በሥራ ቦታህ ጤናማ ሁኔታ መፍጠር
በሥራ ቦታህ ጤናማ ሁኔታ መፍጠር
ስለ ጤናማ የሥራ አካባቢና ስለ ሥራ ደህንነት በርካታ ሕጎች ቢወጡም በሥራ ላይ የሚያጋጥም አደጋና ሞት አሁንም ዋነኛ ችግር መሆኑ አልቀረም። ስለዚህ በሕግ ስለተደነገገ ብቻ በሥራ ቦታ ያለው ሁኔታ ጤናማ አይሆንም። አሠሪዎችና ሠራተኞች ስለ ራሳቸውም ሆነ ስለ ሌሎች ደህንነት መጠነኛ ኃላፊነት መውሰድ ይኖርባቸዋል።
ስለዚህ እያንዳንዱ ሠራተኛ በሥራ ቦታው ያለውን ሁኔታና የሥራ ልማዱን በጥንቃቄ መመርመር ይኖርበታል። ለምሳሌ፣ በእርግጥ በሥራ ቦታህ ያለው ሁኔታ ጤናማ መሆኑን አስተውለሃል? ሥራህ መርዛማ ከሆኑ ንጥረ ነገሮች ጋር ግንኙነት አለው? ከኖረውስ በቂ መከላከያ ታደርጋለህ? ሁልጊዜ ውጥረት ያጋጥምሃል? በሕግ ከተደነገገው የሥራ ሰዓት ውጭ እንድትሠራ የሚጠይቅብህ የሥራ ፕሮግራም ትቀበላለህ?
እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ በሥራ ቦታህ ያለው ሁኔታ ምን ያህል ጤናማ እንደሆነ ብዙ የሚያሳየው ነገር ይኖራል።
አደገኛ ሁኔታዎችን ልብ ማለት
ለረዥም ሰዓታት ለመሥራት መሞከር አደገኛ ሊሆን ይችላል። የአውስትራሊያው ከርቲን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሎሰን ሴቨሪ ከአንድ ሌላ ተመራማሪ ጋር ሆነው 3.6 ሚልዮን በሚያክሉ ሠራተኞችና 37, 200 በሚያክሉ መሥሪያ ቤቶች ላይ የተደረገውን አንድ ጥናት ከመረመሩ በኋላ “ረዥም ሰዓታት በሥራ ማሳለፍ:- በእርግጥ አደገኛ ነው? ሰዎችስ አሜን ብለው ይቀበሉታል?” በሚል ርዕስ አንድ የጥናት ጽሑፍ አሳትመው አውጥተዋል። ለሁለቱም ጥያቄዎች የተሰጠው መልስ አዎን የሚል ነው ለማለት ይቻላል።
በእርግጥም በሥራ የተዳከሙ ሠራተኞች ምርታማነታቸው ይቀንሳል፣ ብዙ ስህተቶችም ይሠራሉ። ዘ ሳን ሄራልድ የተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ እንደዘገበው ፕሮፌሰር ሴቨሪ “ብዙ ኩባንያዎች የሥራ ሱሰኝነትን ያበረታታሉ። የሥራ ሱሰኞችንም ፈልጎ ለማግኘትና ለመሸለም ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ” ብለዋል። የሚያስከትለው መዘዝ ግን በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል። ይህ ችግር ይበልጥ ጎላ ብሎ የሚታየው በትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። አሽከርካሪዎች በአንዳንድ አገሮች በሕግ የተከለከለ ቢሆንም አለምንም ዕረፍት ለረዥም ሰዓታት እንዲያሽከረክሩ ይበረታታሉ፣ ብሎም ይገደዳሉ።
ሌላው ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር የሥራ ልማድ ሲሆን ይህም ዝርክርክ መሆንን ይጨምራል። መፍቻዎችንና የእጅ መሣሪያዎችን ወለል ላይ ማዝረክረክ ወይም የኤሌክትሪክ ገመዶችን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ መተው ለእልፈተ ሕይወት የሚዳርግ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በኤሌክትሪክ በሚሠሩ መሣሪያዎች በምትጠቀምበት ጊዜ ተገቢ ጥንቃቄዎችን አለማድረግም ተመሳሳይ ውጤት ሊኖረው ይችላል። የተደፉ ፈሳሾችን፣ በተለይ መርዛም ፈሳሾችን ቶሎ ብሎ አለማጽዳትም ለጉዳትና ለሞት ይዳርጋል። ዘይት የፈሰሰበት ወይም የረጠበ ወለል አዳልጧቸው ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞች ብዙ ናቸው። ስለዚህ የመጀመሪያው የጥሩ ሠራተኝነት ሕግ ንጹሕና ሥርዓታማ መሆን ነው ሊባል ይችላል።
ሆኖም የጥንቃቄ እርምጃዎችን ችላ የማለት ዝንባሌ ያላቸው ሠራተኞች ብዙ ናቸው። መንዝሊ ሌበር ሪቪው የተባለው መጽሔት “ሠራተኞች የሥራ ጭነት ሲበዛባቸው የሚፈለግባቸውን በፍጥነት ለማከናወን አንዳንድ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ችላ ማለት የሚያስፈልጋቸው ይመስላቸዋል” ብሏል። በዚህ ምክንያት አንድ ሠራተኛ ‘ይህን ጥንቃቄ ባለማድረጌ እስካሁን የደረሰብኝ ነገር የለም’ ብሎ ሊያስብ
ይችላል። አንድ የረዥም ዘመን ተሞክሮ ያለው የፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ስለዚህ ችግር ሲናገር “በሥራ ቦታ የጥንቃቄ ሕጎችን ተላልፈህ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስብህ ከመቅረት የከፋ ነገር ልታደርግ አትችልም” ብሏል። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ማድረግህ ግድየለሽ እንድትሆንና ከመጠን በላይ በራስህ እንድትተማመን ስለሚያደፋፍርህ ለሌላ አደጋ ያጋልጥሃል።በ1986 በዩክሬይን የደረሰው የቼርኖቤል የኑክሊየር ማመንጫ ፍንዳታ “በዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የኑክሊየር አደጋ” ተብሏል። አደጋው የተከሰተው ለምን ነበር? ስለዚህ አደጋ የተጠናቀረ አንድ ሪፖርት “ጥንቃቄ የጎደላቸው በርካታ አሠራሮች” እና “በተደጋጋሚ የተጣሱ የጥንቃቄ ሕጎች” ለአደጋው ምክንያት እንደሆኑ ይገልጻል።
አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ለማወቅ የሠራተኞችና የአሠሪዎች ትብብር አስፈላጊ ነው። አንድ ጥበብ የተሞላ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) አዎን፣ ጠቢብ የሆነ ሰው አደጋ ሊያስከትል የሚችልን ነገር ተመልክቶ ራሱንም ሆነ ሌሎችን ከዚህ አደጋ መጠበቅ የሚችልበትን መንገድ ይፈልጋል።
አሠሪዎች እንዲህ በሚያደርጉበት ጊዜ ራሳቸውም ሆኑ ሠራተኞቻቸው ይጠቀማሉ። ለምሳሌ፣ አንድ ኩባንያ ሠራተኞቹ የሚሠሩባቸውን ቢሮዎች ሕመም ሊያስከትሉ ከሚችሉ ኬሚካሎች ነጻ እንዲሆኑ አድርጎ በአዲስ መልክ በሠራ ጊዜ የሠራተኞቹ ምርታማነትና በሥራቸው የሚያገኙት እርካታ በጣም እንደጨመረ ተገንዝቧል። በተጨማሪም የሕመም ፈቃድ የሚወስዱ ሠራተኞች ቁጥር በጣም ቀንሶ ተገኝቷል። ለሌሎች ጤንነት እንዲህ ያለ አሳቢነት ማሳየት በዚህ ምሳሌ እንደታየው ለአሠሪዎችም ሆነ ለሠራተኞች የተሻለ የሥራ አካባቢ ከመፍጠሩም በላይ የኢኮኖሚ ጠቀሜታም ያስገኛል።
ባለፈው ርዕስ እንደተመለከተው ጠበኝነት ወደ መሥሪያ ቤቶችም ሰርጎ ገብቷል። ራስህን ለመጠበቅ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎች
በሥራ ቦታዎች የተፈጠሩ አነስተኛ ጠቦች ወደ ከፍተኛ ግጭት ያመሩባቸው ጊዜያት አሉ። ሃርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው የሚከተለውን አሳሳቢ ምክር ይሰጣል:- “በመሥሪያ ቤቶች የሚፈጠሩ ጠቦችን ለመቆጣጠር አነስተኛ የሆነ የጠበኝነት ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የጠብ ድርጊት መፈጸማቸው እንደማይቀር መገንዘብ ያስፈልጋል።”
አንዲት ሴት የሥራ ባልደረቦቿን ትኩረት ሆነ ብላ አትስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ አለባበሷ፣ አነጋገሯና ጠባይዋ ልከኝነት የጎደለው ከሆነ ሌሎች ጥሩ ሥነ ምግባር እንደሌላት አድርገው ሊመለከቷት ይችላሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንዶች ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ለመሳብ ብለው ያደረጉት ባይሆንም አለባበሳቸውና ድርጊታቸው ወንዶች አድብተው እንዲከታተሏቸው እንዲሁም የግዳጅ ወሲብና ግድያ እንዲፈጸምባቸው ምክንያት ሆኗል። ስለዚህ አለባበሳችሁና ጠባያችሁ በሌሎች ላይ ስለሚያስከትለው ውጤት አስቡ። “በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተሉ።—1 ጢሞቴዎስ 2:9፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
መንዝሊ ሌበር ሪቪው ሌላም አደገኛ ሊሆን የሚችል ሁኔታ እንዳለ ይገልጻል። “ብዙ ሰው በማይኖርባቸው አካባቢዎች ብቻቸውን የሚሠሩ ሠራተኞች አሳሳቢ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል” ይላል። ስለዚህ ጉዳዩን ማጤን ያስፈልጋል። በተለይ በምሽት ለብቻ ሆኖ መሥራት ሊያስከትል ለሚችለው አደጋ ራስን ማጋለጥ ጥበብ ይሆናል? ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ብቻ እንዲህ ላለው አደጋ መጋለጥ ተገቢ ይሆናል?
በተጨማሪም የሚያበሳጭ ባሕርይ ያላቸው ወይም ለጠብ የሚጋበዙ የሥራ ውጥረት የበዛባቸው ባልደረቦች ሲገጥሙን ስለምንሰጠው ምላሽ በጥንቃቄ ማሰብ አስፈላጊ ነው። አደገኛ ሊሆን የሚችለውን ሁኔታ ለማርገብ ምን ማድረግ ይቻላል? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፤ ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች” ሲል ይመክራል። (ምሳሌ 15:1) አዎን፣ በአቀራረባችሁ ደግና አክባሪ በመሆን የተፈጠረውን የከረረ ሁኔታ ለማርገብና ግጭት ለማስወገድ ትችላላችሁ።
በዛሬው ጊዜ ባለው በውጥረት የተሞላ የሥራ ዓለም የጠበኝነት መንፈስም ሆነ የሚያበሳጩ ባሕርያት በጣም የተስፋፉ ናቸው። ቁጣው በእኛ ላይ ያነጣጠረ መስሎ ይታይ እንጂ ሰውዬው በውስጡ የታመቀውን ብስጭትና ውጥረት መወጣቱ ሊሆን ይችላል። ያን የመሰለ ውርጅብኝ የደረሰብን በአጉል ጊዜ፣ አጉል ቦታ ላይ ስለተገኘን ብቻ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የምንሰጠው ምላሽ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ሁኔታውን ሊያረግብም ሊያባብስም ይችላል።
ይሁን እንጂ የአመለካከት ልዩነቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ሪዞልቪንግ ኮንፍሊክትስ አት ወርክ የተባለው መጽሐፍ “የሐሳብ ግጭት በሚኖርበት ጊዜ . . . በእርግጥ ከልብ የምናምነውን ነገር በግልጽና በቅንነት አናስረዳም” በማለት ጠቃሚ አስተያየት ይሰጣል። ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? መጽሐፉ በመቀጠል “ግጭቱ እኛን ግራ የማጋባትና የማደንዘዝ ችሎታ ስላለው ከዱላ በስተቀር ምንም መውጫ መንገድ የለም ብለን ወደማመን እንደርሳለን” ይላል።
ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? አዳምጥ! ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ “ያልተግባባናቸውን ሰዎች ከልብ ስናዳምጥ . . . ጥሉን ለማፋፋም ያለን ፍላጎት ይዳከምና መፍትሔዎችን መፈለግ እንጀምራለን” ይላል። ይህ አለመግባባቶችና ግጭቶች ተካርረው ከፍተኛ ጠብ ከመሆን ደረጃ እንዳይደርሱ ለማድረግ የሚጠቅም ጥሩ ምክር ነው።
ስለዚህ በሥራ ቦታህ ጤናማ ሁኔታ ለመፍጠር ምክንያታዊና ተገቢ የሆኑ እርምጃዎችን ውሰድ። ይህም የደህንነት ሕጎችን በጥንቃቄ ማክበርን ይጨምራል። ይህን ማድረግ በሥራ ቦታህ ጤናማ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ የሚያበረክተው ድርሻ በጣም ከፍተኛ ነው።
በተጨማሪም ለሕይወት፣ ለሥራና፣ ለዕረፍት ጊዜ ያለን ዝንባሌ በምንመርጠው የሥራ ዓይነትና ለደህንነት ባለን አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምርጫ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወለል ላይ ዘይት ሲፈስ በደንብ አጽዳ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የለዘበ መልስ የተካረረ ሁኔታ እንዲረግብ ሊያደርግ ይችላል