የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ
የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ
በእስራኤል አገር በገሊላ ባሕር ዳርቻ ከሚገኙት ምግብ ቤቶች ወደ አንዱ ጎራ ብትል በምግቦች ዝርዝር ላይ “የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ” የሚል ትመለከትና ስለዚህ ዓሣ ለማወቅ ጉጉት ያድርብህ ይሆናል። አስተናጋጁ በተለይ በቱሪስቶች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ከሆኑት ምግቦች አንዱ እንደሆነ ይነግርህ ይሆናል። እንደተጠመደ ወዲያው ሲጠበስ በጣም ይጣፍጣል። ይሁን እንጂ ይህ ዓሣ ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር የተዛመደው ለምንድን ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማቴዎስ 17:24-27 ላይ የተገለጸ አንድ ክንውን መልሱን ይሰጠናል። እዚህ ላይ ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘውን የቅፍርናሆም ከተማ በሚጎበኝበት ጊዜ ኢየሱስ የቤተ መቅደሱን ግብር ከፍሎ እንደሆነ ይጠየቃል። በኋላም ኢየሱስ የአምላክ ልጅ በመሆኑ ግብሩን የመክፈል ግዴታ እንደሌለበት ያስረዳዋል። ሌሎችን ላለማደናቀፍ ግን ጴጥሮስ ሄዶ መቃጥኑን ወደ ባሕር ጥሎ በሚይዘው የመጀመሪያ ዓሣ አፍ ውስጥ የሚያገኘውን ገንዘብ ወስዶ እንዲከፍል ይነግረዋል።
“የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ” የሚለው ስያሜ በዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ በሚገኘው ክንውን ላይ የተመሠረተ ነው። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ የያዘው ምን ዓይነት ዓሣ ነው?
በዓሦች የተሞላ ባሕር
በገሊላ ባሕር ከሚገኙት 20 የሚያክሉ የዓሣ ዝርያዎች መካከል ጴጥሮስ የያዘውን ዓይነት ሊሆኑ የሚችሉት አሥሩ ብቻ ናቸው። እነዚህ አሥሩ ዝርያዎች ደግሞ የንግድ ጠቀሜታ ባላቸው ሦስት ክፍሎች ተከፍለዋል።
በጣም ትልቅ የሆነው ክፍል ሙሽ ት ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጉሙም በአረብኛ “ማበጠሪያ” ማለት ነው። ይህን መጠሪያ ያገኘው በዚህ ክፍል ውስጥ ከተመደቡት ዝርያዎች አምስቱ ማበጠሪያ የመሰለ ክንፍ ስላላቸው ነው። ከሙሽት ዝርያዎች መካከል አንዱ ቁመቱ እስከ 45 ሳንቲ ሜትር የሚደርስ ሲሆን 2 ኪሎ ግራም ያህል ይመዝናል።
ሁለተኛው ክፍል ኪነሬት ሰርዲን ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በሰሜን አትላንቲክ የሚገኘውን ሄሪንግ የተባለ ትንሽ ዓሣ ይመስላል። ይህ ዓይነቱ ዓሣ በብዛት በሚገኝባቸው ወራት በየምሽቱ በርካታ ቶን ይጠመዳል። በየዓመቱ የሚጠመደው እስከ አንድ ሺህ ቶን ይደርሳል። ከጥንት ጀምሮ ይህ ሰርዲን እንዳይበላሽ በጨው ተዘፍዝፎ እንዲቆይ ይደረጋል።
ሦስተኛው ክፍል ቢኒ የሚባል ሲሆን ባርበል ተብሎም ይጠራል። በዚህ ክፍል ከተመደቡት የዓሣ ዝርያዎች መካከል ሦስቱ በአፋቸው ግራና ቀኝ ጠርዝ እሾህ የመሰለ ጺም ስላላቸው የተሰጠ ስያሜ ነው። ቢኒ የሚለው ሴማዊ ስያሜ “ፀጉር” ማለት ነው። የሚመገበው ቀንድ አውጣዎችንና ትናንሽ ዓሣዎችን ነው። ባለ ረዥም ጭንቅላቱ ባርበል እስከ 75 ሳንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመት ሲኖረው ክብደቱ እስከ 7 ኪሎ ግራም ይመዝናል። ባርበሎች ጠብደል ያሉ ዓሦች ሲሆኑ በአይሁዳውያን ሰንበቶችና ሌሎች በዓላት ይዘወተራሉ።
በገሊላ ባሕር ከሚገኙት ዓሦች በሙሉ ትልቅ የሆነው ካትፊሽ የንግድ ጠቀሜታ ካላቸው ሦስት ክፍሎች ውስጥ አይመደብም። ቁመቱ 1.20 ሜትር የሚደርስ ሲሆን እስከ 11 ኪሎ ግራም ይመዝናል። ካትፊሽ ግን ቅርፊት ስለሌለው በሙሴ ሕግ መሠረት ንጹሕ ያልሆነ የዓሣ ዝርያ ነው። (ዘሌዋውያን 11:9-12) በዚህ ምክንያት አይሁዳውያን ስለማይበሉት ጴጥሮስ የያዘውን ዓይነት ዓሣ ሊሆን አይችልም።
ጴጥሮስ የያዘው የትኛውን ዓይነት ዓሣ ነው?
በተለምዶ “የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ” በመባል ተቀባይነት ያገኘው ሙሽ ት ዓሣ ነው። በገሊላ ባሕር አካባቢ በሚገኙ ምግብ ቤቶችም በዚህ ስያሜ ለእንግዶች ይቀርባል። ብዙ ትናንሽ አጥንቶች ስለሌሉት ለማዘጋጀትም ሆነ ለመመገብ አይከብድም። ይሁን እንጂ በእርግጥ ጴጥሮስ የያዘው ይህንን ዓሣ ነው?
በገሊላ ባሕር ዳርቻዎች ከ50 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ የኖሩት መንደል ኑን የተባሉ ዓሣ አጥማጅ በአካባቢው ስለሚገኙ ዓሣዎች ባላቸው እውቀት ከፍተኛ ከበሬታ አትርፈዋል። እሳቸውም “ሙሽት የሚመገበው በባሕር ላይ የሚንሳፈፉትን ጥቃቅን እፅዋትና ነፍሳት ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት የሚጠመደው በመረብ እንጂ በመቃጥን ወይም በመንጠቆ አይደለም” ይላሉ። ስለዚህ ጴጥሮስ የያዘው ዓሣ ሊሆን አይችልም። ሰርዲንም ቢሆን በጣም ትንሽ ስለሆነ የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ ሊሆን አይችልም።
የሚቀረው ባርበል የተባለው የዓሣ ዓይነት ሲሆን አንዳንዶች ይኸኛው ዝርያ “የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ” ቢባል እንደሚሻል ይናገራሉ። ኑን እንዲህ ይላሉ:- “በገሊላ ባሕር የሚያጠምዱ ዓሣ አጥማጆች ከጥንት ጀምሮ ባርበሎችን ለማጥመድ የሚጠቀሙት ጫፉ ላይ ሰርዲን የተደረገበት መቃጥን ነው። ባርበሎች በባሕር ወለል አካባቢ የሚገኙ ዓሣዎች ተመጋቢ ናቸው።” በማጠቃለያቸው ላይ “ጴጥሮስ ያጠመደው ባርበል ሳይሆን አይቀርም ብሎ ለመናገር ያስደፍራል” ብለዋል።
ታዲያ ሙሽ ት “የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ” በሚል ስያሜ ለምግብነት የሚቀርበው ለምንድን ነው? ኑን እንዲህ በማለት ይመልሳሉ:- “ግራ ለሚያጋባው ለዚህ የስም ለውጥ ሊኖር የሚችለው ምክንያት አንድ ብቻ ነው። የቱሪዝም ንግድ ስለሚስብ ብቻ ነው። . . . ሃይማኖታዊ ጎብኚዎች ከሩቅ አካባቢዎች መምጣት ሲጀምሩ የጥንቶቹ የባሕር ዳርቻ ምግብ ቤቶች ለደንበኞቻቸው ያቀርቡ ለነበረው ሙሽት ‘የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ’ የሚል ስያሜ መስጠት ገበያቸውን እንደሚያደራ የታወቀ ነው። እጅግ ተወዳጅ ለሆነውና ለማዘጋጀትም ለሚቀለው ለዚህ ዓሣ ገበያ የሚስብ ጥሩ ስም ተሰጠ!”
ጴጥሮስ ይዞት የነበረውን ዓሣ በእርግጠኝነት ለመናገር አንቻል እንጂ “የቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ” በሚል ስያሜ የሚቀርብልህ ዓሣ በጣም ጣፋጭ ሳይሆንልህ አይቀርም።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ሙሽት”
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባርበል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Garo Nalbandian