በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ጠብደል የቤት እንስሳት

የካናዳው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል ሪፖርት እንዳደረገው “ዋነኛው የውሾችና የድመቶች የጤና ችግር ከልክ ያለፈ ውፍረት ነው። የችግሩ ምክንያት ከሰው ልጆች የተለየ አይደለም። መጥፎ የአመጋገብ ልማድና በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ ነው።” የካናዳ የእንስሳት ሕክምና ማኅበር ምክር ቤት አባል የሆኑት በርኒ ፑኬ የችግሩ ምክንያት የእንስሳቱ ባለቤቶች አኗኗር እንደሆነ ይናገራሉ። “እኛ ራሳችን በሥራ ስለምንወጠር በቂ የአካል እንቅስቃሴ አናደርግም። ውሻውም ባለቤቱ በሥራ ስለሚወጠር በቂ የአካል እንቅስቃሴ የማድረግ አጋጣሚ አያገኝም። መጽናኛ የምናገኘው ከመብል ስለሆነ ውሾቻችንም ያንኑ የመጽናኛ ምግብ ያገኛሉ።” ግሎብ “ከልክ በላይ የወፈሩ የቤት እንስሳት በስኳር በሽታ፣ በልብ ሕመም፣ በከፍተኛ የደም ግፊትና በአርትራይተስ የመያዛቸው አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ ነው። ከጤነኛ እንስሳት ቀድመው ይሞታሉ” በማለት ያስጠነቅቃል። ከመጠን በላይ ለወፈሩ እንስሳት የሚሰጠው ሕክምና በምግብ ላይ ቁጥጥር ማድረግና ውሾች ከሆኑ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ማድረግን ይጨምራል።

በዓመት ዕረፍት የሚያጋጥም ብስጭት

ዲ ቨልት የተባለው የሐምቡርግ ጋዜጣ “ወደ ዕረፍት ማሳለፊያ ቦታ ለመጓዝ ሻንጣህን በማሳሰር ላይ ከሆንክ ተጠንቀቅ!” ይላል። በጥልና በጭቅጭቅ የሚበላሹ የቤተሰብ የዕረፍት ጊዜያት በርካታ ናቸው። አንድ የጀርመን ጥናት እንደሚያመለክተው “ከሦስት የፍቺ ማመልከቻዎች አንዱ የሚቀርበው ከዕረፍት ጊዜ በኋላ ነው።” ለምን? አንደኛው ምክንያት የቤተሰቡ አባላት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ስለሚቀራረቡና አብረው ስለሚሆኑ አንዳቸው ሌላውን ማስቆጣታቸው ነው። እንዲህ ያለው ችግር እንዳይፈጠር ለጋራ እንቅስቃሴዎች ቀደም ሲሉ ዕቅድና ፕሮግራም ማውጣትና ፕሮግራሙን የእያንዳንዱን ግለሰብ ፍላጎት ማሟላት በሚያስችል መጠን ተለዋዋጭ ማድረግ እንደሚበጅ የሥነ አእምሮ ሊቃውንት ይመክራሉ። “ከዕረፍት ጊዜ ሊገኝ የማይችል ከፍተኛ ነገር መጠበቅ ለችግሩ አንዱ ምክንያት” እንደሚሆን ዲ ቨልት ይናገራል። “በዓመቱ ውስጥ የሥራና የተለመዱ ተደጋጋሚ ተግባራት የሚፈጸሙባቸው አሥራ አንድ ወራት ሲኖሩ የሦስቱ ወይም የአራቱ ሳምንት የዕረፍት ጊዜ ዓመቱን በሙሉ ሳይደረግ የቀረውን ሁሉ እንዲያካክስ ይጠበቃል።”

እየጠፋ የመጣው የሥራ ሥነ ምግባር

“[በዩናይትድ ስቴትስ] ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ከፍተኛ ሥራ አስኪያጆች መካከል 55 በመቶ የሚሆኑት እየተሸረሸረ የመጣው የሥራ ሥነ ምግባር ወደፊት በትላልቅ ኩባንያዎች የሥራ ውጤት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል” ማለታቸውን ዘ ፊውቸሪስት መጽሔት ዘግቧል። እንዲህ ያለ ዝቅጠት ለመድረሱ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ብዙ ሁኔታዎች ቢኖሩም አንደኛው ሕፃናት “ለመሥሪያ ቤቶቻቸው በጣም ታማኝ የሆኑ ወላጆቻቸው ከኖሩበት ሥራ ተቀናሽ ሆነው ሲባረሩ ማየታቸው ነው።” በዚህ ምክንያት በ1960ዎቹ ዓመታት የተወለዱ በርካታ ሰዎች ሥራቸውን ገንዘብ፣ ጨዋታና መዝናኛ ማግኛ ብቻ እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ። ይኸው ጽሑፍ በዚህ ምክንያት “ዛሬ የሥራ ዋስትናና የደመወዝ ጭማሪ ማግኘት አንድ ወቅት የነበራቸውን ተፈላጊነት አጥተዋል” ይላል። የሥራ ሥነ ምግባር እየጠፋ መምጣቱን ከሚያሳዩት ምልክቶች ሁለቱ ዘግይቶ ሥራ መግባትና አለአግባብ የሕመም ፈቃድ መውሰድ ናቸው።

እየበዛ የመጣው የሕፃናት ውፍረት ችግር

የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት በቅርቡ ብሪትሽ መዲካል ጆርናል ስላወጣው የጥናት ውጤት አስተያየት ሲሰጥ “ከመጠን በላይ ወፍራም የሆኑ ሕፃናት ቁጥር ባለፈው አሥርተ ዓመት ከእጥፍ በላይ ጨምሯል” ብሏል። “ከአራት ዓመት በታች ከሆኑ አራት ሕፃናት መካከል አንዱ ወፍራም ሲሆን ከአሥር አንዱ ደግሞ ከመጠን በላይ ወፍራም ነው።” የሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፒተር በንድረድ ብዙ እናቶች “ለልጆቻቸው የሚሰጡት ብዙ ቅባት ያላቸውን ተዘጋጅተው የሚሸጡ ምግቦች ነው” ብለዋል። በተጨማሪም የሚያዝናኑአቸው ቴሌቪዥን እንዲመለከቱ በማድረግ ነው። ለትምህርት በሚደርሱበት ጊዜ ደግሞ ብዙዎቹ ወደ ትምህርት ቤት የሚመላለሱት በእግር ሳይሆን በመኪና ነው። ከትምህርት ቤት ከተመለሱ በኋላ ደግሞ ውጭ ወጥተው ከመጫወት ይልቅ ቴሌቪዥን ይመለከታሉ። “ለመጀመሪያ ጊዜ በሁሉም የልጅነት ዕድሜዎች ከፍተኛ የሆነ የውፍረት መጨመር እየተመለከትን ነው” ይላሉ በንድረድ።

ራሳቸውን የመግደል አዝማሚያ የሚታይባቸው ልጆች

ልጆችን ለመርዳት ለተቋቋመው ቻይልድላይን ለተባለ የብሪታንያ ምግባረ ሠናይ ድርጅት የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች ብዛት በእጥፍ የጨመረ ሲሆን በ1990/91 346 ከነበረው በ1998/99 ወደ 701 ከፍ ማለቱን የለንደኑ ጋርድያን መጽሔት ዘግቧል። “ጉልበተኞች የሚሰነዝሩት ዛቻና ማስፈራሪያ፣ ወሲባዊ ወይም አካላዊ ጥቃት፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣትና ፈተና የሚፈጥረው ውጥረት ከመጠን ያለፈ ድንጋጤና ፍርሃት ያሳድርባቸዋል።” ምግባረ ሠናይ ድርጅቱ እንደሚለው “ልጆች ራሳቸውን የመግደል ሙከራ የሚያደርጉት ትኩረት ለማግኘት ሲሉ ብቻ ነው የሚለው የተለመደ አስተሳሰብ አደገኛ ነው። ራሳቸውን እንደሚገድሉ የሚናገሩ ልጆች ድርጊቱን አይፈጽሙትም የሚለው አስተሳሰብ ፈጽሞ እውነትነት የለውም። ለቻይልድላይን የስልክ ጥሪ ካደረጉት ራሳቸውን የመግደል አዝማሚያ ያለባቸው ልጆች ብዙዎቹ ውጥረቱ የሚያይልባቸው ወላጆቻቸው ወይሞ አሳዳጊዎቻቸው ስለነርሱ ግድየለሾች በሚሆኑበት ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል።” ከመጀመሪያው ራስ የመግደል ሙከራ በኋላ “ልጃቸው በመትረፉ ወላጆች እፎይ ይሉና . . . ችግሩ ዳግመኛ የማይመለስ መስሎ ይታያቸዋል።” ይሁን እንጂ ከመጀመሪያው ሙከራ ጥቂት ወራት ቆይቶ “ዳግመኛ ይሞክራል።” ራሳቸውን የመግደል አዝማሚያ ያለባቸው ሴቶች ከወንዶቹ በአራት እጥፍ የሚበልጡ ቢሆንም በብዛት ራሳቸውን የሚገድሉት ወንዶቹ ናቸው። አብዛኞቹ ስልክ የሚደውሉት ከ13 እስከ 18 በሚሆነው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም 6 ዓመት የሚሆናቸው ሳይቀሩ የስልክ ጥሪ አድርገዋል።

የትንኝ ወጥመድ

አንድ የሲንጋፖር የንግድ ድርጅት ትንኞችን አለመርዝ የሚጨርስ መሣሪያ በመሥራት ላይ ነው። ይህ መሣሪያ 35 ሣንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመት ያለው ጥቁር የፕላስቲክ ሳጥን ሲሆን “ልክ እንደ ሰው አካል ሙቀትና ካርቦን ዳይኦክሳይድ ያወጣል” ሲል የለንደኑ ዚ ኢኮኖሚስት ዘግቧል። ትንኞች የሚነድፉትን ሰው የሚያገኙት በሰውነት ሙቀትና በትንፋሽ በሚወጣው ካርቦን ዳይኦክሳይድ ተስበው ስለሆነ መሣሪያው “ምግባቸውን እንዳገኙ በማስመሰል ያታልላቸዋል።” ሣጥኑ በኤሌክትሪክ አማካኝነት የሚሞቅ ሲሆን በውስጡ ካለ አንድ ትንሽ መሣሪያ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ያወጣል። ከዚያም ትንኞቹ በሚያጥበረብር ብርሃን ይታለሉና በሣጥኑ ውስጥ በሚገኝ ቀዳዳ በኩል ይገባሉ። ከዚያ በኋላ በማራገቢያ መሣሪያ በሚወጣ አየር ተስበው በተጠራቀመ ውኃ ውስጥ እንዲገቡ ይደረግና ይሞታሉ። መሣሪያው በአንድ ሌሊት 1, 200 ትንኞች የማጥመድ ችሎታ ሲኖረው በምሽት ብቻ የሚንቀሳቀሱትን ወባ አማጭ አኖፊለስ ትንኞችን ወይም በቀን ብርሃን ብቻ የሚንቀሳቀሱትን ብጫ ወባና ዴንግ አማጭ ኤይደስ ትንኞች እንዲያጠምድ አድርጎ ማስተካከል ይቻላል። እንደ ቢራቢሮ ያሉትን ጉዳት የሌላቸው ነፍሳት የማይገድል መሆኑ ደግሞ ሌላው የመሣሪያው ጠቃሚነት ነው።

ወንዶች ዓሣ እንዲመገቡ ተመክረዋል

እንደ ሳልሞን፣ ሄሪንግና ማካረል የመሰሉትን ባለ ብዙ ቅባት ዓሣዎች አብዝተው የሚመገቡ ወንዶች በፕሮስቴት ካንሰር የመያዛቸው ዕድል ዓሣ አዘውትረው ከማይመገቡት ወንዶች ከሁለት እስከ ሦስት እጥፍ እንደሚያንስ በስቶክሆልም የካሮሊንስካ ተቋም ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በ6, 272 ወንዶች ላይ የተደረገው ይህ 30 ዓመት የፈጀ ጥናት እንደማጨስ ያሉትን ለካንሰር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ አስገብቷል። ተመራማሪዎቹ “[በተለይ በቅባታማ ዓሣዎች ውስጥ የሚገኘው] ኦሜጋ-3 የተባለው ቅባታማ አሲድ የፕሮስቴት ካንሰርን እድገት የሚገታ ይመስላል።” ይኸው ቅባታማ አሲድ “በልብ ድካም የመያዝን አጋጣሚም እንደሚቀንስ” ሪፖርቱ ይናገራል። በዚህ ምክንያት ሊቃውንቱ “በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ” ዓሣ መብላት ጥሩ እንደሆነ ይመክራሉ።

የአእምሮ ጤናና ሕፃናት

“አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከአምስት ሕፃናት አንዱ 11 ዓመት ዕድሜ ላይ ሲደርስ የአእምሮ ጤና ችግሮች ያጋጥሙታል” ይላል የሞንትሪያል ካናዳው ዘ ጋዜት ጋዜጣ። “ጥሩ የአእምሮ ጤና የአንድን ሰው ማኅበራዊ፣ አካላዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ የሕይወት ዘርፎች ሚዛናዊ ማድረግን ይጠይቃል።” የካናዳ የአእምሮ ጤና ማኅበር የማኅበረሰብ ትምህርት አስተባባሪ የሆኑት ሳንዲ ብሬይ እንዳሉት ለአካላዊ ጤንነታችን እንደምናስብ ሁሉ ለአእምሮአዊ ጤንነታችንም ማሰብ ይኖርብናል። ብሬይ እንዲህ ይላሉ:- “ለአእምሮ ጤንነታችን ከሌሎች ያነሰ ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ በመንፈስ ጭንቀት፣ በስጋትና በውጥረት እንሠቃያለን።” ወላጆች ለቤተሰባቸው ተጨማሪ ጊዜ በመስጠትና አብረው በመብላት የልጆቻቸውን የአእምሮ ጤና እንዲንከባከቡና አስቀድመው የመከላከል እርምጃ እንዲወስዱ ይመከራሉ። ሁሉም ሰው ጥሩ የአእምሮ ጤንነት እንዲኖረው ከሚሰጡት ምክሮች መካከል በቂ እንቅልፍ ማግኘት፣ በሥርዓት መመገብ፣ ጥሩ አካላዊ ብቃት ማዳበር፣ ደስ የምትሰኝበት ሥራ የምትሠራበት ጊዜ መወሰን፣ መሳቅ፣ የፈቃደኛ አገልግሎት ሥራ መሥራት፣ ምሥጋና መስጠትና መቀበል፣ ሌሎችን ከልብ ማዳመጥ እንዲሁም ጥፋት በምትሠራበት ጊዜ ከልክ በላይ ራስህን አለመኮነን ይገኙበታል።

ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ጨምሯል

ዩሮስቴት የተባለው የአውሮፓ ስታትስቲክስ መሥሪያ ቤት በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ኅብረት አገሮች ከሚወለዱት 4 ሕፃናት መካከል አንዱ የሚወለደው ከጋብቻ ውጭ መሆኑን እንደገለጸ ቨስትዶቸ አልገማይነ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። በ1980 አኃዙ ከ10 አንድ በታች ነበር። ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር አነስተኛ ሆኖ የተገኘበት አገር ግሪክ ሲሆን 4 በመቶ ነው። በሌላው ጽንፍ ደግሞ በጣም ከፍተኛ የሆነው በስዊድን ሲሆን ከግማሽ የሚበልጡ ልጆች የሚወለዱት ከጋብቻ ውጭ ነው። ከፍተኛ ለውጥ የታየው በአየርላንድ ነው። በዚህች አገር ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር በ1980 ከነበረው 5 በመቶ ተነስቶ በ2000 ላይ 31.8 በመቶ ደርሷል። ሪፖርቱ እንዲህ ያለው ከፍተኛ ጭማሪ “አውሮፓውያን ለጋብቻና ለቤተሰብ ያላቸው አመለካከት በእጅጉ መለወጡን ያሳያል” ብሏል።