በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሥራ ቦታ የሚያጋጥሙ አደጋዎች ምንድን ናቸው?

በሥራ ቦታ የሚያጋጥሙ አደጋዎች ምንድን ናቸው?

በሥራ ቦታ የሚያጋጥሙ አደጋዎች ምንድን ናቸው?

“በሥራ ቦታ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በመኪና አደጋ ከሚሞቱት ሰዎች ይበልጣል።” ይህ በአውስትራሊያ፣ ኒው ሳውዝ ዌልስ የሚገኝ ወርክከቨር የተባለ የሠራተኞች ደህንነት ድርጅት የሚያሠራጨው አንድ ሥዕላዊ መግለጫ ርዕስ ነው።

ለሞት የሚዳርጉ አደጋዎች የችግሩ አንድ ክፍል ብቻ ናቸው። በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሥራ ቦታቸው ላይ ከባድ፣ አልፎ ተርፎም በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያስከትሉ አደጋዎች ይደርሱባቸዋል። ሌሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ በሥራ ቦታቸው ላይ መርዛማ ለሆኑ ንጥረ ነገሮች ስለሚጋለጡ ወይም ከፍተኛ ውጥረት ስለሚደርስባቸው አለ ዕድሜያቸው ይሞታሉ።

ሰዎች ከሥራ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ምክንያቶች ለሕልፈተ ሕይወትና ለከባድ አደጋ የሚዳረጉት በሁሉም የኢንዱስትሪና የንግድ ዘርፎች በመሆኑ በሥራ ቦታህ ያለው ሁኔታ ምን ያህል ጤናማ ነው? ሕይወትህንና ጤንነትህን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ምን ሁኔታ ይኖራል? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳቱ የተገባ ነው።

በውጥረት የተሞላ የሥራ ቦታ

ብዙ ጊዜ ሠራተኞች ምርታማነታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ከባድ ተጽእኖ ይደረግባቸዋል። በጃፓን አገር በሥራ ብዛት ምክንያት ለሚደርስ ሞት የተሰጠው ቃል ካሮሺ የሚል ሲሆን ይህን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙበት የሟች ቤተሰቦች ከሚጠይቁት የጉዳት ካሣ ጋር በተያያዘ ነው። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በዚህ አገር በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት ከጃፓን የቢሮ ሠራተኞች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በሥራ ብዛት መሞታችን አይቀርም ብለው ይሰጋሉ። በዚህ ዓይነቱ የካሣ ጥያቄ ሥራ ላይ የተሰማሩ አንድ የሕግ ባለሞያ “በጃፓን በየዓመቱ ቢያንስ 30, 000 የሚያክሉ የካሮሺ ሰለባዎች” እንደሚኖሩ ገምተዋል።

የጃፓን ፖሊሶች የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ከ50 እስከ 59 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣው ከሥራ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ምክንያቶች እንደሆነ አመልክተዋል። ዘ ቫዮለንስ-ፕሮን ወርክፕሌስ የተባለ መጽሐፍ እንደገለጸው አንድ ፍርድ ቤት በሥራው ምክንያት በተፈጠረበት ጭንቀት ተሸንፎ ራሱን ለገደለ አንድ ሠራተኛ ሕይወት አሠሪውን ተጠያቂ አድርጓል።

ዘ ካንቤራ ታይምስ የተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ እንዳለው ‘አሜሪካውያን በጣም ረዥም ሰዓት በመሥራት ከዓለም የአንደኛነቱን ቦታ ከጃፓናውያን ወስደዋል’ ብሏል። በዚህ ምክንያት “ረዥም የሥራ ሰዓቶች ሰዎችን ወደ ሞት እየነዱ ነው” እንደሚሉ ያሉ የዜና ርዕሶች እንደ አምቡላንስ ሾፌሮች፣ ፓይለቶች፣ የግንባታና የትራንስፖርት ሠራተኞችና የማታ ፈረቃ ሠራተኞች ስላሉት በሥራ የተዳከሙ ሠራተኞች ይተርካሉ።

ኩባንያዎች የሚያገኙት ትርፍ እንዳይጓደል ሲሉ የመዋቅር ለውጥ በሚያደርጉበትና ሠራተኞቻቸውን በሚቀንሱበት ጊዜ የቀሩት ሠራተኞች ምርታማነታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ከፍተኛ ግፊት ይደረግባቸዋል። ብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል የሠራተኞች ቅነሳ በሠራተኞች ጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ዘግቧል።

በሥራ ቦታ የሚፈጠር ጠብ

በሥራ የተዳከሙና ከፍተኛ ውጥረት የተጫናቸው ሠራተኞች አደጋ ላይ የሚጥሉት ራሳቸውን ብቻ አይደለም። በብሪታንያ የተደረገ አንድ ጥናት ብዙ የቢሮ ሠራተኞች ከሥራ ሰዓታቸው ብዙውን ክፍል የሚያሳልፉት ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመጋጨት ሲሆን ብዙ ጊዜም በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት አምባጓሮ ይፈጠራል።

ቢዝነስ ዊክ የተባለው መጽሔት “በየሣምንቱ 15 የሚያክሉ አሜሪካውያን ሥራ ገበታቸው ላይ እንዳሉ ይገደላሉ” ብሏል። ሃርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው “ሥራ አስኪያጆች በሥራ ቦታ ስለሚፈጠር ጠብ መናገር አይፈቅዱም። ይሁን እንጂ በየዓመቱ በመቶ የሚቆጠሩ ሠራተኞች የሥራ ባልደረቦቻቸውን መደብደባቸው፣ ከዚያም አልፈው እስከ መግደል መድረሳቸው አልቀረም” ሲል ገልጿል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከደንበኞቻቸው ዱላ የሚሰነዘርባቸው ሠራተኞች በርካታ ናቸው። በአውስትራሊያ ስለ ወንጀለኝነት የቀረበ አንድ ሪፖርት ሐኪሞች ጥቃት ይሰነዘርብናል ብለው ስለሚፈሩ ሕሙማኖቻቸውን ቤታቸው ሄደው በሚያክሙበት ጊዜ አጃቢ እንደሚያስከትሉ ገልጿል። ፖሊሶችና መምህራንም እንዲህ ላለው አደጋ የተጋለጡ ናቸው።

በሥራ ቦታ ጠበኝነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ስሜታዊ ጥቃት ሲሆን ይህን ዓይነቱን ጥቃት ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት የሥነ ልቦና ጥቃት ብሎታል። ይህ ዓይነቱ ጥቃት አብዛኛውን ጊዜ የሚገለጸው በዛቻና በማንቋሸሽ ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚነሶታ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሮበርት ኤል ቨኒንጋ “በሁሉም የዓለም ማዕዘናት የሚኖሩ ሠራተኞች በውጥረትና ውጥረት በሚያስከትላቸው በሽታዎች ተነክተዋል” ብለዋል። አክለው ሲገልጹም “የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ባቀረበው የ1993 የዓለም ሠራተኞች ሪፖርት መሠረት ዋነኛው ችግር ለሰዎች ቅንጣት ያህል አሳቢነት የማይንጸባረቅበት፣ ተለዋዋጭ የሆነና አብዛኛውን ጊዜ ጥላቻ የነገሠበት የሥራ ቦታ የሚፈጥረው ውጥረት ነው” ብለዋል።

ስለዚህ ሊነሣ የሚገባው ጥያቄ አሠሪዎችና ሠራተኞች በሥራ ቦታ ጤናማ ሁኔታ እንዲሰፍን ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? የሚል ነው። በሚቀጥለው ርዕስ ይህን እንመለከታለን።