በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

ስለ ሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

ስለ ሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

ለሥራው ሙት የሆነ አንድ ወታደራዊ መኮንን የበላይ አለቃው በአስቸኳይ ይፈልግ የነበረውን ሥራ ለመጨረስ ሲል ምሳውን እንኳን ሳይበላ ሥራው ላይ አቀርቅሯል። የሥራ ባልደረቦቹ ከምሣ ሲመለሱ ግን ጠረጴዛው ላይ ድፍት ብሎ አገኙት። ሞቷል።

ሁለት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አለቃቸው ስልክ ደውሎ “በእገሌ ላይ የደረሰው በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። ከነገ በፊት እሱን የሚተካ ሰው እንዲመደብ እፈልጋለሁ” ባለ ጊዜ ባልደረቦቹ የነበሩት መኮንኖች ክው ብለው ደነገጡ። ሁኔታውን የታዘቡ ሁሉ ከመኮንኑ ሕይወት ይልቅ ሥራው በልጦበታል ማለት ነው? ብለው ተገረሙ።

ይህ እውነተኛ ተሞክሮ አንድ ሐቅ ያረጋግጣል። አንድ ሰው ያለው ዋጋ አብዛኛውን ጊዜ የሚለካው ለአሠሪው በሚሰጠው ጥቅም ነው። እንዲህ ያለው ሁኔታ አንድን ሰው የምኖረው ለመሥራት ነው ወይስ የምሠራው ለመኖር ነው? ለሥራዬ ስል መሥዋዕት ያደረግኩት የትኛውን የሕይወቴን ክፍል ነው? ብሎ እንዲጠይቅ ሊገፋፋው ይችላል።

ጥሩ ምርጫ ማድረግ

በሕይወት ውስጥ በጣም ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ውሳኔዎች መካከል ሁለቱ የትዳር ጓደኛ ምርጫና የሥራ ምርጫ ሲሆኑ አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ሁለት ምርጫዎች የሚደረጉት በችኮላና በስሜታዊነት ነው። በአንድ ወቅት ሥራም ሆነ የትዳር ጓደኛ ምርጫ የዕድሜ ልክ ምርጫዎች ተደርገው ይታዩ ነበር። በዚህ ምክንያት በሁለቱም ምርጫዎች ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር። ብዙ ጊዜ በዕድሜ ከፍ ያሉ ወዳጆችና የወላጆች ምክር ይጠየቅ ነበር።

በዛሬው ጊዜ ግን የትዳር ጓደኛ የሚመረጠው ካልተሳካ ሌላ የትዳር ጓደኛ እቀይራለሁ ብሎ በማሰብ አካላዊ ቁመናና መልክ ብቻ በማየት ነው። በተመሳሳይ ብዙዎች ሥራ የሚመርጡት የሥራውን አሉታዊ ጎን ሳያገናዝቡ እንዲሁ የሚስብ ዓይነት ሥራ መሆኑን ብቻ ተመልክተው ነው። አሉታዊ ጎኖቹን ቢያስቡ እንኳን ‘ግድየለም እቋቋመዋለሁ’ ብለው በማሰብ በጭፍን ይገቡበታል።

በድሀ አገር የሚኖሩ ሴቶች በሌላ አገር የተቀናጣ ኑሮ እንደሚያገኙ ተስፋ በሚሰጡ ማስታወቂያዎች መታለላቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። ከተባለው አገር ሲደርሱ ግን የሚያጋጥማቸው ከቀድሞ ኑሯቸው በጣም የከፋ የዝሙት አዳሪነት ሥራ ነው። እንዲህ ያለው ዘግናኝ የሆነ ዘመናዊ የባርነት ኑሮ ወርልድ ፕሬስ ሪቪው እንዳለው “ሊወገድ ያልቻለ መቅሠፍት” ነው።

የያዙት ሥራ ሕጋዊ ቢሆንም በባርነት እንደወደቁ ሊሰማቸው የሚችሉ ሰዎች ይኖራሉ? አዎን፣ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። ለምሳሌ አንዳንድ ኩባንያዎች ለሠራተኞቻቸው በርካታ ጥቅማ ጥቅሞች ይሰጣሉ። ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን የሚጋብዙባቸው ምግብ ቤቶች፣ ነጻ የመጓጓዣና የላውንደሪ አገልግሎት፣ ነጻ ሕክምና፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ፣ በትላልቅ ምግብ ቤቶች በዝቅተኛ ዋጋ የመስተናገድ መብት ይሰጣሉ።

“እንዲያውም አንድ ኩባንያ በሥራ ለተወጠሩ ሠራተኞቹ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚያገናኝ ድርጅት እስከ መቅጠር መድረሱን” ጋዜጠኛው ሪቻርድ ሪቭዝ ዘግበዋል። ግን እዚህ ላይ ጠንቀቅ ማለት ያስፈልጋል! ጋዜጠኛው እንደሚከተለው በማለት ያብራራሉ:- “እነዚህ ድርጅቶች ኑሮህ የተመቻቸ እንዲሆን እነዚህን ዝግጅቶች የሚያደርጉት አንድ ነገር እስከተሟላላቸው ድረስ ብቻ ነው። ሕይወትህን ሙሉ በሙሉ ለእነርሱ አገልግሎት እስካዋልክ፣ በቀን 18 ሰዓት ለመሥራት ዝግጁ እስከሆንክና አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ በመሥራት ትርፍ ማስገኘት ትችል ዘንድ ቅዳሜና እሁድ ሳትል ቢሮህ ውስጥ ለመብላት፣ ለመጫወት፣ ለመዝናናትና አልፎ ተርፎም ለማደር ፈቃደኛ እስከሆንክ ድረስ ነው።”

የተሻለ አማራጭ መምረጥ

አንድ የጥንት ምሳሌ “ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል” ይላል። (መክብብ 9:​4) እንዲህ ያለው ምሳሌ ከሥራዬና ከሕይወቴ ወይም ከዘላቂ ደህንነቴ የትኛውን አስበልጣለሁ ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ይገፋፋናል። ብዙዎች ራሳቸውን እንዲህ ብለው ከጠየቁ በኋላ ሁኔታቸውን በጥንቃቄ አመዛዝነው ለራሳቸውና ቤተሰብ ያላቸው ከሆኑም ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ሳያጓድሉ ደስተኛና ትርጉም ያለው ኑሮ እንዲኖሩ የሚያስችላቸው ሌላ ሥራ ለማግኘት ችለዋል።

እንዲህ ያለውን እርምጃ ለመውሰድ ራስን ዝቅ ማድረግና የግድ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች አስፈላጊ ካልሆኑ ፍላጎቶች መለየት እንደሚጠይቅ አይካድም። ክብርና ማዕረግ ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች እንዲህ ያለውን ራስን ዝቅ ማድረግ የሚጠይቅ እርምጃ ከሞኝነት በመቁጠር ያቃልሉት ይሆናል። ይሁን እንጂ በሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ቆም ብለህ አስበህ ታውቃለህ?

ከላይ የተጠቀሰውን ምሳሌ የጻፈው ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ምናልባት ማንም ሰው ሊያካብት ከሚችለው የበለጠ ብዙ ሀብት ለማካበት ችሎ ነበር። በእርግጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ሲያጠቃልል ግን “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ” በማለት በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት ጽፏል።​—⁠መክብብ 12:​13

ይሁን እንጂ ሰሎሞን ሥራ የሚጠላ ሰው አልነበረም። “ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም” ሲል ጽፏል። (መክብብ 2:​24) ታላቁ ሰሎሞን ኢየሱስ ክርስቶስና የሰማይ አባቱም ቢሆኑ በተመሳሳይ ለሥራ ከፍተኛ አክብሮት አላቸው። ኢየሱስ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ” ብሏል።​—⁠ዮሐንስ 5:​17፤ ማቴዎስ 12:​42

ሆኖም ባሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ ዕድሜ በጣም አጭር ሆኗል። (መዝሙር 90:​10) ክርስቶስ ግን በምድር ላይ ዘላቂነት ያለው ሕይወት ሊገኝ የሚችለው በአምላክ አገዛዝ ሥር እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይህ አገዛዝ ይመጣ ዘንድ ተከታዮቹ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” ሲል ያሳሰበው በዚህ ምክንያት ነው።​—⁠ማቴዎስ 6:​9, 10, 33

መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ መንግሥት ሥር ስለሚኖረው ሕይወት የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ . . . በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።”​—⁠ኢሳይያስ 65:​21, 22

ዘላለማዊ ሕይወት አግኝቶ አስደሳች ሥራ እየሠሩ መኖር እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! በአምላክ መንግሥት ግዛት የምናገኘውን ይህን “እውነተኛውን ሕይወት” ሊያሳጣን የሚችል አንዳች ነገር እንዳይኖር ስለ ሥራችን ቆም ብለን በጥሞና ማሰብ ሊያስፈልገን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​18, 19) ስለዚህ በሥራችንም ሆነ በምናደርገው ማንኛውም ነገር ሕይወት ለሰጠን አምላክ አክብሮት እንዳለን እናሳይ።​—⁠ቆላስይስ 3:​23

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ መንግሥት ውስጥ ሰዎች በደህንነታቸው ላይ ምንም ዓይነት ሥጋት የማያመጣና የሚያስደስት ሥራ ያገኛሉ