በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተአምረኛው የሰጎን እንቁላል

ተአምረኛው የሰጎን እንቁላል

ተአምረኛው የሰጎን እንቁላል

ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በማስፈልፈያ መሣሪያ ውስጥ የተቀመጠው የሰጎን እንቁላል በውስጡ ያን የመሰለ አስደናቂ ነገር የሚከናወንበት መስሎ አይታይም። እዚህ እኛ ባለንበት የሰጎን እርባታ ጣቢያ ግን እንቁላሉ ተጥሎ ትልቅ ሰጎን እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ የሚፈጸመውን አስደናቂ እድገት የመመልከት አጋጣሚ አግኝተናል።

ለእንቁላሎቹ እንክብካቤ ማድረግ

እናቲቱ ሰጎን ሽሮ መልክ ያለውንና አንድ ተኩል ኪሎ ግራም የሚመዝነውን እንቁላልዋን አሸዋ ላይ እንደነገሩ ሆኖ በተሠራ ጎጆ ውስጥ ትጥላለች። * ከዚያ በኋላ ሠራተኞች በየቀኑ የሚጣሉትን እንቁላሎች እየሰበሰቡ ማስፈልፈያ መሣሪያ ውስጥ ያስቀምጣሉ። እንቁላሎቹ ለስድስት ሳምንታት በዚህ ማስፈልፈያ መሣሪያ ውስጥ ይቆያሉ።

አሁን ማስፈልፈያ መሣሪያ ውስጥ ለገቡት እንቁላሎች እንክብካቤ የሚደረግበት ጊዜ ነው። በመቀፍቀፍ ላይ የሚገኙት አዲስ ጫጩቶች በጣም ተስማሚ በሆነ 37 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ውስጥ እንዲጠበቁ ይደረጋል። የእንቁላሉ አስኳል ወይም አዲስ የተፈጠረው ሽል ወደታች ዘግጦ ከእንቁላሉ ሽፋን ጋር እንዳይጣበቅ የእርባታው ሠራተኛ ራሱ በሚያገላብጥ ልዩ ሣህን ውስጥ ያስቀምጣቸዋል ወይም በየቀኑ በገዛ እጁ ያገላብጣቸዋል። ሰጎኖች በአሸዋ ጎጆአቸው ጫጩቶቻቸውን ሲቀፈቅፉ እንደሚያደርጉት ያደርጋል ማለት ነው።

ከውስጥ የሚሆነውን መመልከት

ታዲያ በእንቁላሉ ውስጥ የሚሆነውን ነገር ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው? የእርባታው ሠራተኛ አንዱን እንቁላል ቀስ ብሎ አነሳና ከውስጥ ደማቅ መብራት በበራበት ሣጥን አናት ላይ በሚገኝ ቀዳዳ ላይ አስቀመጠው። በዚህ ዘዴ በእንቁላሉ ውስጥ የሚካሄደው አስደናቂ እድገት እንደ ጥላ ሆኖ ሊታይ ይችላል። አርቢው ይህን ዘዴ በመጠቀም በየጊዜው በእንቁላሉ ውስጥ በማደግ ላይ የሚገኘውን ሽል ሁኔታ ይመለከታል። እንቁላሉ መሐል ላይ ፈሳሽ እንደሆነ ከቆየ ጫጩት ሊያፈራ የማይችል በመሆኑ ወደ ማስፈልፈያው መሣሪያ አይመለስም።

የሰጎን እንቁላል በማስፈልፈያ መሣሪያ ውስጥ በሚቆይባቸው 39 ቀናት በእንቁላሉ ቅርፊት ውስጥ ተአምራዊ የሆነ እድገት ይካሄዳል። በዚሁ ጊዜ በእንቁላሉ ውስጥ የአየር ማጠራቀሚያ ከረጢት ይፈጠርና የእንቁላሉን አንድ ሦስተኛ የሚሆን ቦታ ይይዛል። * ገና ተቀፍቅፈው ያልወጡት ጫጩቶች በጣም ተጣብበው ይቆዩና ከእንቁላላቸው ውስጥ የሚወጡበትን ጊዜ ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ። ከዚያ በፊት ግን መከናወን ያለበት አንድ ወሳኝ ሂደት አለ። የእንቁላሉ አስኳል በእትብቱ አልፎ በእምብርቱ በኩል ወደ ጫጩቱ ሆድ መግባት ይኖርበታል። ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ጫጩቶቹ ወደ ውጭው ዓለም ሲወጡ የሚያስፈልጋቸውን ንጥረ ምግብና ኃይል የሚያገኙት ከእንቁላሉ አስኳል ነው።

የእንቁላሉን ቅርፊት ሰብሮ መውጣት

በመጨረሻ በጉጉት የሚጠበቀው ቀን ደረሰ። እኛም የሚሆነውን ለማየት ተዘጋጅተናል። በመጀመሪያ ጫጩቶቹ የእንቁላሉን ቅርፊት ከመስበራቸው በፊት በላያቸው ያለውን ገለፈት አልፈው ወደ አየሩ ከረጢት መግባት ይኖርባቸዋል። ሰጎኖች እንደሌሎቹ ጫጩቶች ጠንካራ የሆነ የቅርፊት መስበሪያ አፍ ባይኖራቸውም ለስላሳ የሆነው የአፋቸው ጫፍ ጉዳት እንዳይደርስበት የሚከላከል ውጫዊ ሽፋን አለው። ጫጩቷ የመከላከያ ሽፋን ያለውን አፏን በቅርፊቱ ውስጠኛ ክፍል ላይ ታስደግፍና ከአየሩ ከረጢት የሚለያትን ገለፈት በማጅራቷ ትገፋለች። ከብዙ መግፋትና መታከክ በኋላ ይህ ገለፈት ይቀደዳል። ከዚህ በኋላ በቅርፊቱ ውስጥ ያለውን ቦታ ሙሉ በሙሉ ለመያዝ ትችላለች።​—⁠ሥዕል ሀን ተመልከት።

አሁን የጫጩቷ ትናንሽ ሳንባዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ትንፋሽ ወደ ውስጥ ያስገባሉ። ሳንባዎቿ ሥራ ጀምረዋል ማለት ነው። ይሁን እንጂ ብዙ የሚያደክም ሥራ ስትሠራ ስለቆየች በእንቁላሉ ውስጥ ያለው አየር አይበቃትም። በዚህ ምክንያት ቅርፊቱን ሰብራ ለመውጣት ትጣጣራለች። ባለ በሌለ ኃይሏ ራሷን ወደፊት እየወረወረች በአፏ ጫፍ ቅርፊቱን ደጋግማ ትደበድባለች። ድክምክም ያለችው ጫጩት በቅርፊቱ ስንጥቅ ውስጥ የብርሃን ጭላንጭል ታያለች። ወዲያውም ትኩስ አየር መተንፈስ ትጀምራለች።​—⁠ሥዕል ለን ተመልከት።

ጫጩቷ ከዚህ ሁሉ ድካም በኋላ በቂ እረፍት ታደርግና በቀኝ እግሯና መከላከያ ባለው የአፏ ጫፍ መሰንጠቅ የጀመረውን ቅርፊት መስበር ትቀጥላለች። ከዚያም የተሰባበረውን ቅርፊት በታላቅ ጀግንነት ደረማምሳ ከወጣች በኋላ በኩራት ቁጭ እንደማለት ብላ የውጭውን ዓለም ታማትራለች።​—⁠ሥዕል ሐን ተመልከት

የእርባታው ሠራተኛ ቅርፊቱን ሰብሮ በማውጣት የማይረዳት ለምንድን ነው? ለጫጩቷ ስለማይጠቅም ነው። የእንቁላሉ አስኳል በጫጩቷ እምብርት እስኪገባና እምብርቷም ተኮማትሮ እስኪዘጋ ድረስ ጊዜ ይወስዳል። ሂደቱን ለማፋጠን ሙከራ የሚያደርገው አላዋቂ ረዳት ገና ያልጠናችውን ፍጥረት ሊጎዳ ወይም አደገኛ ለሆነ በሽታ ሊያጋልጣት ይችላል።

ያም ሆነ ይህ በዚህ እርሻ ያሉት ትናንሽ ፍጥረታት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከቅርፊታቸው ይወጣሉ። ለእኛ ለተመልካቾቹ የሰጎን ጫጩቶቹ በጣም አድካሚ ቢሆንባቸውም በድል አድራጊነት ከቅርፊት ስብርባሪ ውስጥ ሲወጡ ማየት በጣም የሚያስደንቅ ነው።

ከሞግዚቶች ጋር ማገናኘት

ከጥቂት ጊዜ በኋላ የማስፈልፈያው ሞቃት አየር የጫጩቶቹን ለስላሳ ላባ ያደርቅላቸዋል። አሁን በጣም የሚያምሩ ከመሆናቸውም በላይ ላባቸው የጥጥ ባዘቶ ይመስላል። ከዚያም ውጭ ይወጡና በትንሽ አጥር ውስጥ ሆነው ፀሐይ እንዲሞቁ ይደረጋል። በዚህ ጊዜ በጣም ደስ ይላቸዋል። አሁን ገና ያልጠኑትን ትናንሽ እግሮቻቸውን ማንጠራራትና ማንቀሳቀስ ይችላሉ።

የሚቀጥለው ቀን ለፀጉራሞቹ ጫጩት ወፎች በጣም ታላቅ ቀን ነው። ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት በሞግዚትነት እንክብካቤ ከሚያደርጉላቸው ትላልቅ ሰጎኖች ጋር ይተዋወቃሉ። እስከዚህ ጊዜ ድረስ ከእንቁላሉ አስኳል ያገኙት ምግብ ስለሚያቆያቸው አይርባቸውም። ከተፈለፈሉ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ግን ሞርሞር ሊያደርጋቸው ይጀምራል። ታዲያ ምን ሊበሉ ይችላሉ? ጫጩቶቹ የሞግዚቶቻቸውን ትኩስ ኩስ መመገብ ይጀምራሉ። ይህን መመገባቸው በሽታን የመከላከል ችሎታቸውን ሳያጠናክረው እንደማይቀር የእርባታው ሠራተኛ ገለጸልን።

ግልገሎቹ ውትር ውትር እያሉ ከሞግዚቶቻቸው ረዣዥም እርምጃ ላይ ለመድረስ ሲጣጣሩ ተመልከቱ። በእርግጥም ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ የሰጎን ጫጩቶች እድገት በጣም ፈጣን ነው። በወር እስከ 30 ሴንቲ ሜትር ያድጋሉ። ስለዚህ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከእነርሱ በጣም ትላልቅ ከሆኑት ጋር እኩል መራመድ ይችላሉ።

ጎረምሶቹ ሰጎኖች ስድስት ወር ሲሞላቸው እድገታቸውን ጨርሰው ቁመታቸው 2.5 ሜትር ይደርሳል። እነዚህ ከአንገታቸውና ከእግራቸው በጣም ዘለግ ያሉ ፍጥረታት ከሰባት ወራት በፊት ሰው ካላገላበጣቸው በቀር የማይንቀሳቀሱ እንቁላሎች ነበሩ ብሎ ለማመን ያዳግታል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 ስለ ሰጎን ተጨማሪ ዝርዝር ማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ በሐምሌ 22, 1999 የእንግሊዝኛ ንቁ ! መጽሔት ከገጽ 16-18 ላይ የወጣውን ርዕስ ይመልከቱ።

^ አን.9 የሰጎን እንቁላል “ዙሪያውን አየር የሚያሳልፉ ትናንሽ ቀዳዳዎች አሉት። እንቁላሉ ከተጣለ በኋላ በሚኖረው ትነት ምክንያት ወፍራም በሆነው የቅርፊቱ ጫፍ በሁለቱ የቅርፊት ገለፈቶች መካከል አየር ብቻ የሚያስገባ ክፍት ቦታ ይፈጠራል።”​—⁠ኦስትሪች ፋርሚንግ ኢን ዘ ሊትል ካሮ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የማስፈልፈል ሂደት

[ምንጭ]]

የሥዕሎቹ ምንጭ:- Dr. D. C. Deeming

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጫጩቶች ቅርፊታቸውን ሰብረው የሚወጡበት ወሳኝ ቀን!

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕሎቹ ምንጮች]

John Dominis/Index Stock Photography