በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምንጣፎች በጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ይኖር ይሆን?

ምንጣፎች በጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ይኖር ይሆን?

ምንጣፎች በጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ይኖር ይሆን ?

ምንጣፍ በተነጠፈባቸው ክፍሎች ውስጥ በየዕለቱ የምታሳልፈው ጊዜ ምን ያህል ነው? ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ዘገባ እንዳመለከተው ምንጣፍ በተነጠፈበት ቤት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የመቆየቱ ጉዳይ በተለይ ለልጆች በጣም አሳሳቢ ነው።

እንደ መጽሔቱ ገለጻ “በቤት ውስጥ ለአብዛኞቹ መርዛማ ንጥረ ነገሮች የምንጋለጥበት አጋጣሚ ከውጭው ይልቅ ከ10 እስከ 50 እጥፍ ከፍ ያለ ነው።” በዩናይትድ ስቴትስ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ የሆኑት ጆን ሮበርትስ ከመኖሪያ ቤቶች ምንጣፍ ላይ ለናሙና የሚወሰደው አቧራ በጣም በሚያስደነግጥ መልኩ ከፍተኛ የመመረዝ አቅም ያላቸው ንጥረ ነገሮችን ሊይዝ እንደሚችል ተናግረዋል። እነዚህ ንጥረ ነገሮች እንደ እርሳስ፣ ካድሚየም፣ ሜርኩሪ፣ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን እንዲሁም ካርሲኖጄኒክ ፓሊክሎሪኔትድ ባይፌኖሎችንና (PCBs) ፖሊሳይክሊክ አሮማቲክ ሃይድሮካርቦኖችን (PAHs) ይጨምራሉ።

በጫማና በቤት እንስሳት መዳፎች አማካኝነት ወደ ቤት የሚገቡት ፀረ ተባይ መድኃኒቶች የምንጣፍ አቧራ የሚይዘውን የፀረ ተባይ መድኃኒት መጠን በ400 እጥፍ ሊያሳድጉት እንደሚችሉ ተዘግቧል። እነዚህ መርዛማ ነገሮች ለዓመታት ሳይጠፉ እንደሚቆዩ ይነገርላቸዋል። ፀረ ተባይ መድኃኒቶቹና ፖሊሳይክሊክ አሮማቲክ ሃይድሮካርቦኖቹ በከፊል የመትነን ባሕርይ ስላላቸው ይተኑና በአየር ላይ ቆይተው እንደገና በምንጣፉ ላይ ወይም በሌሎች ቦታዎች ላይ ያርፋሉ።

ሕፃናት ደግሞ ብዙውን ጊዜ መሬት ላይ እየተንከባለሉ ሲጫወቱ ይቆዩና ጣታቸውን አፋቸው ውስጥ ይከታሉ። ስለዚህ ከሌሎች ይበልጥ ለእነዚህ መርዛማ ነገሮች የተጋለጡ ናቸው። ሕፃናት ክብደታቸው ከአዋቂዎች የሚያንስ ቢሆንም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ምግብ የሚያቃጥሉበት ፍጥነት ከትላልቅ ሰዎች ስለሚጨምር ከአዋቂዎች የበለጠ አየር ይስባሉ።

አንዳንድ ተመራማሪዎች በአስም፣ በአለርጂ እና በካንሰር ለሚያዙ ልጆች ቁጥር በፍጥነት ማሻቀብ አስተዋጽኦ ያደረገው ምንጣፍ የተነጠፈባቸው ቤቶች መብዛት ይሆናል ብለው ያስባሉ። ሮበርትስ እንዲህ ብለዋል:- “በተወሰኑ ቦታዎች ከሚደረግ ትንሽ የእግር ምንጣፍ በስተቀር ምንም ባልተነጠፈበት ቤት ውስጥ የሚኖረው አቧራ ከዳር እስከ ዳር ምንጣፍ በተነጠፈበት ቤት ውስጥ ካለው አቧራ ጋር ሲወዳደር አንድ አስረኛ ያህል ብቻ ነው።”

ሮበርትስ ምንጣፎች ለጤና የማያሰጉ እንዲሆኑ ለማድረግ ጫፉ አቧራ የመሳብ ከፍተኛ አቅም ያለው የምንጣፍ አቧራ ማንሻ (vacuum cleaner) ተጠቅሞ ማጽዳት ያስፈልጋል በማለት ሐሳብ ሰጥተዋል። ከዚያም ለሦስትና ለአራት ሳምንታት በየሳምንቱ አንድ ጊዜ ከዋናው መግቢያ ከአንድ ሜትር ብዙም በማይበልጥ ርቀት ላይ የሚገኘውን የምንጣፉን ክፍል 25 ጊዜ፣ እግር የሚበዛባቸውን ሌሎች ቦታዎች 16 ጊዜ እንዲሁም ቀሪዎቹን የምንጣፉ ቦታዎች 8 ጊዜ በአቧራ ማንሻ መሣሪያው ተመላለሱባቸው።

ለእነዚህ ሦስትና አራት ሳምንታት ይህንን ቀላል የአሠራር ሂደት ከተከተላችሁ በኋላ በየሳምንቱ ከላይ ከተጠቀሱት ምልልሶች ከፊል ያህሉን እንኳ ብታደርጉ የአቧራውን መጠን በእጅጉ መቀነስ ትችላላችሁ። ሮበርትስ እንዲህ በማለት ተጨማሪ ምክር ይሰጣሉ:- “በቤታችሁ በእያንዳንዱ መግቢያ ላይ ወፍራም የሆነ የእግር መጥረጊያ ምንጣፍ አስቀምጡና ወደ ቤት ከመግባታችሁ በፊት ጫማችሁን ሁለት ጊዜ በምንጣፉ ላይ ጥረጉ።”