ጦርነት ደጋፊ ወይስ የሰላም አራማጅ?
ጦርነት ደጋፊ ወይስ የሰላም አራማጅ?
ስዊድን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በየዓመቱ በተለያዩ መስኮች ለሰው ልጅ ደህንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች የኖቤል ሽልማት ይሰጣል። ይህ ልማድ የተጀመረው መቼ ነው? ይህስ በዓለም ሰላም ለማስፈን ከሚደረገው ጥረት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
ስሙ ለሰው ልጆች በጎ አሳቢ ከሆኑ ሰዎች ተርታ ይመደባል። ሆኖም ከፍተኛ የሆነ ሀብት ሊያከማች የቻለው የጦር መሣሪያዎችን በመሸጥ ነው። ይህ ሰው ማን ነው? ስዊድናዊ ባለኢንዱስትሪና የኬሚስትሪ ሊቅ ሲሆን አልፍሬድ ቤርናርድ ኖቤል ይባላል። ኖቤል ለሰው ልጅ ደህንነት አሳቢ በመሆኑ እጅግ የሚወደስ ሰው ሲሆን “የሞት ነጋዴ” ተብሎም ተጠርቷል። ለምን? ኖቤል ደማሚትን የፈለሰፈ ሰው ከመሆኑም በላይ በሕይወት ዘመኑ አውዳሚ ፈንጂዎችን እያመረተ በመሸጥ ከፍተኛ ሀብት ያካበተ በመሆኑ ነው።
ይሁን እንጂ ኖቤል በ1896 ከሞተ በኋላ ያልተጠበቀ ነገር ተገኘ። ከሀብቱ ዘጠኝ ሚልዮን ዶላር ተለይቶ እንዲቀመጥና ከዚህም ገንዘብ የሚገኘው ወለድ በየዓመቱ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በሕክምና፣ በሥነ ጽሑፍና በሰላም ዘርፎች ትልቅ ግምት የሚሰጠው አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች ሽልማት ሆኖ እንዲሰጥ መናዘዙ ታወቀ።
መጀመሪያ ላይ በርካታ ሰዎች በዚህ ኑዛዜ ግራ ተጋብተው ነበር። የፈንጂዎች አምራች የሆነ ባለሀብት በጎ አድራጊ የሆኑና ለሰላም የቆሙ ሰዎችን ለመሸለም ይህን ያህል የተጨነቀበት ምክንያት ምንድን ነው? አንዳንዶች ኖቤል ዕድሜ ልኩን የሠራው ሥራ ከፍተኛ ውድመት የሚያስከትል በመሆኑ የተሰማውን ጸጸት ለማብረድ ሲል ነው ብለው ያስባሉ። ሌሎች ግን ቀድሞውንም ቢሆን ኖቤል ይጣጣር የነበረው ሰላም ለማምጣት ነው የሚል ስሜት አላቸው። በእርግጥም የጦር መሣሪያዎች ይበልጥ አውዳሚ እየሆኑ በመጡ መጠን ጦርነት እየቀረ ይሄዳል የሚል እምነት ሳይኖረው አልቀረም። ለአንዲት ጸሐፊ “እንዲያውም የእኔ ፋብሪካ ከእናንተ ምክር ቤት ቀድሞ ጦርነት እንዲቆም ሳያደርግ አይቀርም” ካለ በኋላ “በሁለት የጦር ሠፈሮች የመሸጉ ሠራዊቶች ከሴኮንድ በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ እርስ በርሳቸው በተጠፋፉ ዕለት ሥልጡን ብሔራት በሙሉ በዚህ ጥፋት ተደናግጠውና ተሰቅቀው ሠራዊታቸውን ይበትናሉ” ብሎ እንደነበረ ተዘግቧል።
ታዲያ የኖቤል ትንቢት እውነት ሆኗል? ኖቤል ከሞተ ወዲህ በነበረው መቶ ዘመን ምን ትምህርት አግኝተናል?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም የሚያደርግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የማውደም ኃይል ያለው መሣሪያ ወይም ንጥረ ነገር መፈልሰፍ እፈልጋለሁ”— አልፍሬድ ቤርናርድ ኖቤል
[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ የሥዕሎቹ ምንጮች]
Page 2: Missile: U.S. Navy photo; building rubble: UN PHOTO 158178/J. Isaac; page 3: Nobel: © Nobelstiftelsen