከትሎበት ነበር። “ኃጢአቴን ሳልናዘዝ ቀኑን ሙሉ በማልቀሴ ምክንያት፣ ሰውነቴ ደከመ [የ1980 ትርጉም ]” በማለት ጽፏል። ኃጢአቱን ለአምላክ ከተናዘዘ በኋላ ግን “ከከበቡኝ ታድነኝ ዘንድ ደስታዬ ነህ” ሲል በደስታ ዘምሯል። (መዝሙር 32:3, 7) በደልን መናዘዝ ተበዳዩ ግለሰብም ጥሩ ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል። ምክንያቱም በዳዩ ጥፋቱን አመነ ማለት ሌላውን ሰው የሚያሳዝን ነገር በማድረጉ ተጸጽቷል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለተበዳዩ ምን ያህል ፍቅር እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው።—2 ሳሙኤል 11:2-15
የበደለኛነትን ስሜት በተመለከተ ሊኖረን የሚገባ ሚዛናዊ አመለካከት
የበደለኛነት ስሜትን በተመለከተ ሊኖረን ስለሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት ለማወቅ ኢየሱስ እና ፈሪሳውያን ኃጢአትንና ኃጢአተኞችን በሚመለከቱበት መንገድ መካከል የነበረውን የጎላ ልዩነት ልብ በል። በሉቃስ 7:36-50 ላይ ኢየሱስ እየተመገበበት ወደነበረው አንድ ፈሪሳዊ ቤት ስለገባች ብልሹ ሥነ ምግባር የነበራት ሴት እናነባለን። ሴትዮዋ ወደ ኢየሱስ ቀርባ እግሮቹን በእንባዋ እያጠበች ውድ የሆነ ሽቶ ቀባችው።
ሃይማኖተኛው ፈሪሳዊ ለዚህች ሴት ጊዜውንና ትኩረቱን ሊሰጣት እንደማይገባ በማሰብ ናቃት። ለራሱም እንዲህ አለ:- “ይህስ [ኢየሱስ] ነቢይ ቢሆን፣ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፣ ኃጢአተኛ ናትና።” (ሉቃስ 7:39) ኢየሱስ ወዲያው አረመው። “አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። ስለዚህ እልሃለሁ፣ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል” አለው። እነዚህ ደግነት የተሞላባቸው ቃላት ሴትዮዋን እንዳበረታቷትና ልቧ በደስታ እንዲፈነድቅ እንዳደረጉት ምንም ጥርጥር የለውም።—ሉቃስ 7:46, 47
ኢየሱስ ሥነ ምግባራዊ ብልግናን በቸልታ መመልከቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አምላክን ለማገልገል የሚገፋፋን ዋነኛው ነገር ፍቅር ሊሆን እንደሚገባ ለኩሩው ፈሪሳዊ እያስተማረው ነበር። (ማቴዎስ 22:36-40) እርግጥ ነው ሴትየዋ ከዚህ ቀደም ለፈጸመችው ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት በደለኛነት ሊሰማት ይገባል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለውም ንስሐ ገብታለች፤ ምክንያቱም ለቀድሞ አኗኗሯ ሰበብ ለመፍጠር ምንም ጥረት ሳታደርግ እንባዋን ያፈሰሰች ከመሆኑም በላይ ኢየሱስን በሕዝብ ፊት በማክበር ተገቢውን እርምጃ ወስዳለች። ኢየሱስ ይህንን ሲመለከት “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።”—ሉቃስ 7:50
በሌላ በኩል ግን ፈሪሳዊው እርስዋን እንደ ኃጢአተኛ መመልከቱን አላቆመም። ምናልባትም ‘በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ እንደሆነች ማሳሰብና’ የበደለኛነት ስሜት እንዲሰማት ማድረግ ፈልጎ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሌሎች አንድን ነገር እኛ በምናስበው መንገድ ስላልሠሩ ያለማቋረጥ መውቀስ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ከመሆኑም በላይ የኋላ ኋላ መጥፎ ውጤት ይኖረዋል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ልክ እንደ ኢየሱስ ትክክለኛ አርዓያ በመሆን፣ ሌሎችን ከልባችን በማመስገን እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ እርማት ወይም ምክር መስጠት ሊያስፈልግ ቢችልም እንኳ እንደምንተማመንባቸው በመግለጽ የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል።—ማቴዎስ 11:28-30፤ ሮሜ 12:10፤ ኤፌሶን 4:29
እንግዲያው ስህተት በምንሠራበት ጊዜ በውስጣችን የሚፈጠረው የበደለኛነት ስሜት ጠቃሚ አልፎ ተርፎም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ምሳሌ 14:9 [የ1980 ትርጉም ] እንዲህ ይላል:- “ሰነፎች ኃጢአት ሲሠሩ በመጸጸት ፈንታ ያፌዛሉ።” የበደለኛነት ስሜት እንድንናዘዝና ሌሎች አስፈላጊ እርምጃዎችን እንድንወስድ ሊገፋፋን ይችላል፣ ይገባልም። ሆኖም ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋን ለማገልገል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት የበደለኛነት ስሜት ሳይሆን ፍቅር ሊሆን ይገባል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) መጽሐፍ ቅዱስ መልካም ሰዎች በዚህ መንገድ ማበረታቻና ማነቃቂያ ሲያገኙ አቅማቸው የፈቀደላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ያረጋግጥልናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ እንደዚያ በማድረጋቸው ይደሰታሉ።