በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ጦርነትን ይደግፋልን?

አምላክ ጦርነትን ይደግፋልን?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

አምላክ ጦርነትን ይደግፋልን?

የአገር መሪዎች፣ ጄኔራሎች አልፎ ተርፎም ቀሳውስት በአምላክ ስም ጦርነት ሲያውጁና ለጦርነት ድጋፍ ሲሰጡ ኖረዋል! “ቅድስቲቱን ከተማ” ኢየሩሳሌምን ለክርስቲያኖች ለማስመለስ በሚል በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ኧርባን ቡራኬ በ1095 የመጀመሪያው የመስቀል ጦርነት ዘመቻ ተጀመረ። ይሁን እንጂ የመስቀል ተዋጊዎቹ በሥላሴ ላይ ከነበራቸው እምነት በማይተናነስ መልኩ ለአላህ ይቀኑ የነበሩት ቱርኮች አንዱን የተዋጊዎች ቡድን ያሰበበት ሳይደርስ ደምስሰውታል።

በነሐሴ 1914 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አንድ ወጣት ጀርመናዊ ከጦር ሰፈሩ የጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል:- “በታሪክ ውስጥ ፍትሕና መለኮታዊ አመራር አለ ካልን ደግሞም እንደሚኖር እርግጠኛ ነኝ፣ ድሉ የኛ መሆኑ የግድ ነው።” በዚያው ወር ደግሞ ዛር ዳግማዊ ኒኮላስ የሩሲያን ሠራዊት በጀርመን ላይ ሲያዘምት:- “ለጀግኖች ወታደሮቼና ለተከበሩ የጦር አጋሮቼ ልባዊ ሰላምታዬ ይድረስ። አምላክ ከእኛ ጋር ነው!” በማለት ተናግሮ ነበር።

በዚህ መንገድ የልብ ልብ የተሰማቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ወታደሮች አምላክ ከጎናቸው መሆኑን ቅንጣት ሳይጠራጠሩ ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል። ብዙ ሰዎች ለነፃነት ተብለው የሚደረጉትን እንደዚህ ዓይነት ውጊያዎች አምላክ ይደግፋል ብለው ያስባሉ። ለዚህም እንደ ማስረጃ አድርገው (በተለምዶ ብሉይ ኪዳን በሚባሉት) የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉትን ጦርነቶች ይጠቅሳሉ። የአምላክን ቃል የተረዱበት መንገድ ትክክል ነውን?

የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ያካሄዳቸው ጦርነቶች

ይሖዋ አምላክ ተስፋይቱን ምድር ምግባረ ብልሹ ከነበሩት ከነዓናውያን ለማጽዳት እስራኤላውያን እንዲዋጉ አዝዟቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 18:1, 24-28፤ ዘዳግም 20:16-18) አምላክ ክፉ አድራጊዎችን በኖኅ ጊዜ በውኃ መጥለቅለቅ በሰዶምና ገሞራ ጊዜ ደግሞ በእሳት እንደቀጣቸው ሁሉ የእስራኤልን ብሔር እንደ ቅጣት አስፈጻሚ አድርጎ ተጠቀመባቸው።​—⁠ዘፍጥረት 6:12, 17፤ 19:13, 24, 25

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መሠረት እስራኤላውያን ከአምላክ ባገኙት መመሪያ ሌሎች ጦርነቶችንም የተዋጉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ያለ ውዴታቸው የሚመጡባቸውን የጠላት ወረራዎች ለመመከት የተደረጉ ነበሩ። ብሔሩ ለአምላክ ታዛዥ ከሆነ ጦርነቶቹን በድል ያጠናቅቅ ነበር። (ዘጸአት 34:24፤ 2 ሳሙኤል 5:17-25) ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ከመለኮታዊ አመራር ውጪ ለመዋጋት በሚቃጡበት ጊዜ በአብዛኛው ውጤቱ ሽንፈት ነበር። የንጉሥ ኢዮርብዓምን ሁኔታ ተመልከት። የተነገረውን ምንም የማያሻማ ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት ከይሁዳ ጋር ለሚያደርገው የእርስ በእርስ ጦርነት ግዙፍ ሠራዊቱን አዘመተ። በዚህ ግጭት 500, 000 የሚያህሉ የኢዮርብዓም ወታደሮች ተገድለዋል። (2 ዜና መዋዕል 13:12-18) ታማኙ ንጉሥ ኢዮስያስ እንኳን በአንድ ወቅት እሱን በማይመለከተው ጦርነት ውስጥ ገብቶ ነበር። ይህ ማስተዋል የጎደለው እርምጃ ሕይወቱን አሳጥቶታል።​—⁠2 ዜና መዋዕል 35:20-24

ከእነዚህ ታሪኮች ምን መረዳት ይቻላል? በጥንቱ የእስራኤል ብሔር ውጊያ እንዲካሄድ የሚወስነው አምላክ ነበር። (ዘዳግም 32:35, 43) በጊዜው የተወሰኑ ዓላማዎችን ዳር ለማድረስ ሕዝቡ እንዲዋጋ አድርጓል። ይሁን እንጂ እነዚህ ዓላማዎች ከተፈጸሙ ዘመናት ተቆጥረዋል። ከዚህም በላይ ይሖዋ ‘በዘመኑ ፍጻሜ’ የሚኖሩትን አገልጋዮቹን በሚመለከት ‘ሰይፋቸውን ማረሻ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም’ በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 2:2-4) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርላቸው ጦርነቶች በጊዜያችን ያሉትን ግጭቶች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንደ ማስረጃ ሆነው ሊቀርቡ አይችሉም። ከዛሬዎቹ ግጭቶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ በአምላክ አመራር ወይም ትእዛዝ የሚከናወኑ አይደሉም።

የክርስቶስ ትምህርት ያመጣው ለውጥ

ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ‘እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ’ የሚል ትእዛዝ በመስጠት ጥላቻ ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ ፍቅር እንዴት ሊተካ እንደሚችል አስገንዝቧል። (ዮሐንስ 15:12) እንዲሁም “ሰላምን የሚያወርዱ ብጹዓን ናቸው” ብሎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:9 አ.መ.ት ) እዚህ ላይ “ሰላምን የሚያወርዱ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሰላም አግኝቶ ከመኖር የበለጠ ትርጉም አለው። ሰላምን መኮትኮት እንዲሁም ሰላም ለመፍጠር በሙሉ ልብ መሥራትን ይጠይቃል።

ኢየሱስ ሲያዝ ሐዋርያው ጴጥሮስ የጦር መሣሪያ በመጠቀም ሊከላከልለት ሞከረ። ይሁን እንጂ የአምላክ ልጅ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ” በማለት ገሰጸው። (ማቴዎስ 26:52) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እነዚህን ቃላት ተግባራዊ ያደረጉት እንዴት ነበር? ቀጥሎ የተሰጡትን አስተያየቶች ተመልከት።

“ባሉት መረጃዎች ሁሉ ላይ በጥንቃቄ የተደረገው ጥናት እንደሚያረጋግጠው እስከ ማርከስ ኦሬሊየስ [121-180 እዘአ] ዘመነ መንግሥት ድረስ ወታደር የሆነ ክርስቲያን አልነበረም፤ እንዲሁም ክርስቲያን ከሆነ በኋላ በወታደራዊ አገልግሎት የቀጠለ አንድም ወታደር የለም።”​—⁠ዘ ራይዝ ኦቭ ክሪስቺያኒቲ

“[የመጀመሪያዎቹ] ክርስቲያኖች አቋም ከሮማውያኑ በጣም የተለየ ነበር። . . . ኢየሱስ ይሰብክ የነበረው ስለ ሰላም ስለ ነበር ወታደር ለመሆን እምቢ ብለዋል።”​—⁠አወር ዎርልድ ስሩ ዚ ኤጅስ

የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በንጉሠ ነገሥቱ ሠራዊት ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው አብዛኞቹ በሮማውያን ተገድለዋል። ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት የተለየ አቋም የያዙት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ ያስተማራቸው ሰላም ፈጣሪ መሆንን ነበር።

የዘመናችን ጦርነቶች

የክርስቶስ ተከታዮች በተለያየ ጎራ ተሰልፈው አንዱ ሌላውን ለመግደል ቢዋጉ የሚፈጠረውን መጥፎ ሁኔታ እስቲ አስበው። ይህ ከክርስቲያናዊ መሠረተ ሥርዓቶች ጋር አይጣጣምም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸውን አምላክ የሚታዘዙ ሁሉ ማንንም ሰው ሌላው ቀርቶ ጠላቶቻቸውን እንኳን አይጎዱም። *​—⁠ማቴዎስ 5:43-45

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አምላክ በዛሬው ጊዜ በሰዎች መካከል የሚደረጉትን ጭካኔ የተሞላባቸው ጦርነቶች አይደግፍም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰላማዊ ስለሆኑ በአምላክ መንግሥት ሥር በመላው ዓለም ላይ የሚሰፍነውን ሰላም ይደግፋሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 መጽሐፍ ቅዱስ ‘በታላቁ ሁሉን በሚገዛ አምላክ ታላቅ ቀን ስለሚሆነው ጦር’ ማለትም ስለ “አርማጌዶን” ይናገራል። ይህ የሚያመለክተው የሰዎችን ጦርነት ሳይሆን አምላክ ክፉዎችን መርጦ የሚያጠፋበትን ጦርነት ነው። በዚህ ምክንያት በዘመናችን የሚካሄዱት ሰብዓዊ ግጭቶች ትክክል ናቸው ወይም አምላክ ይደግፋቸዋል ብሎ ለመናገር አርማጌዶን እንደ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም።​—⁠ራእይ 16:14, 16፤ 21:8

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሰኔ 11, 1999 ወታደሮች ወደ ኮሶቮ ከመዝመታቸው በፊት በግሪክ የኦርቶዶክስ ቄሶች ቡራኬ ሲሰጣቸው

[ምንጭ]

U.S. National Archives photo

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስፔኑ ጄኔራል ፍራንሲስኮ ፍራንኮ ከካቶሊክ ቀሳውስት ጋር

[ምንጭ]

AP Photo/Giorgos Nissiotis