ክርስቲያኖች መለኮታዊ ጥበቃ እንዲደረግላቸው መጠበቅ አለባቸው?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ክርስቲያኖች መለኮታዊ ጥበቃ እንዲደረግላቸው መጠበቅ አለባቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ አምላኪዎቹን ከጉዳት በመጠበቅ ረገድ ስላለው ችሎታ በተደጋጋሚ ይናገራል። ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ ከክፉ ሰው አድነኝ፣ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 140:1) በዛሬው ጊዜ ብዙ የአምላክ አገልጋዮች የዓመፅ ድርጊት፣ ወንጀል ወይም የተፈጥሮ አደጋ አጋጥሟቸው ከሞት ወይም ከጉዳት ለጥቂት ይተርፋሉ። አንዳንዶች እንዲህ ባሉት አጋጣሚዎች ሳቢያ ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ሌሎች ሰዎች ላይ ከባድ አደጋ አልፎ ተርፎም አሰቃቂ ሞት እንደደረሰ ስለሚያውቁ እኔ ከእነዚህ አደጋዎች ያመለጥኩት አምላክ በእርግጥ ተዓምራዊ ጥበቃ ስላደረገልኝ ነውን? የሚል ጥያቄ ይነሳባቸዋል።
ይሖዋ አምላክ አንዳንድ ግለሰቦችን ከአደጋ ሲጠብቅ ሌሎችን አይጠብቅም ማለት ነውን? በዛሬው ጊዜ ከዓመፅ ድርጊቶችና ከተፈጥሮ አደጋዎች ተአምራዊ ጥበቃ ይደረግልናል ብለን መጠበቅ ይኖርብናል?
አምላክ ተአምራዊ ጥበቃ ስለማድረጉ የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች
አምላክ ተአምራዊ በሆነ መንገድ አምላኪዎቹን ለማዳን ጣልቃ ስለመግባቱ የሚገልጹ በርካታ ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። (ኢሳይያስ 38:1-8፤ ሥራ 12:1-11፤ 16:25, 26) በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች የይሖዋ አገልጋዮች ጥበቃ ሳያገኙ የቀሩባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም ይገልጻሉ። (1 ነገሥት 21:1-16፤ ሥራ 12:1, 2፤ ዕብራውያን 11:35-38) እንግዲያው ይሖዋ በአንድ የተለየ ዓላማ ወይም ምክንያት የተነሳ በፈለገበት ጊዜ ጥበቃ ለማድረግ ሊወስን እንደሚችል ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል። ስለሆነም ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ ጥበቃ ሳይደረግላቸው ቢቀር አምላክ እንደተዋቸው አድርገው መደምደም የለባቸውም። ታማኝ በሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ላይ ጭምር መጥፎ ነገሮች ሊደርሱ እንደሚችሉ ሐቁን መቀበል ይኖርብናል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መጥፎ ነገር የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
አንደኛው ምክንያት ሁላችንም ከአዳምና ከሔዋን ኃጢአትንና አለፍጽምናን በመውረሳችን ነው። በዚህ ምክንያት ሮሜ 5:12፤ 6:23) ሌላው ምክንያት ደግሞ በመጨረሻው ቀን ውስጥ የምንኖር መሆናችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በጊዜያችን ያሉትን ሰዎች “ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ” በማለት ይገልጻቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አስገድዶ መድፈር፣ እገታ፣ ነፍስ ግድያና ሌሎች የጭካኔ ወንጀሎች እየበዙ መሄዳቸው ለዚህ ማስረጃ ይሆናል።
ስቃይ፣ መከራና ሞት ይደርስብናል። (ብዙ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሚኖሩትም ሆነ የሚሠሩት ዓመፀኛ በሆኑ ሰዎች መካከል ስለሆነ አንዳንድ ጊዜ የጥቃታቸው ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ። በአጉል ሰዓት አጉል ቦታ ላይ በመገኘታችን ብቻ ለሕይወታችን የሚያሰጋ ሁኔታ ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን። ከዚህም በላይ ሰሎሞን “ጊዜና እድል [“አጋጣሚ፣” NW ] ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል” በማለት የተናገረለት እውነታ ያጋጥመናል።—መክብብ 9:11
በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች አምላክን በማምለካቸው ምክንያት የስደት ዒላማ እንደሚሆኑ ተናግሯል። እንዲህ አለ:- “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:12) በቅርብ ዓመታት በበርካታ አገሮች ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል።
እንግዲያው አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ከዓመፅ፣ ከወንጀል፣ ከተፈጥሮ አደጋ ወይም ድንገተኛ አደጋ ከሚያስከትለው ሞት ሙሉ በሙሉ ነፃ አይደሉም። ሰይጣን፣ ይሖዋ ሕዝቦቹ ምንም ዓይነት አደጋ እንዳይደርስባቸው ዙሪያቸውን ያጥርላቸዋል በማለት ለመከራከር ሞክሮ ነበር። (ኢዮብ 1:9, 10) እንደዚያ ግን አይደለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከአደጋ ባያድነንም ለሕዝቦቹ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው እርግጠኛ መሆን እንችላለን።
በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚጠብቃቸው እንዴት ነው?
ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚጠብቃቸውን መለኮታዊ መመሪያ በቃሉ አማካኝነት ይሰጣቸዋል። መንፈሳዊ መሆናችንና የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘታችን ያልሆነ ስህተት ከመሥራት የሚጠብቀንንና የጥበብ ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዳንን ጥሩ የማመዛዘንና የማስተዋል ችሎታ ይሰጠናል። (መዝሙር 38:4፤ ምሳሌ 3:21፤ 22:3) ለምሳሌ ያህል የጾታ ሥነ ምግባርን፣ ስግብግብነትን፣ ቁጣንና የዓመፅ ድርጊትን በተመለከተ የተሰጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች መከተል ክርስቲያኖችን ከብዙ አደጋዎች ጠብቋቸዋል። እንዲሁም ከክፉዎች ጋር ከመወዳጀት በመራቅ በአጉል ጊዜ አጉል ቦታ ላይ ተገኝተን ሊደርስብን ከሚችለው አደጋ ራሳችንን ልንጠብቅ እንችላለን። (መዝሙር 26:4, 5፤ ምሳሌ 4:14) ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሰዎች የተሻለ አእምሯዊና አካላዊ ጤንነት የሚያስገኝ የላቀ ሕይወት ይኖራቸዋል።
ከሁሉም በላይ የሚያጽናናው ደግሞ አምላክ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ ቢፈቅድም እንኳን አምላኪዎቹ ሊቋቋሙት እንዲችሉ የሚያስፈልጋቸውን ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው ማወቁ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” በማለት ያረጋግጥልናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የደረሱብንን አደጋዎች በጽናት መቋቋም የሚያስችል “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” እንደምናገኝ ተስፋ ይሰጠናል።—2 ቆሮንቶስ 4:7 NW
አምላክ እንደ ፈቃዱ ያደርጋል
ክርስቲያኖች አደጋ ባጋጠማቸው ቁጥር አምላክ ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንዲያድናቸው መጠበቅ አለባቸው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ተስፋ ማድረግን አይደግፍም።
እርግጥ ነው ይሖዋ አምላክ ከአገልጋዮቹ አንዱ አደጋ እንዳይደርስበት በቀጥታ ጣልቃ ለመግባት ሊመርጥ ይችላል። ማንም ሰው በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ከጉዳት እንደተረፈ ቢሰማው በዚህ አስተሳሰቡ ሊነቀፍ አይገባም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ጣልቃ ላለመግባት በሚወስንበት ጊዜ ይህ በግለሰቡ አለመደሰቱን እንደሚያሳይ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።
ምንም ዓይነት መከራ ወይም ችግር ቢያጋጥመን ይሖዋ ችግሩን በማስወገድም ሆነ እንድንቋቋመው የሚያስችል ጥንካሬ በመስጠት ወይም ብንሞት እንኳን በአዲሱ ዓለም ውስጥ ላዘጋጀልን የዘላለም ሕይወት በትንሣኤ በማስነሳት ለታማኝ አገልጋዮቹ መለኮታዊ ጥበቃ እንደሚያደርግ ትምክህት ይኑረን።—መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ዮሐንስ 5:28, 29