በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠብ የነገሠበት ምዕተ ዓመት

ጠብ የነገሠበት ምዕተ ዓመት

ጠብ የነገሠበት ምዕተ ዓመት

አልፍሬድ ኖቤል ሰላም ሊገኝ የሚችለው ብሔራት አደገኛ መሣሪያ ቢኖራቸው እንደሆነ ያምን ነበር። ደግሞም ብሔራት በፍጥነት ግንባር ፈጥረው በማንኛውም ጠብ ጫሪ ላይ አሰቃቂ ውድመት ሊያስከትሉ ይችላሉ። “ጦርነት እንዲቆም የሚያደርገው ኃይል ይህ ብቻ ነው” ሲል ጽፏል። በኖቤል አመለካከት መሠረት ማንኛውም ብሔር አእምሮውን የሳተ ካልሆነ በስተቀር የማያዳግም ጥፋት የሚያስከትልበት መሆኑን እያወቀ ግጭት ለመቀስቀስ አይነሳም። ይሁን እንጂ ያለፈው መቶ ዘመን ያስገነዘበን ምንድን ነው?

ኖቤል ከሞተ ገና 20 ዓመት እንኳን ሳይሞላ አንደኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ። በዚህ ጦርነት ላይ መትረየሶችን፣ የመርዝ ጢስ፣ እሳት ወንጫፊዎችን፣ ታንኮችን፣ አውሮፕላኖችንና ባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን ጨምሮ አዳዲስ አውዳሚ የጦር መሣሪያዎች ሥራ ላይ ውለዋል። አሥር ሚልዮን የሚጠጉ ወታደሮች ሲገደሉ የዚያ እጥፍ የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት የተፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ሰላም የመፍጠር እንቅስቃሴ በአዲስ መንፈስ እንዲጀምር ምክንያት ሆነ። በዚህም ምክንያት የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ተመሠረተ። በዚህ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተው የነበሩት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን በ1919 የኖቤልን የሰላም ሽልማት ተሸለሙ።

ይሁን እንጂ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 ሲፈነዳ ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ የመጥፋቱ ተስፋ መና ሆኖ ቀረ። ይኸኛው ጦርነት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት እንኳን በብዙ ገጽታው የባሰ አሰቃቂ ሆነ። በዚህ ግጭት ወቅት አዶልፍ ሂትለር በክሩመል የነበረውን የኖቤል ፋብሪካ በጣም አስፋፍቶ ከ9,000 በላይ ሠራተኞች ያሉት ትልቁ የጀርመን የጦር መሣሪያ ፋብሪካ ከሚሆንበት ደረጃ ላይ አድርሶት ነበር። ከዚያም በጦርነቱ ማብቂያ ላይ የኖቤል ፋብሪካ ኅብረ ብሔራቱ በጣሉት ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ቦምቦች ሙሉ በሙሉ ወደመ። እነዚህ ቦምቦች ኖቤል በፈለሰፈው ፈንጂ ላይ ተመሥርተው የተሠሩ መሆናቸው የሚያስገርም ነው።

ኖቤል ከሞተ ወዲህ በነበረው መቶ ዘመን ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በተጨማሪ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ትናንሽ ግጭቶችም ታይተዋል። በዚህ ዘመን የጦር መሣሪያዎች በብዛት የተናኙ ሲሆን የአንዳንዶቹ ጠንቀኝነት በጣም ከፍተኛ ሆኗል። ከኖቤል ሞት ወዲህ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ጎላ ብለው ከታዩት የውትድርና መሣሪያዎች ጥቂቶቹን እንመልከት።

ቀላልና የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች። በዚህ ምድብ ከሚጠቃለሉት መሣሪያዎች መካከል ሽጉጦች፣ ጠመንጃዎች፣ ቦምቦች፣ መትረየሶችና ሞርታሮች እንዲሁም ሌሎች ሊነገቡ የሚችሉ መሣሪያዎች ይገኛሉ። ቀላልና የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ርካሽ፣ በቀላሉ ሊጠገኑ የሚችሉና ሥራ ላይ ለማዋልም የማይከብዱ ናቸው።

ታዲያ የእነዚህ መሣሪያዎች እንደልብ መገኘትና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጣሉት ሥጋት ጦርነት እንዳይካሄድ ሊገታ ችሏል? በፍጹም! ማይክል ክላር ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ በተባለው መጽሔት ላይ “ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ በተደረጉት በአብዛኞቹ ግጭቶች በዋነኛነት ያገለገሉት መሣሪያዎች” ቀላል የጦር መሣሪያዎች እንደሆኑ ጽፈዋል። እንዲያውም በቅርብ በተደረጉ ጦርነቶች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የጦር ጉዳቶች የደረሱት በቀላልና በነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ሳቢያ ነው። በ1990ዎቹ ዓመታት ብቻ ከአራት ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በእነዚህ መሣሪያዎች ተገድለዋል። አብዛኛውን ጊዜ ቀላል መሣሪያዎችን የሚታጠቁት የውትድርና ሥልጠና ያልተሰጣቸውና የታወቁትን የውጊያ ሕጎች ስለማክበር ግድ የሌላቸው ወጣቶች ናቸው።

ፈንጂዎች። በ20ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በአ​ማካይ በየቀኑ 70 ሰዎች በፈንጂዎች ምክንያት ሲሞቱ ወይም የአካል ጉዳተኛ ሲሆኑ ቆይቷል! አብዛኞቹ ወታደሮች ሳይሆኑ ሰላማውያን ሰዎች ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ ፈንጂዎች የሚቀበሩት ለመግደል ሳይሆን አካል ለማቁሰልና አደጋ በደረሰባቸው ሰዎች ላይ ፍርሃትና ሽብር ለመንዛት ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፈንጂዎችን ለማስወገድ ብዙ ጥረት እንደተደረገ አይካድም። ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ አንድ ፈንጂ በተወገደ ቁጥር ሌሎች 20 ፈንጂዎች ይቀበራሉ። በመላው ዓለም ደግሞ 60 ሚልዮን ፈንጂዎች ተቀብረው እንደሚገኙ ይገመታል። ፈንጂዎች የወታደሮችን ኮቴ በሜዳ ከሚጫወት ሕፃን ኮቴ የማይለዩ መሆናቸው የእነዚህን ጨካኝ መሣሪያዎች መመረትም ሆነ ሥራ ላይ መዋል ሊገታ አልቻለም።

የኑክሊየር መሣሪያዎች። የኑክሊየር መሣሪያዎች ከተፈለሰፉ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በወታደሮች መካከል ምንም ዓይነት የተኩስ ልውውጥ ሳይደረግ አንድን ከተማ እንዳለ በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ ማውደም ተችሏል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1945 በሂሮሽማና በናጋሳኪ ላይ አቶሚክ ቦንቦች በተጣሉ ጊዜ ምን ያህል አሰቃቂ ጥፋት እንደደረሰ ተመልከት። አንዳንድ ሰዎች ከፍንዳታው በወጣው ኃይለኛ የብርሃን ነጸብራቅ የተነሳ ታውረዋል። ሌሎች በጨረሩ ተመርዘዋል። በእሳትና በሙቀት የሞቱ በርካታዎች ናቸው። በእነዚህ ሁለት ከተሞች የተገደሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር 300, 000 እንደሚደርስ ይገመታል!

እርግጥ ነው፣ በእነዚህ ሁለት ከተሞች ላይ አቶሚክ ቦምቦች መጣላቸው ጦርነቱ በመደበኛ ውጊያ ቢቀጥል ኖሮ ይጠፋ የነበረውን የበርካታ ሰዎች ሕይወት አድኗል ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ይኖራሉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ይህን የሚያክል የሕይወት ጥፋት በመድረሱ ተደናግጠው በእነዚህ አሰቃቂ መሣሪያዎች ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ማካሄድ ጀመሩ። እንዲያውም አንዳንዶች የሰው ልጅ ራሱን ከሚያጠፋበት ደረጃ ላይ ደርሷል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።

ታዲያ የኑክሊየር መሣሪያዎች መሠራት ለሰላም መንገድ ጠራጊ ሊሆን ችሏል? አንዳንዶች አዎን፣ ይላሉ። ለዚህም በማስረጃነት የሚጠቅሱት እነዚህ ከፍተኛ የማውደም ችሎታ ያላቸው መሣሪያዎች ለግማሽ ምዕተ ዓመት ሥራ ላይ ውለው የማያውቁ መሆናቸውን ነው። ቢሆንም ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ጦርነት ራሱን በራሱ አንቆ እንዲያጠፋ ምክንያት ይሆናሉ የሚለው የኖቤል እምነት እውን አልሆነም። ምክንያቱም ዛሬም በመደበኛ መሣሪያዎች የሚደረጉ ውጊያዎች ቀጥለዋል። ከዚህም በላይ በማንኛውም ቅጽበት ቃታቸው ሊሳብ በተጠንቀቅ የሚጠባበቁ በሺህ የሚቆጠሩ የኑክሊየር መሣሪያዎች መኖራቸውን የኑክሊየር ፖሊሲ አውጪ ኮሚቴ ተናግሯል። አሸባሪነት በጣም አሳሳቢ አደጋ ከመሆን ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ዘመን ደግሞ ብዙዎች የኑክሊየር ጥሬ ዕቃዎች አሸባሪዎች እጅ የወደቁስ እንደሆን ብለው ይሰጋሉ። አሸባሪዎች እጅ ውስጥ ባይወድቁም እንኳን በአንድ ቀላል “ስህተት” ምክንያት መላው ዓለም በኑክሊየር መሣሪያዎች ሊወድም የሚችል መሆኑ በጣም ያሳስባቸዋል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አውዳሚ መሣሪያዎች ኖቤል አልሞት የነበረውን ሰላም አላስገኙም።

ባዮሎጂያዊና ኬሚካላዊ መሣሪያዎች። በጀርም ውጊያ እንደ አባ ሰንጋ ያሉት ለሞት የሚዳርጉ ባክቴሪያዎችና እንደ ፈንጣጣ ያሉት ቫይረሶች በመሣሪያነት ያገለግላሉ። በተለይ ፈንጣጣ በከፍተኛ ፍጥነት የሚዛመት በመሆኑ አደገኛ ነው። ከዚህም ሌላ እንደመርዝ ጋዝ ባሉ የኬሚካል መሣሪያዎች ሊሰነዘር የሚችል ጥቃት አለ። እነዚህ መርዛማ ንጥረ ነገሮች በተለያየ መልክ የሚዘጋጁ ሲሆኑ በሕግ ከታገዱ አሥርተ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረግ አልተቻለም።

ታዲያ እነዚህ አውዳሚ መሣሪያዎችና መሣሪያዎቹ የፈጠሩት ስጋት ኖቤል እንደተነበየው ሰዎች “ተደናግጠውና ተሰቅቀው ሠራዊታቸውን እንዲበትኑ” አድርጓልን? በፍጹም። እንዲያውም እነዚህ የጦር መሣሪያዎች አንድ ቀን ጥቅም ላይ ሊውሉ ምናልባትም የውትድርና ሞያ በሌላቸው ሰዎች እጅ ገብተው የከፋ ጉዳት ሊያደርሱ ይችሉ ይሆናል የሚል የባሰ ስጋት ከመፍጠር ባሻገር የፈየዱት ነገር የለም። ከአሥር ዓመት በፊት የዩናይትድ ስቴትስ የጦር መሣሪያ ቁጥጥርና ቅነሳ መሥሪያ ቤት “የሁለተኛ ደረጃ የኬሚስትሪ እውቀት ብቻ ባለው በማንኛውም ሰው የኬሚካል መሣሪያዎች በየጓሮው ሊሠሩ ይችላሉ” ብሏል።

ሃያኛው መቶ ዓመት በማንኛውም ሌላ ዘመን ታይተው በማይታወቁ አውዳሚ ጦርነቶች ተለይቶ የሚታወቅ ስለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም። በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይም ቢሆን፣ በተለይ በኒው ዮርክና በዋሽንግተን ዲ ሲ ከተሞች ላይ አሸባሪዎች ጥቃት ከሰነዘሩ ከመስከረም 11, 2001 ወዲህ የሰላም ተስፋ ፈጽሞ የጨለመ ሆኗል። ስቲቨን ሌቪ በኒውስዊክ መጽሔት ላይ “የቴክኖሎጂ ሚዛን ይበልጥ ወደ እኩይ ተግባር ያደላ ይሆን? ብሎ ለመጠየቅ የሚደፍር ሰው የለም” ሲሉ ጽፈዋል። በማከልም “እንዲህ ያለው ሁኔታ ቢደርስ እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ትንሽ እንኳ ፍንጭ ያለው ሰው ማን ሊኖር ይችላል? የሰው ልጅ አንድ ጉዳይ የሚያስከትለውን መዘዝ ማጤን የሚጀምረው ዕድገት ነው ብሎ ያሰበውን አካሄድ ሲያሳድድ ከኖረ በኋላ ነው። አያድርስ የምንለው ነገር ይደርስ ይሆናል ብለን ለማሰብ እምቢተኞች እየሆንን እንዲከሰት የሚያስችሉትን ሁኔታዎች በማመቻቸት እንቀጥላለን” ብለዋል።

እስካሁን ድረስ አደገኛ ፈንጂዎችና አውዳሚ መሣሪያዎች ይህን ዓለም በምንም መንገድ ወደ ሰላም እንዳላቃረቡ ታሪክ አስተምሮናል። ታዲያ የዓለም ሰላም ሕልም ብቻ ሆኖ የሚቀር ነገር ነውን?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ናይትሮግሊሰሪንን መግራት

አስካንዮ ሶብሬሮ የተባለው ኢጣሊያዊ የኬሚስትሪ ሊቅ በ1846 ናይትሮግሊሰሪን የተባለውን ዘይት መሰል ወፍራም ፈንጂ ፈሳሽ አገኘ። ይህ ንጥረ ነገር በጣም አደገኛ ሆኖ ተገኘ። ሶብሬሮ በዚህ ንጥረ ነገር ምክንያት በደ​ረሰ ፍንዳታ በመስተዋት ፍንጣሪዎች ፊቱ ላይ ክፉኛ ተመትቶ ጉዳት ስለደረሰበት በዚህ ንጥረ ነገር ላይ ያደርግ የነበረውን ምርምር አቆመ። ከዚህም በላይ ይህ ንጥረ ነገር ሶብሬሮ መፍትሔ ሊያገኝለት ያልቻለ አንድ ችግር ነበረው። እንዲፈስስ ቢደረግና በመዶሻ ቢመታ ሌላው የዘይቱ ክፍል ምንም ሳይሆን የተመታው ክፍል ብቻነው የሚፈነዳው።

ኖቤል ከፍተኛ መጠን ያለውን ፈንጂ ማቀጣጠል የሚችል አንድ ትንሽ ፈንጂ በመፈልሰፍ ለዚህ ችግር መፍትሔ አገኘ። ከዚያም በ1865 ናይትሮግሊሰሪን የያዘ ዕቃ ውስጥ ከተጨመረ በኋላ ከሩቅ ሊቀጣጠል የሚችል የሜርኩሪ ባሩድ የተሞላ ቀለህ ፈለሰፈ።

ይሁን እንጂ አሁንም ከናይትሮግሊሰሪን ጋር ግንኙነት ያለው ሥራ መሥራት አደገኛ መሆኑ አልቀረም። ለምሳሌ በ1864 ከስቶክሆልም ወጣ ብሎ ይገኝ በነበረው የኖቤል ቤተ ሙከራ የደረሰ ፍንዳታ የኖቤል ታናሽ ወንድም የነበረውን ኤሚልን ጨምሮ አምስት ሰዎችን ገድሏል። በጀርመን ክሩመል የነበረው የኖቤል ፋብሪካ ሁለት ጊዜ በፍንዳታ ወድሟል። ከዚህም ሌላ ይህን ፈሳሽ ለላምባ፣ ለጫማ ቀለም ወይም እንደ ግራሶ ሲጠቀሙበት ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ነበሩ። ተራሮች በሚፈርሱበት ጊዜ እንኳን ስንጣቂ ዓለቶች ውስጥ የገባው ዘይት ውሎ አድሮ አደጋ ያደርስ ነበር።

በ1867 ኖቤል ናይትሮግሊሰሪንን ኪዘልጉር ከተባለ የፈንጂነት ባሕርይ የሌለው ድንጋይ መሳይ ነገር ጋር በማዋሀድ ዘይቱ ወደ ጠጣርነት እንዲለወጥ አደረገ። ኖቤል ለዚህ ፈንጂ “ኃይል” የሚል ትርጉም ያለውን ዳይናሚስ የሚል የግሪክኛ ቃል በመጠቀም ድማሚት የሚል ስያሜ ሰጠው። ኖቤል ቆየት ብሎ ይበልጥ የተራቀቁ ፈንጂዎችን ሊሠራ ቢችልም ድማሚት በጣም ዋነኛ ከሚባሉት ግኝቶቹ አንዱ በመሆን ይታወቃል።

እርግጥ የኖቤል ፈንጂዎች ለውትድርና አገልግሎት ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። ለምሳሌ የሴይንት ጎትሃርድ የምድር ለምድር መተላለፊያ በተገነባበት ጊዜ (1872-82)፣ የኒው ዮርክ ኢስት ሪቨር የባሕር ውስጥ ቋጥኞች ይፈርሱ በነበረበት ጊዜ (1876, 1885)፣ በግሪክ የቆሮንቶስ ቦይ በተቆፈረበት ጊዜ (1881-93) በጣም አስፈላጊ የሆነ አገልግሎት ሰጥተዋል። ቢሆንም ድማሚት ከተፈለሰፈበት ወቅት ጀምሮ ከፍተኛ ዝና ያተረፈው የማውደሚያና የመግደያ መሣሪያ እንደሆነ ነው።

[ሥዕል]

ድማሚት በተጠመደባቸው ፈንጂዎች የወደመ የኮሎምቢያ ፖሊስ ጣቢያ

[ምንጭ]

© Reuters NewMedia Inc./CORBIS

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኖቤል ከሞተ ገና 20 ዓመት ሳይሞላ አንደኛው የዓለም ጦርነት ፈንድቶ አዳዲስ አውዳሚ መሣሪያዎች ሥራ ላይ ዋሉ

[ምንጭ]

U.S. National Archives photo

[በገጽ 6 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በካምቦዲያ፣ በኢራቅና በአዘርባጃን የሚኖሩ የፈንጂ ሰለባዎች

[ምንጮች]

UN/DPI Photo 186410C by P.S. Sudhakaran

UN/DPI Photo 158198C by J. Isaac

UN/DPI Photo by Armineh Johannes

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማንኛውም ቅጽበት ቃታቸው ሊሳብ በተጠንቀቅ የሚጠባበቁ በሺህ የሚቆጠሩ የኑክሊየር መሣሪያዎች መኖራቸውን የኒክሊየር ፖሊሲ አውጪ ኮሚቴ ተናግሯል

[ምንጭ]

UNITED NATIONS/PHOTO BY SYGMA

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የኬሚካል መሣሪያዎች አደገኛነት በሰፊው የታወቀው በ1995 በቶኪዮ የምድር በታች የባቡር መሥመር ሳሪን የተባለው መርዛማ ጋዝ በተረጨ ጊዜ ነበር

[ምንጭ]

Asahi Shimbun/Sipa Press

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

UN/DPI Photo 158314C by J. Isaac