አብሮኝ የሚኖር ተስማሚ ሰው ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
አብሮኝ የሚኖር ተስማሚ ሰው ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
“የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ እያገለገልኩ የቤት ኪራይ እንዲሁም የመብራትና የውኃ ወጪዎችን ብቻዬን ሸፍኜ መኖር ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው።”—ሊን *
ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው የራሳቸውን ኑሮ መኖር ሲጀምሩ በ‘ገሃዱ ዓለም’ ያለው የኑሮ ውድነት ብዙውን ጊዜ ያልጠበቁት ነገር ይሆንባቸዋል። ብዙዎቹ ይህንን የኑሮ ውድነት አሸንፈው ለመኖር ያላቸው አማራጭ ከአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች ጋር አብሮ በመኖር ወጪዎቻቸውን በጋራ መሸፈን ነው።
ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በዚህ ዓምድ ላይ የወጣው ርዕስ እንዳብራራው ከሌላ ሰው ጋር በተለይም ፈጽሞ ከማያውቁት ሰው ጋር መኖር በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። * የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው ለማገልገል ሲሉ አብረው የሚኖሩ ወጣት ክርስቲያኖችም እንኳን የዚህ ዓይነት ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። የአንተ ሁኔታ ምንም ዓይነት ይሁን ከሌላ ሰው ጋር አብረህ ለመኖር እያሰብክ ከሆነ አብሮህ የሚኖረውን ሰው በምትመርጥበት ጊዜ “መልካም ጥበብን” መጠቀምህ የተገባ ነው። * —ምሳሌ 3:21
ክፉ ባልንጀርነት የሚያስከትለው አደጋ
ብዙ ወጣቶች አብሯቸው ሊኖር የሚችል ሰው ለማግኘት የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን፣ በጋዜጦች ላይ የሚወጡ ማስታወቂያዎችንና ኢንተርኔትን ይመለከታሉ። ይሁን እንጂ ለወጣት ክርስቲያኖች እነዚህ ምንጮች አደጋ አላቸው። የአንተ ዓይነት እምነት፣ የሥነ ምግባር አቋም ወይም መሥፈርት ከሌላቸው ሰዎች ጋር እንድትገናኝ ሊያደርጉህ ይችላሉ። የአንተ ዓይነት እምነት ካለው ሰው ጋር ብቻ ለመኖር መፈለግ ጠባብነት ወይም ፀረ-ማኅበራዊ አመለካከት ነውን? በፍጹም፣ እንዲያውም የጥበብ መንገድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ሲል ያስጠነቅቃል።—1 ቆሮንቶስ 15:33
ሊ የተባለችው ወጣት ያጋጠማትን እንመልከት። በዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች መኝታ ቤት ውስጥ መኖር ስትጀምር ገና የተጠመቀች ክርስቲያን አልሆነችም ነበር። “አደገኛ የሆነ ቦታ ነበር” ስትል ታስታውሳለች። “አንዳንዶቹ ልጃገረዶች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ አብረዋቸው የሚኖሩት ልጆች የጾታ ግንኙነት ሲፈጽሙ ያገኟቸዋል።” ሊ በዚያ መኖሯ ብዙም ሳይቆይ በመንፈሳዊነቷ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳደረ። “በአብዛኞቹ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አልገኝም ነበር” ስትል አምናለች። ባሕርይዋ እየተበላሸ መሄዱ ምንም አያስገርምም። “ይባስ ብዬ አንድ ቀን የብልግና ቃላት ስሰነዝር ከልጃገረዶቹ አንዷ ‘ይሖዋ ይህን ይቀበለዋል?’ አለችኝ።” ምንኛ አሳፋሪ ነው! ደስ የሚለው ግን ሊ ከዚያ ጤናማ ያልሆነ ቦታ ወጥታ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ጀምራለች። ሆኖም የእሷ ተሞክሮ የአንተ ዓይነት የአቋም መሥፈርቶች ከሌላቸው ሰዎች ጋር መኖር የሚያስከትለውን አደጋ ያሳያል።
አብሮህ የሚኖር ተስማሚ ሰው ማግኘት
ታዲያ አብሮህ የሚኖር ሰው ከየት ማግኘት ትችላለህ? አንተ ካለህበት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጀምር። በአብዛኛው የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን የሆኑ ወጣቶች ለእነሱ ተብለው * ወላጆችህ፣ የጉባኤህ ሽማግሌዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሌሎችም ሊረዱህ ይችላሉ። አብረውህ ሊኖሩ የሚችሉ ተስማሚ ወጣቶች ያውቁ ይሆናል።
በሚዘጋጁ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችና ስብሰባዎች ላይ መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሌሎች ወጣቶች ያገኛሉ።አብሮህ የሚኖር ሰው እንደምትፈልግ ለሌሎች መናገርም ጠቃሚ ነው። ፍላጎትህን ለብዙ ሰዎች ባሳወቅህ መጠን ውጤት የማግኘት አጋጣሚህም የዚያኑ ያህል የሰፋ ይሆናል። (መክብብ 11:6) ከሁሉ በላይ ደግሞ አብሮህ የሚኖር ሰው ለማግኘት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው፤ ለጥረትህም መሳካት በእሱ ላይ እምነትህን ጣል።—1 ዮሐንስ 5:14, 15
አስፈላጊ መረጃዎችን መሰብሰብ
አብሮህ ሊኖር የሚችል ሰው ስታገኝ ወዲያው ከዚያ ሰው ጋር መኖር ለመጀመር ትቸኩል ይሆናል። ሆኖም መጀመሪያ አንዳንድ ነገሮችን ለማወቅ መሞከሩ ጥበብ ነው። ግለሰቡ በጉባኤው ባሉ “ወንድሞች ዘንድ መልካም ምስክርነት” ያለው ነውን? (ሥራ 16:1, 2 አ.መ.ት ) ምናልባትም አንተና ወላጆችህ ግለሰቡን የሚያውቁ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሰዎችን ልታነጋግሩ ትችላላችሁ። እንዲህ ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ:- ‘ይህ ሰው ምን ዓይነት ስም አለው? መንፈሳዊና ስሜታዊ አቋሙ የሰከነ ነውን? ለሌሎች በመመስከሩ ሥራ ይካፈላል? በጉባኤስ ሐሳብ በመስጠት ተሳትፎ ያደርጋል? ይህ ሰው በመልካም ሥነ ምግባሩ የታወቀ ነውን?’
‘ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ እንደሚሆን’ አስታውስ። (ምሳሌ 13:20) ዳዊት “አብሮኝ የሚኖረው ልጅ በጣም ጥሩ መንፈሳዊ አቋም አለው” ይላል። “ይህም መንፈሳዊነቴን ጠብቄ ለመኖር አስችሎኛል።” ከተለያዩ ሰዎች ጋር አብራ የኖረችው ረኔም በተመሳሳይ እንዲህ ትላለች:- “አብረውኝ ከኖሩት ልጆች አንዳንዶቹ በየምሽቱ አንድ ላይ ሆነን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ምዕራፍ እንድናነብ ሐሳብ ያቀርባሉ። ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ስላልነበሩ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኖሮን አያውቅም። ስለዚህ አብረውኝ ከሚኖሩት ልጆች ጋር ‘የቤተሰብ ጥናት’ ማድረግ መቻሌ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር!” አዎን፣ እንደ አንተው ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር ካለው ሰው ጋር መኖር መታደል ነው።
በግልጽ ተወያዩ
ፊት ለፊት ተገናኙና ስለ አንዳንድ ነገሮች በግልጽ ተወያዩ። እንደዚህ ዓይነት ውይይት ማድረጋችሁ ባሕርያችሁ የሚጣጣም
እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ያስችላችኋል። ኮምዩኒኬሽን ሪሰርች ሪፖርትስ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንዳመለከተው አብረው የሚኖሩ ሰዎች “ከማንም ይበልጥ የሚዋደዱትና ደስታ የሚኖራቸው” የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ረገድ ተመሳሳይ ባህርይ ሲኖራቸው ነው። በመሆኑም አንተ ግልጽ፣ ተግባቢና ስሜትህን በደንብ አውጥተህ የምትናገር ዓይነት ሰው ከሆንክ ቁጥብና ዝምተኛ ከሆነ ወይም ራሱን የማግለል ባሕርይ ከሚታይበት ሰው ጋር መኖር ሊያስቸግርህ ይችላል።ውይይታችሁ የፖሊስ ጥያቄ ዓይነት መሆን ባይኖርበትም አብሮህ ሊኖር ያሰበው ሰው ስላሉት የቅርብ ጊዜ ግቦችና እቅዶች መወያየቱ ጠቃሚ ነው። ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ከቤት የወጡት መንፈሳዊ ዕድገት ለማድረግ ስለፈለጉ ነው ወይስ ከቁጥጥር ለማምለጥ ሲሉ? ሊን ሊፈጠር የሚችለውን ሌላ ችግር ስትጠቅስ እንዲህ ትላለች:- “አብራኝ ትኖር የነበረችው ልጅ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠረች ትጫወት ነበር፤ የወንድ ጓደኛዋ ሁልጊዜ፣ በጣም ከመሸም በኋላ እንኳን ቤታችን ይቆይ ነበር።” ሊን የሚያሳዩት የፍቅር መግለጫ ተገቢ ያልሆነና የሚረብሽ እንደሆነባት ገልጻለች። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ቀደም ብሎ አንዳንድ መሠረታዊ ደንቦችን በማውጣት እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ማስወገድ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ረኔ እንዲህ ትላለች:- “ወንዶች ከተወሰነ ሰዓት በኋላ መቆየት እንደማይችሉ የሚገልጽ ደንብ አውጥተን ነበር።” አብረው የሚኖሩት ሁለቱም ግለሰቦች ከተቃራኒ ጾታ ጋር በክፍሉ ወይም በመኖሪያው ውስጥ ብቻቸውን ላለመሆን ቢስማሙም መልካም ነው።
የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችን፣ የሚወድዷቸውን ነገሮችና የሙዚቃ ምርጫቸውን በተመለከተም መወያየታቸው ጠቃሚ ነው። ማርክ እንዲህ ይላል:- “እኔ የምወዳቸውን ነገሮች ከሚወድድ፣ ከእኔ ጋር የሚመሳሰል ባህርይ ካለውና እኔ ማከናወን የምፈልጋቸውን ነገሮች ማከናወን ከሚፈልግ ሰው ጋር ብኖር ደስ ይለኛል።” እርግጥ ነው፣ የተለያየ ምርጫ አላችሁ ማለት አብራችሁ መኖር አትችሉም ማለት አይደለም። ዋነኛው ነጥብ ሁለታችሁም እንደ አስፈላጊነቱ ለመለወጥ ፈቃደኞች ናችሁ ወይ የሚለው ነው። እርስ በእርስ ተቻችላችሁ ለመኖር እንድትችሉ ልዩነቶቻችሁን ችላ ብላችሁ ለማለፍ እንዲሁም ማስተካከያዎችን ለማድረግ ፈቃደኞች ናችሁን?
ሊ እንዲህ ትላለች:- “ሌላኛው ሰው ከዚህ ዝግጅት ምን እንደሚጠብቅ መጠየቅም ይኖርባችኋል። አንዳንድ ሰዎች የልብ ጓደኛቸው እንድትሆኑ ይፈልጋሉ። እኔ የምፈልገው ግን ያንን አይደለም።” ዳዊትም በተመሳሳይ እንዲህ ይላል:- “አብሮኝ የተለያዩ ነገሮችን ሊያከናውን ከሚችል ሰው ጋር ብኖር ደስ ይለኛል። ሆኖም ከሌሎች ሰዎች ጋር አንዳንድ ነገሮች ማድረግ ስፈልግም ሙጭጭ የሚልብኝ ዓይነት ሰው መሆን የለበትም።” በተመሳሳይ ግለሰቡ በወንጌላዊነቱ ሥራ የአገልግሎት ጓደኛችሁ ሊሆን ይፈልግ እንደሆነ ወይም በውጪ አገር ቋንቋ በሚካሄድ ጉባኤ እንደማገልገል ባሉ ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች የመካፈል ሐሳብ እንዳለው መጠየቁም ጥሩ ነው።
በመጨረሻም ምግብ ማብሰልን (ከሁለት አንዳችሁ ምግብ ማብሰል ትችላላችሁ?)፣ በቤት ውስጥ ሥራዎች መተጋገዝን፣ የግል ንብረቶቻችሁን አጠቃቀም፣ ቁም ሳጥኑን በጋራ የምትጠቀሙበትን መንገድ፣ የቤት ውስጥ እቃዎችን፣ የእቃ ማስቀመጫ ቦታን፣ የቤት እንስሳትንና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን በተመለከተ መነጋገር እንደሚያስፈልጋችሁ አትርሱ። በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ መነጋገሩ አለመግባባትን ከማስወገዱም በላይ ከስሜት ጉዳት ይጠብቃችኋል። ምሳሌ 20:18 “አሳብ በምክር ትጸናለች” ይላል።
“በአግባብና በሥርዐት”
ሌላው ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ በሉቃስ 14:28 ላይ የሚገኘው ‘ኪሳራውን አስሉ’ የሚለው ምክር ነው። አዎን፣ ወጪዎቻችሁን አስሉ። ለቤት ኪራይ ምን ያህል መክፈል ይኖርባችኋል? ለምግብስ? ለመብራትና ለውኃስ? የስልኩን ወጪ ሁለታችሁም ትከፍላላችሁ? እንደዚያ ከሆነ ሒሳቡን የምትካፈሉት እንዴት ነው? ሊን እንዲህ ትላለች:- “ከአንዲት ልጅ ጋር አብሬ መኖር ከመጀመሬ በፊት ከወጪው ላይ የራሷን ድርሻ መሸፈን መቻል አለመቻሏን አረጋግጣለሁ።” ዘ ኔክስት ስቴፕ የተሰኘው መጽሔት እንዲህ ሲል በትክክል ገልጿል:- “የቤት ኪራይና የምግብ ወጪዎችን ከማይጋሩ . . . ወይም ከፍተኛ የመብራትና የውኃ ወጪዎች ከሚያስወጡ ሰዎች ጋር አብሮ መኖር አላስፈላጊ ጭንቀት ያስከትላል።”
“አንዳንድ ጊዜ ጥያቄው ምን ያህል ነው የሚከፈለው ሳይሆን መቼ ነው የሚከፈለው የሚል ይሆናል” ትላለች ረኔ። ቀጥላም እንዲህ ብላለች:- “የቤት ኪራይ መክፈል ያለብን ወር በገባ በሦስተኛው ቀን ነው። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ አብራኝ የምትኖረው ልጅ ከኪራዩ ላይ የራስዋን ድርሻ ሳትከፍል በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ለእረፍት ትሄድና እኔ አከራያችንን ይቅርታ ለመጠየቅ እገደዳለሁ።” ሁሉንም ነገሮች “በአግባብና በሥርዐት” ማከናወንና ነገሮችን ባወጣ ያውጣው ብሎ አለመተዉ ጥበብ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:40 አ.መ.ት ) ብዙውን ጊዜ ስምምነቶችን በጽሑፍ ማስፈሩም ተገቢ ነው።
ጠንቃቃና አስተዋይ መሆናችሁ ሐዘን ሳይሆን በረከት የሚሆንላችሁ ሰው የማግኘት አጋጣሚያችሁን ይጨምረዋል። ይሁን እንጂ ችግሮችና የባሕርይ ልዩነቶች ቢፈጠሩስ? ከዚህ ቀጥሎ የሚወጣው ርዕስ ይህንን ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.5 በግንቦት፣ 2002 እትማችን ላይ የወጣውን “አብሮኝ የሚኖረው ልጅ ፀባይ ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.5 ዛሬ ብዙዎች ከሥነ ምግባር ውጭ ለሆኑ ዓላማዎች አብረው የሚኖሩ በመሆኑ ይህ ርዕስ የሚያብራራው አብሮ መኖር ለሚያስገኛቸው ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌሎች ጥቅሞች ሲሉ አንድ ላይ ስለሚኖሩ ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ሰዎች መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
^ አን.10 የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አላቸው። በየዓመቱ ከሚከናወኑት የወረዳ ስብሰባዎች ጋር በተያያዘም ከሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ጋር ስብሰባ ይደረጋል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከማይከተሉ ሰዎች ጋር አብሮ መኖር ብዙ አደጋዎች አሉት
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአንድ ሰው ጋር አብራችሁ ለመኖር ከመስማማታችሁ በፊት ፊት ለፊት ተገናኝታችሁ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ