አብሮኝ የሚኖረው ልጅ ፀባይ ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
አብሮኝ የሚኖረው ልጅ ፀባይ ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
“እኔ በተፈጥሮዬ የተዝረከረከ ነገር አልወድም። ሆኖም ወደ ቤት ስመለስ አብሮኝ የሚኖረው ልጅ ክፍሉን በወረቀትና በፈንዲሻ ሞልቶት ወለሉ ላይ ተዘርግቶ ቴሌቪዥን ሲመለከት አገኘዋለሁ። ወደ ቤት ለመሄድ ባሰብሁ ቁጥር ቤት የሚጠብቀኝ ነገር እየታየኝ ‘ኡፍ፣ አሁን ደግሞ እዚያ የተዝረከረከ ቤት ውስጥ ልገባ ነው’ እላለሁ።”— ዳዊት
“አብራኝ ትኖር የነበረችው ልጅ ተሞላቅቃ ያደገች ቀበጥ ልጅ ነበረች። የቀጠረችው ሠራተኛ ያለ ይመስል ሁሉ ነገር እንዲሠራላት ትጠብቃለች። ማንኛውም ነገር እሷ ባለችው መንገድ እንዲከናወን ትፈልጋለች።”— ረኔ *
ዩኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ “የአንድን ሰው ለየት ያሉ ባህርያት ችሎ መኖር . . . ግትር አለመሆንንና ከእኔ ይቅር ማለትን ያስተምራል” ብሏል። “ሆኖም የመማሩ ሂደት ብዙውን ጊዜ ቀላል አይሆንም።” ከሌላ ሰው ጋር አብረው የኖሩ ወጣቶች በዚህ አባባል ሳይስማሙ አይቀሩም።
ብዙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለትምህርት ቤት የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ ሲሉ ከሌላ ሰው ጋር አብረው ይኖራሉ። ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ከወላጆቻቸው ተለይተው ራሳቸውን ችለው ለመኖር ሲሉ አብሯቸው የሚኖር ሰው ይፈልጋሉ። ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች መንፈሳዊ ግቦችን ለመከታተል ሲሉ ከሌሎች ጋር ለመኖር መርጠዋል። (ማቴዎስ 6:33) የኑሮ ወጪዎችን የሚጋራቸው ሰው ማግኘታቸው የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው ለማገልገል አስችሏቸዋል። ለሚስዮናውያንና በተለያዩ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለሚያገለግሉ ወጣቶችም ከሌሎች ጋር አብሮ መኖር አንዱ የሕይወታቸው ክፍል ነው። *
ንቁ! ከሌሎች ጋር አብረው ይኖሩ የነበሩ በርካታ ወጣት ወንዶችንና ሴቶችን አነጋግሯል። ከሌላ ሰው ጋር አብሮ መኖር የቤት ኪራይ ወጪን በመቀነስ ረገድ እገዛ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ስሜትን የሚጋራና አብሮ ነገሮችን የሚያከናውን ጓደኛ እንደሚያስገኝ ሁሉም ይስማማሉ። ሊን “ቁጭ ብለን ስናወራ ወይም ፊልም ስናይ እናመሽ ነበር” በማለት ታስታውሳለች። ረኔ ደግሞ “አብሯችሁ የሚኖር ሰው ሊያበረታታችሁ
ይችላል” ትላለች። “ኑሯችሁን ለማሸነፍ ስትሠሩ፣ ወጪዎቻችሁን ለመሸፈንና ለመስበክ ስትጥሩ አብሯችሁ የሚኖር የሚያበረታታ ሰው ማግኘት ያስደስታል።”ያም ሆኖ ከሌላ ሰው ጋር በተለይም መጀመሪያ ላይ ፈጽሞ ከማታውቀው ሰው ጋር አብሮ መኖር በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት በኮሌጅ ስላለው ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “በርካታ ትምህርት ቤቶች እርስ በርስ ሊጣጣሙ የሚችሉ ወጣቶችን አንድ ላይ ለማድረግ ብዙ ጥረት ቢያደርጉም ውጤቱ የተጠበቀውን ያህል ሆኖ አልተገኘም።” እንዲያውም በኮሌጅ ውስጥ አብረው በሚኖሩ ልጆች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ወደ ብጥብጥ አምርተዋል! በዚህም ምክንያት ተማሪዎች አብረዋቸው ስለሚኖሩት ልጆች የሚሰማቸውን ምሬት የሚገልጹባቸው የኢንተርኔት ዌብ ገጾች ተዘጋጅተዋል። ከሌላ ሰው ጋር አብሮ መኖር አብዛኛውን ጊዜ አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው?
ከማያውቁት ሰው ጋር መኖር
ማርክ እንዲህ ይላል:- “ከማያውቁት ሰው ጋር መኖር አንድ ራሱን የቻለ ገጠመኝ ነው። ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ አታውቁም።” ምናልባት ከአንተ ጋር ብዙም የሚመሳሰልበት ነገር ከሌለው ወይም ጨርሶ ከአንተ ጋር ከማይገጥም ሰው ጋር ለመኖር ማሰብ ራሱ ሊከብድ ይችላል። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች የሚያመሳስሏቸው በርካታ ነገሮች ስለሚኖሯቸው የሚያወሩት አያጡም። ያም ሆኖ ዳዊት እንዲህ ሲል ሐቁን ተናግሯል:- “ከሌላ ሰው ጋር አብሮ መኖር በጣም ያስፈራኝ ነበር።”
ሆኖም ከዳዊት ጋር አብሮ እንዲኖር የተመደበው ልጅ ከእሱ ጋር የሚመሳሰል አስተዳደግ ነበረው። ይሁን እንጂ ሁሉም ወጣቶች እንዲህ እንደሚፈልጉት ይሆንላቸዋል ማለት አይደለም። ማርክ እንዲህ ይላል:- “መጀመሪያ ላይ አብሮኝ ይኖር የነበረው ልጅ እምብዛም የማያወራ ነበር። ከአንድ ሰው ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ አብራችሁ ስትኖሩ ማውራት እንደምትፈልጉ የታወቀ ነው። እሱ ግን አያወራም። ይህም ያናድደኝ ነበር።”
የአስተዳደግ ልዩነትም ለውጥረትና ለጭንቀት ሊዳርግ ይችላል። ሊን እንዲህ ትላለች:- “ራሳችሁን ችላችሁ መኖር ስትጀምሩ ነገሮችን እናንተ በምትፈልጉት መንገድ ማከናወን ትፈልጋላችሁ። ሆኖም ብዙም ሳትቆዩ የሌሎች ሰዎችን ፍላጎትም ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባችሁ ትገነዘባላችሁ።” በእርግጥም የደህንነት ስሜት እንዲሰማህ ከሚያደርግህ የወላጆችህ ቤት ወጥተህ ሌሎች ሰዎች ለነገሮች ያላቸውን ከአንተ የተለየ አመለካከት ስታይ በጣም ትገረም ይሆናል።
የአስተዳደግና የአመለካከት ልዩነት
አብዛኞቹ ልዩነቶች የሚፈጠሩት አንድ ልጅ ከወላጆቹ ስልጠና በማግኘቱ ወይም ባለማግኘቱ ምክንያት ነው። (ምሳሌ 22:6) ወጣቱ ፌርናንዶ እንዲህ ይላል:- “እኔ ንጹሕ ነገር እወዳለሁ፤ አብሮኝ የሚኖረው ልጅ ደግሞ ዝርክርክ ብጤ ነበር። ለምሳሌ ያህል ቁም ሳጥኑን ብንመለከት እሱ ዕቃዎቹን በየቦታው መወርወር ይወድዳል። እኔ ደግሞ ልብሶቼን በመስቀያ አድርጌ ማንጠልጠል ያስደስተኛል።” አንዳንድ ጊዜ በምናወጣቸው መሥፈርቶች መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው።
ረኔ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “በአንድ ወቅት አብራኝ ትኖር የነበረችው ልጅ መኝታ ክፍሏ ቃል በቃል የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ይመስል ነበር! ምግብ ከበሉ በኋላ ጠረጴዛቸውን ከማያጸዱ ወይም የበሉባቸውን ሰሃኖች ለሁለትና ለሦስት ቀናት በዕቃ ማጠቢያው ውስጥ ከሚተዉ ልጆችም ጋር ኖሬአለሁ።” በቤት ውስጥ ሥራዎች ረገድ “መዝጊያ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፣ ሰነፍም በአልጋው ላይ መገላበጥ ያበዛል” የሚሉት የምሳሌ 26:14 [የ1980 ትርጉም ] ቃላት በአንዳንድ ወጣቶች ላይ የሚሠሩ ይመስላል።
በሌላ በኩል ደግሞ በንጽህና ረገድ ወደ ሌላኛው ጽንፍ ከሚሄድ ሰው ጋር መኖርም አስደሳች አይደለም። ሊ የተባለች አንዲት ወጣት ሴት አብራት ስለምትኖረው ልጅ ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “እንደ እስዋ ከሆነ ክፍሉ በየሰዓቱ መጽዳት አለበት። እኔም ብሆን ዝርክርክ የምባል አይደለሁም፤ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ እንደ መጻሕፍት ያሉ ዕቃዎችን አልጋዬ ላይ እተዋለሁ። እሷ ደግሞ እያንዳንዱን ነገር መቆጣጠር ትፈልጋለች።”
አብሮህ የሚኖረው ሰው ንጽህናን በተመለከተ የራሱ የሆነ አመለካከት ይኖረው ይሆናል። ማርክ እንዲህ ይላል:- “አብሮኝ የሚኖረው ልጅ በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ይነሳል። ከዛም ወደ ቧንቧው ይሄድና ራሱ ላይ ውኃ አርከፍክፎ ወጥቶ ይሄዳል።”
የአስተዳደግና የባህርይ ልዩነቶች በመዝናኛ ምርጫ ረገድም ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ማርክ አብሮት ስለሚኖረው ልጅ ሲናገር “የሙዚቃ ምርጫችን ለየቅል ነው”
ብሏል። የጋራ መከባበር ሲኖር እንዲህ ዓይነት ልዩነቶች ምናልባት ሁለቱም አመለካከታቸውን እንዲያሰፉ ስለሚረዷቸው ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ዓይነት ልዩነቶች ግጭት ያስከትላሉ። ፌርናንዶ “እኔ የስፓንኛ ሙዚቃ እወዳለሁ። አብሮኝ የሚኖረው ልጅ ግን ሁልጊዜ ያንቋሽሸዋል” ብሏል።ስልክ–ሌላው ችግር
የስልክ አጠቃቀም ለግጭት መንስኤ ከሚሆኑት ነገሮች መካከል ትልቁን ቦታ ሳይዝ አይቀርም። ማርክ እንዲህ ይላል:- “እኔ መተኛት እፈልግ ይሆናል። ሆኖም አብሮኝ የሚኖረው ልጅ በስልክ ሲያወራ ያመሻል። ይህም ሲደጋገም ያበሳጫል።” ሊንም በተመሳሳይ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “አንዳንድ ጊዜ አብራኝ የምትኖረው ልጅ ጓደኞች ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት ወይም በአሥር ሰዓት ይደውላሉ። እሷ ከሌለች ተነስቼ ስልኩን ማንሳት ይኖርብኛል።” ለዚህ ችግር ምን መፍትሔ አገኙለት? “እያንዳንዳችን የየራሳችን ስልክ እንዲኖረን አደረግን።”
ሆኖም ሁሉም ወጣቶች የየራሳቸው ስልክ እንዲኖራቸው ማድረግ ስለማይችሉ አብዛኞቹ በአንድ ስልክ በጋራ ለመጠቀም ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ ችግሮች እንዲፈጠሩ መንገድ ሊከፍት ይችላል። ረኔ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “አብሬያቸው ከኖርኳቸው ልጆች አንዷ የወንድ ጓደኛ ስለነበራት ለረዥም ሰዓት በስልክ ታወራለች። አንድ ወር ስልኩ 720 ብር ቆጠረ። የስልኩን ወጪ ለሁለት ለመካፈል ተስማምተን ስለነበር ሁለታችንም ግማሽ ግማሽ እንድንከፍል ፈለገች።”
ስልክ ለመጠቀም አጋጣሚ ማግኘት መቻል ራሱ ሌላ አስቸጋሪ ነገር ሊሆን ይችላል። ሊ እንዲህ ትላለች:- “በዕድሜ ከምትበልጠኝ ሴት ጋር እኖር ነበር። ያለን ስልክ ደግሞ አንድ ብቻ ነበር። ብዙ ጓደኞች ስለነበሩኝ ረዘም ላሉ ሰዓታት ስልኩን እይዘዋለሁ። ምንም ብላኝ አታውቅም። ስለዚህ ስልክ መደወል ስትፈልግ ትነግረኛለች ብዬ አሰብኩ። ሆኖም አሳቢ እንዳልነበርኩ አሁን ይሰማኛል።”
ለብቻ መሆን የሚያስችል ነፃ ጊዜ ማጣት
ዳዊት “ሁሉም ሰው አንዳንድ ጊዜ ብቻውን መሆን ይፈልጋል” ይላል። “አንዳንድ ጊዜ በጀርባዬ ጋለል ብዬ ዘና ማለት ያምረኛል።” ሆኖም ከሌላ ሰው ጋር ስትኖር የራስህ ነፃ ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። ማርክም “ለብቻዬ የምሆንበት ጊዜ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ” ይላል። “በዚህም ምክንያት ለእኔ ከባድ የሚሆንብኝ ብቻዬን መሆን የምችልበት ነፃ ጊዜ ማግኘት አለመቻሌ ነው። አብሮኝ የሚኖረው ልጅና እኔ ፕሮግራማችን ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ለብቻዬ የምሆንበት ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ነው።”
ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ሳይቀር አንዳንድ ጊዜ ለብቻው መሆን ይፈልግ ነበር። (ማቴዎስ 14:13) ስለዚህ አብሮህ የሚኖረው ልጅ በክፍሉ ውስጥ በመኖሩ ምክንያት ማንበብ፣ ማጥናት ወይም ማሰላሰል አለመቻልህ ሊያበሳጭ ይችላል። ማርክ እንዲህ ይላል:- “ሁልጊዜ የሆነ ነገር ስለሚያደርግ ማጥናት አልችልም። ወይ ጓደኞቹ ይኖራሉ አሊያም በስልክ ያወራል ወይም ቴሌቪዥን ይመለከታል ወይም ራዲዮ ይሰማል።”
የሆነ ሆኖ ከሌላ ሰው ጋር አብሮ መኖር የቱንም ያህል ከባድ ቢሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተሳክቶላቸዋል። በዚህ አምድ ሥር የሚወጡ ሌሎች ተከታታይ ርዕሶች ከሌላ ሰው ጋር አብሮ በመኖር ረገድ ደስተኛ መሆን ስለሚቻልበት መንገድ ሐሳብ ይሰጣሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.6 ይህ ምክር ያተኮረው በወጣቶች ላይ ቢሆንም እንኳ እንደ መበለትነት ባሉ ሕይወትን በሚለውጡ ሁኔታዎች ምክንያት ከሌሎች ጋር አብረው መኖር ለጀመሩ ትልልቅ ሰዎችም ይሠራል።
[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሙዚቃ ምርጫ ረገድ ያሉ ልዩነቶች ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሳቢ አለመሆን ውጥረት ሊፈጥር ይችላል